Monday, 15 April 2013 10:10

ፍቅረኛን ለማስደመም እስከህይወት መስዋዕትነት!?

Written by 
Rate this item
(168 votes)

ቻይናዊው ሁ ሴንግ አንዲት የሚወዳት ፍቅረኛ አለችው፡ እናም ፍቅሩን ለመግለፅ ብቻ ሳይሆን Surprise ሊያደርጋት (ሊያስደምማት) ያስብና ትንሽ ይቆዝማል - ሃሳብ እያወጣ እያወረደ፡ ብዙዎቹ የመጡለትን ሃሳቦች አናንቆ ጣላቸው - ፍቅረኛውን ለማስደመም ብቃት እንደሌላቸው በመቁጠር፡፡ በአዕምሮው የሃሳብ ጅምናስቲክ ሲሰራ ቆይቶ ግን አንዲት ሃሳብ አንጀቱ ላይ ጠብ አለችለት፡፡ ሃሳቡን ለመተግበርም ሲበዛ ተጣደፈ፡፡ ፍቅረኛውን ሊያስደምምበት በወጠነው ሃሳብ እሱ ራሱ ቀድሞ ተደመመና ቁጭ አለ፡፡ ከድማሜው ሲወጣ ሃሳቡን ወደ ተግባር ለውጦ የማሰቡን በረከት ሊቋደስ ቋመጠ፡፡ በቻይና የቾንኪዊንግ ግዛት ነዋሪ የሆነው ሴንግ፤ ፍቅረኛውን በምን ሰርፕራይዝ እንደሚያደርጋት ለማንም አልተናገረም፡፡ ምስጢር ነው - እሱና እሱ ብቻ የሚያውቁት፡፡ ፍቅረኛውም የምታውቀው ሰርፕራይዝ ከተደረገች በኋላ ይሆናል፡፡ ሁሴንግ በቀጥታ የሄደው እንደ ዲኤች ኤል ያለ ፈጣን መልዕክት አድራሽ ተቋም ጋ ነበር፡፡ እዚያም እንደደረሰ ስለሚያደርሱት እቃ ወይም መልዕክት ምንነት ሳይናገር በካርቶን የታሸገ ስጦታ እፍቅረኛው ቢሮ እንዲወስዱለት ብቻ ተነጋገረና ተስማማ፡፡ የአገልግሎት ክፍያውንም ሳያቅማማ ፈፀመ፡፡

ለፍቅረኛው ሊልክላት ያሰበው ስጦታ አበባ አልነበረም፡፡ ጫማ፣ ወርቅ፣ አልማዝ ወይም ወድ አልባሳትም አይደለም፡፡ ለፍቅረኛው ለመላክ ያሰበው ራሱን ነው፡፡ በዚህ ነው የሚወዳትን ፍቅረኛውን ማዝናናትና ማስደመም ያማረው፡፡ እናም መልዕክቱን የሚያደርሱት የድርጅቱ ሠራተኞች ወደ ቤቱ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ራሱን እንደ ስጦታ እቃ በካርቶን ውስጥ አሳሽጐ ጠበቃቸው፡፡ መልዕክት አድራሾቹ “አገር አማን” ብለው በተለመደ ፈጣን የአገልግሎት አሰጣጣቸው፣ በአደራ የተሰጣቸውን እቃ ወደተባሉበት ሥፍራ ለማድረስ ከነፉ - በዘመናዊ ፈጣን አውቶሞቢላቸው፡፡ ሆኖም መሃል ላይ የቴክኒክ ችግር ገጠማቸው፡፡ የአድራሻ ስህተት ተፈጠረ፡፡ ይሄ ስህተት ደግሞ ከሁሉም በላይ ራሱን በካርቶን ውስጥ ላሳሸገው ምስኪኑ ሴንግ ከባድ ፈተና ነበር - የህይወት መስዋዕትነት እስከማስከፈል የሚደርስ፡፡ ሴንግ በካርቶኑ ውስጥ ታሽጐ የሚቆየው ቢበዛ ለ30 ደቂቃ ያህል መስሎት ነበር፡፡

በተፈጠረው የአድራሻ ስህተት ግን ጊዜው ወደ 3 ሰዓታት ተራዘመበት፡፡ ጉድ ፈላ - ሴንግ! ካርቶኑ ውስጥ በአየር እጦት ተሰቃየ፡፡ የማታ ማታ ግን እሽጉ ካርቶን እፍቅረኛው ቢሮ መድረሱ አልቀረም፡፡ ፍቅረኛው ካርቶኑን ለመክፈት ስትጣደፍ፣ የሥራ ባልደረባዋ ደግሞ ሰርፕራይዙን ቀርፃ ለታሪክ ለማስቀመጥ ካሜራዋን ደግና እየተጠባበቀች ነበር፡፡ ካርቶኑ ሲከፈት ግን ሰርፕራይዝ የሚያደርግ ሳይሆን በድንጋጤ ክው የሚያደርግ ነገር ገጠማቸው፡፡ ሁ ሴንግ ካርቶኑ ውስጥ ሩሁን ስቷል፡፡ በአየር እጥረት ታፍኖ፡፡ በስጦታ ሰርፕራይዝ ለመደረግ ቋምጣ የነበረችው ፍቅረኛው፤ ህይወቱን ለማትረፍ ተጣድፋ የድንገተኛ ህክምና ባለሙያዎችን አስጠራች፡፡ የህክምና እርዳታ ካገኘ በኋላ ሴንግ ነፍሱ ተመለሰችለት፡፡

“ጉዞው ያንን ያህል ረዥም ጊዜ ይወስዳል ብዬ አላሰብኩም ነበር” ያለው የዋሁ አፍቃሪ፤ “በእሽጉ ካርቶን ውስጥ ሆኜ አየር የማገኝበት ቀዳዳ ለማበጀት ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ካርቶኑ በጣም ወፍራም ስለሆነ አልቻልኩም፤ ጩኸት እንዳላሰማ የነገሩን ድንገቴነት (Surprise) ማበላሸት አልፈለግሁም” ብሏል፡፡ የመልዕክት አድራሹ ድርጅት ቃል አቀባይ በበኩሉ፤ “ገና ከመጀመርያው ምን እንዳሰበ ቢነግረን ኖሮ እሽጉን አንወስድለትም ነበር፤ እንስሳትን እንኳን ለማጓጓዝ ስንቀበል አየር ማግኘት እንዲችሉ በተለየ መያዣ ውስጥ ነው የምናደርጋቸው” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል - ለኦሬንጅ ኒውስ፡፡ አይገርምም! ፍቅረኛውን ለማስደመም ሲል ህይወቱን ሊያጣ ለጥቂት እኮ ነው የተረፈው፡፡ ካልጠገቡ አይዘሉ፤ ካልዘለሉ አይሰበሩ የሚለው ሀገራዊ አባባል ለቻይናዊው ሁ ሴንግ አይሰራ ይሆን?!

Read 28951 times