Saturday, 27 June 2015 09:26

“የምርጫው ውጤት የዓለም መጨረሻ አይደለም----”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(3 votes)

ፕሮፌሰር መርጋ በቃና፤ አባባሉ ለኢህአዴግ እንደማይሰራ ያውቁታል
ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫ ማግስት ሊ/መንበሩንና ምክትሉን አስገመገመ

   ሰማያዊ ፓርቲ በምርጫው ማግስት ባደረገው ግምገማ በእጅጉ ተደምሜአለሁ፡፡ (መደመም እኮ ተወዷል!) ያውም ደግሞ -- በተመሳሳይ ሰዓት “ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ አይደለም” የሚል በቁጣ የታሸ ተቃውሞ ለምርጫ ቦርድ፣ ለኢህአዴግና ለዓለም እያቀረበ፡፡ (ቁጣውን ከግምገማ ማምታታት ግን አላስፈለገውም!) በቅድመ ምርጫ ወቅት በ93 ሚ. ብር የምርጫ በጀት የታማው ሰማያዊ ፓርቲ፤ በምርጫ ማግስት ምክትል ሊቀመንበሩን በ10ሺ ብር ምዝበራ ጠርጥሮ መገምገሙን ሰማን፡፡ (የምዝበራ የፈረንጅ አቻው Embezzlement መሆኑን ልብ በሉ!)  
እኔ የምለው ግን----ኢህአዴግስ የምርጫ ማግስት ግምገማ አድርጓ ይሆን? (በተለይ የፋይናንሷን ነገር!) ለነገሩ ምርጫን በ100 ፐርሰንት አሸንፎ፣ እንደነሰማያዊ በገንዘብ ማጉደል መገምገም ሞራል ይነካል፡፡  (ሙድ ያበላሻል!) እናላችሁ… በአዲስ አበባ በምርጫው 2ኛ የወጣው ሰማያዊ፤ ምንም እንኳን የምርጫውን ውጤት ፈጽሞ እንደማይቀበል ቢገልጽም በዚህ ሰበብ የፓርቲውን መደበኛ ሥራ አላስተጓጎለም፡፡ (በቀጥታ ወደ ግምገማ ነው የገባው!)
በነገራችን ላይ --- ያ ፈጽሞ መስማት የማንሻው ምርጫን ታኮ በዜጎች ላይ የሚደርስ እስርና ወከባ፣ዱላና ስቃይ፣ መፈናቀልና መሰደድ ወዘተ-- በምርጫው ማግስት ሳናስበው ከች ማለቱ አሳዝኖናል፡፡ “በምርጫው አንድም ዜጋ አይሞትም” ያልነው የመፈክር አባዜ ተጠናውቶን አልነበረም። እናላችሁ-- ምርጫ 2007ን ሸወድናት ብለን ስለታችንን ልናገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነም። መጀመሪያ የሰማያዊ ፓርቲ አባል ተገደለ ተባለ፡፡ ትንሽ ቆይቶ መድረክ መግለጫ አወጣ፡፡ ባለፈው ሳምንት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በወጣ ዜና፣ መድረክ በትግራይና በሃድያ ሁለት አባላቱ እንደተገደሉበት ጠቁሞ፣ በምርጫው ማግስት የፓርቲው ደጋፊዎችና አባላት በኢህአዴግ ካድሬዎች የሚያስመርር ወከባና ስቃይ፣ ድብደባና እስር እንዲሁም ማስፈራሪያና ዛቻ  እየደረሰባቸው እንደሆነ በመረጃ አስደግፎ አስቀምጧል፡፡ (መንግስትና ህግ የት ናቸው?!)
አንዳንድ የመንግስት መ/ቤት ለሁነኛ ጉዳይ ስትሄዱ---ምን ይገጥማችኋል መሰላችሁ? (ምንም!) ከምሬ ነው---ምንም አይገጥማችሁም! ሥራ አስኪያጁን ፈልጌ ነበር? የሉም! ምክትሉስ? እሳቸውም የሉም! ጸሃፊዋስ? አልመጣችም! ህዝብ ግንኙነቱስ? እሱም ወጥቷል! (“ወይ ጭንቂ” አሉ ትግሬው ቢጨንቃቸው!) ግራ ግብት ብሏችሁ---ዘበኛውን ታዲያ ማን ነው ያለው? ስትሉት፣ አንድ የሆነ ሠራተኛ ከውስጥ የተቆለፈ የቢሮ በር ከፍቶ ይወጣና-- ሁሉም ሥልጠና ላይ መሆናቸውን ነግሯችሁ እሱም ቢሮውን ቆልፎ ይከንፋል፡፡ (የሥልጠና ሰዓት ረፍዶበት ሳይሆን አይቀርም!)
እርግጠኛ ነኝ መንግስትና ህግ ግን አገርን ጥለው ሥልጠና አይገቡም፡፡ እኔ እርግጠኛ ብሆንም አንዳንዴ የምንሰማው ግን ጥርጣሬ ውስጥ ይከተናል፡፡ እናላችሁ---መድረክ በምርጫው ማግስት በአባላቶቼ ላይ ደረሰ ብሎ የዘረዘራቸው በደሎች እኮ አምስተኛ ዙር ምርጫ አካሄደች ከምትባል አገር አይጠበቅም፡፡ ሰበቦቹ ደግሞ አስፈሪና አደገኛ ናቸው፡፡ መድረክ እንደሚለው፤ አባላቱ ለዚህ ሁሉ ግፍና በደል የተዳረጉት--- ለምን ለመድረክ ቀሰቀሳችሁ? ለምን ለተቃዋሚ ፓርቲ ታዛቢ ሆናችሁ? ወዘተ-- በሚል ነው፡፡ (መንግስት ተለወጠ እንዴ?)
እኔ የምለው---ኢህአዴግ ምርጫውን በ100 ፐርሰንት ማሸነፉን ያልሰሙ ካድሬዎች አሉ እንዴ? (ወድጄ እኮ አይደለም!) በምርጫ ሙሉ በሙሉ አሸንፈሃል ከተባሉ ወዲህ---የወከባውና የእስሩ ጋጋታ ምንድነው? (ቁጭት ነው ትቢት?)
በነገራችን ላይ እስካሁን ለሞቱት ሶስት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣መንግስት ሃዘኑን አለመግለፁ ያልሆነ ጥርጣሬ ውስጥ ከቶኛል፡፡ (ኢህአዴግ ምርጫውን ማሸነፉን አላመነም እንዴ?) ለምን መሰላችሁ … ምርጫውን ማሸነፉን ካመነ መንግስትነቱን ያምናል። መንግስትነቱን ካመነ ደግሞ የቆመው ለዚህ ወይም ለዚያ ወገን ሳይሆን ለኢትዮጵያውያን በሙሉ እንደሆነ ባያምን እንኳን ያውቃል (ለደገፈውም ለተቃወመውም!) በዚህ የተነሳ ነው በምርጫው ማግስት ለሞቱት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ሃዘኑን መግለጽ ያለበት፡፡ ሃዘኑን መግለጽ ብቻም አይደል። ገዳዮቹን ለፍርድ ለማቅረብ ቁርጠኝነቱን በይፋ መግለጽ አለበት፡፡ ግድያው ፖለቲካዊም ሆነ የግል ጸብ---ለውጥ የለውም (ሁለቱም  ወንጀል ነው!)
በተለይ በአገሪቱ ላይ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እተክላለሁ ለሚል (ቢያንስ በመርህ ደረጃ!) እንደ ኢህአዴግ ያለ ፓርቲ፣ (ከምርጫ ውጤት በኋላ የአቋም ለውጥ ተድርጓል እንዴ!) የተቃዋሚው ጎራ በካድሬ ሲታመስ ሃይ ማለት ይገባው ነበር (የህልውና ጉዳይ ነዋ!)
እናላችሁ … የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በተቃዋሚነታቸው ባይወዳቸው እንኳ ሊጠላቸው አይገባም (መንግስት ነዋ!) ግፍና በደል ያውም እስከ ግድያ ሲደርስባቸውም፣ “መንግስት ስሆን የሁሉም ነኝ” ብሎ አጋርነቱን ማሳየት ነበረበት፡፡ “ግድያው ከፖለቲካ ጋ አይገናኝም” ምናምን ዓይነት መልስ ውሃ አያነሳም፡፡ (መንግስትና ህግ ያለበት አገር መስሎኝ?)
እኔ የምለው … ምርጫ ቦርድ “Mission accomplished!” ብሎ ቢሮውን ከረቸመ እንዴ? ተቃዋሚዎች በምርጫ ማግስት አባላቶቻችን ተገደሉብን ሲሉ (ባያመለክቱ እንኳን) ለመመርመር፣ ጉዳዩን ለማውገዝ---ጣልቃ ለመግባት --- ምነው ድምጽና አቅም አጣ? ምርጫ ቦርድም እንደ መንግስት ሁሉ፣ የሁላችንም እንጂ የዚህ ወይም የዚያ ወገን አይደለም ብዬ እኮ ነው፡፡ (ከሆነ ንገሩኝ!)
በመጨረሻ ህይወታቸውን ላጡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት፣ (ኢትዮጵያውያን ማለት ይቀላል!) ነፍስ ይማርልን ብዬ በመነሻዬ ወደጀመርኩት ገራገር ወግ እመለሳለሁ (የጨዋታዬን መስመር ስለሳትኩ ግለ ሂሴን ውጫለሁ!)
እናላችሁ…ሰማያዊ በምርጫው ማግስት በራሱ ላይ ባካሄደው “ምህረት የለሽ” ግምገማ የፓርቲውን ሊ/መንበር ኢንጂነር ይልቃልን በዳተኝነት፣ (በምርጫ ቅስቀሳ ሽርሽር ሄደዋል …በሚል!) ም/ሊቀመንበሩን ደግሞ በገንዘብ ማጉደል ወንጅሏል (ኧረ ዲሞክራሲያዊነት!) በእስከዛሬው የጦቢያ ተቃዋሚዎች እውቀቴ፤  የፓርቲ ፕሬዚዳንቶች ወይም ሊ/መንበሮች በስልጣን ላይ እያሉ ሲገመገሙ ሰምቼም አይቼም አላውቅም (በህልሜም እንኳን!) ድንገት ከተገማገሙም (ከተቧቀሱ ማለት ይሻላል!) የማታ ማታ (ቦርዱ ቢኖርም  ባይኖርም!) ፓርቲው መፍረሱ አይቀርም፡፡ እስካሁን በግምገማ ንክችት ያላለው (ከ92 ወዲህ ማለቴ ነው !) ኢህአዴግ ብቻ ነው! (ያደገበት ነዋ!)
 እናላችሁ --- የሰማያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበሩ፤ “የምርጫ ግብረሃይል ሆነው ሲሰሩ ከፓርቲው 10ሺ ብር ያህል ገንዘብ መዝብረዋል?”፣ “በእጩ ተወዳዳሪዎች አመላመል ላይ አሻጥር ሰርተዋል” በሚል  ሲገመገሙ በብስጭት ስብሰባውን ረግጠው ወጥተው ነበር። (“የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል አሉ!”) ወጥተው ግን አልቀሩም፡፡ ምስጋና ለም/ቤቱ አባላት ሸምጋዮች ይሁንና---ተገምጋሚው ወደ ስብሰባው ተመልሰው ገቡ (በግምገማ ኩርፊያ የለም!) ከዚያም 10ሺ ብር መዝብረዋል የተባለውን በተመለከተ ም/ሊቀመንበሩ ከማስተባበል ይልቅ አስተዛዘኑ፡፡ “10ሺ ብር መዝብረሃል ከተባልኩ ከየትም ተበድሬ ለፓርቲው ተመላሽ አደርጋለሁ” አሉ፡፡ (ይሁና!) ለነገሩ የፓርቲው አባላትም ቦንብ ቦንብ የሆኑ የግምገማ ቃላትን ነው የተጠቀሙት፡፡ (ከጥፋቱ ጋር የማይመጣጠን !)
እናላችሁ … ሌሎችም ፓርቲዎች የምርጫ ማግስት ግምገማቸውን አድርገው ውጤቱን ቢነግሩን ምን ይለናል፡፡ አያችሁ----ተቃዋሚዎች ፓርላማ ባይገቡም፣ የመንግስት ሥልጣን ባይጨብጡም ግልጽነታቸውን፣ ዲሞክራሲያዊ አሰራራቸውን ወዘተ--ለራሳቸው እየተለማመዱ ለህዝብም ቢያሳውቁ እምነትና ልብን በጊዜ ለማሸነፍና ለመግዛት ያግዛል፡፡  
በነገራችን ላይ ዘንድሮ ኢህአዴግ፣ ምርጫውን በ“ዝረራ” ያሸነፈውን ያህል፣ ተቃዋሚዎችም (አንጋፋዎቹን ማለቴ ነው!) ውጤቱን በ“ዝረራ” አልተቀበሉትም፡፡ ምነው ሲሏቸው---- ፍትሃዊነት፣ነጻነት፣ተዓማኒነት-- ይጎድለዋል ሲሉ ጣታቸውን ወደ ኢህአዴግና ምርጫ ቦርድ ይሰነዝራሉ፡፡ 50 ገደማ አባላትን ይዞ ከተፍ ያለው የአፍሪካ ህብረት ታዛቢ ቡድን በበኩሉ፤ “ምርጫውን ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ተዓማኒነት ያለው ነው” ቢልም “free and fair የሚል ነገር ትንፍሽ አላለም” እያሉ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ (ንፉግ በሉት!) እኛ ግን እድሜ ለአገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ጥምረቶቻችን፡፡ 40 ሺ ታዛቢዎችን በትኖ ምርጫውን እንዲታዘቡ አድርጓል። (40 ሺ ውጤት እንዳትጠብቁ!) በአጭሩ፤ “ምርጫው ነጻ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ ነበር”ብሎ ተገላግሏል፡፡ (ጣጣ ፈንጣጣ የለም!)
አንድ የኒዮሊበራሊዝም አቀንቃኝ ወዳጄ፣ የኢህአዴግን ፓርላማውን ለብቻው መቆጣጠር ሲሰማ ምን አለ መሰላችሁ? “እንኳንም የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ዲፓርትመንት ተዘጋ” “ለምን እንደዚያ አልክ?” ብዬ ጠየቅሁት ግራ በመጋባት፡፡ ወዳጄም፤ “አንዳንድ ታሪካችን የነጮች መሳለቂያ ስለሚያደርገን በታሪክ ዶሴ ባይካተት ይሻለናል” አይለኝ መሰላችሁ፡፡ (ይሁንለታ!)
አንድ ጋዜጠኛ ወዳጄ ደግሞ “የዩኒቨርሲቲው ሂስትሪ ዲፓርትመንት የተዘጋው የኢትዮጵያ ታሪክ የተጻፈው በአሸናፊዎች ስለሆነ እሱን ለማረም ነው” የሚል ማብራሪያ ከኢህአዴግ ሹማምንት መስማቱን ነግሮኝ ስገረም ሰነበትኩላችሁ፡፡ (ማን ይሆን የታሪካችን ኤዲተር?)
እኔ የምለው ግን ---- የዓለም ታሪክ ራሱ የአሸናፊዎች አይደለም እንዴ? ኢህአዴግ ደርግን አሸነፈ። “ተራራ የሚያንቀጠቅጥ ትውልድ” በማነው የተጻፈው? በኢህአዴግ እኮ ነው- በአሸናፊው ወገን፡፡ ይኼውላችሁ ታሪክ መጻፍ አይደለም---- ኑሮውን የሚኖሩትም እኮ አሸናፊዎቹ ናቸው! (ምርጫን በ100 ፐርሰንት ላሸነፈ ፓርቲ ይሄ ግልጽ ነው!)
 እስኪ አንድ ጥያቄ ልወርውር፡ (ሎሚ አይደለም፤ ጥያቄ ነው!)
የዘንድሮን ምርጫ ታሪክ ማን ቢጽፈው ጥሩ ነው? (ሂስትሪ ዲፓርትመንት የለማ!)
ሀ-አሸናፊው
ለ- ተሸናፊው
ሐ- ምርጫ ቦርድ
መ- ወጣት ሊግ
ሠ- ፓርላማው   
ለማንኛውም ግን አንዳንድ ተቃዋሚዎች የዘንድሮን ምርጫ እያሰላሰሉ -- ምንአልባት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከበረታባቸው ፈጽሞ እጅ እንዳይሰጡ! ባይሆን-- የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢው ፕ/ር መርጋ በቃና የተናገሩትን እያስታወሱ ለመፅናናት ይሞክሩ፡፡ (ምን ነበር ያሉት?) “የምርጫው ውጤት የዓለም መጨረሻ አይደለም … የዛሬ 5 ዓመት  ምርጫ ይኖራል”  (ያፅናናል ያልኩት ሆድ የሚያስብስ ነው ለካ!)
 በነገራችን ላይ ፕሮፌሰሩ ይሄን ያሉት---ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ አይደለም ብለው ለተነጫነጩባቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነበር፡፡ ግን ይሄንኑ አባባል ለኢህአዴግ (ለአውራው ፓርቲ ማለቴ ነው!) ሊደግሙት የሚችሉ ይመስላችኋል? እንበል-- ተቃዋሚዎች በአብላጫ ድምጽ ቢያሸንፉና ቅሬታ አቅራቢ ኢህአዴግ ቢሆን፣ ፕ/ሩ ብድግ ብለው፤ “ኢህአዴግዬ ---- የአለም መጨረሻ እኮ አይደለም---” ምናምን ሲሉ አልታያችሁም? (ቦርዱ ቀውጢ ይሆን ነበር!)
*አቧራውን ለማጥራት (ምርጫ ቦርድን በስሱ ጎሸም ያደረግሁት፣ ለተንኮል ሳይሆን ለራሱ ለቦርዱ ስል ነው፡፡
አያችሁ---አንዳንድ ተቃዋሚዎች “ቦርዱ የማይነቀፍ፣ የማይተች፣ የማይከሰስ፣ አትኩንኝ ባይ ተቋም ሆኗል--”በማለት ሲከሱት ስለሰማሁ፣ ውሸታቸውን ለማጋለጥ ብዬ ነው፡፡ ወደፊትም እቀጥልበታለሁ!)

Read 3896 times