Monday, 27 July 2015 11:04

አስደማሚው የኦባማ አውሮፕላን (Air Force One)

Written by 
Rate this item
(8 votes)

 የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአባታቸውን የትውልድ አገር ኬንያን በመጐብኘት ላይ የሚገኙት ባራክ ኦባማ፤ ትላንት Air Force One በተሰኘው ልዩ አውሮፕላናቸውን ኬንያ ገብተዋል፡፡
ከዋይት ሃውስ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ Air Force One የአውሮፕላን ስም አይደለም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን የሚጭን ማንኛውም የአሜሪካ አየር ሃይል አውሮፕላን በዚህ ስም ነው የሚጠራው፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በወታደራዊ አውሮፕላን  ላይ ከተሳፈሩ “Army One” ተብሎ ይጠራል፡፡ በልዩ ሄሊኮፕተራቸው ላይ ከተሳፈሩ ደግሞ አውሮፕላኑ “Marine one” ይባላል፡፡
ፕሬዚዳንቱ Air Force One በሚል ስያሜ የሚበሩ በልዩ ትእዛዝ የተሰሩ 2 ቦይንግ 747 ጀቶች ያሏቸው ሲሆን እኒህ ጀቶች የባለ 6 ፎቅ ህንፃ ከፍታ አላቸው ተብሏል፡፡
“Air Force One” በከፍተኛ ፍጥነት ሲበር በሰዓት 1ሺ 126 ኪ.ሜ ገደማ መጓዝ የሚችል ሲሆን አውሮፕላኑ በ45ሺ 100 ጫማ ከፍታ ላይ ነው የሚበረው፡፡ ተመሳሳይ የተጓዦች ቦይንግ 747 አውሮፕላን የሚበረው በ30ሺ ጫማ ገደማ ከፍታ ላይ ነው፡፡
አውሮፕላኑ አንዴ ነዳጅ ጢም ተደርጐ ከተሞላ (Full tank) የዓለምን አጋማሽ ማካለል የሚችል ሲሆን ዳግም ለመሙላት መሬት ላይ ማረፍ አያስፈልገውም፡፡ በአጋማሽ አየር ላይ ሆኖ ነዳጅ የመሙላት አቅም አለው፡፡ ከዚያም ይሄ ነው ለማይባል ጊዜ በአየር ላይ ሊቆይ ይችላል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን የአየር ጥቃት መቋቋም ይችላል፡፡ የእሳት ብልጭታ በመርጨት ሚሳየሎችን ከዒላማቸው ውጭ ከማድረጉም በተጨማሪ የጠላት ራዳርንም አገልግሎት አልባ ያደርጋል፡፡ ሌሎችም ለደህንነት ሲባል በምስጢር የተያዙ ገፅታዎች እንዳሉት ታውቋል፡
ግዙፉ የፕሬዚዳንቱ የአየር ላይ ቢሮ በሚል የሚታወቀው Air Force One  ለሰራተኞች፣ ለኃላፊዎችና ለእንግዶች የመኖሪያ ክፍሎች አሉት፡፡
በአውሮፕላኑ ውስጥ እጅግ ከሚያስደንቁ ገፅታዎች መካከል ብዛት ያላቸው የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ይጠቀሳሉ፡፡ አውሮፕላኑ ፕሬዚዳንቱንና ሰራተኞቹን በአየር ላይ ሆነው ከመላው ዓለም ጋር መገናኘት የሚያስችላቸው አስተማማኝ የስልክ መስመር ያለው ነው፡፡ ከተለያዩ የቢሮ እቃዎች በተጨማሪም 85 ስልኮች፣ 19 ቴሌቪዥኖች፣ ፋክስ ማሽኖችና ሬዲዮኖች ተገጥሞለታል፡፡
የፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን 96 ተጓዦችና የበረራ ሰራተኞችን የመጫን አቅም አለው፡፡

Read 5066 times