Monday, 27 July 2015 11:05

“ኦባማ”… የስንቱ ስም ሆነ?! ከኬንያ መንደር እስከ አየርላንድ ገጠር

Written by 
Rate this item
(7 votes)

  የዛሬ 8 ዓመት ኦባማ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በመላው ዓለም ዝናቸው በእጅጉ ናኝቶ ነበር፡፡ ለዚህም ይመስላል ከኬንያ የአባታቸው የትውልድ መንደር አንስቶ እስከ አየርላንድ ገጠር ድረስ ስማቸው ታዋቂ የሆነው፡፡ በተለይ በኬንያ በእሳቸውም ስም ያልተሰየመ ነገር ያለ አይመስልም፡፡ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች፣ ኪዮስኮች፣ መደብሮች… ኧረ ህፃናትም አልቀሩ፡፡ ሁሉም የባራክ ኦባማን ስም የታደሉ ይመስላሉ፡፡ አንዳንድ በኦባማ ስም የተሰየሙ ነገሮች ደግሞ አግራሞትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ራሷ ኬንያ ኦባማ መባል ነው የቀራት፡፡ እስቲ Tuko.co.ke የተሰኘው ድረ-ገፅ በኦባማ ስም የተሰየሙ ነገሮችን በተመለከተ ያወጣቸውን መረጃዎች እናስቃኛችሁ፡፡

                “ኦባማ ተራራ”

   አንቲጓ የተባለችው የኬንያ ግዛት በኦባማ ስም የሚሰየም ትንሽ ነገር ያጣች ትመስላለች፡፡ በግዛቱ ያለ አንድ ትልቅ ተራራ በፕሬዚዳንቱ ስም ተሰይሟል፡፡ “ኦባማ ተራራ” ይባላል፡፡ “ቦZ ፒክ” በአንቲጓ በጣም ረዥሙ ተራራ ሲሆን ኦባማ የሚለው ስም የተሰጠው እ.ኤ.አ በ2009 በፕሬዚዳንቱ የልደት ቀን ነበር ተብሏል፡፡

            “ኦባማ ሹሩባ”

     ኦባማ ፀጉራቸውን ሹሩባ ተሰርተው ባያውቁም በአያቶቻቸው መንደር በኮጌሎ ግን አንድ የሹሩባ አሰራር በሳቸው ስም ተሰይሟል - “ኦባማ ሹሩባ” ተብሎ፡፡ አንዳንዶች “የወንዶች የፀጉር አቆራረጥ እንኳን ቢሆን ምንም አልነበር፤ ክፋቱ ግን ይሄ የፀጉር አሰራር ስታይል ያለው በሴቶች የውበት ሳሎን ነው…” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የሰማቸው ወይም የሚሰማቸው ግን ያለ አይመስልም፡፡ በነገራችን ላይ በመዲናችን በሚገኙ የወንዶች ፀጉር ሴቶች የኦባማን ምስል (ፖስተር) በተለያዩ የፀጉር አቆራረጥ ስታይሎች ማየት የተለመደ ነው፡፡

             የአይሪሾቹ አልባሰም?! (“ኦባማ ነዳጅ ማደያ”)

      የኬንያውያን እንኳ እሺ… ምክንያት አላቸው፡፡ የአገራችን ልጅ ነው ቢሉ ያምርባቸዋል፡፡
የሚያስገርሙት አይሪሾች ናቸው፡፡ ድንገት ተነስተው እኮ ነው የኦባማን ስም የሙጥኝ ያሉት፡፡
ያውም በአየርላንድ እልም ያለ ገጠር መሃል፡፡ በዱብሊን እና ሊመሪክ መሃል ኦፋሊ ውስጥ የሚገኘው የነዳጅ ማደያ አሁን በይፋ በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ስም ተሰይሟል፡፡ “ኦባማ ነዳጅ ማደያ” ነው የሚባለው፡፡ ይሄን እንኳን ራሳቸው ኦባማም የሚያውቁት አይመስለኝም፡፡

               የዬል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶችስ?

   በአሜሪካ የሚገኘው የዬል ዩኒቨርሲቲ ሳይንቲስቶች ደግሞ ምን እንዳሰቡ አይታወቅም፡፡ ከምድረገፅ ጠፍቷል የሚባል ፍጡር በስማቸው ሰይመዋል ተብሏል፡፡ “ኦባማዶን” በዓለም ረዥሙ (አንድ ጫማ ርዝመት አለው) እንሽላሊት ሲሆን እንደ በቆሎ የተደረደሩ ጥርሶች እንዳሉት ሳይንቲስቶቹ ገልፀዋል፡፡ ለዚህ ተሳቢ ፍጥረት ስሙን ያወጡለት ሳይንቲስቶች እ.ኤ.አ በ2012 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ኦባማ ማሸነፋቸው በይፋ እስኪነገር ድረስ ዝም ብለው ሲጠብቁ ነበር፡፡ ለምን ቢባል… ድንገት ኦባማ ቢሸነፉ እንደ እንሽላሊቱ “ከምድረ ገፅ የጠፉ” የሚል በአግቦ ወይም በሾርኒ የተነገረ ስድብ እንዳይመስልባቸው ስለፈሩ ነበር፡፡

            አሁንስ አበዙት ያሰኛል!
    ይሄኛውስ ደስ አይልም፡፡ ኬንያውያን መካሪ የላቸውም እንዴ? ያሰኛል፡፡ የፀጉር ትሎች የተገኙት የኦባማ አባት የትውልድ ስፍራ በሆነችው ኮጌሎ መሆኑን የጠቆመው Tuko.co.ke የተሰኘው ድረ-ገፅ፤ እንደተለመደው አዲስ የተገኘው ትል በፕሬዚዳንቱ ስም ተሰየመ ይለናል፡፡ ለአሜሪካው መሪ ክብር ሲባልም የትሉ ሳይንሳዊ ስም “Paragordius Obamai” ተብሏል፡፡ ግን አይገርምም… የኦባማ ስም?! (ለአፍ ስለሚመች ይሆን?)   

Read 4168 times