Monday, 24 August 2015 09:54

ኢህአዴግ የግምገማ ባህሉን ይገምግም!!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(7 votes)

        አሁን ገና ባለሃብቶች የሆዳቸውን ተነፈሱ!
እዚያ ማዶ አንድ ጋቢ
እዚህ ማዶ አንድ ጋቢ
የእኔማ ጋሽዬ ኪራይ ሰብሳቢ!
እኔ የምላችሁ ----- በዘንድሮ ቡሄ የሰማችሁት አዲስ ግጥም አለ? (መኖርማ አለበት!) የቡሄ ጭፈራም እኮ  የኑሮአችን ነጸብራቅ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የቡሄ ጭፈራ ከተጀመረ ከ1500 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል ሲባል ሰምቼ ደነቀኝ፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ዲፓርትመንት ቢዘጋም ታሪካችንም አብሮ አለመዘጋቱ ያጽናናል፡፡
 በዘንድሮ ቡሄ የሰማሁት አንድ የሆያሆዬ ግጥም ምን ይላል መሰላችሁ? እዚያ ማዶ አንድ ጋቢ/ እዚህ ማዶ አንድ ጋቢ/ የእኔማ ጋሽዬ ኪራይ ሰብሳቢ! (ግምገማ መሰለ እኮ?!) መቼም  ጨፋሪዎቹ፣ያለምክንያት  ሰው ደጃፍ ላይ ሄደው ኪራይ ሰብሳቢ ሊሉ አይችሉም። የሚያውቁት ነገር  ቢኖር ነው እንጂ፡፡ (ለጸረ ሙስና ኮሚሽን መጠቆማቸው ቢሆንስ?)
በነካ እጃችን ጥቂት ፖለቲካ - ተኮር የቡሄ ግጥሞችን እንመልከት፡፡ እዚህ ማዶ ዛፍ ይታያል/ እዚያ ማዶ ዛፍ ይታያል/ የእኔማ እንትና ኒዮሊበራል! (#የባሰ አለና አገር አትልቀቅ” አሉ!) ሌላው ደግሞ እንዲህ ይላል፡- እዚህ ማዶ ይታያል በግ/ እዚያ ማዶ ይታያል በግ/የኔማ ጋሼ ኢህአዴግ! (ወቸ ጉድ አትሉም!)
ሚዛናዊ መሆን ስላለብን እነሆ ሌላ ግጥም፡- እዚያ ማዶ አንድ ሎሚ/ እዚህ ማዶ አንድ ሎሚ/ አባባ እንትና ተቃዋሚ! አንድ የመጨረሻ ወቅታዊ ግጥም አይተን ከቡሄ ጭፈራ እንውጣ፡፡ እዚያ ማዶ አንድ ጋራ/ እዚህ ማዶ አንድ ጋራ/ የእኔማ እንትና ዳያስፖራ! (ማስታወሻነቱ፡- በዳያስፖራነታቸው ለሚኮሩ የጦቢያ ልጆች!)
አሁን በቀጥታ ባለፈው ሳምንት ትኩረቴን ወደሳበው የ“ሪፖርተር” ጋዜጣ አንድ ዘገባ ልውሰዳችሁ፡፡ “ለውጭ ንግድ ዘርፍ መዳከም የመንግሥት ቢሮክራሲ ተጠያቂ ተደረገ” የሚለው ጋዜጣው፤ በንኡስ ርዕሱም “የውጭ ምንዛሪ ክምችት ማሽ    ቆልቆል አሳሳቢ ሆኗል” ሲል ዘግቧል፡፡ (አሁን ነው ዳያስፖራውን ማነቃቃት!)
አያችሁ----ዳያስፖራው በውጭ አገር ባንኮች ያስቀመጠውን ዶላር ወደ አገሩ ባንክ እንዲያዛውር ማሳመን ከተቻለ፣ (መክሊታችን አይደለማ!) ወይም ምድረ ዳያስፖራ ገንዘቡን አውጥቶ በአገሩ ኢንቨስት እንዲያደርግ ዋስትና ከተሰጠው፣ የውጭ ምንዛሪ ክምችቱ ያለጥርጥር ይመነደጋል፡፡  ባይሆን ዳያስፖራው የጠየቀውን ማሟላት ነው (ትርፍና ኪሳራውን አስልቶ!)
ቆይ ግን-----ዳያስፖራው ምንድነው ጠየቀ የተባለው? (መቼም ሥልጣን ሊሆን አይችልም!) እንደሰማሁት ከሆነ አንዱ ጥያቄው፣ “የዳያስፖራ ሚኒስቴር” ይዋቀርልን …የሚል ነው (ባጀቱን ይሸፍና!) ሌላው ጥያቄ ደግሞ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች ይፈቱ … የሚል መሰለኝ፡፡ በተለይ ለዚህኛው ጥያቄ ልማታዊ መንግስታችን በዚሁ ሳምንት መልስ መስጠት ጀምሯል፡፡ ጥቂት ፖለቲከኞች ከተከሰሱበት ወንጀል በነጻ ተሰናብተዋል (ግጥምጥሞሽ ነው እንዳትሉኝ!)  
ወደ ሪፖርተር ዘገባ እንመለስ፡፡ “በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ዘርፍ የተመዘገበው ደካማ ውጤት፣ በመንግሥት ቢሮክራሲና በአስፈፃሚዎች ድክመት ጭምር መሆኑ ተገለፀ” ይላል፡፡  
ባለፈው ሳምንት ለሁለት ቀናት (ነሐሴ 11 እና 12) በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ በሆኑት ዶ/ር አርከበ ዕቁባይ (የኦክስፎርድ ምሩቅ ናቸው!) የተመራ ውይይት፣ ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተደረገ ሲሆን በማኑፋክቸሪንግና በወጪ ንግድ ላይ የሚፈለገውን ያህል ውጤት ያልተገኘበት ምክንያት በዝርዝር ተዳስሷል፡፡ እውነቱን ለመናገር … እስከ ዛሬ ድረስ መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ እንዲህ በድፍረትና በሃቀኝነት ተወያይተው አያውቁም፡፡ (ቢወያዩ  እንሰማ ነበራ!) በተለይ የንግዱ ማህበረሰብ የሆድ የሆዱን ነው የተናገረው (ከ25 ዓመት በኋላ ያየነው ጉደኛ ለውጥ!)
የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከገቡ በኋላ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ምርት ማምረት ሲገባቸው፣ለምንድነው አራት አምስት ዓመታት የሚፈጅባቸው ያሉት ዶ/ር አርከበ፤ “ችግሩ የመንግሥት ነው? ወይስ የባለሀብቱ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት ምላሽም፣ ችግሩ የመንግሥት መሆኑን በድፍረት ተናግረዋል፡፡ (“እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር” አሉ!) በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን፣ መደገም የለባቸውም ያሏቸውን ጉዳዮችም በዝርዝር አስቀምጠዋል - ባለሀብቶቹ፡፡
ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመግባት ትልቅ እንቅፋት ሆነዋል ከተባሉት ጉዳዮች አንዱ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መስተጓጎል መሆኑን በርካቶች ተናግረዋል፡፡ የግል ዘርፉ ተወካዮች፤የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ ለወጪ ንግድ መዳከም አንድ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡  “ወደ ኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ቢኖሩም እንኳ የኃይል አቅርቦት መቆራረጥና በበቂ ደረጃ ያለመቅረቡ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ በመሆኑ፣ይህ የማይስተካከል ከሆነ ወደፊትም ችግሩ ይቀጥላል” ሲሉም ቁርጡን ተናግረዋል (የሃይል መቆራረጥንማ ለፈጣሪ ትተነዋል!)
ሁለተኛውን የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ለማስቀጠል ምን መደረግ አለበት? ሲሉ ዶ/ር አርከበ የጠየቁ ሲሆን አብዛኞቹ ተሳታፊዎች በሰጡት ምላሽ፤ በመጀመሪያው ዕቅድ ዘመን የታዩትን ችግሮች አለመድገምን እንደ መፍትሄ ጠቁመው፣ በአስፈፃሚ መ/ቤቶች ውስጥ ያሉ ቢሮክራሲዎች አላሰራ ማለታቸውን  ተናግረዋል፡፡ (ቢሮክራሲው ቀላል ተጫወተብን!)
 የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው በሰጡት ለየት ያለ አስተያየት፤ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ እንቅፋት የሆነው ብርቱ ጉዳይ፣የመንግሥት ስብሰባዎችና የግምገማ ባህሎች ናቸው ብለዋል (ኢህአዴግ የግምገማ ባህሉን መገምግ አለበት!) ግምገማ ቃሉ ራሱ አሉታዊ ትርጉም አለው ያሉት ዶ/ር አረጋ፤ ሰራተኞች ብዙ ጊዜያቸውን የሚያጠፉት እገመገማለሁ ብለው ተሸማቀው በመሆኑ፣ ለአገልግሎት መጓደል ምክንያት እየሆነ መምጣቱን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ የግል ዘርፉንና የመንግስትን ግንኙነት የተመለከተ አስተያየት የሰነዘሩት የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው፤“የግል ዘርፉ የኢኮኖሚው ሞተር ነው ይባላል፤ ነገር ግን መንግስት የግል ዘርፉን ምን ያህል ይፈልገዋል?” ሲሉ ጠይቀዋል። (ከአንጀት ነው ከአንገት? እንደማለት!) የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ፈፃሚ የግል ዘርፉ ነው ከተባለ በዕቅዱ ላይ ተሳታፊ መሆን ነበረበት ያሉት አቶ ሰለሞን፤ በተለይ በመጀመሪያው ዕቅድ ላይ እንደ ተቋም የግል ዘርፉ ያልተሳተፈ መሆኑን በማስታወስ፣መንግስት በትክክል የግል ዘርፉን መጥቀም አለበት ብለዋል፡፡
በነገራችን ላይ መንግስት----ተቃዋሚዎችን በሁለተኛው የዕድገትና ትራስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ አወያያለሁ ቢልም እስካሁን ግን የውይይት ፍንጭ አላየንም፡፡ (ሃሳቡን መቀየር መብቱ ነው!)  ቢያንስ ግን ለምን አይነግራቸውም?
 ሰናይ ሰንበት!

Read 6626 times