Friday, 11 September 2015 08:50

እንቁጣጣሽን በፖለቲካ ቀልዶች “በአገሬ ቀልድ እኮራለሁ!!”

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(23 votes)

እንኳን ለአዲሱ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ!!
ሁልጊዜ በልቤ የምፀልየውና አውራውን ፓርቲ ኢህአዴግን አብዝቼ አደራ የምለው፣አንዳንድ መብቶችን ጨርሶ እንዳይነካብን ነው፡፡ (ለመንካት ባያስብ ሁሉ ደስ ይለኛል!) ይሄን የምለው ዝም ብዬ አይደለም፡፡ እንደ ልብ እየታተሙ የሚወጡትን መፃህፍት ለመቆጣጠር የሚያስችል የመፃህፍት ፖሊሲ ይወጣል የሚባል ነገር ሽው ስላለኝ ነው፡፡ የመፃህፍት  ፖሊሲ ከሚባለው ነገር ጋር ችግር የለብኝም፡፡ ስሙን አሳምሮ ግን ወደ ቁልቁለት እንዳይሰደን ነው - ፍርሃቴ፡፡  ወደ ሳንሱር እንዳይመለስ ነው ስጋቴ፡፡ (እስካሁን ያልተሸራረፈ መብት ቢኖር … መፃህፍትን  የማሳተም መብት
ይመስለኛል!)  እናም ኢህአዴግ ------ በግጥም ተሰደብኩ፣ በትያትር ተነቀፍኩ፣ በቀልድ
ተፌዘብኝ፣ በዘፈን ተብጠለጠልኩ፣በመጽሐፍ ገበናዬ ወጣ -- ወዘተ በሚል አትንኩኝ ባይነት ወደ
አፈናና እገዳ እንዳይገባ ይጠንቀቅ (እስከዛሬ አልሞከረውም አልወጣኝም!)  በአዲሱ ዓመት ምን
እንዳሰብኩ ልንገራችሁና ወደ ፖለቲካ ቀልዶቻችን እንሂድ፡፡
የቲቪ የፖለቲካ ሾው የመጀመር ዕቅድ አለኝ፡፡ እግረመንገዴን የIdea ኮፒራይት ማስመዝገቤ
እንደሆነ ልብ በሉልኝ፡፡ ቀልዳችንን የምንጀምረው ከፈረንጆቹ ነው፡፡ በእነሱ ጀምረን በኛ
እናሳርገዋለን፡፡ (በአገሬ ፖለቲካዊ ቀልድ እኮራለሁ!)
********   
በቀድሞው የሶቭየት ህብረት ዘመን ነው፡፡ ሁለት የእስር ቤት ጓደኛሞች የታሰሩበትን ምክንያት እርስ በርስ ይጠያየቃሉ፡፡ አንደኛው እስረኛ፤ “በምን ምክንያት ነው ያሰሩህ? በፖለቲካ ነው ወይስ በተራ ወንጀል?” ሲል የወህኒ ቤት ጓደኛውን ይጠይቀዋል፡፡ “በፖለቲካ ነው እንጂ፡፡ አየህ---እኔ ቧንቧ ሰራተኛ ነኝ፡፡ አንድ ቀን ወደ ወረዳው የፓርቲ ጽ/ቤት ጠርተው የፍሳሽ ማስተላለፊያውን ቱቦ እንድጠግንላቸው ነገሩኝ፡፡ እኔም ችግሩን በደንብ ተመለከትኩና፤‹ሲስተሙ በሙሉ መለወጥ አለበት› አልኳቸው፡፡ ወዲያው ወሰዱና የ7 ዓመት እስር

አጠጡኛ፡፡;
********   
በህንድ ዴልሂ አንድ ሹፌር ከፓርላማው ፊት ለፊት በትራፊክ መጨናነቅ መንገድ ተዘግቶባት ቆሟል፡፡ በመሃል አንድ ሰው ድንገት የመኪናውን መስተዋት ያንኳኳል፡፡ ሹፌሩ መስኮቱን አውርዶ፤ “ምንድነው የተፈጠረው?” ሲል ጠየቀ፡፡ “ሽብርተኞች፤የህንድ ፖለቲከኞችን በሙሉ አፍነው፣ የ100ሚ. ዶላር ክፍያ ጠይቀዋል፡፡ ገንዘቡ ካልተሰጣቸው ሁሉም ላይ ነዳጅ አፍሰው እሳት ሊለቁባቸው ነው፤ እናም በየመኪናው እየዞርን እርዳታ እያሰባሰብን ነው” “እያንዳንዱ ሰው በአማካይ ስንት እያዋጣ ነው?” ጠየቀ ሹፌሩ፡፡ ሰውየውም፤ “2 ሊትር ገደማ ነው” መለሰ፡፡
********   
     አንድ ብላቴና አባቱ ዘንድ ይሄድና “ፖለቲካ ምንድነው?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ አባትም፤ “ልጄ፤ እስቲ በዚህ መንገድ ለማስረዳት ልሞክር፡- እኔ የቤተሰቡ ቀለብ አቅራቢ ነኝ፤ ስለዚህ ካፒታሊዝም በለኝ፡፡ እናትህ ገንዘቡን ስለምታስተዳድር መንግስት እንበላት፡፡ እኛ እዚህ ያለነው ያንተን ፍላጎቶች ለማሟላት ስለሆነ … አንተን ህዝብ እንልሃለን፡፡ ሞግዚቷን ደግሞ እንደ ሰራተኛው መደብ እንቁጠራት፡፡ ህፃኑ ወንድምህን መጪው ዘመን እንበለው፡፡ እስቲ  ይሄን አስብና ስሜት ይሰጥ እንደሆነ እየው” በማለት አስረዳው፡፡
ብላቴናው አባቱ የነገረውን እያሰላሰለ ወደ መኝታው ሄደ፡፡ የዚያኑ ዕለት ሌሊት ህፃን ወንድሙ ሲያለቅስ ሰምቶ ከእንቅልፉ ተነሳ፡፡  ወንድሙ ጋ ሄዶም የሆነውን ተመለከተ፡፡ የሽንት ጨርቁ በሽንትና በሌላም ተበለሻሽቶ ነበር፡፡ እየተጣደፈ ወደ ወላጆቹ መኝታ ክፍል አመራ፡፡ እናቱ ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ነበረች፡፡ ሊቀሰቅሳት አልፈለገም፡፡ ወደ ሞግዚቷ መኝታ ክፍልም ደግሞ ሄደ፡፡ በሩ ተቆልፏል፡፡ በቀዳዳ ሲያጮልቅ፣ አባቱን ከሞግዚቷ ጋር ተኝቶ ተመለከተው፡፡ ከዚያም ተስፋ ቆርጦ ወደ መኝታ ክፍሉ ተመለሰ፡፡ በነጋታው ብላቴናው ለአባቱ፤ “አባዬ፤ አሁን ፖለቲካ ምን ማለት እንደሆነ የገባኝ ይመስለኛል” ይለዋል፡፡
አባትም፤“ጎሽ ልጄ፤ ስለ ፖለቲካ የገባህን በራስህ ቋንቋ ንገረኝ” አለው፡፡ ልጅም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ካፒታሊዝም ከሰራተኛው መደብ ጋር አንሶላ ሲጋፈፍ፣ መንግስት ለጥ ብሎ ይተኛል፡፡ ህዝቡን ዞር ብሎ የሚያየው የለም፡፡ መጪው ዘመንም በጥልቅ አረንቋ ውስጥ
ተዘፍቋል”
********   
እስቲ አሁን ደግሞ አንድ ሁለት አገር በቀል የፖለቲካ ቀልዶችን እንመልከት (በአገር ቀልድ መኩራት ይልመድባችሁ!) በሀይሉ ገብረእግዚአብሔር ዝነኛ ወግ ፀሐፊ ነዋ! ምርጥ የፖለቲካ ስላቆችንም ይጽፋል፡፡ “ኑሮና ፖለቲካ” በሚል ርዕስ 3 የመፃህፍት ጥራዞች ላይ ደርሷል፡፡  መፃህፍቱን አድናችሁ ታነቡ ዘንድ እየጠቆምኩ፣ ለዛሬ ከፌስቡኩ ላይ ያገኘኋትን የጨረሰች የፖለቲካ ስላቅ ልጋብዛችሁ፡፡ አንድ የገዢው ፓርቲ አባል “ምርጫ በማሸነፉ” ደስ ተሰኝቶ ሚስቱ ጋ ደወለ አሉ፡፡ “ሄሎ ማሬ!”
“አቤት ውዴ!”
“ምርጫውን እኮ አሸነፍኩኝ!”  አለ ደስታ ባመጣው ፈገግታ ታጅቦ፡፡ “እውነት?” እሷም ደስታ የሚያደርጋትን አሳጥቷት ባለማመን ጠየቀች፡፡ ጥያቄዋ ግን ባልን አስቆጣው፡፡
“እ!? ምን አልሽ አንቺ!”
“እውነት አሸነፍክልኝ ወይ ነው ያልኩት”
አሁንም ደስታዋ አላበራም፡፡
“አንቺ ሴት ከፀረ ሰላም ኃይሎች ጋር መዋል ጀመርሽ ማለት ነው!?” ንዴት የሚያደርገውን

እያሳጣው፡፡
“ምን እያልክ ነው እንዴ?” ግራ ቢገባት ጠየቀች፡፡
“እዚህ ጋ ‹እውነት› የሚለውን ቃል ምን አመጣው!? ‹አሸነፍኩ› ማለት ያው  አሸነፍኩ ነው!

አይገባሽም እንዴ!”
********   
የእኛ አገር የቀልድ ምንጭ ይገርመኛል፡፡ ከትራጄዲ ውስጥ ነው የሚፈጠረው፡፡ ለዚህ እኮ ነውቀልዶቻችን መራራ የሆኑት - በተለይ የፖለቲካዎቹ፡፡ ለምሳሌ በ97 ምርጫ ማግስት የተፈጠሩ ቀልዶችን ብዛት ስናይ፣ የግንቦት 2007 ምርጫን ተከትሎ ምንም ቀልድ አልተፈጠረም ማለት ይቻላል፡፡ (እንደ 97ቱ ቀውጢ አልነበረማ!) ለማንኛውም ግን አንድ የሰማኋትን ቀልድ ከእነ አካቴው ከመርሳቴ በፊት እንደ ታሪክ ልዘግባት፡፡  ገዢው ፓርቲ ምርጫውን 100 በመቶ አሸነፈ ተብሎ የተወራ ሰሞን ነው (ምርጫ ቦርድ መሰረተ ቢስ ነው ብሏል!) ቀልዷ ግን ከቦርዱ ማስተባበያ በፊት ስለተፈጠረች … እንስማት (ቀልድና
ቁምነገር አይደባለቅም!) እናላችሁ … አንዲት እናት ለዕድርተኛቸው የልጃቸውን በትምህርት እሳት መሆን በኩራት ይደሰኩራሉ፡፡ “ይገርምሻል … ሂሳብ 100 ከመቶ፣ ሳይንስ 100 ከመቶ፣ አማርኛ 100 ከመቶ፣
እንግሊዝኛ 100 ከመቶ …!!” ዕድርተኛዋ ተገርመውና ተደንቀው ይሄዳሉ፡፡ ብዙ ተለያይተው… አንድ ቀን ይገናኛሉ - ዕድርተኛሞቹ፡፡ አንደኛዋ ዕድርተኛ እንዲህ አሉ፤ “አንቺ፤ያ ኢህአዴግሽ አደገልሽ??”
(100በመቶባመጣእኮነው!)አዲሱንዓመት የፍቅር፣የደስታ፣የሰላም፣የመቻቻል፣የሥልጣኔ፣የዲሞክራሲ፣የፍትህ፣የመልካም
አስተዳደር፣የልማት፣የብልጸግና፣----ያድርግልን!! (ረዥሙ ምርቃት ተብሎ በጊነስ እንዲመዘገብልኝ
ጥረት ጀምሬአለሁ!)

Read 9704 times