Saturday, 24 October 2015 08:50

ወጣቶቹ ሉሲዎች ለዓለም ዋንጫን ተሳትፎ 2 ጨዋታ ቀርቷቸዋል

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(2 votes)

       የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በታሪክ የመጀመርያውን  የዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ለማሳካት  በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ናቸው፡፡ ጥቁር ልዕልቶች ከሚባለው የጋና አቻው ጋር በደርሶ መልስ ግጥሚያዎች የሚገናኘው ብሄራዊ  ቡድኑ፤ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታድዬም  የመጀመርያውን ጨዋታ  ይደረጋል፡፡ የጋና ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ከትናንት በስቲያ አዲስ አበባ  የገባ ሲሆን ከሜዳ ውጭ በሚያደርገው ጨዋታ ውጤታማ ለመሆን እንድሚችሉ የአገራቸው ጋዜጦች በስፋት ዘግበዋል፡፡ የሁለቱን ቡድኖች ጨዋታ በዳኝነት የሚመሩት ኡጋንዳውያን ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ቡድን ወደ የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሜዳው በሚያደርገው የመጀመርያ ጨዋታ በሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፉ ሲጠበቅ፤ ወጣቶቹ ሉሲዎች አስቀድመው ባካሄዷቸው የማጣርያ ግጥሚያዎች ያለፉባቸው ውጣውረዶች እና ያስመዘገቧቸው ውጤቶች ለዓለም ዋንጫ ቢያልፉም ባያልፉም ዳጎስ ያለ የገንዘብ ሽልማት ሊበረከትላቸው እንደሚገባ የስፖርት ቤተሰቡ እየጠየቀ ነው፡፡   ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ
ሴቶች ብሄራዊ ቡድኑ ከጋና ጋር ከመጫወቱ በፊት ግን ትናንት ምሽት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ
የማበረታቻ ሽልማት የተበረከተለት ሲሆን፤ በግል የተገኘው ከፍተኛው 25ሺህ ዝቅተኛው 5 ሺህ
ብር መሆኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫውን ጉዞ የጀመረው በ1ኛ ዙር ቅድመ ማጣርያ ከካሜሮን ጋር በመገናኘት ነበር፡፡ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ካሜሮን ላይ ሲያደርግ 1ለ0 ቢሸነፍም ባህርዳር ላይ በመልስ ጨዋታ  በሎዛ አበራ ጎሎች 2ለ0 በማሸነፍ በአጠቃላይ 2ለ1 የደርሶ መልስ ውጤትም የካሜሮን አቻውን ጥሎ ለማለፍ በቅቷል፡፡  በሁለተኛው ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸው ወጣቶቹ ሉሲዎች ከቡርኪናፋሶ ጋር ከሜዳቸው ውጭ 2ለ0 ያሸነፉ ሲሆን አሁንም ሁለቱን ጎሎች ያስመዘገበችው ሎዛ አበራ ነበረች፡፡ ባለፈው ሳምንት በመልሱ ጨዋታ እዚህ
አዲስ አበባ ላይ ከቡርኪናፋሶ ጋር በተገናኙበት ወቅት 0ለ0 ቢለያዩም በአጠቃላይ በ2ለ0 ድምር ውጤት ለመጨረሻ የማጣርያ ምዕራፍ አልፈዋል፡፡ ጥቁር ልዕልቶች የሚባሉት የጋና ከ20 ዓመት በታች  የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በበኩላቸው በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ሴኔጋልን 8ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት በደርሶ መልስ ካሸነፉ በኋላ ፤በሁለተኛ ዙር ማጣርያ ደግሞ ኢኳቶርያል ጊኒን 3ለ0 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት በመርታት ለመጨረሻው የማጣርያ ምዕራፍ በቅተዋል፡፡8ኛውን ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ በ2016 እኤአ ፓፓዋ ጊኒ የምታዘጋጀው ሲሆን፤ ለአፍሪካ አህጉር የሁለት ብሄራዊ ቡድኖች ተሳትፎ ኮታ ተሰጥቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ጋና ትንቅንቅ ባሻገር ሌላው የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚደረገው በደቡብ አፍሪካ እና ናይጄርያ መካከል ይሆናል፡፡የኢትዮጵያ ሴቶች ወጣት ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አሥራት አባተ ቡድናቸው በዛሬው ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጥሪ አቅርቧል፡፡ ዋና አሠልጣኝ አሥራት አባተ በ2003 ዓ.ም. የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሲጀመር ደደቢትን በማሰልጠን ለዋንጫ
ያበቃ ሲሆን በደደቢት ክለብ ከሰራባቸው አምስት ዓመታት በሦስቱ የውድድር ዘመናት  ዓመት
በፕሪሚየር ሊጉ በመወዳደር ከፍተኛ ልምድ አካብቷል፡፡

Read 3833 times