Saturday, 07 November 2015 10:11

ወጣቶቹ ሉሲዎች በዓለም ዋንጫ ዋዜማ ላይ ናቸው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

    የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ለ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ በማለፍ የሉሲዎችን ታሪክ ሊለውጥ እንደሚችል ተገለፀ፡፡ በሴቶች እግር ኳስ ከፍተኛ ልምድ ያለውና ልሳን የሴቶች ስፖርት መፅሄትና ራድዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ዳግም ዝናቡ ለስፖርት አድማስ እንደገለፀው ‹‹የአባይ ፈርጦች›› በጋና ኩማሲ የጋና አቻቸውን ገጥመው ማሸነፍ ከቻሉ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን ላይ ጫና በማሳደር የተበላሸው የሉሲዎችን  የአፍሪካ ዋንጫ እና የኦሎምፒክ ተሳትፎ እድልን ሊመልሱ ይችላሉ  ብሏል፡፡  
በጋና ኩማሲ የሚገኘውና ከስፖርት አድማስ ጋር አጭር ቃለምልልስ ያደረገው ዳግም እንዳወሳው ወጣቶቹ ሉሲዎች  በጉዞ ከፍተኛ ድካም ቢገጥማቸውም ሃሙስ ማታ ቀላልና የሚያፍታታ ‹‹ዎክ›› እንደሰሩ ትናንት ከሰዓት ደግሞ አየሩን ለመለማመድ እና ቅንጅታቸውን ለማሳመር ቀላል ልምምድ እንደሰሩ ተናግሯል ፡፡ የወጣት ሴቶቹ ብሄራዊ ቡድኑ  ወደ ጋና ያቀናው ባለፈው ረቡእ ሲሆን  የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይዘሮ ጊፍቲ አባሲያ አቀባበል እንዳደረጉለት፤ በዘመናዊው የጎልደን ቱሊፕ ሆቴል እንዳረፈና በከፍተኛ የሞራል መነቃቃት ውስጥ እንደሚገኝ ዳግም ዝናቡ ገልጿል፡፡ በጋና የኢትዮጵያ አምባሳደር ወይዘሮ ጊፍቲ አባሲያ ቡድኑን በከፍተኛ ሁኔታ ማበረታታቸውን ለስፖርት አድማስ የገለፀው ዳግም፤ በኩማሲ በርካታ ደጋፊዎችን ባያገኙብ በነገው ጨዋታ ከአክራ ከተማ የተወሰኑ ደጋፊዎች ስታድዬም ገብተው  እንደሚያበረታቷቸው ቃል ገብተዋል ብሏል፡፡ የመልስ ልበል ጨዋታው በጋና ጋዜጦች ከፍተኛ ሽፋን ማግኘቱን በተጨማሪ የጠቀሰው ዳግም፤ ምንም እንኳን ለቡድናቸው አድልተው ቢፅፉም ለወጣቶቹ ሉሲዎች ከፍተኛ ትኩረት እንደሰጡ የሚያሳዩ ትንተናዎች ማቅረባቸውን አመልክቷል። በማጣርያው በምንም ጨዋታ ያልተሸነፉት፤ 13 ጎሎችን ያገቡት ጥቋቁሮቹ ልዕልቶች ነጥብ የተጋሩት እንዲሁም ሁለት ግብ የተቆጠረባቸው  በኢትዮጵያ  አቻቸው  በመሆኑ ከባድ ግምት መስጠታቸውንም አክሎበታል፡፡ ዋና አሰልጣኝ አስራት አባተ  የቡድኑን ቋሚ አሰላለፍ ባይገልፅም ምናልባትም በ4- 1- 2 - 3 አሰላለፍ ሊጫወቱ እንደሚችሉ እገምታለሁ ያለው ዳግም፤ ወጣቶቹ ሉሲዎች ምንም አይነት ጫና ሳይሰማቸው ታሪክ ለመስራት እየተዘጋጁ ነው ብሏል፡፡ የስፖርት ጋዜጠኛው ዳግም ዝናቡ በነገው እለት የሚደረገውን ጨዋታ ከኩማሲ በቀጥታ የሬድዮ ስርጭት በኤፍኤም 96.3 እንደሚያስተላልፍ አስታውቋል፡፡ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ቡድኑ ተጋጣሚውን ጋና ላይ በማሸነፍ ለዓለም ዋንጫው ያልፋል” ያሉት ዋና አሰልጣኝ አስራት አባተ  ፤ “ በቡድኑ ውስጥ ጥሩ መግባባት አለ። ባለፈው የነበረን የአቻ ውጤት መቀልበስ እንችላለን።ከሜዳ ውጭ ማሸነፍ ለቡድኑ አዲስ አይደለም። ይህ ነገር ይሳካል። ደጋፊዎች ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም” ብለዋል። የቡድኑ አምበል ሎዛ አበራ በበኩሏ “ጋናዎቹ ጠንካራ ቡድን ናቸው፣ ነገር ግን ጨዋታውን ተበልጠን አቻ አልወጣንም። በሜዳቸው በማሸነፍ ወደ ዓለም ዋንጫው እንቀላቀላለን’’ በማለት የአሰልጣኙን ሐሳብ ለኢዜአ በሰጠችው አስተያየት አጠናክራለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በመጀመርያው ጨዋታ ተጨዋቾቻቸው የፈፀሟቸው ስህተቶች  በሜዳቸው እንደማይደገሙና ጎል እንዳይቆጠርባቸው ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ለግራፊክ ስፖርስ የተናገሩት የጋናው አሰልጣኝ ማሱድ ዲዲ ድራማኒ በነገው ጨዋታ ቡድናቸው በሜዳው አስፈላጊውን ጫና በማድረግ ለማሸነፍ በቁርጠኛነት ይፋለማል ብለዋል፡፡ ለመልሱ ጨዋታ በኩማሲ በሚገኘው ባባ ያራ ስፖርትስ ስታድዬም የተፈጠረው ድባብ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለፀው የግራፊክ ስፖርትስ ዘገባ፤ አሰልጣኙ ወሳኝ ተጨዋቾቻቸው ከጉዳት በመመለሳቸው ቡድናቸው እንደተጠናከረ እንደሚያስቡ ጠቅሶ፤ ከአየቅጣጫው የግብ ሙከራዎች በማድረግ በብዙ ጎሎች ልዩነት የማሸነፍ እቅድ ይዘናል ማለታቸውን አትቷል። የኢትዮጵያን ቡድን አምበል እና እና ግብ አዳኝ ሎዛ አበራ ለማቆም የሚችሉበትን ስትራቴጂ መንደፋቸውንም አመልክተዋል። በሌላ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ በጆሃንስበርግ በሚገኘው የማክሁሎንግ ስታድዬም ናይጄርያን ታስተናግዳለች፡፡ በመጀመርያ ጨዋታው ኢትዮጰያ ከናይጄርያ ጋር በሜዳዋ 2 እኩል አቻ ስትለያይ፤ ናይጄርያ ደግሞ በሜዳዋ ደቡብ አፍሪካን 2ለ1 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ወጣቶቹ ሉሲዎች ለዓለም ዋንጫ ዋዜማ ሲደርሱ እግር ኳስ ፌደሬሽኑ ለቀጣይ ውድድሮቻቸው በነፈገው ትኩረት እየተወቀሰ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በካሜሮን አስተናጋጅነት በ2016  ህዳር ወር ላይ ከሚካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውጪ መሆኑ በከፍተኛ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኗል። ሁኔታው ዋናው ብሄራዊ ቡድኑ በኦሎምፒክ ሊኖረው የሚችለውንም እድል አጥብቦታል ተብሏል፡፡  
ከህዳር 21 እስከ 28 2015 በካይሮ በተደረገው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የማጣርያ ጨዋታዎቹ ድልድል ሲወጣ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን በማጣርያው ድልድል ላይ አለመካተቱ በፌደሬሽኑ የአፈፃፀም ችግር መሆኑ ውግዘት አስከትሏል፡፡
በፊፋ የዓለም እግር ኳስ ደረጃ ከዓለም በ109ኛ ደረጃ የሚገኙት ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ለ3 ጊዜያት የተሳተፉ ሲሆን በ2004 እኤአ ላይ አራተኛ ደረጃ በማግኘት ከፍተኛውን ውጤት ማስመዝገባቸው ይታወሳል፡፡

Read 3883 times