Thursday, 09 March 2017 07:53

‹‹ስድን ሁሉንም አቢሲኒያውያን መፍጀት እፈልጋለሁ…››

Written by 
Rate this item
(7 votes)

 --- መሣሪያዎቻቸውንና ልብሶቻቸውን በሲቪሎች የተነጠቁ ብዙዎች ተራፊዎች የለበሱት ቡቱቶ ነበር፣ ጥቂቶቹም እርቃናቸውን ነበሩ። አንዳንዶቹ ደግሞ ተሰልበዋል፤ከመሀላቸው አንዱ እሱን በኃይል ለመቆጣጠር ስምንት ሰዎች እንዳስፈለጉ ሲፎክር ነበር፡፡ ‹‹እጆቼ ደህና ናቸው›› ሲል ጮኸ፡፡ ‹‹ስድን ሁሉንም አቢሲኒያውያን መፍጀት እፈልጋለሁ…››
በዮሐንስ ዘመን የንጉሣዊ ግዛቱ ዋና ከተማ የነበረችው መቀሌ የተወሰነ ትኩረት ያላት ከተማ ነበረች፡፡ በ1895 የታህሳሥ ወር አብዛኛውን ጣልያኖቹ መከላከያዎችን ገነቡ። አንድ ቤተክርስቲያን የጥይት ማከማቻ ሆነ፡፡ የጣልያን ወታደሮችና አስካሪ ምልምሎቻቸው ዋና መከላከያቸው የሚሆነውን 230 ጫማ ርዝመት ያለውን ግምብ ሲገነቡ፣ ጣልያንኛ ዘፈኖችን ይዘፍኑ ነበር፡፡ ግንቦቹ ሲጠናቀቁም ግዙፍ ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያን ቀላል መሣሪያዎች ከላይ በኩል ስድስት ጫማ፣ ከስር ደግሞ አስራ ስድስት ጫማ ውፍረት ያለውን ግምብ ለመደርመስ አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል፡፡
የተከላካዮች ተስፋ የኢትዮጵያ ጦር አዛዦች በሰው ብዛት ምሽጉን ለመስበር እግረኛ ወታደሮችን በማከታተል ይልካሉ የሚል ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የእግረኛ ጦር ጥቃት የጣልያን መድፎች ሥራቸውን እንዲሠሩ ያደርጓቸዋል፡፡ ጣልያኖቹ ለዚህ ዓይነት ፍልሚያ የተዘጋጁት በጥንቃቄ ነበር፡፡ ለአጥቂዎቹ ሽፋን ሊሆኑ የሚችሉና ለጣልያን መድፍ የእይታ መስመር የሚከልሉ ምሽጉ አካባቢ የነበሩ ጎጆዎችን አፈረሱ፡፡ ከምሽጉ ውጪም የመከላከያ ክልል በሽቦ አጠሩ፡፡ ከደቡብ በኩል ወደ ምሽጉ ዋና መዳረሻ፣ ግራና ቀኝ ኢንጂነሮች ጥልቅ ምሽጎች ቆፈሩ፡፡ እነዚህ አሥር ጫማ ጥልቀት ያላቸው ምሽጎች ስር በየሁለት ጫማ ርቀት አንድ፣ አንድ ሜትር የሚረዝሙ ሹል እንጨቶች ቀበሩ፡፡ ከደቡብ አቅጣጫ ወደ ምሽጉ የሚንደረደሩ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሹል እንጨት የተሰካባቸው ምሽጎች አልፎ ለመሄድ ወደ መንገዱ መውጣት ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ሲያደርጉም ለጣልያን ተኩስ ምቹና ሰብሰብ ያሉ ኢላማዎች ይሆናሉ፡፡
ተርፈው ወደ ምሽጉ ግምቦች የሚጠጉ ወታደሮች፣ተጨማሪ አደጋዎች ይገጥሟቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች የሚዋጉት ባዶ እግራቸውን ነበር፡፡ ስለሆነም ጣልያኖቹ የጠርሙስና የሸክላ ስብርባሪዎችን በመንገዱ ላይ በተኑ። ኢትዮጵያውያኑ አደጋዎቹን አልፈው ከሄዱም ለጣልያን አልሞ ተኳሾች ይጋለጣሉ፡፡
አንድ ምሽግ ራሱን የቻለ ተቋም ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እንዲህ አይሆንም፡፡ ታህሣሥ ዘጠኝ አንድ ቡድን ለሰዎቹ ምግብ፣ ለእንስሶቹ መኖ ፍለጋ ምሽጉን ለቆ ወጣ፡፡ የቡድኑ አባላት በፍለጋቸው የተገነዘቡት ነገር አብዛኛው የአካባቢው ህብረተሰብ መሰወሩን ነው፡፡ ይህ የወታደሮቹን ሥራ ይበልጥ አስቸጋሪ አደረገው፡፡ የአካባቢ ገበሬዎችን እቃዎቻቸውን እንዲለዋወጡ፣ እንዲሸጡ ከማሳመን ይልቅ ወታደሮቹ ገበሬዎቹ ምግባቸውንና የከብት መኖውን የት እንደ ደበቁ ለማሰስ ተገደዱ፡፡
እነኚህ የምግብ ፍለጋ ተልዕኮዎች ቀጠሉ፡፡ የእንቅስቃሴው ክልል መስፋት ነበረበት፡፡ ውሎ አድሮ እነኚህ የምግብ ፍለጋ እንቅስቃሴዎች ከምሽጉ በስድስት ማይል ርቀት ተለጠጡ፡፡ ሌሎች የመጥፎ ገድ ምልክቶችም ነበሩ፡፡ ከሰሜኑ ጋር ያለው ግንኙነት የማያስተማምን ሆኗል፡፡ ከአምባ አላጌ በኋላ የአካባቢው ህብረተሰብ አምርሯል፡፡ በቀን የሚጓጓዙ መልእክተኞች እንቅፋቶች ገጠሟቸው፡፡ ማለፍ የሚችለው በሌሊት የሚጓጓዝ ደብዳቤ ብቻ ሆነ፡፡
በየቀኑ በሚሰጣቸው የወይን ጠጅ፤ የቡናና የመጠጥ ራሽን ሳቢያ የጣልያኖች መንፈስ የተነቃቃ ነበር፡፡ ለአውሮፓውያን ወታደሮች በተጨማሪ ሲጋሮችና ትምባሆ ይሰጧዋል፡፡ ወታደሮቹ በጭንቀትና በመጠጥ በመገፋፋት ኢትዮጵያውያኑን እንዴት እንደሚፈጇቸው ጉራ ይቸረችራሉ። ‹‹አቢሲኒያዎች! የገሃነምን መንገድ እንድታገኙ እንረዳችኋለን!›› ሲል አንዱ ጮኸ፡፡ ማታ ማታ አውሮፓውያን መኮንኖች ተሰብስበው እየጠጡ ይጮኹ ነበር፡፡
‹‹የቺያንቲ ፋሽኮዎች፣ የባርቤራ ጠርሙሶች በጠረጴዛ ስር ተንከባለሉ›› ሲል አንድ መኮንን ያስታውሳል፡፡ ‹‹ረጅም ዕድሜ ለጣልያን! ረጅም ዕድሜ ለንጉሥ ኡምቤርቶ! ረጅም ዕድሜ ለሜጀር ጋሊያኖ! ረጅም ዕድሜ ለሜጀር ቶዜሊ!›› እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡ ሜጀር ቶዜሊ ለጄኔራል ባራቲዮሪ በቃላት የተዋበ ዘገባ ላከ፡፡ ‹‹ሞራል እስከ ጫፍ ተሰቅሏል፡፡››
ታህሳስ 19 ይህ ሁሉ መንፈስ በአስደናቂ ሁኔታ ተለወጠ፡፡ ጠዋት አራት ሰዓት አካባቢ በደቡብ ምሥራቅ በሸለቆው ዳርቻ፣ ከፍታው ወደሜዳው በሚያዘቀዝቅበት አካባቢ ከፍተኛ የአቧራ ደመና ተነሳ፡፡ መሠረቱ በእግርና በፈረስ የሚተም ግዙፍ የጦር ክፍል ቅርፅም ያዘ፡፡ የራስ መኮንን ጦር ከአምባ አላጌ ድሉ እየተመለሰ ነበር፡፡
(በሬይሞንድ ጆናስ ከተጻፈውና በኤፍሬም እንዳለ ከተተረጎመው “የአድዋ ጦርነት”
መጽሐፍ የተቀነጨበ፤ 2009)

Read 6016 times