Monday, 17 July 2017 13:24

“…ሰፋ አድርጎ ማሰብ ጥሩ ነው... ”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት አቅርቦቱ ቢስተካከል የእናቶችን ጤና መጎዳትና ሕይወት መጥፋት በ40 % እና የጨቅላ ሕጻናቱን ሞት ደግሞ በ10 % እንደሚቀንስ እሙን ነው።   እንዲሁም የህጻናት ሞት በ21 % ሊቀንስ ይችላል።  ባለፈው እትም ማስነበብ የጀመርነው የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ቀጣይ ክፍል የዶ/ር ደመቀ ደሰታ በአይፓስ ኢትዮጵያ የፕሮግራም ማናጀር ማብራሪያን ከኢትዮፕያ የቤተሰብ እቅድ አፈጻጸም ጋር በማከል ለንባብ ብለናል።    
ኢትዮጵያ የእናቶችን ሞት በመቀነስ ረገድ የሚታይ ለውጥ ያስመዘገበች ሲሆን ይህም በ1990/ ከ1000፣ 000 በሕይወት ከሚወለዱ 1400/ የነበረው በ2013/ 420/ሆኖአል።  የሚሊኒየም የልማት ግቡ ባስቀመጠው የእናቶች ሞት መቀነስ መሰረት በ2015/ ከ100፡000 በሕይወት ከሚወለዱ 267/ ደርሶአል።  ሀገሪቱ በዚሁ መሰረት ጥረትዋን መቀጠል  እና አሰራሮችን ማሻሻል እንዲሁም የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ጥራት ባለው መንገድ ማዳረስ እንዳለባት የታመነ በመሆኑ በተወሰደው እርምጃ የሴቶች የስነተዋልዶ ጤና እንደሚሻሻልና ረጅም እድሜንø ጤናማነትን øምርታማ ሕይወትን እንደሚያላብሳቸው ይታመናል።
አቶ ደመቀ እንደገለጹት ህብረተሰቡ በተገቢው ሁኔታ የቤተሰብ እቅድን ተጠቃሚ ሊሆን የማይችልበት ምንድነው የሚለውን በትክክል  ይህ ነው ለማለት የተጠና ጥናት ባይኖርም ብዙ ምክንያቶች አሉት።  ለምሳሌም የሀይማኖት ተጽእኖø የቤተሰብ ተጽእኖ ø የወንድ አጋር ተጽእኖ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል በዚህም ምክንያት አብዛኞቹ ተጠቃሚዎች በመርፌ መልክ የሚሰጠውን መከላከያ ይጠቀማሉ።  መድሀኒቱን የሚወስዱትም ወደገበያ ሲሄዱ ነው።  ምክንያቱም የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ለመጠቀም መሄዴ ነው ብለው ፊትለፊት መሄድ ስለማይ ችሉ እግረመንገዳቸውን ፕሮግራማቸውን አስተካክለው መርፌአቸውን ይወስዳሉ። እነዚህ ሴቶች ቢሳካላቸው ኖሮ የረጅም ጊዜውን ወይንም ዘላቂ የሆነውን አለበለዚያም በየቀኑ የሚወሰደውን መከላከያ ይጠቀሙ ነበር።  
እንደአቶ ደመቀ ማብራተሪያ በእርግጥ አገልግሎቱ ለውጥ የለውም ማለት አይቻልም።  አገልግሎቱ እየተሻሻለ የመጣው የህብረተሰቡም ግንዛቤ መጨመርና አገልግሎቱም እየተሻሻለ በመምጣቱ የተጠቃሚው ደረጃ በፊት ከነበረው ከ4% ወደ 8 %-ከ8% ወደ 14%- ከ14% ወደ 28.29…ወዘተ እያለ አሁን ወደ 36% ደርሶአል።  በእርግጥ የተለያዩ ድርጅቶች በቤተሰብ እቅድ ዙሪያ ቀድሞውኑም ቢሰሩም እንኩዋን በትኩረት አገልግሎቱ በቅርብ እንዲገኝ øበጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲሰፋ øትምህርት መስጠት የመሳሰሉት ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶአቸው በስፋት የጀመሩት የጤና ኤክስቴንሽን ስራ ከተጀመረ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው።  ስለሆነም ችግሩ ቢኖርም እንኩዋን እድገትም መሻሻልም አለ።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ያልታቀደ እርግዝና ወዳልታቀደ ልጅ መውለድ øደህንነቱ ወዳልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ እና የእናቶችን አካል እና ስነልቡና ጉዳት እንዲሁም ሞት ያስከትላል።  ከአስር አመት በፊት ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከፍተኛ የእናቶች ሞት ከሚመዘገ ብባቸው አገሮች አንዱዋ የነበረች እና ዝቅተኛ ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ የምታቀርብ ነበረች። የዚህም ውጤት ወደ40 % የሚሆኑ እርግዝናዎች ያልታቀዱ ሲሆኑከ2 % በላይ የሚሆኑ ሴቶች ደግሞ በየአመቱ ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለማድረግ ይገደዱ ነበር።  ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የሚቻልባቸው ሕግና መመሪያ በመውጣቱና አሰራሩ በመለወጡ ምክን ያት በአስገራሚ ሁኔታ በጽንስ ማቋረጥ ምክንያት ይደርስ የነበረውን የሞት እና የተጎ ጂዎች ቁጥር እንዲቀንስ ሆኖአል።  ቢሆንም ግን አሁንም ፍላጎትን ለማርካት የሚቻልበት ደረጃ አልተደረሰም።  የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች ለህብረተሰቡ ቅርብ ሆነው ከሚሰጡት አገልግሎት አንዱ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ቢሆንም ዛሬም መጠቀም እየፈለጉ ነገር ግን አገል ግሎቱን የማያገኙ ብዙ ናቸው።    
ያልተፈለገ የእርግዝና መከላከያ በየጊዜው እየተሸሻለ እና በአይነቱም እየሰፋ በመምጣቱ ለአጠቃቀምም ምቹ የሚሆንበት አሰራርን የሚከተል ሲሆን በኪኒን ከሚዋጠው ጀምሮ በክንድ የሚቀበርø በመርፌ መልክ የሚሰጥ øሉፕ እየተባለ በሚጠራው እና ዘለቄታዊ መከላከያ ጭምር አገልግሎት ላይ ውሎአል።  ስለዚህም (2016-2020) ድረስ በታቀደው መሰረት ቁጥሩ ወደ 55/በመቶ እንዲደርስ ይጠበቃል።  
 ዶ/ር ደመቀ እንደገለጹት በመንግስት ደረጃ  በ2020/ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ ዎች ልክ ወደ 55% ይደርሳል የሚል ግምት ቢኖርም  አሁን ያለነው 2017/አጋማሽ ላይ ስለሆነ የቀሩት አመታት ትንሽ ሊመስሉ ይችላሉ።  ነገር ግን ሰፋ አድርጎ ማሰብ ጥሩ እና ከታለመው ለመድረስ በጥንካሬ ለመስራት ይረዳል።  ነገር ግን ይህ በእውነት ይደረስበታል ወይ; የሚለውን ለመመለስ ብዙ ችግሮች መፈታት ይገባቸዋል።  ለምሳሌም የወንዶችን ተሳትፎ ማጎልበት አንዱ ነው።  አንዳንድ ጊዜ ሚስቶቻቸው ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል በሚወስ ዱት እርምጃ ትዳርን እስከማፍረስ የሚደርስ ጸብ የሚፈጠርበት ሁኔታ ያጋጥማል። ወንዶቹ የልጅ ፍላጎታቸው ብዙ ጊዜ ከፍ ያለ ስለሚሆን አልፈው ተርፈውም ሌላ ሚስት በማግባት ልጆችን በርከት አድርጎ የመውለድ ነገር ይታያል።  ስለዚህም ወንዶች የሴቶችን ችግር እንዲያ ቃልሉ እና ተሳታፊ እንዲሆኑ ብዙ መስራት ይገባል።  
በአለም አቀፍ ደረጃ እንደሚታመነው የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ በእናቶችና ጨቅላዎች እንዲሁም ሕጻናት ጤናን በመጠበቅ እና ሞትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እሙን ነው።  የቤተሰብ እቅድ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ ለምእተ አመቱ ግብ መሳካት እንደ አንድ ዋና ነጠብ ተደርጎ እንደመያዙ በመቀጠል ለታለመውም ቀጣይነት ላለው የልማት ግብ አስተዋጽኦው ተፈላጊ ነው።  ያልተፈለገ እርግዝናን መከላከል ላልተፈለገ የልጅ መውለድ እንደማያጋልጥና ከዚህም ውጤት እናቶች እንደሚድኑ የታዩት ውጤቶች አስመስ ክረዋል።  ከዚህም በተጨማሪ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን መጠቀም ድህነትን ይቀንሳል øየጾታ እኩልነትን ያሰፍናልø የኤችኤቪ ኤይድስን ስርጭት ይከላከላል።  እንዲሁም የጨቅላ ሕጻናቱን ሞት በእጅጉ ይቀንሳል።  
በመልማት ላይ ባሉ ሀገራት ከ200/ ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ሴቶች አራርቆ ለመውለድ ወይንም በመጠኑ ለመውለድ እርግዝናዎች እንዲራራቁ  ለማድረግ እንዲያስችላቸው የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ዛሬም በሚገባ መልኩ አላገኙም።  በመልማት ላይ ባሉ ሀገራት (867/ ሚሊየን) በመውለጃ እድሜ ላይ ያሉ ሴቶች( 57%) አሁንም ፍላጎታቸው እንዲሟላላቸው የሚጠብቁ ናቸው።  ስለዚህም ችግሩን ለማስወገድና የእናቶችንና የጨቅላዎቻቸውን ጤንነት እንዲሁም ሕይወት ለመጠበቅ ኢትዮጵያ የሚከተሉትን እርምጃዎች ለመውሰድ ቃል ገብታለች።  
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 55%እንዲያድግ እና እስከ 2020/ የተጠቃሚዎቹ ቁጥር አሁን ባለው ተጨማሪ ወደ 6.2 ሚሊዮን ሴቶችና ልጃገረዶች እንዲያድግ ይፈለጋል።  ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያ በኢትዮጵያ እንደውጭው አቆጣጠር ከ2000/ጀምሮ በእጥፍ አድጎአል።  መንግስት አሁንም የተጠቃሚዎችን መብት በመጠበቅ እንደአስፈላጊነቱ በፈቃደኝነት መከላከያዎችን መጠቀም ለሚፈልጉ ሁሉ በሰለጠነ ባለሙያ አማካኝነት እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየሰራ ይገኛል።  ስለዚህም ፡-
ለቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት የሚውሉ መድሀኒቶችን እና የህክምና መገልገያዎችን በበቂ ሁኔታ እንዲኖሩø
የረጅም ጊዜ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ተጠቃሚዎች እንዲረዱትና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንገዶችን ማመቻቸትø
ወጣቶች  በተለይም እድሜያቸው ለታዳጊነት የደረሱ ልጃገረዶች በሚመቻቸው መንገድ አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማስቻልø
የመከላከያ መድሀኒቶች በትክክል እና በተገቢ ሁኔታ ለተጠቃሚዎች መዘጋጀታቸውን ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይገባል።  
በአለም ላይ በዳሰሳ ጥናት እንደተረጋገጠው ብዙዎች በመውለድ ላይ ያሉ ሴቶች ቢያንስ ከሁለት አመት ወዲህ ልጅ መውለድ እንደማይፈልጉ ምላሽ ተገኝቶአል።  ከእነዚህም ሴቶች 645 ሚሊዮን(74%)ሚሆኑት ዘመናዊ መከላከያዎችን የሚጠቀሙ ሲሆኑ ቀሪዎቹ ማለትም 222/ ሚሊዮን ሴቶች ግን ተጠቃሚ አልሆኑም።  የዚህም ምከንያቱ መገልገል እየፈለጉ ለፍላጎታቸው ምላሽ ያላገኙ በመሆናቸው ናቸው።  በተለይም ወጣቶች ወይንም ታዳጊዎች እድሜአቸው ወሲብ ለመፈጸም ዝግጁ በመሆኑ ብቻ ተገፋፍተው መፈጸም ቢፈልጉም ልጅ መውለድ ግን ስለማይፈልጉ ለጥንቃቄው በሚረዳቸው መንገድ ከአገልግሎቱም ባሻገር ትምህርት ማግኘት ይገባቸዋል። 

Read 809 times