Saturday, 07 October 2017 14:28

ሰንደቅ ዓላማ እና አገራዊ መግባባት?

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

የዘንድሮው አሥረኛ የሰንደቅ አላማ ቀን ጥቅምት 6 ቀን 2010 ዓ.ም ይከበራል፡፡ የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አማኑኤልአብርሃም ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፤የዘንድሮ በአል “ራዕይ ሰንቀናል ለላቀ ድል
ተነስተናል” በሚል መሪ ቃል ይከበራል ብለዋል።“የኢትዮጵያ ህዝብ የትግል ታሪክና የኢትዮጵያህዳሴ” በሚል ርዕስ በተዘጋጀ ሰነድም ላይ የፓናል
ውይይት ይደረጋል ተብሏል፡፡“ሰንደቅ አላማውን የማክበር ጉዳይ የሁሉም ዜጎች ሃላፊነት ሊሆን ይገባል” ያሉት አቶ አማኑኤል፤ ሰንደቅ አላማን በተመለከተ ጉድለቶችና እጥረቶች ካሉ፣ እንዲፈቱ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ ነው ብለዋል፡፡ የሰንደቅ አላማን ምንነትና ክብር በወጣቱ ዘንድ ለማስረፅ ዘንድሮ በት/ቤት በተሰራው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ የተሻለ ግንዛቤ ተፈጥሯል ያሉት አቶ አማኑኤል፤ከዚህ የበለጠ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያሻም ተናግረዋል፡፡የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ በተመለከተ በሶስት ንኡስ አንቀፆች የሚደነግገው የህገ መንግስት አንቀፅ 3 የመጀመሪያው ንኡስ አንቀፅ፤ “የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከላይ አረንጓዴ፣ ከመሃል ቢጫ፣ከታች ቀይ ሆኖ በመሃሉ ብሄራዊ አርማ ይኖረዋል”ይላል፡፡ መንግስት፤ ይህን የህገ መንግስቱን ድንጋጌ ለማስከበር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንቅስቃሴ እያደረገመሆኑም ተገልጧል፡፡
በአንፃሩ በሀገሪቱ ከሚታዩ ተቃውሞዎች ጋር በተገናኘ አርማ የሌለው ሰንደቅ አላማና ሌሎች የቀድሞ ዘመን ሰንደቅ ዓላማዎች በስፋት
ሲውለበለቡ ይስተዋላል፡፡ ለመሆኑ በሰንደቅ አላማ ጉዳይ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያልተቻለው ለምንድን ነው? እንዴትስ ነው አገራዊ
መግባባት መፍጠር የሚቻለው? ይህ አለመግባባት በሀገር አንድነት ላይ ተፅዕኖ ይኖረው ይሆን?
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤በሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ላይ አንጋፋ ተቃዋሚፖለቲከኞችን አነጋግሮ ሃሳባቸውን እንደሚከተለው
አጠናቅሮታል፡፡ ለፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሄው ፖለቲካዊ ውይይት ነው፡፡


============
“አሁን ያለው ሰንደቅ አላማ አቀራራቢ ነው”
አቶ ገብሩ ገ/ማርያም (የመድረክ አመራር)

በሰንደቅ አላማው ላይ መግባባት የመጥፋቱን ጉዳይ ከሌላው የሀገሪቷ የፖለቲካ ቀውስ ነጥሎ ማየት አይቻልም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የማይስማሙት ሁለት ጎራዎች ናቸው፡፡ አንደኛው ጎራ፤ የኢህአዴግና ህገ መንግስቱን ያፀደቁ ሲሆን፣ “ብሔር ብሔረሰቦች በቃልኪዳናቸው ማህተም ነው ባለ ኮከቡን ሰንደቅ አላማ ያፀደቁት፣ የቀድሞው በአንፃሩ በእሱም ስም ብሔር ብሔረሰቦች ሲጨቆኑ ነበር” የሚለው ነው። ይህ ጎራ በሰንደቅ ዓላማው ላይ ምልክት መኖሩን በቀናነት የተቀበለ ነው፡፡
ሁለተኛው ጎራ ደግሞ የቀድሞ ባንዲራ ሌጣውን ሆኖ መጠቀም አለብን የሚለው ነው፡፡ ሌጣውን እንጠቀም የሚሉት ከኢትዮጵያ አንድነት በስተጀርባ ቀድሞ የነበረውን የጨቋኝ ስርአት በድጋሚ የማምጣት ድብቅ ፍላጎት ያላቸው ናቸው። እነዚህ ሰዎች የያዙትን ድብቅ አላማ በቅጡ ያልተገነዘቡና ፖለቲካው በደንብ ያልገባቸው የዋሃን ደግሞ እነዚህን በስፋት  ሲከተሉ ይስተዋላል፡፡
እነዚህኞቹ ኢትዮጵያዊነትን የሚመነዝሩት በአሁን ዘመን ባለው ነባራዊ እውነታ ሳይሆን በቀድሞ ዘመን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በምኒልክ ዘመን መሰረት መሆን አለበት፤ ኢትዮጵያዊነት በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ወይም ኢትዮጵያዊነት በደርግ ዘመን መሰረት መሆን አለበት የሚሉ ለኔ የዋሆች ናቸው፡፡ ፖለቲካው ያልገባቸው ከፖለቲካ ውጪ የሆኑ ወገኖች ናቸው፡፡ እነዚህን የሚጠቀሙባቸው ደግሞ ድብቅ አላማ ያላቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ለእኔ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩ እስካለ ድረስ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት የሚያንፀባርቅ አርማ መቀመጡ ያስማማኛል፡፡ የድሮውን እንጠቀም የሚሉት “አንዲት ኢትዮጵያ” ካልሆነች ሞተን እንገኛለን የሚሉት ናቸው። “አንዲት ኢትዮጵያ ወይም ሞት!” የሚለውን ዘፈን ደግሞ እስኪሰለቸን በደርግ ዘመን ዘፍነናል፡፡ ግን ህዝቦች ካልተስማሙበት በዘፈንና በመፈክር ብቻ አይሆንም፡፡ ህዝቦች የአንዲት ኢትዮጵያ ወይም ሞት መርህን ከልባቸው እስካልተቀበሉ ድረስ እንዲሁ የሚሆን አይደለም፡፡ ስለዚህ አሁን ያለው የፌደራሉ ሰንደቅ አላማ ቢያንስ ይሄን ርቀት የሚያቀራርብ፣ ህገ መንግስታዊ ነው። ይሄ ፌደራሊዝም የተቋቋመው በህገ መንግስት ነው፡፡ ኢህአዴግን የፈለገ ብንቃወምና ብንጠላ፣ በህገ መንግስቱ የምንቀበላቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ ስልጣን ስንይዝ ደግሞ የምናሻሽላቸው ይኖራሉ። ነገር ግን ይሄን ህገ መንግስታዊ የሆነ ሰንደቅ አላማ አልቀበልም የሚል ሰው ኢ-ህገመንግስታዊ ነው። የፈለገውን ያህል ኢትዮጵያን ቢወድ  ይሄን ካልተቀበለ፣ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፡፡
ህግ እስከወጣ ድረስ ህጉን ተቀብሎ መተግበር ግዴታ ነው፡፡ ወደ ድሮው እንመለሳለን የሚለው ህልም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ይሄን ትውልድ በአሃዳዊ አስተዳደር ስር እጨፈልቃለሁ ብሎ የሚያስብ ሰው ፀረ-ኢትዮጵያ ነው የሚሆነው፡፡ ስህተቶችን ስናርምም ህገ መንግስቱን መሰረት አድርገን መሆን አለበት፡፡ ኢህአዴግ የሚሳሳታቸውን ስህተቶች የምንታገለውን ያህል “አክራሪ የድሮ ኢትዮጵያ አቀንቃኞችንም” እንታገላለን። እኛ ሁለቱም ላይ  ትግል እናደርጋለን፡፡
መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር አለበት። ህገ መንግስቱ እስካልተሻሻለ ድረስ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይሆንም። የፌደራል ስርአቱን በመቃወም ወደ ድሮው አሃዳዊ ስርአት እንመጣለን የሚሉ ህልመኞችም አላማቸው የሚሳካ አይመስለኝም። ፌደራል መንግስቱን የመሰረቱ ክልሎች የተስማሙበት ሰንደቅ አላማ እስከሆነ ድረስ ባለቤቶቹ እነዚህ ክልሎች ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱ ላይም ይህ ድንጋጌ ሲቀመጥም በግልፅ ተስማምተው ነው፡፡ ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር የህልውናዋ ምልክት ነው፡፡ ይሄ የማይሻር ሃቅ ነው፡፡
የፌደራሉ አካል ክልሎችም የየራሳቸው ሰንደቅ አላማ የማበጀታቸው ጉዳይ በኛ ሀገር ብቻ አይደለም፤ በሌሎችም የሰለጠኑ የፌደራል ስርአት ተከታይ ሀገራትም አለ፡፡ ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካን የመሰረቱ ስቴቶች የየራሳቸው መለያ ሰንደቅ አላማ አላቸው። በህንድም ተመሳሳይ ነው፡፡ የዚህችን ሀገር አንድነትና መግባባትን መፍጠር የሚችለው ይሄ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ ዋናው መስማማትና መግባባት ያለበት፣ ለዚህች ሀገር ፌደራል ስርአት ይበጃል? አይበጅም? በሚለው ላይ ነው፡፡
ለእኔ ፌደራል ስርአት ለዚህ ሀገር መፍትሄ ነው። ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት፣ኢህአዴግ በተገቢው መንገድ ህገ መንግስቱን ስራ ላይ ባለማዋሉ ነው እንጂ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ ፌደራሊዝም ስለሆነ አይደለም። አሁንም ለዚህች ሀገር አንድነት መጠንከር የምንተጋ ከሆነ፣ መጀመሪያ ከህሊናችን ጋር እንታረቅ፡፡ ሁለቱ ፅንፈኞች ይህቺን ሀገር የትም አያደርሷትም። ፌደራል ስርአት አንፈልግም የሚሉትም ሆነ እንደ ድሮው አሃዳዊ ትሁን የሚሉት፣ ለዚህች ሀገር ጉድጓድ እየቆፈሩ መሆኑ መታወቅ አለበት። ይህቺን ሀገር ወደፊት ማስቀጠል የሚቻለው በመነጋገርና በመደማመጥ ብቻ ነው፡፡ ይህቺን ሀገር በአንድነት ለማኖር ፌደራሊዝሙ መፍትሄ ነው፡፡
ካናዳ፣ ህንድ፣ ስዊዘርላንድ፣ አሜሪካ --- ጠንካራ ኢኮኖሚ የገነቡት በፌደራል ስርአት ነው፡፡ የፌደራል ስርአት በሌለበት እንደ ስፔን ባሉ ሃገራት እኮ መገንጠል አለ፡፡ ካታሎኒያ ተገንጥላለች፡፡ ስለዚህ አሃዳዊነት በራሱ የሀገር አንድነት ዋስትና አይሆንም፡፡ እኔ የምለው፣ እባካችሁ ይህቺን ሀገር ቆም ብላችሁ አስቧት ነው፡፡

=======================

“በሰንደቅ አላማው ጉዳይ ህዝበ ውሳኔ መደረግ አለበት”

አቶ አስገደ ገ/ስላሴ (የቀድሞ የህወሓት መስራች አባል)


የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከጅምሩ በህገ መንግስቱ ሲፀድቅ በአብዛኛው አካባቢ ብዥታ ነበር፡፡ በተለይ የሃይማኖት አባቶች፣ አዛውንቶች ጎልማሶች በቀድሞ ባንዲራ መቀየር ጉዳይ ላይ ብዥታ ነበራቸው፡፡ በርካታ ወጣትም ሲቃወም ነበር፡፡ የሰንደቅ አላማው ጉዳይ በህገ መንግስት ሲቀመጥ ደግሞ የህዝብ ተሳትፎ ውስንነት ነበረው። በአመዛኙ በኢህአዴግ ምልአተ ጉባኤ የፀደቀ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ሌሎች የህዝብ ወኪል ነን የሚሉ እንደ ኦነግ ያሉ ድርጅቶች፣ እነ ኢሰፓ አልተሳተፉበትም፡፡ በጎንደርም በትግራይም የሰንደቅ አላማውን ጉዳይ የሞት ሽረት አድርገው የሚመለከቱና መቀየሩን የማይሹ ነበሩ፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው በወቅቱ በሰንደቅ አላማው ላይ አሁን ያለው ምልክት እንዲቀመጥ በህገ መንግስት ሲሰፍር፣ የብዙ ሰዎችን ፍላጎት ያሟላ ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡
በሌላ በኩል፤ አንዳንድ የኮሚኒስት ስርአትን የሚጠሉ ሰዎች አርማው ኮከብ መሆኑ፣ የኮሚኒስት ፅንሰ ሃሳብ ነው የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። ምንም እንኳ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትን ያሳያል ቢባልም   ኮሚኒስቶች ቀይ ኮከብ መለያ እንደማድረጋቸው ሁሉ ይሄም ለዚህ ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለ፡፡ ኢህአዴግን  “ካፒታሊስት ለመምሰል የሚሞክር ኮሚኒስት ነው” የሚሉ ምሁራንም አሉ፡፡
እኔ እንኳ እስከማውቀው በትግራይ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በለቅሶ፣ በሠርግ እንዲሁም በግንቦት 20 በዓል ሳይቀር የድሮውን (ሌጣውን) ሠንደቅ አላማ ይዘው የሚወጡ ሰዎች ነበሩ፡፡ በኋላ በትዕዛዝ ሲከለከል ነው ሰው ስጋት አድሮበት ያቆመው፡፡ አሁን ላይ የሚታየው ደግሞ የኢትዮጵያ ሠንደቅ አላማን ከመያዝ ይልቅ የክልል ሠንደቅ አላማን የመያዝ ነገር ነው፡፡ በትግራይ የህውሓት፣ በአማራ የብአዴን፣ በኦሮሚያ የኦህዴድ ክልላዊ መስተዳደሮችን ሠንደቅ አላማ መያዝ አሁን በስፋት እየታየ ነው፡፡ ስለዚህ የፌደራሉ ባንዲራ ተገልሏል ማለት ነው፡፡ ለመገለሉ ምክንያቱ ደግሞ ህዝቡ ልቡ ያለው ከድሮው ሠንደቅ አላማ ጋር ስለሆነ ይመስለኛል፡፡ የአሁኑን ሠንደቅ አላማ የሚቃወሙ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ በሌላ በኩል ሠንደቅ አላማውን ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝ የሚሞክሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይሄ ተገቢ አይደለም፡፡
እንደ እኔ ለዚህ ሁሉ ዝብርቅርቅ አካሄድ መፍትሄው የኮሚኒስት ፅንሠ ሃሣብን ይዟል የሚባለውን አንድ ኮከብ ከመጠቀም ይልቅ ልክ እንደ አሜሪካው ሁሉንም ክልሎች የሚወክሉ ነገሮች ማስቀመጥ አንዱ አማራጭ ነው፡፡ በሌላ በኩል ህገ መንግስቱ ስለ ሠንደቅ አላማ ያስቀመጠው ድንጋጌ ቢፈተሽና እንደገና ህዝበ ውሣኔ ተካሂዶ እልባት ቢያገኝ መልካም ነው፡፡
ይሄ አሁን ያለው አርማ ከኮሚኒስት ጋር ይገናኛል የሚለው መላምት ዝም ብሎ የተፈጠረ አይደለም፡፡ በ1983 በተደረገው የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ “የኮሚኒስት ስርአት በመላው አለም እየወደቀ ስለሆነ ውስጣችን ኮሚኒስት ቢሆንም ላያችንን ካፒታሊስት አድርገን መቅረብ አለብን” ተብሎ ተወስኖ ነበር፡፡ አሁንም አደረጃጀቱም ሆነ ካድሬዎች የሚቀኙት በዚህ አሠራር መሠረት ነው። ይሄ መልክ መያዝ አለበት፡፡
የሠንደቅ አላማው ጉዳይ ላይ ያሉ እውነታዎች ለህዝብ ይፋ ተደርገው፣ ድጋሚ ውይይትና ህዝበ ውሣኔ መካሄድ አለበት። መሻሻያ ቢደረግ የተሻለ ነው፡፡ አሁን እኔን የሚያሠጋኝ፣ የኢትዮጵያ ዋናው ሠንደቅ አላማ እየደበዘዘ፣ የክልሎች እየጎላና በወጣቱ ተቀባይነት እያገኘ የመምጣቱ ጉዳይ ነው። ይሄ ደግሞ የሃገር አንድነት ጉዳይንም ጥያቄ ውስጥ እያስገባ ነው፡፡
ለአንድ ሠንደቅ አላማ መገዛት ማለት አንድነትን ማጠናከር ማለት ነው፡፡ ይሄ እንዲመጣ በዚህ ሠንደቅ አላማ ጉዳይ ላይ ህዝበ ውሳኔ መካሄድ አለበት፡፡


==============================

“ሁላችንም የተስማማንበት ሰንደቅ አላማ ቢኖረን ጥሩ ነበር”

አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

በአጠቃላይ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መስማማት ስለሌለ ነው በሰንደቅ አላማው ጉዳይም ወጥነት ያለው መግባባት የጠፋው፡፡ በአጠቃላይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መታጣቱ ሰንደቅ አላማው ላይም ተንፀባረቀ እንጂ በራሱ ብቻውን የቆመ ችግር አይደለም፡፡ በተገቢው መንገድ ወደ ስልጣን አልመጡም የሚላቸውን ህዝብ በራሱ መንገድ ይቃወማል፡፡ ተቃውሞው የተለያየ መገለጫ አለው። አንደኛው በእነሱ ዘመን የመጣውን ሰንደቅ አላማ በመቃወም ነው የሚያንፀባርቀው፡፡ ሰንደቅ አላማው ላይ ያን ያህል የከረረ ልዩነት ኖሮ ሳይሆን፣ የፖለቲካ አለመግባባቱ አንዱ መገለጫ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡
በእርግጥ ስርአት በተለወጠ  ቁጥር ሰንደቅ አላማችን የሚለዋወጥ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡ ሁሉም ወደ ስልጣን የሚመጡ አካላት መገለጫችን የሚሉትን አርማዎች ቢያስቀምጡበትም መሰረታዊ ቀለማቱ አልተቀየረም፡፡ ይሄ ግን በራሱ የልዩነት ምንጭ መሆኑ የሚያሳዝን ነው፡፡ የሁላችንም ስምምነት ያለበት ሰንደቅ አላማ ቢኖረን ጥሩ ነበር። አንድ ፓርቲ ወይም ድርጅት የራሴ የሚለውን ነገር ሲያደርግ የሌሎችን ስምምነት ያገኛል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እያየን ያለነው ይሄንኑ ነው፡፡ ሁልጊዜ ትውልድ ይዞት የሚቀጥል፣ የስርአት ለውጥ ወይም የመንግስት ለውጥ በመጣ ቁጥር የማይለወጥ ሰንደቅ አላማ ቢኖረን ጥሩ ነው። ይሄ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ይህ አይነቱን ነገር ትልቅ የልዩነት አጀንዳ ማድረግ ተገቢ አይሆንም፡፡ ብዙ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለብን ህዝቦች ነን፡፡ እያንዳንዱን ነገር የልዩነት ማዕከል አድርገን መናቆር ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አሁን በኢትዮጵያ  በህግ እውቅና ያለው ሰንደቅ አላማ በኔ እምነት ኮከቡ ባይጨመርበት ይሻል ነበር ብዬ አምናለሁ፤ ግን እሱ ተጨመረ ብዬ ከፍተኛ የልዩነት አጀንዳ ማድረግ ደግሞ አልፈልግም፡፡ በዚህ ዘመን መሰረታዊ በሚባሉ ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች፡- በብሄራዊ መዝሙር፣ በሰንደቅ አላማ፣ በካርታ፣ በድንበር ልዩነት ውስጥ ወድቀን መታየታችን በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ በርካታ ሀገሮች እንዲህ ያለውን ጉዳይ ከተሻገሩት በርካታ አመታት አስቆጥረዋል። ስለዚህ እኛም ከዚህ ነገሮች በመሻገር፣ ሌሎች በህብረተሰቡ የእለት ተእለት ኑሮ ላይ ተፅዕኖ በሚያሳድሩ ውስብስብ ችግሮች ላይ ማተኮሩ ይሻላል፡፡
መንግስትም ሁሉም ያልተግባባበትን ነገር ማስመቀጡ  ተገቢ አይሆንም፡፡ ትውልድን ማግባባት የሚችል ነገር እየፈጠርን ነው መሄድ ያለብን፡፡ ሰንደቅ አላማ እንደ አንድ ተቋም ነው የሚቆጠረው፤ ስለዚህ መንግስት በተለዋወጠ ቁጥር ተቋማቶቻችን እየተለዋወጡ መቀጠል የለባቸውም። ቀጣይ ሆነው በእነሱ ላይ እየገነባንባቸው መሄድ መቻል አለብን። እንደኔ ከሆነ፣ በሰንደቅ አላማው ላይ የሚታየው ልዩነት የአጠቃላይ የብሔራዊ መግባባት እጦታችን አንዱ መገለጫ ነው፡፡
የሰው ልጅ አንድ ነገር መቀበል የሚችለው ስለተገደደ አይደለም፡፡ ልቦናው ነው መቀበል የሚችለው፡፡ ስለዚህ የሚሻለው ከሆነ አርማውን ከሰንደቅ አላማው ላይ ማውጣት፤ ይሄ ካልተቻለ ደግሞ ሌላው ህዝብ ከነቅሬታው ዋና ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ማተኮር ነው፡፡ አርማው ቢሻክረንም ተቀብለን መሄዱ ጉዳት የለውም፡፡
በሰንደቅ አላማውም ሆነ በአጠቃላይ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚቻለው መንግስት በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሲመረጥ ነው። በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት የሚያወጣቸው ደንቦች፣ መመሪያዎች የመከበር አቅማቸው ከፍተኛ ነው፡፡ የኔ መንግስት ነው የሚል ስሜት ይፈጠራል፡፡ በዚህ መንገድ ያልመጣ መንግስት ከሆነ  ግን ብሄራዊ መግባባት መፍጠር አይቻልም፡፡ ህብረተሰቡ ተቃውሞውን በተለያየ አግባብ ሊያንፀባርቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ ዋናው መፍትሄ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አድርጎ፣በህዝብ  የተመረጠ መንግስት ወደ ስልጣን ማምጣት ነው። ለዚህ ቁልፉ ጉዳይ ደግሞ ዲሞክራሲ ነው፡፡

=============================


“በሰንደቅ አላማ ጉዳይ የህዝብ ድምፅ
የሚሰማበት መድረክ መፈጠር አለበት”

ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (ፖለቲከኛ)

ሁሉም ነገር ከፖለቲካ ጋር ስለሚያያዝ ነው በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይም መግባባት የማይቻለው፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ስላልተፈቱም ነው ውዝግቡ የቀጠለው፡፡ ሰንደቅ አላማ በአሁን ወቅት የአንድ ሉአላዊ ሀገር መገለጫ ከመሆን አንሶ የፖለቲካ አመለካከትን እየወከለ ነው የመጣው፡፡ በዚህ ደግሞ ሃገርንና የፖለቲካ አመለካከትን ነጥሎ ማየት እስከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡
የዜግነት የሉአላዊነት ጉዳይ እና ሀገር ምንድን ነው? የሚሉ ነገሮችን በተለይ መንግስት ከጎሰኝነትና ከፖለቲካ አመለካከት ጋር እያደበላለቀ ስለሚመለከት፤ የጠራ መልክና የመጨረሻ ፖለቲካዊ መፍትሄ ባለማግኘቱ፣ እነዚህ ሁሉ ተደበላልቀው የሰንደቅ አላማ ጉዳይ ከሀገር ውክልና ወርዶ፣ የፖለቲካ አመለካከት ወካይ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ የማያግባቡ ነገሮች ቢኖሩም እነዚያ የታሪክ ሂደት መሆናቸው ታውቆ፣ ላሉት የፖለቲካ ጥያቄዎች ብሄራዊ እርቅም ይሁን ብሄራዊ መግባባት ወይም ሌሎች መፍትሄዎች ቀርበው፣ ህዝቡ ወዶና ፈቅዶ የያዘው ወጥ አቋም እስካልተፈጠረ ድረስ እንዲህ ያለው ነገር የሚቀጥል ይሆናል፡፡
ኢህአዴግ የራሴ ባንዲራ ይላል፣ ሌሎች የራሳቸውን ባንዲራ ይመርጣሉ፣ ቀሪዎች ደግሞ በፊት የነበረውን ባንዲራ ይከተላሉ፡፡ አገዛዙ ይሄን ልዩነት እስከዛሬ መፍታት  አልቻለም፡፡ ከሰንደቅ አላማው በመለስ ኢትዮጵያ ብለን የምንግባባበት የጋራ ስነ ልቦና እና አገር እንዲሁም  ዜግነት ጉዳይ ከፖለቲካ አመለካከት ጋር ተደበላልቋል፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ኢትዮጵያን አንድ ሉአላዊ አገር አድርጎ ለመቀበል እስከመቸገር አድርሶናል ማለት ነው። ይሄ ደግሞ በሀገራችንና በሉአላዊነታችን ላይም የተቃጣ አደጋ አድርጎ ማየት ይቻላል፡፡
ፖለቲካ መሰራት ያለበት ከሀገር በታች ነው፤ ነገር ግን አገርን በመተርጎም ደረጃም ገና አለመግባባት መኖሩን ከውዥንብሮቹ መረዳት እንችላለን፡፡ ስንጥቅ መኖሩንና በስጋት ላይ ያለ ነገር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ያለው ስርአት ደግሞ ልዩነትን ከፍ ከፍ አድርጎ፣ አንድነትን ዝቅ ዝቅ የሚያደርግ ስለሆነ ፍሬው በሚገባ እየታየ መሆኑን የሚያመላክቱ  በርካታ ምልክቶች አሉ፡፡
እርግጥ ነው ፍፁም እንከን አልባ ሆኖ የተገነባ ሀገር በአለም ላይ የለም፤ ነገር ግን እነዚያን የቀደሙትን ችግሮች ዋና ጉዳይ አድርጎ አሁንም ለፖለቲካ ጥቅም ማዋል፣ መራራቅና መለያየትን ይፈጥራሉ። ቅኝ ገዥዎች እንደሚያደርጉት የከፋፍለህ ግዛው ስልት፣ መናናቅና መፈራረጅ ስለተንሰራፋ፣ ሰንደቅ አላማውም የዚያ ማንፀባረቂያ እየሆነ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትም አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
በአሁን ወቅት ህዝብ ምን ይፈልጋል? መንግስት ምን ይፈልጋል? ለማለትና ለመወያየት የሚያስችል መድረክ የለንም፡፡ እውነት አሁን በየቦታው የሚደመጠው  አመለካከት የኢትዮጵያን ህዝብ ይወክላል ወይስ አይወክልም? የሚለውን የምንፈትሽበት መድረክ የለም፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ በሰንደቅ አላማው ጉዳይ ያለው አቋምም በእነዚህ መድረኮች መፈተሽ  የሚችል ነው፡፡  ያ እንዲሆን ግን መድረኮቹ መከፈት አለባቸው፡፡  አሁን ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ምን እንደሚሉ ማወቅ የማይቻልበት፣ በአንፃሩ የፖለቲካ ልሂቃን የፅንፍ አስተሳሰቦች ሽኩቻ ብቻ የሚንፀባረቅበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡
አሁንም ቢሆን በሰንደቅ አላማውም ሆነ በሀገሩ ጉዳይ የህዝቡ ድምፅ የሚሰማበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ አሁን የሚሰማው ድምፅ በስልጣን ሻሞ ሻሞ ሽኩቻ ውስጥ የገባው፣ የኢትዮጵያ የከሸፈው የፖለቲካ ልሂቅ ድምፅ ነው። እውነተኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ድምፅ እየተሰማ አይደለም፡፡ የሚሰማበት አማራጭ መመቻቸት አለበት፡፡

Read 4540 times