Saturday, 09 December 2017 14:03

ከዓሳ አስጋሪነት እስከ ኢንቨስተርነት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ተወልደው ያደጉት በባህርዳር ዙሪያ ጣና አካባቢ ነው፡፡ ቤተሰቦቻቸው ዓሳ አስጋሪዎች ነበሩ፡፡ ከልጅነታቸው አንስተው ዓሳ እያሰገሩ ነው ያደጉት፡፡ የዓሳ ኮርፖሬሽን የሚባለው የመንግስት ድርጅት ተቋቁሞ፣በግል ዓሳ ማስገር ሲከለከል የሥራ ዘርፋቸውን ቀየሩ፡፡ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እየገዙ በበቅሎ መሸጥ እንደጀመሩ ይናገራሉ - የዛሬው ኢንቨስተር አቶ ካሣሁን ምስጋናው፡፡ በ1982 ዓ.ም በራሳቸው ስም ንግድ የጀመሩት ባለሃብቱ፤ከመንግስት ለውጥ በኋላ በፀደቀው የንግድ ህግ መሰረት ድርጅታቸውን ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ ፒኤልሲ ብለው በማቋቋም በከፊል ተቋራጭነትና በማሽነሪ ኪራይ ሥራ የጀመሩ ሲሆን ዛሬ የ5 ቢሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ባለቤትና የ5 ሺህ ሰራተኞች ቀጣሪ ለመሆን በቅተዋል፡፡
         ባለሀብቱ በቅርቡ በባህርዳር 360 ሚ. ብር የፈጁ የእብነበረድና የቀለም ፋብሪካዎችን ገንብተው አስመርቀዋል፡፡ በቅርቡ ሥራ የሚጀምር የዘይት ፋብሪካም እየተከሉ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ባለሀብቱ ከዓሳ ማስገር ተነስተው አሁን እስከደረሱበት ስኬት ያለውን ጉዞ ከባለሃብቱ ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ ታስቃኘናለች፡፡ የወደፊት ዕቅዳቸውንና ህልማቸውንም አውግተዋታል፡፡ የአቶ ካሣሁን ምስጋናውን አስደማሚ የንግድ ሥራ ግስጋሴ ከአንደበታቸው እነሆ፡-


    ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ እንዴት ነው የተመሰረተው?
ስለ ቢአኤካ ከመናገሬ በፊት በግል ስሜ ነበር የንግድ ስራዬን የጀመርኩት፡፡ እስከ 1982 ዓ.ም በግል ስሜ ስሰራ ከቆየሁ በኋላ በአገራችን በተፈጠረው የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና ለውጥ ፒኤልሲ የሚባል ነገር ሲመጣ፣ ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ በሚል አቋቁመን መስራት ጀመርን ማለት ነው፡፡ ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ  ቀደም ብለው የነበሩትን የእኔን ልምዶችና ሀብት ይዞ ነው የተመሰረተው፡፡
ቢአኤካ ሲመሰረት መጀመሪያ ምን ነበር የሚሰራው?
መጀመሪያ የተነሳነው በኮንስትራክሽን ሥራ ነበር፡፡ ስራ የጀመርነው ከፊል ተቋራጭ በመሆንና የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች በማከራየት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ ወደ ግብርና ገባን፡፡ ግብርናው በቡና እርሻ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ዛሬ ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ፣ 2700 ሄክታር መሬት ላይ ቡና ያለማል፡፡ ሰፊ የቡና እርሻ ያለው ድርጅት ነው፡፡
በአስመጪና ላኪነት ላይም መሰማራታችሁን ሰምቻለሁ---
እውነት ነው፡፡ እንግዲህ ሰፊ የቡና እርሻ ባለቤት እንደመሆናችን፣ ቡና በአብዛኛው ወደ ውጭ የሚላክ በመሆኑ የራሳችንን ቡና በጥራት እሴት ጨምረን ለመላክ በኤክስፖርቱ ዘርፍ ተሰማራን፡፡ ቡናው ለመላክ እስኪደርስ በሰሊጥና በአጠቃላይ በጥራጥሬና በቅባት እህሎች የላኪነት ስራውን ስንሰራ ቆየን፡፡ ድርጅታችን በቅባት እህሎችና ጥራጥሬ ይዞት የቆየውን ልምድ በመንተራስ፣ ከራሱ እርሻ “ስፔሻሊቲ ቡና” የሚባል የቡና ምርት ለውጭ ገበያ መላክ ጀመረ፡፡
የቡና እርሻችሁ የት ነው የሚገኘው?
የቡና እርሻው በማጂንግ ዞን ጎደሬ የተባለ ወረዳ ውስጥ ይገኛል፤
የምትልኩት “ስፔሻሊቲ ቡና” ከሌላው የቡና ምርት ልዩነቱ ምንድን ነው?
ቡናው በጣም ኦርጋኒክ ነው፤ ከየትኛውም ንክኪ ነፃ የሆነና ደረጃውን የጠበቀ ቡና ሲሆን ለዚህም የተሰጠን ሰርተፍኬት አለ፡፡ አሁን በቅርቡ መንግስት ባሻሻለው የቡናና ሻይ አዋጅ፤ “አውት ግሮስ” የተባለ የአካባቢውን ቡና እርሻ ያላቸው ኢንቨስተሮች፣ ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ይላኩ በሚለው መሰረት፤ እኛም የአካባቢውን ቡና እየገዛን፣ ከራሳችን ቡና ጋር እያደረግን ደረጃውን የጠበቀ “ስፔሻሊቲ ቡና” በተለይም ለአውሮፓ ገበያ እንልካለን፡፡ ድርጅታችን ኤክስፖርቱን በማስፋፋት ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ወደ ማምረት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ገብቷል፡፡ በቅርቡ ሥራ የጀመረው “ኮከብ የእብነበረድ ፋብሪካ” ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ፋብሪካው ለጊዜው የእብነበረድ ምርቱን ለአገር ውስጥ ገበያ ያቅርብ እንጂ በሁለት መልኩ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡
በሁለት አይነት ሲባል ምን ማለት ነው?
አንደኛው ቀጥታ ከቦታው የእብነብረድ ቋጥኝ ቆርጦ እንዳለ መላክ ነው፡፡ ሁለተኛው በደንብ ሰርቶና እሴት ጨምሮ ያለቀለት ምርት መላክ ነው። እንግዲህ ይህ ፋብሪካ ከ”ኮከብ ቀለም ፋብሪካ” ጋር በአንድ ላይ በ18ሺህ ካሬ ሜትር ላይ አርፎ፣ በባህርዳር ተገንብቷል፡፡ የእብነበረድና የቀለሙ ፋብሪካ በአጠቃላይ 360 ሚ. ብር ነው የወጣበት። የቀለም ፋብሪካው የተቋቋመበት ዋና አላማ የእብነበረዱን ተረፈ ምርት እየተጠቀመ፣ ጥራት ያለው የኳርትዝና የውሃ ቀለም ለማምረት ታስቦ ነው፡፡ ስለዚህ በተረፈ ምርትነት የሚጣል ነገር አይኖረውም፡፡ ፋብሪካዎቹ በሙሉ ሀይላቸው ስራ ሲጀምሩ ለ500 ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራሉ። ሌላው እንግዲህ ምርቱ ወደ ውጭ ገበያ ሲቀርብ ትልቅ የውጭ ምንዛሪን ያመጣል፡፡ ጥቅማቸው ዘርፈ ብዙ ነው፡፡
የእብነበረዱ ጥሬ እቃ ምንጩ ከየት ነው?
ማዕድኑ የሚወጣው ማንኩሽ ከተባለ ቦታ ነው፡፡ እዛው ቦታ ላይ “ዳይመንድ ዋየር” የተባለ የእብነበረድ ፕሮስስ ማድረጊያ ፋብሪካም ተክለናል። ይህ ፋብሪካ የእብነበረዱ ማዕድን እንደወጣ እዛው እየቆረጠና እያስተካከለ ኤክስፖርት ለማድረግ ያግዛል፡፡ የቀለም ፋብሪካውንም ብንወስድ በዓመት 25 ሚ. ሊትር በላይ የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ከአገር ውስጥ ገበያ ተርፎ ለጎረቤት አገራት ምርቱን ኤክስፖርት የማድረግ እቅድ ይዞ ነው እንቅስቃሴውን የጀመረው፡፡ ለዚህም ነው ከአገራችን አቅም በላይ የሆኑ የአውሮፓ ማሽኖችን መርጠን አምጥተን የተከልነው፡፡ ማሽኖቹ የጣሊያን የዴንማርክና የቤልጂየም ስሪት ናቸው፡፡ እነዚህ ማሽነሪዎች ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶችን ለማምረት የሚረዱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁለት ፋብሪካዎች በከፊል ስራ ጀምረዋል፡፡ እስካሁን በአንድ ሺፍት ነው የሚሰሩት፤ከ200 በላይ ሰራተኞች ሥራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ቢአኤካ ጀነራል ቢዝነስ በአሁኑ ወቅት ጠቅላላ ኢንቨስትመንቱ ምን ያህል ነው? በአጠቃላይ ምን ያህል ሰራተኞች አሉት?
የድርጅቱ ጠቅላላ ኢንቨስትመንት ወደ 5 ቢ. ብር ነው፤ በስሩ ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞችን ይዟል። እንግዲህ በቀጣይ የሚከፈቱ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ ከ5ሺህ ሰራተኞች ውስጥ ግማሽ ያህሉ በእርሻውና በኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ላይ እየሰሩ ይገኛል፡፡
የኮንስትራክሽኑ ዘርፍ ምን ምን ስራዎችን ያከናውናል?
ኮንስትራክሽኑ በአገራችን የሚሰሩ ትልልቅ መንገዶችን፣ የባቡር መንገዶችንና እንደ ሳሊኒ ባሉ ትልልቅ ዓለማቀፍ ኩባንያዎች የሚገነቡ ፓወር ሀውሶችን “Earth work” ወይም የአፈር ስራዎችን በከፊል ቢአኤካ ነው የሚሰራው፡፡
የእብነበረድ ፋብሪካው የማምረት አቅሙ ምን ያህል ነው?
በዓመት 500 ሺህ ሜትር ካሬ ያለቀለት እብነበረድ ያመርታል፡፡ ይሄ በዳይመንድ ዋየር እየተቆረጠ እንዲሁ የሚላከውን ያላለቀለት እብነበረድ አይመለከትም፡፡ በዚህም በዓመት እስከ 5 ሚ. ዶላር የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት እንደ ጅምር እቅድ የያዝን ሲሆን በሙሉ ሀይላችን ወደ ስራ ስንገባና የውጭ ገበያን ስናስፋፋ ገቢውን ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር ለማድረስ አቅደን እየሰራን ነው፡፡ ይሄ ለአገርም ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ቀላል አይደለም፡፡
ቢአኤካ እያስገነባቸው ያሉና በቀጣይ የሚገነቡ ፋብሪካዎችም እንዳሉ ይነገራል፡፡ እስቲ ስለዚህ ጉዳይ ያብራሩልን?
እንግዲህ ድርጅታችን ትኩረቱን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አድርጓል፡፡ በቅርቡ የሚጠናቀቅና በአዲስ አበባ ዙሪያ ታጠቅ ኢንዱስትሪ መንደር እየተገነባ ያለ ትልቅ የዘይት ፋብሪካ አለን፡፡ ፋብሪካው 200 ሚ. ብር ነው የወጣበት፡፡ ዋና መጭመቂያ ማሽኑ የመጣው ከአሜሪካ ሲሆን መፍጫው ከቻይና፣ ማጣሪያው ከህንድ ነው የመጣው፡፡ በአሁኑ ሰዓት የውጭ አገር ባለሙያዎች መጥተው፣ የማሽን ተከላ ስራ እያካሄዱ ሲሆን ከአንድ ወር በኋላ ወደ ስራ ይገባል፡፡ ፋብሪካው በዓመት 10 ሚሊዮን ሊትር የሱፍ የኑግ፣ የሰሊጥ፣ የአኩሪ አተርና የተልባ ዘይት የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ከፋብሪካው ብዙ ጠቃሚ አላማዎች መካከል አንዱ ደህንነቱ የተጠበቀ ዘይት ለአገራችን ህዝብ ማቅረብ ነው፡፡ ሁለተኛ ከውጭ የምናስመጣውን የፓልም ዘይት በማስቀረት የውጭ ምንዛሪን ማዳን ነው፡፡ በሌላ በኩል ለ200 ሰዎችም የስራ እድል የሚፈጥር ነው። እኛ ሰሊጥ ኑግ፣ አኩሪ አተር፣ ተልባና ሱፍ ወደ ውጭ እየላክን የፓልም ዘይት እናስገባለን፡፡ ያለንን ምርት እዚሁ ጤናማ ዘይት ለምን አናመርትበትም በሚል ታስቦ ነው የተቋቋመው፡፡ ከስድስት ወር በኋላ ወደ ተከላ የሚመጡ ሌሎች ፋብሪካዎችም አሉን፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች የግራናይትና የቴራዞ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ፋብሪካዎች ልክ እንደ እብነበረዱና እንደ ቀለሙ ፋብሪካ ተመጋጋቢ ናቸው፡፡ የግራናይት ፋብሪካ ተረፈ ምርት ለቴራዞ ፋብሪካው ዋና ግብአት የሚሆን ነው፡፡ የማርብልና ግራናይት ፍቅፋቂ በመፍጨትና መልሶ በመጋገር ደረጃውን የጠበቀ ቴራዞ መስራት ይቻላል፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በባህርዳር ነው የሚገነቡት፡፡ የሁለት ዓመት ዕቅድ የተያዘላቸው የሴራሚክስና የጥቅል መስታወት ፋብሪካዎችም ጠቅላላ ንድፍና ስራ አልቆ ከሁለት ዓመት በኋላ እውን ይሆናሉ፡፡ መሬት ወስደን ጨርሰናል፡፡ የነዚህ ምርቶች 98 በመቶ ጥሬ እቃ ከአገር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
ሌላው በአዲስ አበባ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ በ50 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ “ጀነራል ኬሚካል እና ፓኪንግ” የሚባል ፋብሪካን ግንባታ ላይ ነው ያለነው፡፡ በዚህ መልኩ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪውን በሰፊው እየተቀላቀልን እንገኛለን፡፡ ለዚህም ቀን ከሌሊት ያለ እረፍት ነው የምንሰራው።
በንግድ ሥራ ስኬታማ ለመሆን የረዳዎት ትምህርት ወይም ልምድ ካለ ቢነግሩኝ---
እንግዲህ ወደ ኋላ ልትመልሺኝ ነው፡፡ እኔ ባህር ዳር ዙሪያ ነው ጣና አካባቢ ተወልጄ ያደግሁት። ዓሳ በማስገር ህይወት የሚመራ ቤተሰብ ልጅ ነኝ። ዓሳ በማስገርም ላይ ነበርኩ፡፡ በ1982 ዓ.ም አካባቢ የለውጡ ሰሞን ዓሳ ኮርፖሬሽን የሚባል ተቋቋመና ዓሳው ሁሉ ለኮርፖሬሽኑ እንዲሆንና ግለሰቦች ዓሳ እንዳያሰግሩ ሲከለከል፣ ከ7ኛ ወደ 8ኛ ክፍል ባለፍኩበት ወቅት ነበር ትምህርቴን አቋርጨ ሸቀጣ ሸቀጥ እየገዛሁ በበቅሎ እየሸጥኩ ንግድ የተለማመድኩት፡፡ ከ1983 ዓ.ም ለውጡ ተደርጎ አገር ነፃ ሆነ ከተባለ በኋላ መጀመሪያ ላይ እንደነገርኩሽ፣ መጀመሪያ በግል ስሜ፣ ከዚያም ፒኤልሲ ከፍቼ ስሰራ ቆይቼ እዚህ ደርሻለሁ፡፡ ይሄው ነው፡፡
እንዲህ አይነት ሰፊ ኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ከንግድ ፈቃድ ጀምሮ መሬት እስከመረከብ ከፍተኛ ውጣ ውረድና ቢሮክራሲ እንደሚያጋጥማቸው ብዙ ባለሀብቶች ሲያማርሩ ይሰማል፡፡ እርስዎ በዚህ ረገድ የገጠመዎት ችግር አለ?
ብዙዎች ቦታ ይወስዱና ለረጅም ጊዜ አጥረው ያስቀምጣሉ፡፡ እኛ አካባቢ አጥሮ የሚያስቀምጠውንና ቶሎ ወደ ሥራ የሚገባውን ለመለየት ከሚወስደው ጊዜ በስተቀር ምንም ችግር የለም፡፡ እኔም እስከ ዛሬ እሰራለሁ ያልኩትን በወቅቱና በአግባቡ እየሰራሁ በማሳየት ነው እዚህ የደረስኩት፡፡ እንደውም የበለጠ ትብብርና ድጋፍ እንጂ ያጋጠመኝ ችግር የለም፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በፋብሪካው ምርቃት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በስራ ላይ አንዳንድ ችግሮች አይጠፉም ግን በትዕግስት ማለፍ ያስፈልጋል፡፡ ያው በፋብሪካዎቹ በርካታ ሰዎች በመቅጠር ከሴራሚክሱ በካሬ 10 ብር፣ ከቀለም ፋብሪካው ከሊትር 10 ሳንቲም በመቁረጥ እንቦጭን ለመዋጋት የሚደረገውን ትግል በማገዝ፣ ለአገራችንና ለወገናችን የበኩላችንን እያደረግን እንገኛለን፡፡

Read 3291 times