Sunday, 10 June 2018 00:00

“ምች ምግብ ቤት እንገናኝ”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(5 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እዚህ መዲናችን ምስራቃዊ ክፍለ ከተማ አካባቢ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤት አለ፡፡ እናም… በአካባቢያቸው ብቅ የሚሉባት አንዲት ምግብ ቤት አለች፡፡ ታዲያ ምግብ ቤቷ ስም ሲወጣላት ታሳቢ የተደረጉት…(እንደ ዘመኑ ለመናገር ያህል ነው!…) በአካባቢው ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። እናማ…የቤቷ ስም ምን መሰላችሁ…‘ምች ምግብ ቤት!’ ለምን ቢባል፣ የመንግሥት ሠራተኞቹ በወር ሦስት ቀን ይመጡና ከዛ ይጠፋሉ፡፡ በቃ…አለ አይደል… በበሯ እንኳን አያልፉም፣ ኪስ ባዶ ነዋ! ያውም ይሄ ስም ለምግብ ቤቷ የወጣላት፣ የሰሞኑ አስደንጋጭ የዋጋ ንረት ከመምጣቱ በፊት ነው፡፡ እንደውም የመንግሥት ሠራተኞቹ ሲገቡ “ምቾች መጡ…” ነው የሚባለው አሉ፡፡ ደግነቱ ፌጦ ምናምን ሳይነሰንሱባቸው በሦስተኛው ቀን ይጠፋሉ፡፡ ያኔ “ምች” ያሏት አሁን ምን ሊሏት ነው!…‘መጋኛ’ ምግብ ቤት! የምር እኮ…ሁለት ሦስት ሆኖ ምሳ ቢጤ ለመገባበዝ፣ ፕሮፎርማ መሰበሰብና የጠቅላይ ግምጃ ቤትን የሦስት ወር ብድር መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ የእውነት ግን…እሱ ነገር አሁንም አለ እንዴ!
እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የዶሮዎች መብት አስጠባቂ ድርጅት የማናቋቋምሳ! ልክ ነዋ… እነሱ የሚጥሏት አንዷ እንቁላል አይደለች እንዴ፣ ከአንድ ብር ከምናምን ስትል፣ ስትል ስድስት፣ ስምንት ብር የገባችው! ዶሮዎቹ ግን አሁንም ቀለባቸው በአብዛኛው ጓሮ ነው፡፡ የዶሮዎች መብት ይጠበቅ! ምን እናድርግ…ለዶሮ እንቁም እንጂ። እናላችሁ… ኮሚክ ዘመን ነው…ምን የመሰለ ቆዳ ጫማውን እያብለጨለጨባችሁ ስለ እንስሳት መብት የሚከራከር ‘አክቲቪስት’ የሞላበት ዘመን ነው፡፡ የሚናገረው እውነቱን ከሆነ ለምን የአትክልት ጫማ አያደርግም!. ቂ…ቂ…ቂ…እናማ ዶሮስ ቢከራከሩላት ምን ያንሳታል!
ታዲያላችሁ…የታክሲ ሾፌርና ረዳቶች “ቁርስ ምን በላህ?” “እርጥብ ነው የበላሁት፣” ሲባባሉ ይገርመን ነበር፡፡ ለካስ ‘እርጥብ’ ማለት ድንች ሳንድዊች ነገር ነች፡፡ ቅቅል ድንች በዳቦ ማለት ነው፡፡   አሁን እሷም ተወዳለች አሉ፡፡
እኔ የምለው… የዚህ አገር የቢዝነስ ፈጠራ እኮ ለየት ያለ ነው፡፡ የጠረጴዛ ጨርቅና የእጅ ማድረቂያ ፎጣ የለወጠ ምግብ ቤት… “ምግብ በአዲስ መልክ ጀምረናል” የሚልበት ዘመን ነው። እናማ… ከውሀ የቀጠነችና…አለ አይደል… የሹሮ ዱቄቱን ጨምረውባት ሳይሆን በተን አድርገውባት ‘ነገርዬ’ ሲቀርብላችሁ…“በአዲስ መልክ ጀምረናል የተባለውስ?!” “አሻሽለናል የተባለውስ?!” “ምግባችን ጣት ያስቆረጥማል የተባለውስ?!” ትላላችሁ…በልባችሁ!
ሀሳብ አለን…ከጊዜ ጋር አብሮ መለወጥ ስለሚያስፈልግ… “በአዲስ መልክ ጀምረናል፣” የሚለውን ንዝንዝ ትተውን ይልቁንስ… “የዚህ ምግብ ቤት የምግብ ዋጋ፣ ከሌሎቹ የ55% ቅናሽ አለው” ምናምን የሚል ይለጥፉልን፡፡ ለሹሮ ሰባ፣ ሰማንያ ብር የምታወጡበት ጊዜ እነሆ አበቃ፡፡ በእኛ ምግብ ቤት ሹሮ ከሁለት ጭልፋ ጭማሪ ጋር ቫትን ጨምሮ በሀያ አንድ ብር ከሀምሳ ብቻ!” የሚል ይለጥፉልንማ!
እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ፣” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
የምር ግን፣ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ሰው ውጪ ይመገባል፣ ወዶ ሳይሆን ተገዶ፡፡ በመቶ አንድ ምክንያቶች ቤቱ አብስሎ መመገብ አይችልም፡፡ እናም ይታያችሁ ትናንት በአርባ ብር የበላት ምግብ፤ በማግስቱ “ሀምሳ አምስት ብር ገብታለች” ሲባል! (“አርባ ብር ያልከው ሙሉ ምሳ ነው ወይስ ቡና በወተትና ቦከሰኛ ኬክ?!” ብሎ እሚጠይቅ እውነት አለው፡፡) 
“ስማ ገንዘብህን በሆቴሉ ከምትገፈግፍ ለምን ቤትህ አትበላም? ውጪ በሀያ አምስት ብር የምትበላውን እንቁላል ፍርፍር እኮ፣ ቤትህ ስምንት ብር በማይሞላ ወጪ መብላት ትችላለህ፣” የሚለው ምክር አንድ ሰሞን ሠርቶ ይሆናል፡፡ ግን እንደ ብዙ ነገሮች፣ ‘አንድ ሰሞን ብቻ’ ሆኖ እየቀረ ነው እንጂ፡፡
“እርቦኝ ሹሮ ከምበላ የደለበ ሰንጋ ተደግፌ ፎቶ ብነሳ ይሻለኛል” አይነት ነገር የድሮ መሸለያ ነው፡፡ አሁን ‘እሜቴ ሹሮ’ አይደለም እንዲህ ልንዘባበትባት “መካከለኛ ገቢ ላይ ነኝ፣” ምናምን ነገር ለሚለውም እንኳን እየራቀች ነው… “መካከለኛ ገቢ ማለት ምን ማለት ነው?” የሚለው ‘ያልተፈታልን እንቆቅልሽ’ እንዳለ ሆኖ ማለት ነው፡፡ ፈረሰኛ…መላላጫ…አጭሬ ምናምን ብሎ ---- የጤና ቡድኖች ስም የሚመስሉትን የምስኪኗን ዶሮ ብልቶች ማማረጥ “በናፍቆት ሲጠበቅ” ለቆየ ፊልም እንኳን አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
እግረ መንገዴን ሰዉ እኮ ከራሱ ጋር ብቻ እያወራ እየሄደ፣ ‘የመንገድ ላይ ስነ ስርአት’ ምናምን የሚባል ነገር ሹክ የሚለው ሰው ጠፍቶ በአድ ኪሎሜትር ሀያና ሠላሳ ጊዜ ትከሻችን እየተነደለ ተቸግረናል። የመንገድ ላይ ግፊያው ከኑሮ ጋር ተዳብሎ መንተብ የጀመረች ነጠላ ቢጤ አደረገን እኮ! በዚህ ላይ ደግሞ…አለ አይደል… ጡንቻኛና፣ ጡንቸኛ ነኝ ብሎ የሚያስብ መብዛቱ፡፡ በተለይ ኑሮ ተስፋ በሚያስቆርጥ ደረጃ እየከፋ ባለበት ሰዓት፣ ቢያንስ ትከሻችንን ተዉልንማ!
እኔ የምለው...ፍሬቻ አይገጠምልን ነገር! ጥሩምባ አይገጠምልን ነገር! አሀ…በሰላም መንገዳችሁን ስትሄዱ ዝም ብሎ ትከሻ መግጨት እኮ “ልብ አድርጉልኝ እየተነኮሰኝ ነው፣” ምናምን ሊያስብል ይችላል፡፡ ግን ምን ያደርጋል… “ልብ አድርጉልኝ፣” የሚባል ነገር ቀርቷል መሰለኝ፡፡ “ልብ አድርጉልኝ” እኮ እንዴት አይነት አሪፍ መከላከያ ነበረች…‘ሰባት፣ ሁለት፣ አንድ’ እንደሚጫወት ቡድን አይነት ነገር ማለት ነው፡፡ እናማ…በፊት ጊዜ እኮ…“በኃይለ ሥላሴ አምላክ!” ከተባለ አለቀ ማለት ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ያንን ስም ተክተን “በእንትና አምላክ” ማለት ያልቻልነው…አምላክ ‘የእውቅና ሰርተፊኬት ሳይልክ’ ቀርቶ ነው እንዴ! ለማወቅ ያህል ነው፡፡
እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
ታዲያላችሁ…ነገራችን አለ ሲሉት እንደሚሰናበተው ጸጉራም ውሻ እየመሰለ ነው፡፡ “ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው የቸገረኝ የምመስለው፣” በሚል ወዛዝተን የምንወጣው…አለ አይደል… ልምድ አልለቅ እያለ ነው፡፡ በፊት ጊዜ በኰልፌ ልብስና በ‘ኮሎኝ’ ምናምን በለጭለጭ ብሎ የሰውን አስተያየት ማስቀየስ ይቻል ነበር፡፡ “እኔ እኮ የሚገርምኝ እንዴት ነው እንዲህ ያማረበት! ጉንጩ ሊፈርጥ ደርሷል እኮ!” ማለት ይቻል ነበር፡፡ አሁን አይሠራም፡፡ ሁላችንም እንተዋወቃለና!
የፈለገውን ያህል ‘ኮንስርት’ ቢበዛ፣ የፈለገውን ያህል ‘ፌስቲቫል’ ቢበዛ፣ የፈለገውን ያህል ‘ሽልል ተብሎ የሚኬድበት ግብዣ’ ቢበዛ… እውነቱን ምንም ነገር አይደብቀውም፡፡ እውነቱ ደግሞ ሰዉ ፈገግታው ከገጽታው ላይ እየደበዘዘ ያለው፣ ፈገግ ማለት ስላልፈለገ ሳይሆን የሚመለከታቸው ነርቮችና ደም ስሮች አቅም ስላነሳቸው ነው…ምን አገኝተው ይጠንክሩ፡፡ የኑሮ መወደድ ዋና መለኪያ ሆና የቆየችው፣ ከጠዋት ጸሎታችን እኩል ደጋግመን የምንጠራት የምትመስለው፣ ሌላው አገር ለጨዋታ እየተወራወረ የሚደባደቡባት ቲማቲም እንኳን በኪሎ ሀያ አምስት ብር በገባችበት ሰዓት፣ የመብራት መቆራረጥ ፍዳችንን እያበላን ባለ ሰዓት፣ ለአንዲት ሻማ እስከ ስምንት ብር ድረስ እየተጠየቀ ባለበት ሰዓት…ኑሮ ህይወትን ማቆየት ብቻ እየሆነች ነው፡፡
 እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
በነገራችን ላይ…የፈገግታ ነገር ካነሳን አይቀር፣ ይቺን ስሙኝማ… “ሁሉም ነገር በተበላሸበት ሰዓት ፈገግ የሚል ሰው፤ ችግሩ ማን ላይ እንደሚላክክ ወስኗል ማለት ነው” የሚሏት ነገር አለች፡፡ እና ነገርዬው ሁሉ ተተራምሶ ፈገግ ማለት ከቀጠለ፣ ችግር አለ ማለት ነው፡፡
 የምር ግን… ስለ ኑሮ አስቸጋሪ መሆን ስናወራ ‘መነጫነጭ ስለለመደብን’ አይደለም… ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገንም እያየን ስለሆነ እንጂ፡፡ እንሰጋለን…በዚህ ምክንያት፣ ልጆች እንደሚሉት፣ ነገሮች “እንቁልልጭ” ሆነው እንዳይቀሩ እንሰጋለን፡፡ በኑሮ መወደዱ የተነሳ ውሎ አድሮ “ይሄን ነገር ልንወጣው ይሆን!…” ያልነው የአንድ ሺህ አንድ ነገሮች ጥልፍልፍ ውስጥ ደግመን ላለመግባት እንሰጋለን፡፡ “ፈገግ ማለት ልንጀምር ይሆን!” ያልነውን ድርግም እንዳይል አንሰጋለን፡፡
እግረ መንገድ ይቺን ስሙኝማ…ቀበሮና ተኩላ አንድን ሰው ሊያገለግሉ ተቀጠሩ፡፡ ሌሊት ላይ ቀበሮ ሆዬ ሹክክ ብሎ ይነሳና ቅቤውን ከማሰሮ ያወጣል፡፡ የተወሰነውንም ተኩላው ጭራ ላይ ይለቀልቀዋል፡፡ የቀረውን ደግሞ ግጥም አድርጎ ይበላል፡፡ በማግስቱ ሰውየው ቅቤውን ሲያጣው፣ ቀበሮውን “አንተ ነህ የበላኸው!” ብሎ ያፈጥበታል፡፡  ቀበሮም “እኔ አይደለሁም፣ ተኩላው ነው፤ጭራውን ተመልከተው» ይለዋል፡፡ ሰውየው ተኩላው ጭራ ላይ ቅቤውን ሲያይ “ለካስ አንተ ነህ የበላኸው!” ብሎ ሊሞት ጫፍ እስኪደርስ ድረስ ይደበድበዋል፡፡ ዘንድሮ ከ‘ቀበሮም ከተኩላም’ ጠንቀቅ ማለት ነው፡፡
እናማ… “ምች ምግብ ቤት እንገናኝ፣” መባባልን እንኳን አትንፈጉንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 3716 times