Sunday, 01 July 2018 00:00

እውን አዲስ አበባ ‘ዘመናዊ’ ከተማ ነች!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)


   እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ… አዲስ አበባ የእውነት ‘ዘመናዊ ከተማ’ ነች? የቱርክ ፊልሞች ላይ ከተሞቻቸውን እንዴት አድርገው እግረመንገዳቸውን እንደሚያስተዋውቁ እያየን ነው፡፡ (እኛ ደግሞ ሶፋዎቻችንና የ‘ጂ ፕላስ ምናምን’ ቤቶች ሳሎናችንን እያስተዋወቅን ነው። ቂ…ቂ…ቂ…) የእኛ ፊልም ሠሪዎች አዲስ አበባን እናሳይ ቢሉ የሚቸግራቸው ይመስለኛል፡፡ “ከት፣ ከት” ማለቱ ድምጻቸውን ሳያሰልለው አይቀርም፡፡ ልክ ነዋ…‘ካሜራማኑ’ ከሰባተኛ ፎቅ ጀምሮ ቁልቁል ይሄድና ታች ሲደርስ የቆሻሻ መአት! 
ከተማዋ…‘መስታወት በመስታወት’ የሆኑ ህንጻዎች አሏት፣ (እውነተኛዎቹ የህንጻ ባለሙያዎች በአብዛኛው “ድንቄም ህንጻ ተገነባ!” የሚሏቸውን ማለት ነው)፡፡ እናማ… ዘለቄታቸውን ያሳምርላቸው እንጂ የእግረኛ መንገዶቿ እየሰፉና ለዓይን የማይረብሹ እየሆኑ ነው (በየመንደሩ መግቢያና መውጫ ያጣው ህዝብ “የሰሚ ያለህ” እያለም ማለት ነው)፡፡  ግን እነኚህ ብቻ ዘመናዊ ያደርጓቷል ማለት ነው! አሀ… ኑሯችን እንደ ከተማ አልሆነማ! በእነኚህ ለመራመድ ምቹ ናቸው በምንላቸው የእግረኛ መንገዶች ላይ እንደልባችን መረማመድ እኮ አስቸጋሪ ነው፡ ግፊያው! ትርምሱ! (“ቀላል ግፊያና ትርምስ አለ እንዴ!” እንዲሉ ወጣቶቹ፡፡) ሰው ቢበዛም እኮ የግድ መገፋፋት የለብንም፡፡ ሌሎች ዘመናዊ የሚባሉት ከተሞች ውስጥ ሰዉ እንደ ችቦ ችምችም ብሎም ህዝብ ሳይገፋፋና ሳይደነቃቀፍ ሲረማመድ፣ በየፊልሙና በየዜናው ‘ክሊፕ’ እናይ የለም እንዴ!
የከተማዋን ንጽህና ልብ በሉልኝማ፡፡ ይኸው በየማታው “ልጆቹን አትወዳቸውም እንዴ!” እየተባለ በህጻን አንደበት እየተነገረን እንኳን ሲሻሻሉ የምናያቸው ነገሮች የሉም፡፡ እናማ… ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እኰ በጠራራ ጸሀይ ዚፑን ዝቅ አድርጎ መአት መኪና በተደረደረበት፣ መአት እግረኛ በሚተላለፍበት፣ በነጻነት ፊኛውን የሚያቃልል ‘ባለ ሙሉ ልብስ’ እኮ መአት ነው። አሁንም እኮ ሙዝ እየገመጡ፣ ልጣጩን መሀል እግረኛ መንገድ ላይ የሚወረውሩ፣ ዘመናዊነት ‘ክላውድ ናይን’ ላይ ያወጣቸው ‘ከተሜዎች’ መአት ናቸው፡፡ የጫቱ ገረባ በግለሰቦች የተወረወረ ሳይሆን በአይሱዙ እየመጣ የተራገፈ ሊመስል ምንም አይቀረው፡፡ “እነኚህ ሰዎች ቄጤማ የጎዘጎዙ እየመሰላቸው ነው እንዴ!” ያስብላል፡፡ መሀል መንገድ ላይ ተመጦ የሚጣለው  ሸንኮራ የጉድ አኮ ነው፡፡ እና እውን አዲስ አበባ ‘ዘመናዊ’ ከተማ ነች?
ብዙ ጊዜ የሚነገር ነገር አለ…ሲንጋፖር ውስጥ ምራቅ መንገድ ላይ መትፋት አይቻልም ይባላል። ብዙ አገራትም በህግ ባያስቀምጡትም ነዋሪው ራሱ እንዲህ አይነት ነገር አያደርግም፡፡ ምናልባት መንገድ ላይ ‘እንትፍ’ ማለት ፈልጎ አገር ያጣ፣ እኛ ዘንድ ቢመጣ እንደልቡ ይሆን ነበር፡፡ እዚህ እኮ ያውም ‘ጢቅ’ ማድረግ ብቻ አይደለም… ለኦሎምፒክ የአሎሎ ውርወራ ውድድር ልምምድ እያደረገ ይመስል ከምንሊክ አደባባይ ጫፍ እስከ ደጎል አደባባይ ሊያደርሰው የሚሞክር ነው የሚመስለው፡፡
እውን አዲስ አባባ ዘመናዊ ከተማ ነች? ዘመናዊነት እኮ የባህሪይ ጉዳይም ነው፡፡ ብዙ ወገኖቻችን ፈልሰው እየመጡ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ፍልሰት ለምናያቸው የከተሜነት ያልሆኑ ባህሪያት ክፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው፡፡ ግን “ከተሜ ነኝ፣” “አዲስ አበባን የቆረቆርኩ እኔ ነኝ” ምናምን ሲል የነበረው ሁሉ፣ አሁን ‘ከተሜነት’ ከባህሪው እየወጣ ነው፡፡
እውን አዲስ አበባ ዘመናዊ ከተማ ነች! ኢርፎን ጆሮ ላይ ሰክቶ ወዲህ ወዲያ ማለት እኮ እንደ ትልቅ ስልጣኔ እየታየባት ያለች አገር ናት፡፡ በነገራችን ላይ፣ በከተማችን አንድ ክፍል፣ አንድ ወዳጃችን፣ ኢርፎን አድርጎ ይለምን የነበረ ሰው ማየቱን ነገሮናል፡፡ በዛ ሰሞን ሞባይል ከደረታቸው ስር አውጥተው “ሀሎ…” እያሉ መንገድ ላይ ቁጭ ብለው የሚለምኑ እናት አይተናል፡፡ የምር እኮ ብዙው ባህሪያችን ለትንታኔ እንኳን የሚያስቸግር ሆኗል፡፡ ምናልባትም ሞባይል ባላቸው በልመና የሚተዳደሩ ሰዎች ብዛት አደለም ከአፍሪካ፣ “ከዓለምም አንደኛ” ሳንሆን አንቀርም፡ ለምንድነው ‘ጊነስ’ ላይ የማይመዘገብልንሳ!
ስሙኝማ… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ለዓለም ‘የምናስተምረው’ አንድ ነገር ምን መሰላችሁ… እኛ ዘንድ “እድሜያቸው ከፍ ላሉ የማይመጥን” የሚባል አለባበስ ብሎ ነገር የለም። የተበጫጨቀ ጂንስ የሚለብሱ ወንዶች እድሜ ጠገቦች፣ ‘ፎሎው ሚ’ መቀመጫው ላይ የተጻፈበት ሱሪ የሚለብስ ሴቶች እድሜ ጠገቦች እያየን ነው፡፡
የትራንስፖርቱ ችግር “እውን አዲስ አበባ ዘመናዊ ከተማ ነች!” የሚያስብል ነው፡፡ ከመሀል ከተማ እየራቁ በሄዱ ቁጥር እኮ እንደልብ መጓጓዙ አስቸጋሪ ነው፡፡ አውቶብስ እንዳያመልጥ ተብሎ እኮ ሰዉ አሁንም ከየኮንዶሚኒየሙ ሌሊት አሥራ አንድ ሰዓት ምናምን ይወጣል፡፡
በትራንስፖርት ችግር በጊዜ ከሥራ ቤቷ መግባት ያልቻለች እማወራ እኮ ሰውየዋ ብዙ ነገር ሊያስብባት ይችላል፡፡
“የት አምሽታ ይሆን?”
“ያ ዓይኑን ጥሎብኛል ካለችው ሥራ አስኪያጅ ጋር ትሆን እንዴ!”
ለስንትና ስንት ጊዜ ውሀና መብራት ሳይገባላቸው የኮንደሚኒየም ቤታቸውን ታቅፈው ያሉ መአት ናቸው! አይደለም መንግሥት የሚሠራቸው ኮንዶሚኒየሞች … በግል ሪል እስቴቶች  ተሠርተው ለዓመታት መብራት ያላገኙ ያሉባት ከተማ ነች፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… የምር ግን፣ እግረ መንገድ፣ ይሄ የተበጫጨቀው ጂንስ ፋሺን… ግርም ይላል፡፡ መጀመሪያ ላይ ይበጨቁ የነበሩ ቦታዎች ጥቂት ነበሩ፡፡ አሁን ነገሬ ብላችሁ እንደሁ፣ ፉክክሩ በተበጫጨቀው ቦታ ብዛት ይመስል ጂንስ ሳይሆን ሲባጎ ቀጣጥለው የለበሱ የሚመስሉ መአት ናቸው፡፡ እኛ ዘንድ “ሊሆን አይችልም፣” የሚባል ነገር የለም!
እኔ የምለው… እንግዲህ ጨዋታም አይደል… ‘አርቲስቶች’ ወዳጆቻችን፣ ቤተ መንግሥቱን ተንሸራሸራችሁበት አሉ! አሁን… የጉብኝት ተሞክሯችሁን በኪነ ጥበብ ሥራዎች  አቅርቡልንማ! አለበለዛ ነገሩ “እየበሉ፣ እየጠጡ ዝም፣ የምናምን ወንድም፣” አይነት ነገር ይሆናል፡፡ ደራሲዎች “እኔና የቤተ መንግሥት ቆይታዬ’ አይነትም አጭርም ሆነ ረጅም ልብወለድ እንዲጽፉልን እንጠብቃለን። አሀ… ራሱ ምንጣፉን መርገጡ ለፈጠራ ‘ኢንስፒሬሽን’ ምናምን መሆን ይችላል!
ከፊልም ጽሁፍ ጸሃፊዎቻችን ደግሞ ‘ባይገርምሽ፣ ቤተ መንግሥት ላግባሽ’ ምናምን የሚል ፊልም እንጠብቃለን፡፡ ወይንም ‘የቤተ መንግሥቱ ሚስተር ቢን’ ምናምን የሚል ኮሜዲ ነገር ይጻፉልንማ! ከድምጻውያኖቻችን…
ኩራት ኩራት አይልሽም ወይ
ቤተመንግሥት የአንቺ አይደለም ወይ
ምናምን አይነት የሰርግ ዘፈኖች እንጠብቃለን፡፡ ወይንም ደግሞ…
ሄይ ሜን! ቴክ ኢት ኢዚ
ቤተመንግሥት የእኛ ነው…
አይነት የሮክና፣ “የአንቺ ሆዬ…” ምት ያለበት ዜማ ይዘጋጅልንማ!
ከገጣሚዎቻችን ደግሞ…
በሌሊት ጨረቃ በንጋት ፀሀይ
ነፍሴ ዙፋን ወጥታ…ሲቀርበኝ ፀሀይ
ምናምን አይነት ስንኝ እንዲቋጥሩልን እንጠብቃለን፡፡
የምር ግን…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ… አንዳንድ ‘አርቲስቶች’ “እንዲህ የሚያምር መሆኑን ባውቅ ድሮውንም ‘ምናምንዴድ’… ‘ምናምን ሊበራል ፓርቲ’ አቋቁም አልነበር፣” ሳይሉ አይቀሩም፡፡
ቢሯቸው ያሉ ‘የምርመራ ጋዜጠኞች’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ደግሞ…
“በቀደም አርቲስቶች በቤተ መንግሥት ባደረጉት ጉብኝት ከመሀላቸው ሀምሳ በመቶ የሚሆኑት በሆዳችው ‘መቼ ነው እዚሀ ገብቼ ዙፋኑ ላይ የምንፈላሰስበት’ ብለው ሲመኙ እንደነበር ከታማኝ ምንጮች በደረሰን ጥቆማ መሰረት፣ ጉዳዩን እየተከታተልነው ነው…” ምናምን አይነት ‘ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርቲንግ’ ምናምን እንጠብቃለን፡፡ ፖለቲከኞች ደግሞ  የቤተ መንግሥቱ ጉብኝት ሰፊውን ህዝብ ያገለለና ፍትሃዊ ያልሆነ ነው…” ምናምን ብለው ለፍትሀዊና ‘አሳታፊ’ ጉብኝት ቆርጠው መነሳታቸውን እንዲገልጹልን እንጠብቃለን፡፡ (እዚች አገር እኮ ሊሆን የማይችል ነገር የለም!)
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ምን ይመስለኛል መሰላችሁ፣ እንደ አክራሞታችን ነገሮች ሙሉ ለሙሉ ባይስተካከሉም ጥሩና “ሊያሠራ የሚችል” የሚባል መሻሻል ከታየ፣ የኪነጥበብ ሰዎች ጉድ ሊፈላ ነው፡፡ “በትንሽ ትልቁ ሥራችንን እያገዱብን እጀ ሰባራ አደረጉን፣” ምናምን አይነት ሲባል እንደከረመው አሁን “እጃችሁ ከምን!” ሊባል ነው ማለት ነው፡፡ ሜዳውም፣ ፈረሱም… ሊባል ነው ማለት ነው፡፡
እናማ… እውን አዲስ አበባ ዘመናዊ ከተማ ነች?
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 4355 times