Sunday, 01 July 2018 00:00

ጥበብን በደቦ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

እንዳለጌታ ከበደ፤ በርካታ አጫጭርና ረዥም ልቦለድ መጻህፍትን ያሳተመ ደራሲ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን፣ የብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደ ሥላሴ የሥነጥበባት ማዕከል ዳይሬክተርና በቅርቡ ለንባብ የበቃው “ደቦ” የተሰኘ መጽሐፍ አርታኢና አሳታሚ ነው፡፡ 60 የተለያዩ ጸሃፍትና ደራሲያን የተሳተፉበት ይሄ የበለጸገ የጥበብ መጽሐፍ፤ እንዴትና በምን ዓላማ ታተመ? ደራሲው ያብራራልናል፡፡


    የዕድሜና የዘመን ልዩነት ያላቸው 60 ያህል ደራሲያን፣ ፀሐፍት፣ ሃያስያን፣ ጋዜጠኞች፣ የታሪክ ተንታኞችና ሌሎችም የተሳተፉበት “ደቦ” የተሰኘ መፅሐፍ በቅርቡ አሳትመሃል የመፅሃፉ አርታኢም አንተ ነህ ይሄን መፅሃፍ ለማሳተም ምን አነሳሳህ፡፡ ከስሙ እንደምንረዳው፣ “ደቦ” በሀገራችን ባህል፣ በተለይ በገጠሩ ማህበረሰብ ዘንድ፣ አንድ ሥራ በጋራ ለመስራት፣ የሚደረግ የሥራ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ብዙ ዘመን ያስቆጠረ ልማድ ነው፡፡ እኛ ሃገር ብዙ ጊዜ የሌሎች ሀገርን ርዕዮተ ዓለም አንብበን፣ ወይም ሰምተን አንድ ፓርቲ እንመሰርታለን፤ ያ ፓርቲ ዕድሜው አጭር ሲሆን፤ ሀገርኛ የሆኑት ግን ዕድሜያቸው ይረዝማል፡፡ ለምሳሌ ዕቁብ፣ ዕድርና የመሳሰሉት፡፡
“ደቦ” የሚለውን ሀሳብ ይዘን፣ ወደ መጽሐፉ ስንገባ፣ በተለያዩ የዕድሜ ክልሎች የሚገኙ፣ በተለያዩ ገጠመኞች የተፃፉ፣ የተለያየ ህይወትን የሚያንፀባርቁ፣ የወረደውም የወጣውም፣ በሕይወት አጋጣሚ የኖሩባቸውን ሁነቶች በጽሑፍ ያቆዩትን ሰዎች ሥራ ሰብስቦ ማሳተም፣ ለደራሲውም ጥቅም አለው፡፡ እንደ ዋዛ የዘራው ነገር ፍሬ እንደሚኖረው እንድንገነዘብ ያደርጋል፡፡ ወይም ጊዜ ወስዶ የሰራው ነገር ወደ አደባባይ ቢወጣ ረብ ያለው ነገር እንደሆነ እንዲገነዘብና አንድም ለአንባቢው ነው፡፡ አንባቢው የተለያዩ ጣዕም ያላቸውን ነገሮች ማግኘት እንዲችል ዕድል ይሰጠዋል። በተለምዶ ማሕበራዊ ወይም በያይነት የሚባለውን የምግብ አቀራረብ ይመስላል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ አንባቢው ወደ ራሱ ምርጫ አዘንብሎ ማንበብ ይችላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ስም ያያሉ፣ ስም አይተው፣ “እገሌ የፃፈው አለና ላንብብ” ይላሉ፤ አንዳንዱ ደግሞ ርዕሰ ጉዳይ ይመርጣል፡፡ ስለ ፍልስፍና ማንበብ እፈልጋለሁ፤ ዶክተር ዳኛቸውን እዚህ ውስጥ አገኘሁት፤ ስብሀትም አለ… ብሎ ያነብባል፡፡ ሌላኛው ደግሞ የሀገር ውስጥ ደራስያን አጫጭር ትረካዎችን ሊወድ ይችላል።
ይህ ማለት “ደቦ” በህብረት የተዘመረ መዝሙር ነው፡፡ በጋራ የታረሰ እርሻ ነው፡፡ ሰዎች ያላቸውን ነገር ይዘው፣ አንድ ሕንፃ ሰሩ ማለት ነው፡፡ ጋሽ ስብሀት “ማስታወሻ” መጽሐፍ ላይ እንዲህ ይላል፡- “እናቴን ተከትዬ ረጂም መንገድ ስንጓዝ በረሀ ነው፣ ትልቅ ድንጋይ ትሸከማለች፡፡ አንተ ደግሞ የአቅምህን ያዝ ትለኛለች፡፡ እይዛለሁ፡፡ ተራራ እንወጣለን፣ ቁልቁለት እንወርዳለን፡፡ ከዚያ ‹አሁን ደርሰናል፣ እዚህ ጋ ጣለው› ትለኝና የድንጋይ ክምር ላይ እንጥለዋለን፡፡ በዚያ የሚያልፍ ማንም ሰው፣ የየራሱን ድንጋይ መጣል አለበት፡፡ ምክንያቱም እዚያ ቦታ ትልቅ ቤተ ክርስቲያን እንደሚሰራ አንድ ባህታዊ ተናግረዋል፡፡ ለመስራት አቅም የለም፤ ሩቅ ነው፡፡ የእምነቱ ተከታይ የሆነ መንገደኛ በሚያመጣው ድንጋይ ጥርቅም ግን መስራት ይቻላል፡፡ እኛም እያደረግን ያለነው፣ በተለያየ አጋጣሚ በየመንደሩ፣ በየሳጥኑ፣ በየመጽሔቱ፣ የተረሱ ወይም በጥንቃቄ የተቀመጡ ስራዎች ሰብስቦ በአንድ ማዕድ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደራሲያኑን ያስደስታል ብለን እናስባለን፤ የመንፈስ ህብረትም ይፈጥራል ብለን እናምናለን፡፡
ይህ በሌላው ዓለም የተለመደ ነው፡፡ የአፍሪካ ደራሲያን ብቻ የሚሳተፉበት መጽሐፍ አለ፡፡ ጥራዙ ትልቅ ነው፡፡ ከእኛ ሀገር ጋሽ ፀጋዬ በዚያ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ ይህ በጣም ሊበረታታ የሚገባው ነው፡፡ ወደ እኛ ሀገር ሲመጣ ተጀምሮ ይቋረጣል፡፡ እኛም ለማስቀጠል እየሞከርን ነው፡፡
በ“ደቦ” ውስጥ ሶስት ያህል የትውልድ እርከን ያለ ይመስለኛል፡፡ በሕይወት ያሉ፣ በሕይወት የሌሉ፣ ታዳጊና መካከለኛ ፀሃፍት አሉበት፡፡ በዚህ ውስጥ የዘመኑን ማህበረ - ፍልስፍና፣ የየዘመኑን ፖለቲካ፣ የየዘመኑ እምነት፣ ማህበረ ባህላዊ  ዳና ወዘተ… ትኩረት አድርገህበታል?
እንደ መጽሐፉ አርታኢ ማድረግ ከሚገቡኝ ነገሮች መካከል፣ አንድ መሰብሰብ ነው፡፡ ከዚያም መምረጥ፣ ቀጥሎ መለየት ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎቸ በእጄ ካሉትና አንብቤ ከወደድኳቸው ጽሑፎች ወይም አንብቤ እጄ ላይ ከሌለ፣ ደራሲው ጋ ደውዬ ጽሑፍ እቀበላለሁ፡፡
ወደ ጥያቄህ ስመጣ፤ በሕይወት የሌሉ ተካትተዋል፡፡ የዛሬ ሰማንያ ዐመት የተለዩን ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴም አሉ፡፡ በመግቢያው ላይ አንድም ዐረፍተ ነገር እንዳልተቀነሰ፣ የስርዐተ ነጥብ ለውጥ እንኳ እንዳልተደረገ ገልጫለሁ፡፡ ይህን ያደረግሁት የዘመኑን መልክ ያሳያል ብዬ ስለገመትኩ ነው፡፡ በወቅቱ ከአንድ ቃል ቀጥሎ ሁለት ነጥብ ይደረግ ነበረ፡፡ ያ የዘመን አሻራ ለዚህ ትውልድ መታየቱ ይሻላል ብዬ ልለውጠው አልወደድኩም፡፡ ከፍ ብለናል? ወይስ ዝቅ ብለናል? ወዴት እየሄድን ነው? የሚለው ለተመራማሪው ይተውለታል፡፡ በ1916 ዓ.ም ከታተመ መጽሐፍ ተቀንጭቦ የቀረበ ትረካም አለ፡፡ ፍልስፍና ነው፡፡ ስለ ሰው ኑሮ እየጠየቀ፣ አንተም እንድትጠይቅ የሚገፋፋ ነው፡፡ ያ ብቻ ሳይሆን የገለፀበትም ቋንቋ ይለያል፡፡
ሌላው ከታሪክ አንፃር የአድዋ ድል አለ፡፡ አድዋን በተለያየ መንገድ ለመግለፅ ተሞክሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከሽፋን ስዕሉ ይጀምራል፡፡ የሽፋን ስዕሉን የአድዋ ተጓዦች ያደረግንበት ምክንያት አለ፡፡ ምክንያቱም የነበረውን ሥናነሳ፣ ያለውን እንዳንዘነጋ በሚል ነው፡፡ አረረም መረረም ያሁኑም ትውልድ የራሱን አሻራ እያሳረፈ ነው፡፡ የራሱን ድርሻ እያበረከተ ነው። አንዳንድ ትውልድ ታሪክ ይሰራል፣ አንዳንዱ ያንን ታሪክ ሰሪ ይከተላል፡፡ አንዳንዱ ታዛቢ ነው፤ አጠገቡ የማይመለስ ወራጅ ወንዝ እየሄደ እንደሆነ ይዘነጋል፡፡
በእኛ ትውልድ የሚታየው፣ አባቶቻችን ታሪክ የሰሩበትን ቦታ፣ በእግራችን እየሄድን እንዘክራለን የሚሉ ናቸው፡፡ እስከ አምስት ጊዜ አድዋ የተጓዙ ተጓዦች አሉ፡፡ ይህ በራሱ ቀላል አይደለም፡፡ የዚህ ዘመን አንድ መልክ ነው፡፡
በአድዋ ዙሪያ የሰርፀ ፍሬስብሃት በጣም መሳጭና፣ ከጀርባው ብዙ የታሪክ ፈትሎችን የጠመጠመ ፅሁፍ ነው፣ እስቲ ስለርሱ ትንሽ ንገረኝ…?
ስመ - አድዋ በአዝማሪዎች እንዴት ተገለፀ? የሚለው፣ አንድ መድረክ ላይ ያቀረበው ጥናት ነው፡፡ ወደ መጣጥፉ ስትመጣ፣ የንባብ አድማሱን ልክ የምታይበትና የትንታኔውን ደረጃ የምትመዝንበት ነው፡፡ የሚገርመው ስለ ዐድዋ የተፃፈ አንድ ልቦለድ እንኳ የለንም፡፡ ዘፈን ብትል ከአንድ እጅ ጣት አይበልጡም፡፡ ቲያትርም እንደዚያው፡፡ በዐል በመጣ ቁጥር ጋዜጠኞች የሚያነብቡት ሲያጡ ሲቸገሩ እናያለን፡፡ እዚህ መፅሃፍ ላይ ስለ አድዋ ሰርፀ ጽፏል፤ አቶ ማሙ ውድነህ ስለ አሉላ አባነጋ ጽፈዋል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ደግሞ “አድዋ በጎሰኞች ዐይን” ብሎ ፅፏል፡፡ ስለዚህ በቅፅ አንድ ላይ ከኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዕማድ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆነውን አድዋ እንደ ሰበዝ ተጠቀምንበት ማለት ነው፡፡ ስለ አንድ ጉዳይ በአንድ ሰው የተጻፈ ከማቅረብ ይልቅ ስለ አንድ ጉዳይ በተለያዩ ሰዎች የተፃፉ ሥራዎች ይበልጥ ስለሚጠቅም፣ የነዚያን ሰዎች ስራ አስገባን፡፡ በቀጣይ ደግሞ ሌላ ታሪካዊ ሁነት ላይ ይተኮራል፡፡
ሀገሬን እወዳለሁ ስትል የምትገልፅበት መንገድ፣ በቀድሞውና በአሁኑ ትውልድ መካከል ልዩነት አለ፡፡ ያኔ አርበኛ የምትልበትና አሁን ያለው የተለያየ ነው፡፡ በሂደት የሚቀየሩ ነገሮች አሉ፡፡
ወደ መጽሐፉ ስንመለስ፤ በሕይወት የሌሉ ደራሲያን አሉ፤ በአሁኑ ሰዓት ሀገር ውስጥ ያሉ አሉ፤ ከአገር ውጭ ያሉም ተካተዋል፡፡ ስድሳ ደራሲያንን ስናካትት፣ ሩቅ ያሉትን በኢ-ሜልና በስልክ፣ ሀገር ውስጥ ያሉትን በአካልና በስልክ በማግኘት ነው፡፡ በሕይወት የሌሉትን ደግሞ ቤተሰቦችን በማስፈቀድና ከእነርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት ሰላማዊ በማድረግ ነው የሰራነው፡፡ አንድም ደራሲ ወይም የደራሲ ቤተሰብ ይሁንታውን ሳይገልፅ ጽሑፉ እንዳይካተት ጥረት አድርገናል፡፡
መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱትን ጽሑፎች ሳያቸው፣ አሁን ካለው ተደራሲ ባላነሰ፣ ምናልባትም በላቀ ሁኔታ ለቀጣዩ ትውልድ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ስነ ጽሑፍ (ዘውጎቹን ጨምሮ) ፍልስፍና፣ እምነትና ስነ ልቡና በየዘመኑ አንጓ የሚያሳይ ካርታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንዲያው ቀጣዩን ትወልድም አስበኸው ነው?
የሚያለያየንን ሳይሆን አንድ የሚያደርገንን ሀሳብ ማምጣት፣ ሰው የራሱን ሀሳብ እንዲገልፅ መድረክ መስጠት፣ ሰውና ስራው ተረስቶ እንዳይባክን ማድረግ ነው፡፡ አንዳንዴ ስታስብ፤ የተለየ ነገር ይዘው መጥተው፣ በተቃውሞ ያቋረጡ ሰዎች አሉ፡፡ በ1950ዎቹ የልቅሶ ስነ ስርዓታችን አንድ ወጥ እንዲሆን በማለት፣ ዜማ ደርሶ ከነክዋኔው አቅርቦ ነበር፡፡ የሟች ዘመዶች የት ቦታ መቀመጥ እንዳለባቸው፣ አጃቢዎች የት መቆም እንዳለባቸው ሳይቀር የተመረጠ፣ ቋሚ የሆነ ይሁን የሚል ሀሳብ ነበረው፡፡ ይሁን እንጂ ተቃውሞ ቀርቦበት ሸሸ፡፡ ይህ ሰውዬ ማነው? እንዴት ነበር ያሰበው? መታወቅ፣ መፈተሽ አለበት፡፡ የሚገርም ሀሳብ ያላቸው ሰዎች፤ ሀሳባቸውን በጋዜጣ ይፅፉ ይሆናል፡፡ ያ ፅሑፍ አቧራ አስነስቶ ወይ በዝምታ ታልፎ ይሆናል፡፡ ግን ያንን የተለየ ሀሳብ ልናውቅለት፣ ልናይለት ይገባል፡፡ ያ ነው የተደረገው - በመፅሃፉ፡፡
የሚቀጥለው ትውልድ ይህን መጽሐፍ ሲያነብብ ሊማርበት፣ ሊዝናናበት ይችላል፤ ግን የኛ ድርሻ ሰርቶ ማስቀመጥ፣ ጡብ ማዋጣት ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች እንደ ሃይማኖት የሚከተሉት ቋሚ የሆነ ፍልስፍና አላቸው፡፡ ለምሳሌ ዮሐንስ ሰ. ስለ አየን ራንድ የፃፈው፣ ተስተናግዷል፡፡ ይህ ፀሐፊ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ የዚህችን ፀሐፊ (ፈላስፋ) አቋም ሲያንፀባርቅ የቆየ ነው፡፡ አንድ ሰው የሆነ ፍልስፍና የህይወት ፍልስፍና ሲያደርግ፣ ለምን መረጠው ብሎ መጠየቅና መመርመር ራሱን የቻለ ጥያቄ ነው፡፡
በፊት በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን፣ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሽልማት ድርጅት” ደራሲ ከበደ ሚካኤል መሸለማቸው ልክ አይደለም በማለት ሰብስበው ጠርተው፣ ንግግር አድርገዋል። “ከበደ ሚካኤል ተርጓሚ እንጂ ደራሲ አይደለም፣ ስለዚህ ለምን በደራሲ ዘርፍ ተሸለሙ?” በሚል ሞግተዋል፡፡ አስበው … ከበደ ሚካኤል በዘመኑ ዝነኛ ናቸው፤ ተምረንባቸዋል፡፡ ግን “ልክ አይደለም” አሉ፡፡ እኔ እዚህ ላይ የማየው “ሰውየው ልክ ናቸው፤ አይደለም” የሚለውን ሳይሆን ሀሳባቸውን ለመግለፅ ያላቸው ድፍረት ነው፡፡
አንድ ሰው ያመነበትን ነገር መናገሩ፣ ያኛውን ሰው ይጠላዋል ማለት አይደለም፡፡ “ደቦ” ውስጥም የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ እኔ የምስማማባቸውን ሀሳቦችና አመለካከቶች ብቻ መሰብሰብ የለብኝም፡፡ ይልቅም የአርታኢው ጥያቄ፣ ፀሃፊው ማለት የፈለገውን፣ የራሱን ሀሳብ በትክክል ብሎታል ወይ? የሚል ነው፡፡ ቃላቱ፣ ቋንቋው ሃሳቡ! …
የዕድሜ ልዩነት ሲነሳ ጋሽ አስፋው አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መላኩ ይርዳው የሚባል በሃያዎቹ ውስጥ ያለ ፀሐፊ ተካቷል፡፡ እነዚህን ሁለቱን ስታቀርባቸው፣ የመከባበር ሀሳብ ያመነጫል፡፡ ተተኪ ትውልድም እንዳለ ማሳያ ይሆናል፡፡ እኔ እያደረግሁ ያለሁት፣ ለኔ የተደረገልኝን ነው። ማንም በማያውቀኝ ጊዜ ሥራዬ “እፍታ” ውስጥ ሲካተት፣ የፈጠረብኝን ስሜት አውቀዋለሁ፡፡ አንድ ወቅት ላይ የፃፍኩት መጽሐፍ ሲወጣ ተደስቻለሁ፡፡ ተስፋዬ ገብረአብ አያውቀኝም፤ ግን ጽሑፌን አስተናግዶልኛል፡፡ ስለዚህ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ መቀባበል ያስፈልጋል፡፡ መቀጠል አለበት። ስልሳ ሰው ስለተሳተፈ ብቻ ሳይሆን ስልሳኛ ቅፅ መባል አለበት፡፡ ሌላው ቀርቶ ኤፍኤም ሬዲዮኖች በተለያየ ርዕሰ ጉዳይ ለሚያዘጋጁት ፕሮግራም የሚሆን ነገር ታቀርባለህ፡፡
የመጽሐፉን የውስጥ አደረጃጀት በርዕሰ ጉዳይና በቅርፅ የከፋፈልክበት መንገድ እንዴት ነው? አንድ ሰው ንዑስ ርዕሱን እያየ፣ የሚፈልገውን ነገር በቀላሉ እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ በሌላ በኩል የዚህ ዓይነቱ ሥራ ያደክማል? አንተ እንደዚህ ያደረግህበት ምክንያት የተለየ ይሆን?
ቀደም ብዬ እንዳልኩት፤ የአፍሪካ ደራሲያን የሚታደሙበት ጥራዝ ውስጥ ሲከፋፍሉ፣ ምስራቅ አፍሪካ ይሉና፣ እገሌ እገሌ በሚል ይደረድሯቸዋል፡፡ ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ የመጣ ካለ፣ እዚህ ይካተታል፡፡ ከሰሜንም እንደዚያው፡፡ እኔ ማንበብ እንደምፈልገው ነው ያደረግሁት፡፡ አንድ ጋዜጣ ዐምድ እንደሚኖረው ሁሉ፣ በየርዕሰ ጉዳዮቹ ለምን አይካተቱም? ሕግ ለሚፈልግ ሕግ፣ ፖለቲካ ለሚፈልግ ፖለቲካ፣ ትረካ ለሚፈልግ ትረካ አለ፡፡ ፍልስፍና በሚለው ርዕስ ሥር፤ ፍልስፍና ነክ ፅሑፎች ይገኛሉ፡፡
አጫጭር ትረካዎች፣ ግጥሞች፣ ክፍል አንድ፣ ክፍል ሁለት ብሎ ከማስቀመጥ በተጨማሪ፣ ልክ ሙዚቃ ስንሰማ፣ ከአንዱ ወደ አንዱ የሚሸጋገርበት መንገድ እንዳለ ሁሉ መጽሐፉ ውስጥ ያንን ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
ለምሳሌ ኃይለመለኮት መዋዕል “የከርቸሌው መምህር” ብሎ በቀይ ሽብር ዘመን ኢሕአፓ ተብሎ ታስሮ ስለተገረፈ አንድ ሰው ይተርክልንና ይህ መምህር እስር ቤት በቆየበት ጊዜ በራሱ ፍቃድ እስረኞችን እንዴት እንዳስተማረና ማትሪክ ተፈትነውም ጥሩ ውጤት እንዳመጡ ይገልፃል፡፡ የመከራና የጥርጣሬ ዘመን እንደሆነ ስታነብበው ይገባሃል፡፡ ታሪኩ ፀሐፊው እስር ቤት በነበረ ጊዜ ያስተዋለው ነው፡፡ ከእርሱ ጽሑፍ ቀጥሎ የነቢዩ ተካልኝ “ትናንት፣ ዛሬ ነገ” በሚል የፃፈው አለ፡፡ የገዛ ወንድሙ በቀይ ሽብር ዘመን ሲገደልበት፣ የእናቱ ሐዘን ጥልቀት ምን ያህል እንደነበረ፣ ሀዘን እንዴት እንደሰበራት፣ እንዴት ማንነቷን እንደለወጠው ውብ በሆነ መንገድ ፅፎታል፡፡
እነዚህን ጽሑፎች በተከታታይ ሳመጣ ሆን ብዬ ነው። እዚህም ስለተበደልነው በደል እየተናገርን ነው፡፡ አሁን ዕድሜ ለዶክተር ዐቢይ አህመድ፣ የይቅርታ መንፈስ በአየሩ ላይ እንዲናኝ እየተደረገ ነው፡፡
በሩቅ ዘመን ጥላቻ የተዋጡ፣ በአንድ ዘመን ቂምና ጥላቻ ተይዘው፣ የቀሩ ሰዎች አሉ፡፡ ይቅርታ በማድረግ እንዴት ራስን መፈወስ እንደሚቻል አልተረዳንም፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ በመጽሐፉ ውስጥ ፍሰታቸውን ጠብቀው የተሰደሩ ብዙ ርዕሰ ጉዳዮች አሉ፡፡ ሁሉም ነገር በምክንያት እንዲሆን ለማድረግ ተሞክሯል፡፡
ሌላው ቀርቶ ከሞክሼ ፊደላት ውስጥ ሰውየው ስሙን ሲፅፍ፣ የትኛውን ነው የሚጠቀመው የሚለውን በጥንቃቄ ለማየት ሞክሬአለሁ፡፡ ለምሳሌ ሥዩም ተፈራ “ንጉሡ ሠ” ካልሆነች እንጣላለን እያለ ነበር የመጣው፡፡ ይህንን በሌላ ሞክሼ ፊደል ሲቀይሩብኝ አልወድድም፣ ምክንያቱም በሕይወቴ አባቴ የገረፈኝ በዚህች ፊደል ምክንያት ነው፡፡ ሥዩም ሲፃፍ በዚህኛው “ሰ” አይደለም ብሎ አባቴ ገርፎኛል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲቀይሩብኝ ደስ አይለኝም” ብሎ ነግሮኛል፡፡ ስለዚህ እኔም በዚህ ላይ ጥንቃቄ አድርጌያለሁ። ደስ ስላለህ አትጠቀምበትም፡፡ በየትኛውም ብትጠቀም ምንም የማይመስላቸው ያሉትን ያህል አምርረው የሚቆጡ አሉ፡፡
መጽሐፉ በአጠቃላይ በብዙ ጥንቃቄና በዓላማ የተዘጋጀ ነው፡፡ አሳታሚው “ሀሁ አሳታሚ” ድርጅት፣ ይህን በጎ ዓላማ ለማገዝና በዐላማው ለመጠቀም ተባባሪ መሆኑ የሚያስመሰግነው ነው፡፡      


Read 1595 times