Print this page
Saturday, 07 July 2018 10:40

ታላላቅ የሃገሪቱ ገዳማት ሁለቱ ሲኖዶሶች እርቅ እንዲፈፅሙ ተማፀኑ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 በሃገር ውስጥ የሚገኙ አስር ታላላቅ ገዳማት፤ በኢትዮጵያና በአሜሪካ በሚገኙት ሁለቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶች መካከል የሚካሄደው የእርቅ ጉባኤ፣ በአልባሌ ምክንያት እንዳይስተጓጎል ተማፅነዋል፡፡
ገደማቱ በጋራ በሶስት ገፅ ደብዳቤ ለሁለቱ ሲኖዶሶች ባቀረቡት ተማፅኖ፤ “የሃይማኖት አባቶች ለትውልድ መለያየትን ማውረስ የለብንም፤ የእስከዛሬው መለያየት ይበቃል፤ በታሪክ ተወቃሽ ከመሆን እርቁ ያለምንም እንቅፋት በአፋጣኝ ይካሄድ” ብለዋል፡፡
“ሁለት እረኛ፣ ሁለት መንጋ ከመሆን አንድ እረኛ፣ አንድ መንጋ እንሁን” ያሉት ገዳማቱ፤ እስከ ዛሬ ተፈጥሮ የቆየው መከፋፈል ምዕመናንን በእምነታቸው እንዳይፀኑ፣ ቤተክርስቲያኒቱም ሃዋሪያዊ ተልዕኮዎችን በአግባቡ እንዳትወጣ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡
“ልዩነቱ ከተፈጠረ ጊዜ አንስቶ የታዩና እየታዩ ያሉት ነገሮች በቶሎ መፍትሄ ካላገኙ፣ መለያየቱ ለቤተክርስቲያኒቱ ምን ያህል ከባድ ፈተና እንደሆነ ግልፅ ነው” ያሉት ገዳማቱ “ለትውልዱ መለያየትን ማውረስ የለብንም” ሲሉ ለሁለቱ ሲኖዶሶች ተማፅኖአቸውን በቅዱሳንና በፈጣሪ ስም አቅርበዋል፡፡
የእርቁን ተማፅኖ ያቀረቡት የዋልድባ እንዳልሽሃ ኪዳነ ምህረት አንድነት ገዳም፣ የአሠቦት ድብረ ወገግ ቅድስት ስላሴ ገዳም፣ ማህበረስላሴ አንድነት ገዳም፣ ዳጋ ቅዱስ እስጢፋኖስ ገዳም፣ ዝቋላ አቦ ገዳም ክብራን ገብርኤል ገዳም፣ ደብረ ፅጌ ማርያም ገዳም፣ ደብረ ሊባኖስ ገዳም፣ ሃይቅ አቡነ ኢየሱስ ገዳም እና የምሁር ኢየሱስ ገዳም ናቸው፡፡

Read 4072 times