Saturday, 07 July 2018 11:18

የመደመር ሥነ ልቦናዊ ቁመናዎች

Written by  ከወንድወሰን ተሾመ (የማህበራዊ ሳይንስና የሥነልቦና ባለሙያ) ከአልታ ምርምር፣ ሥልጠናና ካውንስሊግ
Rate this item
(3 votes)

 አንድ ሰው  አንድ በቀቀን (ፓሮት) ጓደኛ ነበረው። ከበቀቀኑ ጋር ለረዥም ጊዜ አብሮ ኖሯል፡፡ ሰውየው  አንዴ ትከሻው ላይ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ አናቱ ላይ እያስቀመጠው፣ ቤት ውስጥ ካኖረው የስኳር ጆንያ፣ ስኳር  በማንኪያ እያወጣ ለበቀቀኑ ያበለዋል፡፡ አንድ ቀን  ሰው ሁሉ ስላልነበረ ማታ ሊተኙ ሲሉ፣ ሰውየው በቀቀኑን፤ “አንዳችን እንተኛ፤ ሌላችን ደግሞ ቤቱን እንጠብቅ” ይለዋል፡፡ በቀቀኑም ፤ “ዛሬ እኔ ስጠብቅ ልደር፤ አንተ ተኛ” ይለውና ሰውየው ይተኛል፡፡ ፀጥ ባለ ሁኔታ ሌሊቱ ተጋመሰ፡፡ ከእኩለ ሌሌት በኋላ ግን ሌባ ማንኮሻኮሽ ጀመረ፡፡ ሌባው ቀስ ብሎ ቤት ውስጥ ገባና፣ እቃዎችን ማንሳት ጀመረ፡፡ ሰውዬው ማለዳ ሲነሳ፤ ከስኳር ጆንያው በቀር ቤቱ ውስጥ ያሉት ንብረቶች በሙሉ ተወስደዋል፡፡ ከዚያም በቀቀኑን “ውድ እቃዎች በሙሉ’ኮ ተወስደዋል” ይለዋል፡፡ በቀቀኑም “የስኳሩ ጆንያው እ’ኮ አለ” ይለዋል፡፡ “ወርቁ፣ቴሊቪዥኑ፣ ምርጥ ሶፋዎቻችን እኮ ተወስደዋል” ይላል ሰውዬው። በቀቀኑም “አይኔን ከስኳር ጆንያ  ላይ ሳላነሳ ነው ያደርኩት፤ ለኛ እኮ ዋናው ሃብታችን የስኳር ጆንያው ነው” አለው ይባላል፡፡ አሁን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልገው “የስኳር ጆንያው”ን ብቻ ማየት ሳይሆን ኢትዮጵያን ማየት ነው፤ትልቁ ስዕል ላይ አይንን መትከል ነው፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን  ዶክተር አብይ አህመድ መንገድ፣ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትና በእጅጉ የሚበጃት መንገድ ነው፡፡ ይህ መንገድ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር መንገድ ሲሆን በዚህ መንገድ ላይ ተደላድሎ ለመጓዝ፣ ከእያንዳንዱ ዜጋ የስነልቦና (የአስተሳሰብ፣ የስሜት እና የጠባይ) ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በፊት አብሮ የኖረን አሉታዊ አሳብ፣ ስሜትና ጠባይ መሞገት እና ከራስ ጋር መጣላት ያስፈልጋል፡፡ የዚህም ውጤት አዎንታዊ አሳብ፤ስሜትና ጠባይ መፍጠር ሊሆን ይገባዋል፡፡ መፅሐፍ ቅዱስ፤ “በአረጀ ልብስ አዲስ እራፊ የሚያኖር የለም፤ - በአረጀ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም” እንደሚለው፤ በአሮጌ ማንነት መገለጫ አዲሱን የመደመር መንገድ ይዞ መጓዝ አይቻልም፡፡ ይህም ማለት በዘረኝነት አስተሳሰብ ፣ይቅርታን ማምጣት አይቻልም፤ በጥላቻ ስሜት ፍቅርን ማንገስ አይቻልም፤ በክፉ ንግግርና ድርጊት መልካምን ውጤት ማምጣት አይቻልም፤ የመቀነስ ስሌት በተጠናወተው የአዕምሮ ቅኝት መደመር አይቻልም፤ ስለዚህም  መደመር የሚጠይቃቸው ስነልቦናዊ ቁመናዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እነዚህንም በሶስት ከፍለን እናያቸዋለን፡፡
1ኛ፡- የአስተሳሰብ ቁመና
በአገራችን ላለፉት በርካታ አመታት የሰዎች አስተሳሰብ በዘርና በቋንቋ ቅኝቶች፤ “ለኔና ለወገኔ” ብቻ በሚል ስነልቦና ውቅሮች፤ “እኛና እነሱ” በሚሉ የክፍፍል እሳቤዎች  ሲቃኝ ኖሯል፡፡ በተለይ የሶስቱ የጥቁር ስነልቦና ቀውሶች ሰለባ የሆኑ በርካታ ዜጎች ተፈጥረዋል፡፡ ሞራል የለሹ፤ በሌላው ሰው እግር ሆኖ የማያየው፤ ተደጋጋሚ ውሸት የሚዋሸው፣ ከትናንትና ስህተቱ የማይማረው ሳይኮፓት የተባለው የስነልቦና ችግር አንዱ ሲሆን፤ የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ፍልስፍና የሚከተለው፤ ውጤቱን እንጂ ውጤቱን ለማግኘት የሚኬድበትን መንገድ (ሂደቱን) ፈፅሞ ከግምት ውስጥ የማያስገባው፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል የሚለው አይነት ፍልስፍና የሚከተለው ማካቬሊዝም የተሰኘው የስነልቦና ችግር ሁለተኛው ነው፡፡ ሶስተኛው፤ ራሱን ብቻ ሃይለኛ፣ አገር አዳኝ፤ ሁሉን አድራጊና ፈጣሪ አድርጎ የሚቆጥረው ናርሲዝም የተባለው የስነልቦና ችግር ነው፡፡ እነዚህ አስተሳሰቦች በግለሰብ ደረጃ የሚታዩ እንደሆኑ ቢነገርላቸውም፣ ተቋማዊ አደረጃጀትና አካሄድ ሊፈጠርላቸው የሚችሉ እንደሆነ ከስነልቦና ሳይንስ አንፃር መተንተን ይቻላል። አስተሳሰቦች ወደ ንግግሮችና ድርጊቶች የመቀየር ሃይላቸው ከፍተኛ በመሆኑ፣ከላይ የተጠቀሱት አሉታዊ የልቦና ውቅሮች አገራችንን በእጅጉ ጎድተዋታል፡፡ እነዚህ አሉታዊ አስተሳሰቦች ሊለወጡ ይችላሉ፤ ነገር ግን ጊዜ የሚጠይቁ የግንዛቤ መፍጠሪያ ትምህርቶች፣ ሥልጠናዎችና የባለሙያ ምክሮች ያስፈልጓቸዋል፡፡
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶ/ር አብይ የመደመር መንገድ፣ አዲስ የአስተሳሰብ ቁመና ይጠይቃል፡፡
ስለ ራስ ግንዛቤ፡- ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ከሌላው ሰው አልበልጥም፤ ደግሞም አላንስም፤ ለአገሬ አንዳች ነገር ማበርከት እችላለሁ፤ ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ስደመር፣ ተጠቃሚነቴ፣ ደህንነቴ፣ ሁለንተናዊ ጤንነቴ፣ ዕደገቴ ወዘተ የተሻለ ይሆናል፤ የሚል የአስተሳሰብ ቁመና ያስፈልጋል፡፡
ከሌሎች ጋር ባለ ግንኙነት ግንዛቤ፡- ሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ነው፣ ልወደው፣ ላከብረው፣ ችግር ሲኖር ልረዳውና ላግዘው ይገባኛል፤ ዘሩን፣ ጎሳውን፣ ሃይማኖቱን፣ የተወለደበትን ሥፍራ፣ ወንድሜን ለማራቅና ለማቅረብ መመዘኛ አላደርገውም፤ ጉዳቱ ጉዳቴ ነው፤ ደስታው ደስታዬ ነው፤ ሃዘኑ ሃዘኔ ነው፤ ከዚህ በፊት የሰራውን ስህተት ይቅር እለዋለሁ፤ አልበቀለውም፤ አልፈርጀውም፤ የሚሉ አስተሳሰቦች መፈጠር፣ ማደግና ፍሬ ማፍራት፣ በአጠቃላይ ስለ ሌላው ሰው አውነተኛ የሆነ፣ ፍቅር ያለበት፣ መልካም ወሬ ያለበት፣ ምስጋና ያለበት አስተሳሰብ  የአዲሱ መንገድ ቁመና ሊሆን ይገባል፡፡
ስለ አገር ግንዛቤ፡- ጠቅላይ ሚንስትራችን በተደጋጋሚ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለሁላችንም እንደምትበቃ፣ ገበታው ሰፊ እና ሁሉንም ማጥገብ እንደሚችል፤ አገርን መውደድ አገርን መጠበቅ፣ መንከባከብ፣ ማሳደግ፣ ለአገር የበኩልን አስተዋፅኦ ማበርከት ወዘተ-- እንደሆነ ማሰብ፤ ለልጆቼና ለልጅ ልጆቼ የተሻለችና ምቹ አገር እንዴት ልፍጠር ብሎ መጠበብ ወዘተ-- የአዲሱ መንገድ የአሳብ ቁመና ሊሆን ይገባል፡፡
በአብዛኛው የሃሳብ ምንጮች አምስቱ የስሜት ህዋሳቶቻችን ናቸው፡፡ ለምሳሌ የምንሰማውና የምናየው ነገር ሃሳብ ይፈጥራል፤ ይህ ደግሞ ስሜትና ጠባይ ላይ ተፅእኖ ያመጣል፡፡ ስለዚህ በአዲሱ የመደመር መንገድ ስለምንሰማውና ስለምናየው ነገር መጠንቀቅ አለብን፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊነት፣ ስለ ህብረት፣ ስለ መደመር፣ስለ ፍቅር እና ስለ ይቅርታ እንስማ፤ ታሪኮችን እናንብብ፤ በዚህ ዙሪያ የተሰሩ ፊልሞችን እንመልከት፡፡
2ኛ፡-  የስሜት ቁመና
አዎንታዊ ስሜቶችና አሉታዊ ስሜቶች አሉ። ከአዎንታዊ ስሜቶች መካከል፣ ለአዲሱ መንገድ የሚያስፈልጉን፡- ተስፋ፣ ፍቅር፣ ደስታ፣ ይቅርታ፣ አንድን ጥሩ ነገር የማድረግ ፍላጎት፣ መደነቅ የመሳሰሉት ሲሆኑ ሊወገዱ የሚገባቸው አሉታዊ ስሜቶች፡- ጥላቻ፣ ከፍተኛ ፍርሃት፣ ከፍተኛ ሃዘን፣ ጭንቀት፣ ከፍተኛ ንዴት የመሳሰሉት ናቸው፡፡ አዲሱ የመደመር መንገድ፤ በትናንትና ውስጥ የነበሩ ቁጭቶችን፣ ፀፀቶችንና ሃዘኖችን ማስወገድ ይጠይቃል፤ በነገ ውስጥ የሚኖሩ ፍርሃቶችንና ስጋቶችን ማስወገድም ይጠይቃል። ዛሬ ላይ  ሰላምን፣ ደስታንና ጤንነትን ሊያጎናፅፉ የሚችሉ፣ የይቅርታና የፍቅር መንገዶችን መምረጥ ይጠይቃል። ይህንን የስሜት ቁመና ማምጣት ቀላል አይደለም፤ ደግሞም የማይቻል አይደለም፡፡ በየእለቱ ሰብዕናችን ላይ መስራትን ይጠይቃል፡፡ በዚህም መሰረት፤ ስሜታዊነትን ገትተን፣ ራስን በመግዛት፣ አዲሱን የስሜት ቁመና መያዝ ያስፈልጋል፡፡
3ኛ፡- የጠባይ ቁመና
ጠባይ (ካሁን በፊት በነበሩ ፅሁፎቼ ላይ ባህርይ ብዬ ተጠቅሜዋለሁ) በንግግርና በድርጊት ይገለፃል፡፡
ንግግር፡- አዲሱ የመደመር መንገድ የሚጠይቃቸው ንግግሮች አሉ፡፡ ንግግሮቹ፤ ጥላቻን የማያንፀባርቁ፣ በአንድ የህብረተሰብ ክፍል ላይ ወይም ዘር ላይ ያላነጣጠሩ፤ ሰዎችንና ቡድኖችን የማይፈርጁ (የፍረጃ ፖለቲካ ምን ያህል ኢትዮጵያን እንደጎዳት መዘንጋት የለብንም)፣ ግጭትንና መከፋፈልን የማያመጡ ሊሆኑ ይገባቸዋል፡፡ አዲሱ የመደመር መንገድ፣ የንግግር ቁመና የሚከተለውን መምሰል ይጠበቅበታል፡፡ ሌሎችን የሚያከብር ንግግር፣ በውስጡ ፍቅርንና ይቅርታን የቋጠረ ንግግር፣ ርህራሄንና ቸርነትን የሚገልጥ ንግግር፣ መደመርን ከፍ የሚያደርግ ንግግር፣ ኢትዮጵያዊነትን የሚያጎላ ንግግር፣ ህብረትንና አንድነትን የሚያወድስ ንግግር- የአዲሱ የመደመር መንገድ የንግግር ቁመና ነው፡፡
ድርጊት፡- ድርጊቶቻችን በአብዛኛው የሃሳቦቻችንና የስሜቶቻችን ተከታዮች ናቸው። ከላይ የተጠቀሱትን የሃሳብና የስሜት ቁመናዎች ከተለማመድን፣ እነሱን የሚመስሉ ድርጊቶች ይወለዳሉ፡፡ መልካምን ሥራ በመስራት የተጀመረውን ለውጥ ማጠናከር፣ ፍትህን፣ እኩልነትን የሚያንፀባርቁ ተግባራትን መፈጸም፤ መሪዎቻችን ለሚጠይቁን ጥያቄ በፍጥነት ተግባራዊ ምላሽ መስጠት፤ በተሰማራንባቸው የሥራ መስኮች ጠንክሮ መስራት፣ ለአገር የሚበጅን ማንኛውንም ተግባር መፈፀም፣ የመገናኛ ብዙሃኖች በፊልም፣ በውይይት፣ በጭውውት፣ በድራማ፣ በዜማና በቅኔ ወዘተ ስለ ህብረት፣ ስለ ኢትዮጵያዊነት ማቀንቀን  የመደመር መንገድ የድርጊት ቁመናዎች ናቸው፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ቁመናዎች፤ በአንድ ጀምበር የሚመጡ አይደሉም፤ በሂደት የምንጎናፀፋቸው ናቸው። የመደመር ቁመና እየበረታ ሲሄድ፣ ተንሰራፍተው የሚገኙት አሉታዊ አስተሳሰቦች፣ አሰራሮችና ስሜቶች እየደከሙ ይሄዳሉ፡፡
እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 19 1863 አብርሃም ሊንከን በእርስ በእርስ ጦርነት ለተከፋፈለችው አገራቸው አሜሪካ፣ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ከ87 ዓመታት በፊት አባቶቻችን፤ በዚህ አህጉር በነፃነት የተፀነሰ ‘ሁሉም ሰው፣ እኩል ተፈጥሯል’ የሚል አዲስ ህዝብ አምጥተውልናል፡፡ ነገር ግን እኛ ዛሬ በከፍተኛ የእርስበእርስ ጦርነት ተጠምደናል፡፡ መስራት ያለብን አባቶቻችን ለነፃነታችን የሞቱት፣ ሞት በከንቱ እንዳይቀር፤ ከእግዚአብሔር በታች ይህ ህዝብ አዲስ ነፃነት እንዲኖረው፤ የህዝብ፣ በህዝብ እና ለህዝብ የሆነ መንግስት ከምድረ ገፅ እንዳይጠፋ ነው፡፡ ‘’ አብርሃም ሊንከን፤ ይህንን ንግግር ከተናገሩ ከ100 ዓመታት በኋላ ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ኦገስት 28፤ 1963 ‘’ህልም አለኝ” የሚለውን አስደናቂ ንግግሩን፣ ሁለት መቶ ሺህ የሚሆኑ ደጋፊዎቹ በተገኙበት ተናግሯል፡፡ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄ ያነሳበት ይህ ንግግሩ፤ አሜሪካ ከአብርሃም ሊንከን በኋላ በለውጥ ሂደት ውስጥ ብትሆንም  ለህዝቦቿ በሙሉ እኩልነትንና ፍትህን ለማጎናፀፍ፣ ገና ሩቅ እንደነበረች ያሳያል፡፡ ይህንን ያነሳሁት የተሟላ አኩልነትና ፍትህ ለኢትዮጵያ ህዝብ ማጎናፀፍ፣ ቅፅበት ሳይሆን ሂደት መሆኑን ለመግለፅና በእያንዳንዷ ቀን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር ንግግሮችና ድርጊቶች አድናቆት እንደሚሹ ለመግለጽ እንጂ የአገራችን የፍትህና የእኩልነት ጥያቄ፣ ረዥም ዓመታት ይወስዳል ለማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ከፍተኛ ትዕግስት፤ ጥንቃቄ፤ ሌት ተቀን የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር ባህልን የማዳበር እና የማሳደግ ጥረትን ይጠይቃል፡፡  ከላይ በፅሁፉ የተቀመጡትን የመደመር ስነልቦናዊ ቁመናዎች ለመጎናጸፍ አጥብቆ መሥራት ያስፈልጋል፡፡  በነገራችን ላይ መደመርን የማውቀው ሂሳብ ትምህርት ውስጥ ነበር፤ ጠቅላይ ሚኒስተራችን ግን ማህበራዊ ሳይንስ ውስጥ ከትተውታል! ቸር እንሰንብት!
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል።

Read 2145 times