Saturday, 07 July 2018 11:47

የቬንዙዌላ መሪ፤ ጦሩ አሜሪካን ለመመከት በተጠንቀቅ እንዲቆም አዘዙ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ የሌሎች አጋር አገራት መሪዎችን በማስተባበር፣ ቬንዙዌላን ለመውረር ሲያሴሩ እንደነበር የሚያሳይ መረጃ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ፣ የጦር ሃይላቸው የአሜሪካን ወረራ ለመመከት በተጠንቀቅ እንዲቆም ማዘዛቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ፤ ከአራት የላቲን አሜሪካ አገራት መሪዎች ጋር ባለፈው አመት ባደረጉት የድብቅ ስብሰባ፣ በቬንዙዌላ ላይ ወታደራዊ ጥቃትና ወረራ የማድረግ ሃሳብ በማቅረብ፣ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መምከራቸውን የሚያሳይ መረጃ በአሶሼትድ ፕሬስ ባለፈው ረቡዕ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ ከአሜሪካ ጋር ባላንጣ ሆነው የዘለቁት የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ማዱሮም በይፋ የአሜሪካንና የአጋሮቿን ጥቃት ለመመከት፣ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እንዲታጠቅና ራሱን እንዲያዘጋጅ ለጦር ሃይላቸው መመሪያ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
የታጠቃችሁ ሁሉ፣ ለአንዲት ሰከንድም ቢሆን ተዘናግታችሁ ጠመንጃችሁን እንዳታወርዱ፣ ምክንያቱም ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚመጣብንን ወራሪ ሃይል ለመመከትና ሉአላዊነታችንን ለማስከበር በጀግንነት የምንዋደቅበት ታሪካዊ ጊዜ ላይ ደርሰናል ብለዋል- ፕሬዚዳንት ማዱሮ፡፡ ትራምፕ፤ቬንዙዌላን የመውረር ሃሳብ አቅርበዋል የሚለውን መረጃ በተመለከተ አስተያየቱን እንዲሰጥ የተጠየቀው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር፣ “በግለሰብ ደረጃ በተደረገ ውይይት ላይ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለሁም” ማለቱንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ”ዲሞክራሲን ያጠፋውና የህዝቡን መብት በአደባባይ የጣሰው የለየለት አምባገነን የሆነው ማዱሮ፤ በስልጣን ላይ መቀጠል የለበትም፤ የኒኮላስ ማዱሮን አምባገነን መንግስት አደብ ለማስገዛት የተለያዩ አማራጮችን መውሰድ እንችላለን፤ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድም ከእነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ ነው” ማለታቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ማዱሮ በበኩላቸው በወቅቱ በሰጡት ምላሽ፤ ትራምፕ ጦሩን አዝምቶ እንዳይወጋን እርዱን በሚል ለአለማቀፉ ማህበረሰብና ለሮማው ሊቀጳጳስ ፍራንሲስ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡


Read 2044 times