Saturday, 28 July 2018 15:33

በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ፅ/ቤቶች እየከፈትን ነው - ኦፌኮ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(3 votes)

   • ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ጠንካራ ድጋፍ አላቸው
  • ብሄርተኝነት አስጊ የሚሆነው መልካም አስተዳደር ከጠፋ ብቻ ነው
  • የብሔራዊ ሠንደቅ አላማ ጉዳይ መወሰን ያለበት በህዝቡ ነው
  • የህዝብ መፈናቀል መንስኤዎች ክፉ ግለሰቦች ናቸው

      አገሪቱ በከፍተኛ የህዝብ አመጽና የፖለቲካ ቀውስ በምትታመስበት ወቅት አብዛኞቹ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ታስረው እንደነበር የሚያስታውሰው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፤ በቅርቡ የአመራሮቹ ከእስር መፈታትን ተከትሎ፣ ከተለያዩ የውጭ አገራት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ይገልጻል።
ይሄን ተከትሎም በኦሮሚያ ከሚገኙ 20 ዞኖች በ16ቱ የፓርቲውን ጽ/ቤቶች መከፈቱን የኦፌኮ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥሩነህ ገሞታ ይናገራሉ፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ፤ ከሥራ አስፈጻሚው ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፤ ኦህዴድን ጨምሮ ከሌሎች ለኦሮሞ ህዝብ ከሚታገሉ ፓርቲዎች ኦፌኮ በምን እንደሚለይ፣ የብሄር አደረጃጀት በደቀነው ስጋት ላይ፣ በኦሮሚያ እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶችና የህዝብ መፈናቀሎች እንዲሁም
በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አመራር ዙሪያ ተነጋግረዋል። እነሆ፡-


    ኦፌኮ አመራሮቹ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በምን አይነት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል?
አመራሮቻችን ከተፈቱ በኋላ በጠንካራ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፓርቲውም የእለት ተእለት ስራ በሚገባ እየተሠራ ነው፡፡ ሊቀ መንበራችንም ወደተለያዩ የውጭ ሃገራት ተጉዘው ስለ ኦፌኮ ትግል ማብራሪያዎች እየሰጡ ነው፡፡ ፓርቲውም በብዙ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች ላይ ቢሮዎች በመክፈት ላይ ይገኛል፡፡ ከ2007 ዓ.ም ምርጫ ወዲህ ለምን እንደሆነ አላውቅም በርካታ ቢሮዎቻችን በገዥው ፓርቲ ተዘግተውብን ነበር፡፡ አሁን እነዚያን እየከፈትን ነው፡፡ አዳዲስ ቢሮዎችም እየከፈትን ነው፡፡ አሁን አባሎቻችን በየቦታው መፈታታቸውን ተከትሎ፣ እንደገና የመደራጀትና ፅ/ቤቶቻችንን የማደራጀት ተግባር እያከናወንን ነው፡፡
ምን ያህል ቢሮዎችን ነው የከፈታችሁት?
በኦሮሚያ ክልል 20 ዞኖች ናቸው ያሉት፤እኛ በ16ቱ ዞኖች ላይ በተጠናከረ መልኩ ፅ/ቤቶች አሉን፡፡
ኦፌኮ ከኦሮሚያ ውጪ ይንቀሳቀሳል?
አዎ፡፡ ለምሣሌ ሃዋሣ ላይ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ከሚሴ አካባቢ ቢሮ ለመክፈት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በቅርቡ በቤኒሻንጉል መተከል ዞን ፅ/ቤት እንከፍታለን፡፡ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይም ቢሮዎች እንከፍታለን፡፡ ህዝቡ ሰፊ ድጋፍ እየሠጠን ስለሆነ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ በበርካታ የሃገሪቱ አካባቢዎች ፅ/ቤቶች ለመክፈት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
የኦሮሞን ህዝብ መሠረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ በርካታ ድርጅቶች አሉ፤ በእናንተ እና በሌሎቹ የኦሮሞ ፓርቲዎች መካከል ያለው መሰረታዊ ልዩነት ምንድን ነው?
የኦሮሞን ህዝብ መሰረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች 11 እና 12 ያህል ቢሆኑ ነው፡፡ ከየቆሙበት የፖለቲካ አቅጣጫ አንፃር ሲታይ ደግሞ ከሦስት የሚበልጡ አይሆንም፡፡ እኛ የምናካሂደው ሠላማዊ ትግል ነው፤ እኛ ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን፡፡ በቀጣይ በዚህ ላይ የምንሠራቸው ስራዎች ይኖራሉ፡፡ ከገዥው ፓርቲ ኦህዴድ ጋር ያለን ልዩነት እኛ እውነተኛ ፌደራሊዝም እንዲመሠረት፣ የዲሞክራሲ የፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ፣ ፍትሃዊና ነፃ ምርጫ እንዲካሄድ እንፈልጋለን። ስራዎች በሙሉ ተቋማዊ እንዲሆኑ እንሻለን፡፡ ፍትሃዊ የሆነ የኢኮኖሚ ክፍፍል እንዲኖርም እንታገላለን፡፡
ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሲባል ምን ማለት ነው-----ቢያብራሩት?
ለምሳሌ ኦሮሚያ የህዝብ ብዛቱ 40 ሚሊዮን ቢሆን፣ 5 ሚሊዮን ሕዝብ ካለው ሌላ ክልል ጋር እኩል መታየት የለበትም፡፡ መንገድ ሲሰራ፣ ልማት ሲካሄድ ለምሳሌ ት/ቤት፣ ጤና ጣቢያ ሲሰራ ይህን የህዝብ ብዛት ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ሌላው ለልማት ተብሎ የኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ከቀዬው መፈናቀል የለበትም፤ በልማት የሚነሱ ሰዎች ፍትሃዊ ካሳ ሊያገኙ ይገባል፡፡ በሥራ ቦታ ፍትሃዊ የሆነ አዳዲስ የፀዳ አሰራር እንዲኖር ነው የሚፈለገው። እኛ አፋን ኦሮሞ የፌደራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ይህም ፍትሃዊ ነው፡፡
ኦህዴድ አፋን ኦሮሞ የፌደራል የሥራ ቋንቋ ለማድረግ እታገላለሁ ብሏል፡፡ ሌሎች የእናንተ አጀንዳዎችም በኦህዴድ ሲቀነቀኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አጀንዳችሁን እየተነጠቃችሁ አይመስላችሁም?
በነገራችን ላይ አጀንዳችንን እየተነጠቅን አይደለም። አሁንም እነዚህ ጉዳዮች የምንታገልባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡ ኦፌኮ ዘላለማዊ ፓርቲ አይደለም፡፡ የተነሳለት የህዝብ አላማ የሚሳካ ከሆነ ደስተኞች ነን፡፡ ማንም አጀንዳውን ወስዶ ታግሎ ለህዝቡ ምላሽ እስካመጣ ድረስ ደስተኞች ነን፡፡ ነገር ግን ኦህዴድ እስካሁን ቀድሞ የነበረውን ፖሊሲውን፣ ፕሮግራሙን አልቀየረም፡፡ ዛሬም አብዮታዊ ዲሞክራሲን ነው የሚያጠነጥነው፡፡ በውስጡ ያሉ ግለሰቦች ናቸው የኛን ሃሳብ እያራመዱ ያየናቸው እንጂ እስካሁን የድርጅቱ ፕሮግራም አልተቀየረም፡፡ ዋናው ጥያቄ ኦህዴድ የለውጥ ሃይል መሆን የሚለው ምን ሲያደርግ ነው የሚለው ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ ተለውጧል? የፍትህ ተቋማት ነፃነትና ገለልተኝነት ምን ያህል ሰፍኗል? ሌሎችም ጥያቄዎች አሉ፡፡ እኛ ከድርጅቱ ውስጥ ተራማጅ ሆነው የወጡትን ግለሰቦች እናደንቃለን፡፡ ከጨለማ ውስጥ ራሳቸው ታግለው መውጣታቸውን ፓርቲያችን ያደንቃል። ቀጣዩ ፈተና ይህ የግለሰቦቹ የለውጥ እንቅስቃሴ ምን ያህል ወደ ድርጅቱ ይወርዳል? ይህም ካልሆነ ምን ያህል ተቋማዊ ይሆናል የሚለው ነው፡፡ ለውጡ ከግለሰቦቹ ተሻግሮ ተቋማዊ ካልሆነ የመቀልበስ እድሉ ሰፊ ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ ፅ/ቤት ለመክፈት በየቦታው ስንንቀሳቀስ የድሮው ተግዳሮት ተመልሶ እያጋጠመን ነው፡፡ ይህ ማለት ለውጡ እታች ድረስ አልዘለቀም  ማለት ነው፡፡
ኦፌኮ የብሄር ድርጅት ነው፡፡ ሃገሪቱ ደግሞ የብሄርተኝነት ስጋት የተደቀነባት እንደሆነች ምሁራን እያሣሠቡ ነው፡፡ ድርጅታችሁ ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከተዋል? በብሄርተኝነት እንቅስቃሴዎች ላይ ያላችሁ አቋም ምንድን ነው?
የብሄር አደረጃጀት የኢትዮጵያን አንድነት ያፈርሳል የሚል ስጋት የለንም፡፡ ይልቅስ የኢትዮጵያ አንድነት የሚፈርሰው እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለማኮላሸት ጥረት የሚደረግ ከሆነ ነው፡፡ ፌደራላዊ ስርአቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተመሰረተ ወዲህ ኦሮሞ እና ኦሮሞውን፣ አማራ እና አማራውን፣ ጉራጌ እና ጉራጌውን ነው ለማገናኘት ጥረት የተደረገው፡፡ ተመሳሳይ ባህል ቋንቋ፣ ሥነ ልቦና ያላቸውን ነው ለማገናኘት ጥረት የተደረገው። በተቃራኒው እነዚህን የመለያየት ባህሪ፣የቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡ በሃገራችን ላይ ፌደራሊዝም የአንድነት ፀር አይደለም፡፡ በዚያው ልክ አሃዳዊነት ደግሞ የአንድነት ወዳጅ አይደለም፡፡ አሃዳዊነት እና አንድነት የተለያዩ ፅንሰ ሃሳቦች ናቸው። አንድነት በፌደራላዊነትም ሆነ በአሃዳዊነት ስር የሚኖር ነው፡፡ አሃዳዊነት በአንድ አዝ ስር መተዳደር ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው አሃዳዊነት ደግሞ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ አልነበረውም፡፡ አንዱን ብሄር የማስበለጥ ባህሪ የነበረው ነው፡፡ ዋናው የብሄረሰቦችን መብት ሙሉ ለሙሉ የፈቀደ ፌደራላዊ ስርአት ቢመሠረት አንድነቱን የበለጠ ያጠናከረዋል፡፡ ለዚህች ሃገር መፍረስ ምክንያት የሚሆነው ትልቁ ስጋት፣ ፌደራሊዝም ሳይሆን ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ እንዳይወስን ሲደረግ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ ግንድ ነው፡፡ በኢኮኖሚውም በጂኦግራፊያዊ አቀማመጡም ብንመለከት፣ የኦሮሞ ህዝብ ለዚህች ሀገር ግንድ እንጂ ቅርንጫፍ አይደለም፡፡ ግንድ አይገነጠልም፤ የሚገነጠለው ቅርንጫፍ ነው፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ራሱን በራሱ እንዳያስተዳደር የሚያደርጉ አካላት ናቸው ጭንቀት ውስጥ የሚገቡት። የብሄር ብሄረሰቦችን ማንነት የማያውቁ ሰዎች ናቸው ለኢትዮጵያ አንድነት ፀር የሚሆኑት፡፡ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሚገባውን ቦታ ካላገኘም ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡
ይህ የብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ዜጎች በመጤነት እየተፈረጁ ያለአግባብ እንዲፈናቀሉ እያደረገ መሆኑን የሚናገሩ ወገኖች አሉ፡፡ ኦፌኮ በዚህ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
ይሄ ስለ ሃገር ምንነት የማያውቁ ሰዎች የሚፈጥሩት ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ ወደ አንድ ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለዋል፡፡ ይሄን ያደረገው ማን ነው ብለን ስንጠይቅ፤ ሶማሌው እንደ ሶማሌነቱ ተደራጅቶ አይደለም ያፈናቀለው ወይም ኦሮሞ እንደ ኦሮሞነቱ አይደለም ተደራጅቶ ያፈናቀለው፡፡ ይሄን ያደረጉት ክፋት የሚያስቡ ግለሰቦች ናቸው፡፡ ህዝብ እንደ ህዝብ ፈፅሞ አፈናቅሎ አያውቅም፡፡ ህዝብን ከህዝብ ጋር የሚያጋጩ ሃይሎች ናቸው ይህን የሚፈፅሙት፡፡
ብሄርተኝነት አስጊ ሊሆን የሚችለው መልካም አስተዳደር ከጠፋ ብቻ ነው፡፡ ጥሩ መሪ ከሌለ ችግር ይፈጥራል ማለት ነው፡፡ ሕገ መንግስቱ ነው በአግባቡ መተግበር ያለበት፡፡ ህገ መንግስቱ እንኳ ዘመኑን አይመጥንም ከተባለ መሻሻል አለበት፡፡ ህገ መንግስት እስከተከበረ ድረስ ብሄርተኝነት ለዚህች ሃገር ስጋት አይደለም፡፡
ኦሮሞ ተገቢው ቦታ አላገኘም የሚል መከራከሪያ ድርጅታችሁ ሲያቀርብ ቆይቷል፤ አሁን ቁልፍ የሥልጣን ቦታዎች በኦሮሞ ተወላጆች እየተያዘ መምጣቱ፣ለጥያቄያችሁ ምላሽ ሰጥቷችኋል ማለት ይቻላል?
ኦሮሞ የሚገባውን ጃኬት በቁመቱ ልክ አልለበሰም ስንል፣ ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዝዳንት ይሁን እያልን አይደለም፡፡ ማንም ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ፕሬዝዳንት መሆን ይችላል፤ ነገር ግን ሥርአቱ ፍፁም ዲሞክራሲያዊ ይሁን ነው ጥያቄያችን እንጂ የሥልጣን ብቻ አይደለም፡፡ ኦሮሞ በዚህች ሃገር ታሪክ ውስጥ ከኢኮኖሚው፣ ከፖለቲካውና ከማህበራዊ መስተጋብሩ ተገልሎ ቆይቷል፣ ከዚህ በኋላ መገለል የለበትም ነው ትግሉ፡፡ ኦሮሞ ሥልጣን ይዞ ሌላውንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው መሆን ያለበት፡፡ አሁንም ሰዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ነገር ኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ አልሆነ አይደለም ጥያቄው፤ ዋነኛ ጥያቄው ሥርአቱ ዲሞክራሲያዊ ይሁን ነው፡፡  ፍትሃዊ የሆነ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መስፈን አለበት፡፡ አንዱ የእናት ልጅ፣ አንዱ የእንጀራ ልጅ መሆን የለበትም ነው ጥያቄው እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ስትሰፋ የግድ የኦሮሞ ተወላጆች መስዋዕት መሆን የለባቸውም፡፡ እነሡ ከቀዬአቸው ያለ በቂ ካሳ እየተፈናቀሉ፣ ሌላው በቦታቸው ባለፎቅ መሆኑ ፍትሃዊ አይደለም ነው ጥያቄው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ሁሉም የሚባለውን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማግኘት አለበት የሚለው ነው፡፡ የኛም ትግል ዋና ግቡ፤ ሥልጣን ሳይሆን የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ሲታጣ ነው በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ብሄርተኝነት ከፍ የሚለው፡፡ ህዝብ ጥቅሙ ሲነካ ነው ብሄርተኝነት የሚያይለው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሄር ለብሄር እስካሁን ምንም የተፈጠረ ግጭት የለም፤ ለወደፊትም የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡
ኦሮሚያ አካባቢ የሚታየው  የፀጥታ መደፍረስና ግጭት ከምን የመነጨ ነው?
እነዚህ ግጭቶች በፊትም ያሉ ናቸው፡፡ ተስፋ ባልቆረጡ የገዥው ፓርቲ ሃይሎች የሚነሱ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ በዚህ ሃገር ውስጥ ተቃዋሚዎች በሁለት አቅጣጫ ማለትም በሠላማዊና በመሣሪያ ሲታገሉ የነበሩ አሉ፡፡ በሠላማዊ መንገድ ሲታገሉ የነበሩ የኛን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎችም አሉ፡፡ እነሡ ይሄን እድል ተጠቅመው ሠላማዊ ትግላቸውን እያጠናከሩ ነው። ሌላው ደግሞ በመሳሪያ ሲታገሉ የነበሩት ናቸው፡፡ መንግስት ከእነዚህ ሃይሎች ጋር ምን ያህል ተነጋግሯል? መሣሪያቸውን አስቀምጠው እንዲታገሉ ምን ያህል ሁኔታዎች ተመቻችተዋል? የሚለው የኛም ጥያቄ ነው። ሌላው የገዥው ፓርቲ አባላት የነበሩ እና የተባረሩ ናቸው፡፡ እነሡ ዛሬም ቢሆን ሌብነትና ዘረፋ ያካሂዳሉ፡፡ ይሄን ለማካሄድ ደግሞ እንዲህ ያለው ማደናገሪያ ያስፈልጋል፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ አሁንም የሚከብዳቸው ይሄን ህዝብ ማስተዳደር ሳይሆን የራሳቸውን (ኢህአዴግን) ድርጅት ማስተዳደርና መግዛት ነው፡፡ ይህን ድርጅት መግዛት ይኖርባቸዋል። በየቦታው የሚታየው ግጭት ይህን ያለማድረጋቸው ውጤት ነው፡፡ በሌላ በኩል በሶስት ወራት ሙሉ ለሙሉ ችግር መፍታት ይከብዳል፤በቀጣይ ብዙ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነፃነት ፅ/ቤታቸውን ከፍተው እንዲንቀሳቀሱና ህዝብ በእነሱ ስር እየገባ በሠላም የሚታገልበትን እድል መፍጠርም ያስፈልጋቸዋል፡፡
የዶ/ር ዐቢይ አመራር በኦሮሚያ ያላቸው ድጋፍ  ምን ያህል ነው?
ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ሲመጡ የመጀመሪያው ትልቁ የድጋፍ ሰልፍ የተደረገው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ዋና ከተማው አዲስ አበባ - ፊንፊኔ ከተማ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የአዲስ አበባ ፊንፊኔ እና በዙሪያዋ ያሉ የኦሮሚያ ከተሞች ህዝብ ወጥቶ ነው ድጋፍ የሰጠው፤ ይሄ እነ ዶ/ር ዐቢይ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ድጋፍ እንዳላቸው ያመላክታል፡፡ የኛ ፓርቲ አባላትም በዚህ የድጋፍ ሰልፍ ላይ በስፋት ተገኝተዋል። የኦሮሚያ ህዝብም ሆነ የኛ ፓርቲ በእነ ዶ/ር ዐቢይ አመራር ላይ ቅሬታ የለውም፡፡
ለአመራሩ ሙሉ ድጋፍ ትሰጣላችሁ ማለት ነው?
አዎ! ድጋፍ እንሰጣቸዋለን፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አደገኛ እሳት ሲነድ እንደነበር ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡ የእነ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣኑ መምጣት  እሣቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲጠፋ ማድረግ ባይችል እንኳ እንዲዳፈን አድርጎታል፡፡ ተቀጣጥሎ በነበረው እሳት ውስጥ ሁላችንም እንቃጠል ነበር፡፡ ከዚህ እሣት እነ ዶ/ር ዐቢይ አስጥለውናል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አሁን በሃገሪቱ የመንግሥት ወይም የሥርዓት ለውጥ መጥቷል ማለት አይደለም፡፡ የግለሰቦች ለውጥ ነው የመጣው፡፡ የግለሰቦች ቅንነት ነው የሚታየው፡፡ ነገር ግን ይሄን ያህል በእነዚህ ሰዎች ቅንነት ተንፈስ ማለት ስለቻልን፣ ለወደፊት ለሚፈለገው ለውጥ ጠቃሚ ነው፡፡ እነዚህን የለውጥ ሃይሎች ደግሞ ከኢህአዴግ ውስጥ መንጭቆ ያወጣቸው የቄሮ እና ቃሬ ትግል እንጂ የኢህአዴግ ሪፎርም አይደለም፡፡
በአገሪቱ ውስጥ አወዛጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የሠንደቅ አላማ ጉዳይ ነው፤ በሠንደቅ አላማ ላይ ኦፌኮ ያለው አቋም ምንድን ነው?
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሠንደቅ አላማን በተመለከተ ውይይት መካሄድ አለበት፡፡ በጉዳዩ ላይ ምሁራን ጥናት ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ህዝብን አማክሎ ጥናት መደረግ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሃገርነት ግንባታ በአንድ ጀንበር የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ካልተጠናቀቁት ጉዳዮች አንዱ ደግሞ የሠንደቅ አላማው ጉዳይ ነው፡፡ የሠንደቅ አላማ ጉዳይ እልባት ሊያገኝ የሚችለው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ህዝብ ነው መወሰን ያለበት፡፡ ምሁራን አጥንተው በሚያቀርቡት አማራጭ ላይ ህዝበ ውሳኔ  ነው መደረግ ያለበት፡፡ እኛ እንደ ፓርቲ እስካሁን በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ላይ የያዝነው አቋም የለም፡፡ እኛ ህገ መንግስቱን ተቀብለን ሠላማዊ ትግል የምናደርግ እንደመሆኑ፣ በዚያ ነው ስንንቀሳቀስ የቆየነው፡፡ አሁን ደግሞ ህዝብ የፈለገው ነው መሆን ያለበት፡፡ ህዝብ ነው በሠንደቅ አላማ ጉዳይ መወሰን ያለበት፤እኛ የፖለቲካ ድርጅቶች አይደለንም፡፡ እንደኔ ግን ሠንደቅ አላማው ኢትዮጵያዊነታችንን፣ አፍሪካዊነታችንን የሚገልፅ ቢሆን እመርጣለሁ፡፡
ኦፌኮ እንዴት ነው ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ያሰበው?
ቀጣዩ ትልቁ ሥራችን ህዝብን ማወያየት ነው፡፡ ፖሊሲያችንን ከወትሮው በተለየ ለህዝብ እናስረዳለን። ገና ብዙ የሚቀሩን ሥራዎች አሉ፡፡ አባሎቻችንን ማሠልጠን ማስተማር ይኖርብናል፡፡ የህዝብ ውሣኔ የሚከበርበትና ህዝብ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የምንሠራው፡፡

Read 6401 times