Saturday, 04 August 2018 10:18

የቤተ ክርስቲያኒቱን አንድነት ማብሰሪያ ጉባኤ ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(5 votes)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አንድ መሆንና የተፈጠረውን እርቀ ሠላም የሚያበስር ጉባኤ፣ በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ 25 ሺህ  ተሳታፊዎች በሚገኙበት በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡
ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ መሆኑ የተነገረለት ጉባኤ፤ ሙሉ ለሙሉ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና በጠበቀ መልኩ በመንፈሳዊ መርሃ ግብሮች እንደሚከወን የተገለጸ ሲሆን ጉባኤው በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በቀጥታ እንደሚተላለፍም  ታውቋል፡፡
በሚሊኒየም አዳራሽ ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው መርሃ ግብር፤ በዋናነት ላለፉት 26 ዓመታት ለሁለት ተከፍሎ የነበረው የቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አንድነት መምጣቱን ማወጂያና በአሜሪካ በስደት ላይ የነበሩትን ፓትርያርክ አቡነ መርቆሪዎስ ይፋዊ የአቀባበል መርሃ ግብር የሚከናወንበት ነው ተብሏል፡፡
ለቤተ ክርስቲያኒቱ የእርቅ ሂደት መፍጠን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድም በእለቱ በቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ መዝገብ ላይ መስፈራቸው ይፋ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዚህ ጉባኤ ላይ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ የተለያዩ ሃገራት አምባሣደሮችና ዲፕሎማቶች፣ የቤተ እምነቶችና ሃይማኖቶች ተወካዮችና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እንደሚታደሙበት ተጠቁሟል፡፡  
ጉባኤውን መንግስት በራሱ ወጪ እንዳዘጋጀው የታወቀ ሲሆን በጉባኤው ላይ በቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ለሃገሪቱ ቀጣይነት ያለው ሠላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር እንደሚደረግ ለማወቅ ተችሏል፡፡  
በአሜሪካ ሃገር የተፈፀመውን እርቀ ሠላም ተከትሎ ረቡዕ ሐምሌ 25 ቀን 2010 ዓ.ም ላለፉት 26 አመታት በስደት ላይ የነበሩት 4ኛው የኢ/ኦተ/ቤ/ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዎስ እና የሲኖዶስ አባላት ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡


Read 5954 times