Saturday, 04 August 2018 10:34

ብህትውናና ዘመናዊነት

Written by  ብሩህ ዓለምነህ (በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር)
Rate this item
(2 votes)

 ክፍል-7 ‹‹ቅድስቲቱን›› ሀገር የመፍጠር ፕሮጀክትና የአማራነት ንቃተ ህሊና መደብዘዝ
          
    እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በአማራ ክልል ውስጥ ‹‹እኔ አማራ ነኝ›› ማለት ‹‹እኔ ክርስትያን ነኝ›› እንደ ማለት ነበር የሚቆጠረው፡፡ ከ1966ቱ አብዮት በኋላ የዘውግ ማንነት በተፋፋመበት ወቅት ሳይቀር አማራው ራሱን ከብሄር ይልቅ በሃይማኖታዊ ማንነት ሲገልፅ ነበር፡፡ ይሄም አማራው በአዲሱ የብሄር ፖለቲካ ውስጥ ግራ እንዲጋባ፣ ትክክለኛ ስፍራ እንዳያገኝና ብሎም ለጥቃት እንዲጋለጥ ዳርጎታል፡፡  
ክስተቱ ከዚህም በላይ ሄዶ ‹‹አማራ የሚባል ብሄር አለ? ወይስ የለም?›› እስከማለት የደረሰ ውዝግብን አስነስቷል፡፡ ለመሆኑ፣ ሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ራሳቸውን በብሄር ማንነት በሚገልፁበት ወቅት፣ አማራው እንዴት ተለይቶ በሃይማኖታዊ ማንነት ሊገኝ ቻለ? ይሄ የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ? ይህ ፅሁፍ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ይሞክራል፡፡
በመጀመሪያ ትንሽ ወደ ኋላ ልመልሳችሁና በክፍል-2 ፅሁፌ ላይ ‹‹ብህትውና ከግሪክ ተነስቶ በአሌክሳንደሪያ አድርጎ ገና አክሱም ላይ ከመድረሱ ከፖለቲካ ጋር ጋብቻ መፈፀሙ፣ አክሱማውያን ላይ ሁለት ዓይነት ዘላቂ አሻራዎችን እንዲያስቀምጥ አድርጎታል›› በማለት ገልጬ  ነበር፡፡
‹‹የመጀመሪያው፣ የብህትውና አስተሳሰብ በጣም በፍጥነት እንዲስፋፋና በአጭር ጊዜ ውስጥም የህዝቡ ባህል ሆኖ እንዲወጣ ማድረጉ ነው፡፡ የዚህ ማሳያው ደግሞ የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ከብህትውናው ባህል መነሳቱ ነው። ምክንያቱም ሙዚቃም ሆነ ማንኛውም ዓይነት የኪነጥበብ ሥራ የፈጠራ ስሜቱን (Creative impulse) የሚቀዳው ማህበረሰቡ ውስጥ ከተነጠፈው ባህል ነውና፡፡››
‹‹ሁለተኛው ደግሞ፣ ብህትውና ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› ለመፍጠር ‹‹የብሄራዊ ሀገር ግንባታ›› ፕሮጀክት ይዞ መነሳቱ ነው›› በማለት ዝርዝሩን በሌላ ጊዜ እንደምመለስበት ቃል ገብቼ ነበር፡፡ ይህ የዛሬው ፅሁፍም ይሄንን በእንጥልጥል ያቆየሁትን ሐሳብ የሚቋጭ ነው፡፡
ብህትውና በፍልስፍና ውስጥም ሆነ በሃይማኖት ውስጥ የተከሰተው ቀድሞ የነበረውን ሰው በአዲስ አስተሳሰብና ስነ ምግባር ለመቅረፅ ታስቦ ነው፡፡ ባጭሩ፣ የብህትውና ፕሮጀክት ‹‹አዲሱን ሰው›› መፍጠር ነው - ልክ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አዲሱን ሰው ልበሱ!!›› እንዳለው፡፡
ለምሳሌ፣ ፕሌቶ የብህትውናን አስተሳሰብ ለፍልስፍናው የተጠቀመበት፣ የሰውን ልጅ ከስሜታዊነት ግልቢያ ወደ የምክንያታዊነት እርካብ ለማሻገር ነው- በምክንያታዊነት የተገራ ‹‹አዲሱን በጎ ሰው›› ለመፍጠር ነው፡፡ ፕሌቶ ‹‹በጎ ሰው›› (Virtuous Person) የሚለው ሦስት ነገሮችን የሚያሟላ ነው- የተረጋጋ (moderate)፣ ብርቱ (courageous) እና ምክንያታዊ (prudent) ሲሆን ነው፡፡ በፕሌቶ አመለካከት የስሜት መገራትን፣ የሞራልና የምክንያታዊነት ልዕልናን ጥምረት በማምጣት ‹‹በጎነት››ን መፍጠር የሚችለው ብህትውና ብቻ ነው፡፡
ሃይማኖታዊ በሆነው እሳቤ ደግሞ ብህትውና አዲሱን ‹‹መንፈሳዊ ሰው›› የመፍጠሪያ መንገድ ነው፡፡ የፕሌቶ ብህትውና የመጨረሻ ግቡ ሞራላዊነት ሲሆን፣ ሃይማኖታዊው ብህትውና ደግሞ ግቡ ከሞራላዊነት በተጨማሪ መንፈሳዊነትንም መቀዳጀት ነው፡፡
ሃይማኖታዊውም ሆነ ፍልስፍናዊው የብህትውና አስተሳሰብ መነሻው በግለሰብ ደረጃ ‹‹አዲሱን ሰው›› መፍጠር ቢሆንም፣ የመጨረሻ ግቡ ግን አዲስ ማህበረሰብን መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ረገድ የፕሌቶ ርዕይ በፈላስፎች የሚመራ ማህበረሰብ መፍጠር ሲሆን፣ የሃይማኖታዊው ብህትውና ርዕይ ደግሞ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› መፍጠር ነው፡፡ ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› ለሰማያዊዋ እየሩሳሌም ዝግጅት የሚደረግባት በቅዱሳን የተሞላች ምድራዊ ሀገር ናት፡፡
የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ተሻለ ጥበቡ ‹‹The Making of Modern Ethiopia›› በተባለው የዶክትሬት ማሟያ መፅሐፉ ውስጥ ይሄንን በኢትዮጵያ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› የመፍጠር ፕሮጀክት፣ ‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ›› ይለዋል (1995፡ 13)፡፡ ይህ ሥልጣኔ (ፕሮጀክት) በሃይማኖት፣ በስነ መንግስት፣ በሰንደቅ ዓላማና በህገ መንግስት ደረጃ ከጥንታዊ የአክሱም ዘመን ጀምሮ የራሱን መለያዎች ይዞ የወጣ ነው፡፡ እነዚህም መለያዎች ‹‹በሃይማኖት ረገድ ‹‹የእስራኤል አምላክ››ን ሲያመልክ፣ በስነ መንግስት ደረጃ ደግሞ ‹‹ሰሎሞናዊ ሥርወ መንግስት››ን ይከተላል፤ በሀገር ደረጃ ‹‹መንግስተ እግዚአብሔር››ን፣ በሰንደቅ ዓላማ ደግሞ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ››ን፣ እንዲሁም በህገ መንግስት ‹‹ክብረ ነገስት››ን ይከተላል›› (1995፡ 14)፤ በቋንቋ ደግሞ ግዕዝን ይጠቀማል፤ በአማርኛ እስኪተካ ድረስ፡፡
ይሄ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ነገር አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ‹‹ብሄር ዘለል›› የሃይማኖት ፕሮጀክት፣ ክርስትናና እስልምና በተስፋፋባቸው የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅ አካባቢዎች ላይም ታይቷል፡፡ የአውሮፓውያኑን የ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› ፕሮጀክት በደንብ ተንትኖ የፃፈው ቅዱስ ኦገስቲን (354-430) ነው- ‹‹The City of God›› በተባለው ስራው ውስጥ፡፡ በዚህም ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› (Heavenly City) እንዴት ከ‹‹አሕዛባውያን ሀገር›› (Earthly City) በባህሪ እንደምትለይ በዝርዝር ፅፏል፡፡ ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› ዓለማዊ ህይወት፣ ፖለቲካ፣ ሀብት፣ ዓለማዊ ዕውቀትና ፈንጠዝያ የማያጓጓት፣ መጪውን ዓለም ብቻ ተስፋ እያደረገች በመንፈሳዊነት የምትኖር ሀገር ናት›› ይላል ኦገስቲን፡፡ በእኛም ሀገር ተመሳሳይ ፕሮጀክት ነው ተግባራዊ የተደረገው፡፡
ብህትውና ገና አክሱም ከመድረሱ ፖለቲካዊ ቅቡልነት ማግኘቱ በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹‹አዲሱን መንፈሳዊ ሰው መፍጠር›› ከሚለው የቅርብ ጊዜ ግብ በአንድ ጊዜ ወደ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር መፍጠር›› ወደሚል የሩቅ ጊዜ ርዕይ እንዲሸጋገር አደረገው። ይህ ርዕይ የተጀመረው ደግሞ 6ኛው ክፍለ ዘመን ላይ መጀመሪያ በዘጠኙ ቅዱሳን፣ ቀጥሎ በቅዱስ ያሬድ፣ ከዚያም በራሳቸው በነገስታቱ ነው፡፡ ለምሳሌ፣ በ9ኛው ክፍለ ዘመን  ላይ አፄ ደግናዥን (837-856) ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር ለመፍጠር›› ዋና መቀመጫቸውን ከአክሱም ወደ ወይናደጋ (ጎንደር) በማድረግ፣ 150 የሚሆኑ የአክሱም ካህናትን ከወታደሮች ጋር ወደ ሸዋና አምሐራ አገር አሰማርተዋል፡፡ በዚህም፣ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር‹‹ የመፍጠር ፕሮጀክቱ በ300 ዓመታት ውስጥ ከአክሱም ተነስቶ አማሮች ወደ ሰፈሩበት ወደ ጎንደር፣ ወሎ፣ ጎጃምና ሸዋ ድረስ መስፋፋት ችሏል፡፡
ይሄንን ‹‹ብሄር ዘለል›› ፕሮጀክት ሸዋ ላይ በስፋት በማስፈፀም ትልቅ አበርክቶት ያደረጉት ደግሞ አባ ተክለ ሃይማኖት (1207-1305) ናቸው፡፡ አባ ተክለ ሃይማኖት ላይ የደረሰው ይህ ፕሮጀክት መነሻው ከዘጠኙ ቅዱሳን አንዱ የሆኑት አቡነ አረጋዊ ናቸው። ታሪኩም ሲተረክ፤ ‹‹አቡነ አረጋዊ አባ ዮሐኒን፣ አባ ዮሐኒ አባ እየሱስ ሞአን፣ አባ እየሱስ ሞአ ደግሞ አባ ተክለ ሃይማኖትን በመንፈስ ወለዱ›› የሚል ነው፡፡
አባ ተክለ ሃይማኖት ይሄንን ፕሮጀክት ይዘው ከሸዋ አልፈው እስከ ሀድያና ወላይታ ድረስ ተጉዘዋል። ሆኖም ግን ዘመናቸው አልበቃ ስላላቸው ርዕያቸውን ለተከታዮቻቸው አውርሰው አልፈዋል፡፡ ሸዋ ላይ የተተከለው ይህ የአባ ተክለ ሃይማኖት ርዕይ፤ የሰሎሞናዊ ስርወ መንግስት መመለስን ተከትሎ፣ ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› የመፍጠር ፕሮጀክት፣ በአዲስ ጉልበት እንደ አዲስ ተነሳስቷል፡፡ በዚህም ከ12ኛው እስከ 15ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ይሄንን ፕሮጀክት በሁሉም አቅጣጫ የሚያስፋፉ በርካታ መነኮሳት ተነስተዋል፡፡
ፕሮጀክቱን የአክሱም ነገስታት ብቻ ሳይሆን የዛጉዌና የሰሎሞናውያን ነገስታትም በባለቤትነት ሲያስፈፅሙት ነበር፡፡ ፍጥነቱና ቁርጠኝነቱ ግን ከአፄ ይኩኖ አምላክ እስከ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ድረስ የነገሱ ተከታታይ የሸዋ አማራ ነገስታትን የሚደርስበት የለም። የመጨረሻው የዚህ ፕሮጀክት ትልቁ ፈፃሚ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ናቸው፡፡ አፄ ምኒሊክ ወደ ደቡብ፣ ምዕራብና ምስራቅ ሲስፋፉ፣ ይሄንን ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› የመፍጠር ፕሮጀክት ይዘው ነው፡፡
የ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› አባል ለመሆንና በዚህ ሩቅ ርዕይ ውስጥ ለመታቀፍ ደግሞ ብቸኛው መስፈርት ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፤ ‹‹ወንድ-ሴት፣ የተገረዘ-ያልተገረዘ፣ እብራዊ-ግሪካዊ መሆን አይደለም››፤ አማራ-ትግሬ፣ አገው-ቅማንት መሆን አይደለም፤ ይልቅስ ‹‹በክርስቶስ የተዋጀ ‹‹አንድ ሰው-ነት›› (ገላ 3፡ 28) ነው እንጂ፡፡
የአክሱም ብህትውና በዚህ ርዕይና ‹‹አንድ የሰው-ነት›› መስፈርት ነበር ወደ ደቡብ እስከ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎና ሸዋ ድረስ የተስፋፋው፡፡ በዚህ ‹‹አንድ የሰው-ነት›› ፕሮጀክት ውስጥ የብሄር ማንነቱን በመጀመሪያ ያጣው አማራው ነው፡፡ አማራው በ6ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ራሱን በብሄር ይገልፅ እንደነበር የፕ/ር አሸናፊ ከበደ፣ የመሪራስ አማን በላይና የአለቃ ታዬ ገ/ማርያም ስራዎች ፍንጭ ይሰጡናል፡፡
ፕ/ር አሸናፊ ከበደ ‹‹The Music of Ethiopia: Its Development and Cultural Setting›› በሚለው የዶክትሬት ማሟያ ፅሁፋቸው ውስጥ ቅዱስ ያሬድን ከትግሬ እናትና ከአማራ አባት፣ በአክሱም የተወለደ ነው›› ይሉታል (1971፡ 41)። ቅዱስ ያሬድ የዜማ ምልክቶቹን ‹‹ቅናት፣ ደረት፣ ጭረት …›› እያለ በአማርኛ መሰየሙ ያሬድ በኖረበት 6ኛው ክፍለ ዘመን ላይ አማራና አማርኛ መኖራቸውን ያሳያል፡፡
መሪራስ አማን በላይም ‹‹መፅሐፈ አብርሂት›› በሚለው መፅሐፋቸው ውስጥ “አፄ ካሌብ በ518 ዓ.ም የናግራን ክርስትያኖችን ከግድያ ለመታደግ ወደ የመን ካዘመቱት ሰባ ሺ ሰራዊት ውስጥ አብዛኛው የአማራ ወታደር ነበር” ይላሉ (2009፡ 232)፡፡ በአፄ ምኒሊክ ዘመን ባለስልጣን የነበሩት አለቃ ታዬ ገ/ማርያም ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ›› በሚለው መፅሀፋቸው ውስጥ ‹‹በጥንት አክሱማውያን ነገስታት ውስጥ የአማርኛ ስሞች መኖራቸው፣ ከጥንት ዘመን ጀምሮ አማሮች መኖራቸውን ያሳያል›› ይላሉ (2008፡ 38)፡፡
ከእነዚህ ማስረጃዎች ተነስተን ራሱን ‹‹አማራ›› ብሎ በብሄር የሚጠራ ህዝብ፣ በጥንታዊ አክሱም ስልጣኔ ዘመን እንደነበረ መደምደም እንችላለን። ሆኖም ግን ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› የመፍጠር ፕሮጀክት አማራውን ከብሄር ይልቅ ራሱን በሃይማኖታዊ ማንነት እንዲገልፅ አድርጎታል። በርግጥ ይሄ ነገር በትክክል መቼ እንደተጀመረ ባይታወቅም፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ግራኝ መሐመድ ክርስቲያናዊውን ግዛት በወረረበት ወቅት የግራኝ መሐመድ ወታደሮች ክርስትያኖችን ለይቶ ለማጥቃት እንዲመቻቸው የህዝቡን አባባል በመውሰድ ‹‹አንተ አማራ ነህ? ወይስ ሙስሊም?›› የሚል ቃል ይጠቀሙ እንደነበር መሪራስ አማን በላይ ፅፈዋል፡፡
ይህ ፕሮጀክት በተለያዩ ታሪካዊ ወቅቶች ላይ ሦስት ተግዳሮቶች ገጥሞታል፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ተግዳሮቶች፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከምስራቅ (ከእስላማዊ ሱልጣኔቶች) እና ከደቡብ (ከኦሮሞ ማህበረሰብ) የመጣ ነው፡፡ ምስራቃዊው ተግዳሮት ራሱን በእስላማዊ ሃይማኖት የሚገልፅ ሲሆን፤ የደቡቡ ተግዳሮት ደግሞ ራሱን በብሄር የሚገልፅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ‹‹ቅድስቲቱን ሀገር›› የመፍጠር ፕሮጀክቱ እነዚህን ሁለት ተግዳሮቶች በመቋቋም ዳግም በ19ኛው ክ/ዘ በዳግማዊ አፄ ምኒሊክ እንደገና ወደ ደቡብ መስፋፋት ጀመረ። ፕሮጀክቱ የከረረ ተቃውሞ ማስተናገድ የጀመረውም በዚህ በ19ኛው ክ/ዘ መጨረሻ ላይ በአፄ ምኒሊክ ዘመን ነበር፡፡
የቅራኔው መነሻ ደግሞ ‹‹ብሄር ዘለል›› የሆነው የ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› የብሄራዊ ሀገር ግንባታ ፕሮጀክት፣ ራሳቸውን በብሄር ማንነት ከሚገልፁ ህዝቦች ጋር ሊጣጣም አለመቻሉ ነው፡፡ ይሄም ቅራኔ እያደገ ሄዶ የ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› ፕሮጀክት ከአብዮቱ ‹‹የብሄር ብሔረሰቦች ሀገራዊ ፕሮጀክት›› ጋር በተቃርኖ ቆመ። እንግዲህ ይህ ተቃርኖ ነው ከአብዮቱ ጊዜ ጀምሮ የአማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ የዘውግ ፖለቲካ እንዲፈለፈል ያደረገው፡፡
የ‹‹ቅድስቲቱ ሀገር›› የብሄራዊ ሀገር ግንባታ ፕሮጀክት የዘውግ ፖለቲከኞች እንደሚያወሩት፣ የብሄር ፕሮጀክት ሳይሆን ሃይማኖታዊ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ ብሄር ዘለል መሆኑ ደግሞ ሁለት ፖለቲካዊ ባህሪዎች እንዲኖሩት አድርጎታል፡፡ የመጀመሪያው፣ ምንም እንኳ ነገስታቱ በዘር አማራ ቢሆኑም፣ በፕሮጀክቱ ጥንታዊነትና ባህሪ የተነሳ ግን የአማራነት ንቃተ ህሊና በሂደት በማህበረሰብ ደረጃ ስለተተወ፣ ነገስታቱ ራሳቸውን በክርስቲያናዊነት ብቻ እንዲገልፁ አድርጓቸዋል፡፡ ይሄም፣ ነገስታቱን ከብሄር አድልዖ የፀዱ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ፣ ፕሮጀክቱ የብሄር አድልዖ ስላልነበረው፣ የፕሮጀክቱ ብቸኛ መስፈርት የሆነውን ‹‹ክርስትያናዊነትን›› የሚያሟላ የማንኛውም ብሄር አባል የሆነ ሰው እንደ ችሎታው ወደ ከፍተኛው የሥልጣን መሰላል ለመውጣት ክፍት መሆኑ ነው፡፡ ከምርኮ ተነስተው የአፄ ምኒሊክ የጦር ሚኒስትር እስከ መሆን የደረሱት ፊታውራሪ ሐብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ (አባ መላ) ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡
የፕሮጀክቱ ዋነኛ ችግር ደግሞ ዘመናዊነት ካመጣው የሥነ መንግስት እሳቤ ጋር ራሱን ከማሻሻል ይልቅ በድሮው ባህሪና እሳቤ ለመጓዝ መፈለጉ ነው፡፡ ይሄም ዝንባሌው በአብዮቱ ተማሪዎች ክፉኛ እንዲተችና ፕሮጀክቱ ‹‹አግላይና ጠቅላይ ነው›› የሚሉ ድምፆች እንዲበዙበት አድርጎታል፡፡ ነጋድራስ ገብረ ህይወት ባይከዳኝ ከአብዮቱ 60 ዓመታት ቀድሞ ‹‹የሃይማኖት ነፃነት ይታወጅ›› በማለት የሀገር ግንባታው ፕሮጀክት ከሃይማኖታዊ ይዘት ወጥቶ ዓለማዊ ይዘት እንዲኖረው ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊው በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር እና ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› መፅሐፍ ደራሲ ሲሆን በኢ-ሜይል አድራሻው -  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 1582 times