Monday, 10 September 2018 00:00

“ዶ/ር ዐቢይ የኢህአዴግ ሽታ እንኳን የላቸውም”?!

Written by  ኤልያስ
Rate this item
(25 votes)

 • ኢህአዴግን ያተረፈው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይሆን የመደመር ፍልስፍና ነው
   • ህጻናት የሚወዷቸውና እናቶች የሚጸልዩላቸው ጠ/ሚኒስትር አግኝተናል
   • አዲሱ ዓመት ለጦቢያና ልጆቿ ታላቅ የምህረትና የእርቅ ዓመት ነው
         

    አንዳንድ ፖለቲከኞች፣ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፣ በማይታመን ፍጥነት እየከወኑ ያሉትን አስደማሚ ሁለንተናዊ ለውጥ (ሪፎርም) ለማጣጣል ሲከጅሉ፣ ኢህአዴግነታቸውን ሊያስታውሱን ይዳዳቸዋል፡፡ (ለማድነቅ ያልታደሉ ናቸው!) እናም፤ “ዞሮ ዞሮ እኮ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር መሆናቸውን መርሳት የለብንም!” ይላሉ፤ አዲስ ግኝት የነገሩን ይመስል፡፡ (ማንም የተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀ መንበር ናቸው አላለም!) ጠ/ሚኒስትሩም፤ለመሸወድም ሆነ ለማስመሰል ሞክረው አያውቁም፡፡ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር መሆናቸውን ከልባቸው አምነው፣ በትጋት እየመሩ መሆኑን ደጋግመው ነግረውናል፡፡ (እኛም እያየን ነው!) ግን እኮ ከሳቸው በፊት ቢያንስ ሁለት የኢህአዴግ ሊቀ መንበሮችን እናውቃለን፡፡ ሆኖም ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ጨርሶ አይመሳሰሉም፡፡ በዕድሜ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር፡፡ (የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ከተባለ፣የኢህአዴግ ሊቀ መንበርነታቸው ብቻ ነው!)  በአጭሩ አራምባና ቆቦ ናቸው!
የበዓለ ሲመታቸው ዕለት የፓርማ አባላትን ጭምር ካፈዘዘው አስደማሚ ንግግራቸው አንስቶ ከቀድሞ አቻዎቻቸው በእጅጉ ይለያሉ - ዶ/ር ዐቢይ፡፡ በኢህአዴግ ታሪክ እናታቸውንና ውድ ባለቤታቸውን በአደባባይ ያመሰገኑና ያከበሩ የመጀመሪያው ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣን (የኢህአዴግ አመራር) ይመስሉኛል፡፡ (እናትንና ሚስትን ማመስገን ማስገምገሙ ይገርማል!) ላለፉት 27 ዓመታት የኢህአዴግ አመራሮች----ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ የሌላቸው ይመስል፣ መቼ ስለ እናት አባት ወይም ልጆቻቸው አሊያም የትዳር ጓደኞቻቸው አንስተው ያውቃሉ? (Taboo እኮ ነው የሚመስለው!) ሌላው ቀርቶ የመንግስት ባለስልጣናት መቼ ከትዳር አጋራቸው ጋር በአደባባይ ታይተው ያውቁና ነው!! (በኢትዮጵያ ሚሊኒየም በዓል ላይ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ከባለቤታቸው ጋር ደነሱ ልበል?!) የሆኖ ሆኖ ግን ዶ/ር ዐቢይ፣ ይህንን በጎ ያልሆነ የፓርቲያቸውን ባህል ሰብረውታል፡፡ (ምን ያልሰባበሩት ነገር አለ!?)
በነገራችን ላይ ከስልጣናቸው በፈቃዳቸው የለቀቁት የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ባለቤታቸውን በአደባባይ ያመሰገኑት እኮ በቤተ መንግስት በተዘጋጀላቸው  የሽልማትና የአሸኛኘት ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ (ዕድሜ ለዶ/ር ዐቢይ!) በእርግጥ አሁን ነጻ ሳይሆኑ አይቀሩም - ከኢህአዴግ የግምገማ ወጥመድ ተላቀዋል!
ዶ/ር ዐቢይ ፓርቲያቸው ሲከተለው ከኖረው የጎሳ ፖለቲካ (ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን ከሚያቀነቅነው!) በተቃራኒው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ በማተኮር፣ አንድነትን የሰበኩ የመጀመሪያው የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ይመስሉኛል፡፡ “ስንኖር ኢትዮጵያዊ፣ ስንሞት ኢትዮጵያ እንሆናለን” የሚለው ዝነኛ አባባላቸው የብዙዎችን ቀልብና ስሜት ገዝቷል። (የኦቦ ለማ መገርሳም “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” የክፍለ ዘመኑ ምርጥ ጥቅስ ነው!!) የለውጡ አንዱ ትሩፋት ለዓመታት ያንቀላፋውን ኢትዮጵያዊነትን ማነቃቃቱ ነው፡፡ ይሄን ጊዜ ታዲያ አንዳንዶች፣ እውነት የሚመራን ኢህአዴግ ነውን? የሚል ጥያቄ አንስተው ይሆናል፡፡ (ተዓምርም አስማትም ሊመስላቸው ይችላል!!) ግን አይፈረድባቸውም። በኢህአዴግ ዘመን ኢትዮጵያዊነትን ማቀንቀን እንግዳ ነገር ነበራ!! ዶ/ር ዐቢይ ግን ይህንንም ለውጠውታል፡፡
“ኢትዮጵያ ለሁላችንም ትበቃናለች”----- “እኛ ብቻ ሳንሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ይቆረቆራል” በሚል ታሪካዊ ንግግራቸውም፣ በዓለም አገራት እንደ አሸዋ የተበተነው ስደተኛ ኢትዮጵያዊ፤ወደ አገሩ እንዲገባ በይፋ ጥሪ ያቀረቡ የመጀመሪያው የኢህአዴግ  ሊቀ መንበር ናቸው-  ዶ/ር ዐቢይ!!
ፓርቲውን ወደድነውም ጠላነውም፣ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ዘንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ተወዳጅነትና ተቀባይነት የተቀዳጁት ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ናቸው፡፡ የምርጫው ሂደት የራሱ ታሪክ ቢኖረውም፣ ፓርቲያቸው ኢህአዴግ ነው ወደ ጠ/ሚኒስትርነት ሥልጣን ያመጣቸው ወይም ያወጣቸው፡፡ ግን እንዴት ህዝብ ሲቃወመውና ሲያምጽበት የነበረው አውራው ፓርቲ፣ ኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆነው፣ የህዝብ ድጋፍና ተቀባይነት ሊያገኙ ቻሉ? (ተዓምር ቢመስለን አይገርምም!) እንደኔ ግምገማ፣ ጠ/ሚኒስትሩን ለተወዳጅነት ያበቃቸው ከሁሉም በፊት ሰው ሆነው መቅረባቸው ነው፡፡ መልካም ሰብዕናቸውም ለተወዳጅነታቸው አስተዋጽኦ አበርክቷል። ኢትዮጵያዊነትን አጥብቀው ማቀንቀናቸው---ለዜጎች ትልቅ ክብር መስጠታቸው----ለቃላቸው መታመናቸው----- አዛኝና ርህሩህ መሆናቸው ወዘተ--፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ አስደማሚ ለውጥና ስኬት ለማስመዝገባቸው ደግሞ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የመደመር የፍቅርና የይቅርታ ፍልስፍናቸው ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ቢሆኑም ባለፉት ጥቂት ወራት ተዓምር የሚያሰኙ ስኬቶችን የተቀዳጁት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮት ሳይሆን በመደመር ፍልስፍናቸው ነው፡፡ በምሳሌ አስደግፈን እናየዋለን፡፡  
ለተቃሚዎች ተፎካካሪ የሚል መጠሪያ በመስጠት ከእንግዲህ መንግስታቸው፣ እንደ ጠላት ሳይሆን ለአንድ አገር እንደሚሰሩ ኢትዮጵያዊ ወንድሞች እንደሚቆጥራቸው በመግለፅም መላ ኢትዮጵያውያንን  አስደምመዋል፡፡ ነባር የኢህአዴግ አመራሮች እኮ “ከተቃዋሚዎች ጋር የማይታረቅ ቅራኔ ምናምን---” ሲሉ ነው የከረሙት፡፡ (ዕድሜ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ!)  
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራም የሚመራው ኢህአዴግ፤ ላለፉት 27 ዓመታት ሥራዬ ብሎ ጠላቶችን ሲፈጥር እንደኖረ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ዛሬ መሪው ሲለወጥለት ግን የተለወጠ ይመስላል - ኢህአዴግ ነፍሴ! በእርግጥም ዶ/ር ዐቢይ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ኢህአዴግ፤ ባለፉት 27 ዓመታት የተፈጠሩ ጠላቶችን እየቀነሰ፣ ወዳጆችና ደጋፊዎች ማድረግ ይዟል -በመደመር በፍቅርና በይቅርታ ፍልስፍና!!  
ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ጦቢያን አንቀጥቅጦ የገዛት አውራው ፓርቲ፤ የፖለቲካ ልዩነት ያላቸው ዜጎችን፣ መንግስትን ክፉኛ የሚተቹ ጋዜጠኞችንና ተገዳዳሪ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ሲያዋክብና ሲያስር ኖሯል፡፡ ከእስር የተረፉት ደግሞ  ለስደት ተዳርገዋል፡፡ (አሁንም ዕድሜ ለአብዮታዊ ዲሞክራሲ!)
ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ላይ በወጡባቸው ያለፉት ጥቂት ወራት ታዲያ የጥንቱ ኢህአዴግ፣ ሲያበላሽና ሲያቆሽሽ የኖረውን በማጽዳት ተጠምደው ነው ያሳለፉት፡፡ ቁስል ሲያክሙ፣ ብሶትና ምሬት ሲያደምጡ፣ ግጭት ሲፈቱ፣ ሲያስታርቁና ሲመክሩ ከርመዋል፡፡ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና አክቲቪስቶችን በይቅርታ ከእስር እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ለበርካታ ዓመታት በስደት የኖሩ ዜጎችንና ፖለቲከኞችንም ለአገራቸው አፈር አብቅተዋል - በይቅርታና መደመር መርህ!!  በአሸባሪነት ተፈርጀው የትጥቅ ትግል ሲያካሂዱ የቆዩ የፖለቲካ ድርጅቶችም ትጥቃቸውን ፈትተው ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል - በፍቅርና በይቅርታ ተደምረው!!  (በነገራችን ላይ ኢህአዴግ የሚታወቀው በፍረጃ ነው!!) የድሮ ሥርዓት ናፋቂ፣ ኪራይ ሰብሳቢ፣ የሻዕቢያ ተላላኪዎች፣ ነፍጠኛ፣ ጠባብ፣ ትምክህተኛ፣ ወዘተ-- ሲፈርጅና ሲከፋፍል ነው የኖረው - ኢህአዴግ ነፍሴ!! (ያለ ምክንያት እኮ ጠላቶቹ አልበዙም!)
አዲሱ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ባለፉት ጥቂት ወራት፣ ወደ ጎረቤት አገራትም ሆነ ሌሎች አገራት ለሥራ ጉብኝት በወጡ ቁጥር፣ እንጀራ ፍለጋ ወጥተው፣ በባዕድ አገራት ለእስር የተዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እያስፈቱ ለአገራቸው መሬት አብቅተዋል። (ያውም በራሳቸው አውሮፕላን እያሳፈሩ!) “አንተ ስትታሰር--- ኢትዮጵያ ትታሰራለች፣ አንተ ስትታመም--- ኢትዮጵያ ትታመማለች---- አንተ ስትማር--- ኢትዮጵያ ትማራለች!!” የሚል ልብ ውስጥ ሰርስሮ የሚገባ ሃረግም ፈጥረዋል - ኢትዮጵያዊነትን ያቀጣጠሉት ዶ/ር ዐቢይ፡፡  
ሁሌም መዝጋት፣ ማፈንና መከልከል -- የሚቀናው የቀድሞው ኢህአዴግና ጡንቸኛ አመራሩ፤ ባለፉት ዓመታት ጋዜጦችና መጽሄቶችን ብቻ አይደለም የዘጋው፡፡ በመንግስት ላይ የሰላ ሂስና ነቀፋ የሚሰነዝሩ በርካታ ድረ-ገጾችን ዘግቶ ነበር፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ አዲስ አስተዳደር፣ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ወራት፣ ከ200 በላይ የተዘጉ ድረ-ገፆችን መክፈቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ ኢህአዴግ በጠላትነትና በአሸባሪነት ፈርጆ፣ ጃም ሲያደርጋቸው የቆዩት እነ ኢሳትና ኦኤምኤንም ነጻነታቸውን አውጀዋል፡፡ እንደ ቀድሞው ከፈረንጅ አገር ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባም ቢሮአቸውን ከፍተው ሥርጭት የጀመሩ ሚዲያዎች አሉ፡፡ (በአሜሪካ በነጻነት የሚሰሩ  ሚዲያዎች፣ በአገራቸው ዓይናችሁ ላፈር መባሉ ያሳዝናል!)
ኢቢሲ፣ ፋና ብሮድካስቲንግና ዋልታን የመሳሰሉ የመንግሥት ሚዲያዎችም፤ የፓርቲና የመንግስት ልሳን ከመሆን ወጥተው የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች የሚያስተናግዱ መድረክ ለመሆን በቅተዋል፡፡ ይሄ ብቻ አይደለም---በቅርቡ በየማረሚያ ቤቶቹ በእስረኞች ላይ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲያጋልጡም ታዝበናል፡፡ ይሄን ተከትሎም አብዛኞቹ የማረሚያ ቤቶች ሃላፊዎች ከሥልጣናቸው ተነስተዋል። (የኢህአዴግ ነባር አመራሮች ማፈር አለባቸው!!) በእርግጥ ሃቋን ከመናገር ወደ ኋላ የማይሉት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ መንግስትም የአሸባሪነት ሥራ ሲሰራ እንደነበር በፓርላማ በይፋ ተናግረዋል። (“ህዝቡን በራሴና በመንግስት ስም ይቅርታ የጠየቅሁት የተሰራ ጥፋት ስለነበር ነው” በማለት!)
በእነ ዶ/ር ዐቢይ አመራር የመጣው ለውጥ ያልተዋጠላቸው (“ለውጡን አደናቃፊ” ይሏቸዋል!) አንዳንድ በጡረታ የተገለሉ የቀድሞ ባለስልጣናት፣ በዚያ ሰሞን እንዲህ ሲሉ ሰማኋቸው፡- “ዶ/ር ዐቢይ የኢህአዴግ ሽታ እንኳን የላቸውም” ይሄ እንግዲህ ትችት መሆኑ ነው፡፡ (ለእኔ ግን ትችት ሳይሆን ምርቃት ነው!) የቀድሞ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ባይገባቸው ነው እንጂ ኢህአዴግን ከጥፋት ያተረፈው፣ እነሱንም ከተጠያቂነት ነጻ ያወጣቸው፣ ዶ/ር ዐቢይ “የኢህአዴግ ሽታ የሌላቸው” በመሆናቸው እኮ ነው፡፡ (የኢህአዴግ ሽታን እኮ አሳምረን እናውቀዋለን!) አብዮታዊ ዲሞክራሲን ያለ ቅጥ እያቀነቀኑ፣ ኢህአዴግ አህአዴግ ቢሸቱማ ኖሮ፣ህዝቡ ዶ/ር ዐቢይን አይቀበላቸውም ነበር። አሁን ግን የኢህአዴግ ሊ/ቀመንበር ቢሆኑም ምናቸውም ኢህአዴግን አይመስልም፡፡ ህዝቡ በ27 ዓመታት የኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን፤ ኢትዮጵያዊነትን ከልቡ የሚያቀነቅን፣ ለዜጎች ሁሉ ክብር የሚሰጥ፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት፣ በፍቅርና በይቅርታ እንደመር---የሚል የኢህአዴግ ሊቀመንበር አይቶ አያውቅም፡፡ ለዚህ ነው ዶ/ር ዐቢይን ከልቡ የተቀበለው፡፡ የተለመደውን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮፓጋንዳ ሊግቱት ቢሞክሩስ ኖሮ? የዛሬው ለውጥ እውን አይሆንም ነበር፡፡ እናም ለአገሪቱም … ለህዝቡም … ለራሱ ለገዢው ፓርቲም የሚሻለው ጠ/ሚኒስትሩ መቼም የኢህአዴግ  “ሽታ” ባይኖራቸው ነው፡፡
ወዳጆቼ፤ አንድ ነገር ልብ በሉልኝ፡፡ ኢትዮጵያን ከፖለቲካ ቀውስና የእርስ በርስ ግጭት ያዳናት፣ ከመበታተን አደጋ የታደጋት የኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይሆን የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የመደመር ፍልስፍና ነው፡፡ ነፍጥ ያነገቱ ኃይሎች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር መደመር የሚለው ወርቃማ ፍልስፍና ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩ ሰሜን አሜሪካ ድረስ ተጉዘው ከዳያስፖራው ጋር የጥላቻን ግንብ አፍርሰው፣ የፍቅር ድልድዩን የገነቡት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፕሮግራም አይደለም። በመደመር መርህ እንጂ! በገዛ አገሩ ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ሲታገል የኖረ ኢትዮጵያዊ ዳያስፖራ፤በትረስት ፈንድ ዶላር ለአገሩ ሊያዋጣ፣ በዕውቀቱ አገሩን ሊያግዝ የፈቀደው እኮ በኢህአዴግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተማርኮ አይደለም፡፡ በጠ/ሚኒስትሩ ፍቅር  ተሸንፎ ነው፡፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው የፍጥጫ ግድግዳ ፈርሶ፣ እርቅ የወረደው፣ በፍቅርና በይቅርታ በመደመር መርህ እንጂ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮት እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
አሁን በስደት ላይ የነበሩ በርካታ ፖለቲከኞች፣ አክቲቪስቶች፣ አርቲስቶች ወዘተ-- ለአዲስ ዓመት ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው፤ በፍቅርና በይቅርታ እየተደመሩ ነው፡፡ (ለጦቢያና ለልጆቿ የምህረት ዘመን ነው!) ትንሽ ያሳሰበኝ ምን መሰላችሁ? ፖለቲከኞች፣ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች በዙብኝ፡፡ ሲቪል ዳያስፖራዎችስ? ማለቴ  ዕውቀት ያላቸው ምሁራን፣ ገንዘብ ያላቸው የቢዝነስ ሰዎች፣የኩባንያ አመራሮች፣ የፋይናንስና ባንክ ባለሙያዎች ወዘተ-- በብዛት ያስፈልጉናል፡፡ መቼም ፖለቲከኞች ኢንቨስትመንት አያመጡም፡፡ የሥራ ዕድል አይፈጥሩም፡፡ (የዳያስፖራ ኢንቨስተር ፖለቲከኞች እንዳሉ አላውቅም፡፡) በነገራችን ላይ ላይ የአዲስ አበባ አስተዳደር የአዲስ ዓመት መርህ - በፍቅር ተደምረን በይቅርታ እንሻገር!! የሚለው ተመችቶኛል፡፡
አዲሱን ዓመት የፍቅር፣ የሰላም፣ የጤና፣ የብልጽግና ያድርግልን!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!!

Read 5562 times