Monday, 12 November 2018 00:00

በመከላከያ ሰራዊት አደረጃጀት ላይ ለውጥ ይደረጋል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(10 votes)

 አዲሱ አደረጃጀት የምድር፣ የአየር፣ የባህር፣ የሳይበር እና የህዋ ምህዳሮችን ያካተተ ነው
             
    የመከላከያ ሰራዊት ከዚህ ቀደም የነበረው አደረጃጀት በርካታ ማነቆዎች የነበሩበት መሆኑን የጠቆሙት ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤ አዲስ የአደረጃጀት ጥናት ተደርጎ፣ ወደ ተግባር መገባቱን አስታውቀዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ ከመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ መከላከያን በቴክኖሎጂ ለማዘመንና የግዳጅ መመርያዎች ላይ ማሻሻያ በማድረግ፣ ሰራዊቱ በጥብቅ ዲሲፕሊን እንዲመራ ይደረጋል ብለዋል፡፡
በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ከዚህ ጋር በተያያዘ ውይይቶች ሲካሄዱ መቆየታቸው የተጠቆመ ሲሆን ለውይይቱ መነሻ የሆነውም በቅርቡ በቤተ መንግስት ውስጥ በተወሰኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተፈፀመው የዲሲፕሊን ግድፈት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአመራሮቹ ጋር ባደረጉት ውይይት በዋናነት የሰራዊቱ አባላት በጥብቅ ዲሲፕሊን በሚመሩበት እንዲሁም በግዳጅ አፈፃፀም ላይ ትኩረት አድርገው መምከራቸው ታውቋል፡፡
“መከላከያ በማናቸውም ጊዜ ለህገ መንግስቱ ተገዥ ይሆናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት ላይ የምታፈሰው በጀትና የምትሰጠው ትኩረትም ይህን ቃል ኪዳን መሰረት በማድረግ ነው ብለዋል፡፡
መከላከያ ሰራዊት በማናቸውም ሁኔታ የሚወስደው የኃይል እርምጃ ምክንያታዊ እና ተቀባይነት ያለው መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ፣ በጥንቃቄ መሆን እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ “በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ የሚደረገው ሁለንተናዊ ለውጥ በህጋዊ ማዕቀፎች፣ በአደረጃጀት፣ በመፈፀም ብቃትና በዘመናዊ ትጥቅ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሰራዊቱ በህገ መንግስቱ በተቀመጠው መሰረት የሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦች ተዋፅኦ ያካተተ ለማድረግ፣ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡
በአደረጃጀት በኩል ከዚህ በፊት የነበረው የሲቪልና መከላከያ ቅንብርን በሚገባው ደረጃ ያላካተተ በመሆኑ ሰፊ ጥናት ተደርጎ፣ አዲስ አደረጃጀት መፅደቁንም ጠ/ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡
በፋይናንስ አወጣጥና አጠቃቀም ረገድ ዘርፉ የሚጠብቀው ሚስጥራዊነት እንደተጠበቀ ሆኖ በግልፅ መመሪያዎች እንዲመራ እንዲሁም ሰራዊቱ በዘመናዊ ትጥቅ እንዲደራጅና ግዳጅ የመፈፀም ብቃቱ ከፍተኛ እንዲሆን የሚያስችሉ የተጠኑ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ጠ/ሚሩ አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የሰራዊት ማቋቋሚያ አዋጅ የባህር ኃይልን አካቶ እንዲሁም ወደፊት የሳይበርና የህግ ምህዳሮችን ለማካተት በሚያስችል መልኩ ተሻሽሎ የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
በዚህም ዘመናዊ አውደ ውጊያ በሚጠይቃቸው የምድር፣ አየር፣ ባህር፣ ሳይበር እና ህዋ አውዶች ዝግጁ የሆነ የመከላከያ ሰራዊት ይገነባል ተብሏል። ሰራዊቱ ቴክኖሎጂን የሚታጠቅ፣ በራሱ አቅም መጠገን፣ ማሳደግ ብሎም መፍጠር የሚችል እንዲሆን የአቅም ግንባታዎች እየተሰሩ መሆኑም በዚሁ መድረክ ተገልጿል፡፡  

Read 6451 times