Tuesday, 13 November 2018 00:00

ኢልሃን ኡመር - ከስደተኞች ካምፕ ወደ ታላቁ ምክር ቤት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በማክሰኞው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በማሸነፍ፣ ታሪክ ከሰሩት ሁለቱ ሙስሊም ስደተኛ ሴቶች አንዷ ናት - ትውልደ ሶማሊያዊቷ ኢልሃን ኡመር፡፡ የሶማሊያ የእርስ በእርስ ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት፣ እናትና አባቷ ነፍሳቸውን ለማዳን ማቄን ጨርቄን ሳይሉ የ8 አመቷን ልጃቸውን ኢልሃንን አዝለው፣ ከቤትና ከአገራቸው ርቀው ተሰደዱ፡፡
ከወላጆቿ ጋር አገሯን ጥላ የተሰደደቺው ኢልሃን ማረፊያዋ በአፍሪካ ግዙፉ የኬንያው ዳባብ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ነበር፡፡ በአስከፊው ዳባብ የስደተኞች የመጠለያ ካምፕ አራት አመታትን የገፋቺው ኢልሃም፣ የ10 አመት ህጻን ሳለች ነበር ወደ አሜሪካ የተጓዘቺው፡፡ በወቅቱ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ባለማወቋ ለመግባባትና ለመማር ተቸግራ እንደነበር ይነገራል፡፡
በሚኒያፖሊስ የማህበራዊ ንቅናቄ ስራዎችን በመስራት የምትታወቀው የ36 አመቷ ትውልደ ሶማሊያዊት ኢልሃም፤ በአፍሪካን አሜሪካን የሲቭል መብቶች ቡድን ውስጥም ንቁ ተሳትፎ ታደርግ ነበር፡፡ የትራምፕን የስደተኞች ፖሊሲ አጥብቃ በመቃወም የምትታወቀው ኢልሃም በዘንድሮው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ፣ ሚኒሶታ ላይ ዲሞክራቶችን ወክላ በመወዳደር፣ ታሪካዊ ድልን የተቀዳጀቺው ኢልሃን፤ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የእስልምና እምነት ተከታይ፣ ጥቁር ስደተኛ የምክር ቤት አባል ሆና ስሟን በደማቅ ቀለም አስጽፋለች፡፡
“በዚህች ምሽት እነሆ ወኪላችሁ ሆኜ ከፊታችሁ ቆሜያለሁ!... ከስሜ ጀርባ የተሸከምኩት ብዙ ኃይል አለኝ። ግዛታችንን ወክላ የምክር ቤት አባል የሆነች የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት፤ ሂጃብ ለብሰው በኩራት በምክር ቤት ውስጥ ለመሰየም ከታደሉት የመጀመሪዎቹ ሁለት ሴት ሙስሊም ስደተኞች አንዷ ነኝ!” ብላለች፤ ኢልሃም ታሪካዊውን ድል መጎናጸፏን ተከትሎ ለደጋፊዎቿ ባደረገቺው ንግግር፡፡

Read 1634 times