Wednesday, 14 November 2018 00:00

ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በጥቂቱ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአሜሪካ አንድ ፕሬዚዳንት ወደ ስልጣን በመጣ በ2 አመቱ ወይም በስልጣን ዘመኑ እኩሌታ ላይ የሚካሄደውና የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በመባል የሚታወቀው የኮንግረስ  ምርጫ በሳምንቱ መጀመሪያ ተከናውኗል፡፡
በየአራት አመቱ በወርሃ ህዳር በሚካሄደውና ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዴሞክራቶች 219 ወንበሮችን በማግኘት ሲያሸንፉ፣ ሪፐብሊካኑ ደግሞ በሴኔት ምርጫ ድል ቀንቷቸዋል፡፡
ከአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ጋር በተያያዘ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ከዘገቧቸው ጉዳዮች መካከል ጎላ ያሉትን መራርጠን እንዲህ አቅርበናል፡፡
***

ሴቶች ታሪክ ሰርተዋል
በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ታሪክ እንዳሁኑ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ለምክር ቤቶች ተወዳድረውም አሸንፈውም አያውቁም፡፡ ለሁለቱም ምክር ቤቶች በዕጩ ተወዳዳሪነት የቀረቡት ዲሞክራትና ሪፐብሊካን ሴቶች ድምር ቁጥር 3 ሺህ 379 ሲሆን ይህም በምርጫው ታሪክ ከፍተኛው ቁጥር እንደሆነ ሎሳንጀለስ ታይምስ ዘግቧል፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ 99 ያህል ሴቶች ያሸነፉ ሲሆን፣ ሁሉም ማለት ይቻላል ዲሞክራቶች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ በሴኔት አሸናፊ የሆኑት ሴቶች ቁጥርም 22 ነው ተብሏል፡፡
የ29 አመት ዕድሜ ያላቸው አሌክሳንድራ ኮርቴዝና አቢ ፊንከኖር በአሜሪካ ታሪክ በለጋ ዕድሜያቸው የምክር ቤት አባል በመሆን ተመዝግበዋል፡፡
ሶማሌ-አሜሪካዊቷ ስደተኛ ኢሃን ኡመር እና ትውልደ ፍልስጤማዊቷ ራሺዳ ጠይባ፤ በአሜሪካ ምክር ቤት አባል በመሆን የመጀመሪያዎቹ የሙስሊም እምነት ተከታይ ሴቶች ሆነው በታሪክ ተመዝግበዋል፡፡
እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የወጣበት ምርጫ
የማክሰኞው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በአገሪቱ ታሪክ እጅግ ከፍተኛው የምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅት ወጪ የተደረገበት መሆኑ ተነግሯል። ሴንተር ፎር ሪስፖንሲቭ ፖለቲክስ የተባለው ተቋም ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ የአጋማሽ ዘመን ምርጫው በአጠቃላይ 5.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ወጪ እንደተደረገበት ይገመታል፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ቅስቀሳና ዝግጅት ዲሞክራቶች 624.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ሪፐብሊካኖች ደግሞ 471.6 ሚሊዮን ዶላር ያህል ወጪ አድርገዋል፡፡ ለሴኔት ምርጫ በአንጻሩ ዲሞክራቶች 368.6 ሚሊዮን ዶላር፣ ሪፐብሊካኖች ደግሞ 233.9 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገንዘብ ማውጣታቸው ተዘግቧል።
113 ሚሊዮን ድምጾች
በዘንድሮው የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ፤ 113 ሚሊዮን ያህል መራጮች ድምጻቸውን እንደሰጡ ይገመታል ሲል ሲቢኤስ ኒውስ ዘግቧል፡፡ በምርጫው ድምጻቸውን ለመስጠት ከሚችሉት ዜጎች መካከል 48 በመቶው መብታቸውን ተጠቅመው ድምጻቸውን መስጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በ2014 በተደረገው ምርጫ መብታቸውን የተጠቀሙ ዜጎች 39 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበሩ አስታውሷል፡፡
36 ሚሊዮን የቴሌቪዥን ተመልካቾች
የአጋማሽ ዘመን ምርጫውን የድምጽ አሰጣጥና የምርጫ ውጤት ገለጻ አጠቃላይ ሂደት በርካታ አለማቀፍ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመላው አለም ያሰራጩ ሲሆን፣ በታላላቆቹ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብቻ የምርጫ ሂደቱን የተከታተሉት ተመልካቾች ቁጥር 36.1 ሚሊዮን ያህል እንደሚደርስ ተዘግቧል፡፡
ፎክስ ኒውስ፣ ኤንቢሲ፣ አቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ኤምኤስኤንቢሲ እና ሲቢኤስ በበርካታ ተመልካቾች በመታየት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃን የያዙት የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ናቸው፡፡
የመጀመሪያው ትውልደ ኤርትራዊ  
ከስደተኛ ኤርትራውያን ወላጆች በአሜሪካ የተወለደው ጆ ንጉሴ፤ በአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን የመጀመሪያው ትውልደ ኤርትራዊ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡
በኮሎራዶ ዲሞክራቶችን ወክሎ የተወዳደረው የ34 አመቱ ትውልደ ኤርትራዊ ጆ ንጉሴ፤ 60 በመቶ ድምጽ በማግኘት ያሸነፈ ሲሆን፣ በኮሎራዶ የመጀመሪያው ጥቁር የኮንግረስ አባልና ግዛቱን ከወከሉ ዘጠኝ ተወካዮች መካከልም በእድሜ ትንሹ እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

Read 5148 times