Sunday, 02 December 2018 00:00

የሬጌ ሙዚቃ በአለም ቅርስነት ተመዘገበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)


    የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ፤ የሬጌ ሙዚቃን በአለማቀፍ መድረክ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ለመፍጠር ባበረከተው አስተዋጽኦ በአለም ቅርስነት መዝግቦታል፡፡
ሬጌ ኢፍትሃዊነትንና ጭቆናን የመሳሰሉ ጉዳዮችን ለመቃወምና ለውጥን ለማቀጣጠል ጥቅም ላይ ሲውል የኖረ ተወዳጅ የሙዚቃ ስልት መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በአለም ቅርስነት እንደመዘገበው ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ፍቅርና አንድነት፣ ፍትህና እኩልነት ሲዘመርበት የኖረውና ከጃማይካ ምድር የፈለቀው የሬጌ የሙዚቃ ስልት፤ “በቀጣይ ዘመናትም የሁሉንም ብሶት የሚያሰማ ድምጽ ሆኖ ይቀጥላል” ሲልም ተቋሙ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የጃማይካ መንግስት የሙዚቃ ስልቱ በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ እንደነበር የዘገበው ሮይተርስ፤ እ.ኤ.አ በ1960ዎቹ መጨረሻ በጃማይካ እንደተፈጠረ የሚነገረው ሬጌ፣ በመላው አለም ድንበር ሳያግደው የሚቀነቀን ተወዳጅ የሙዚቃ ስልት እንደሆነም ገልጧል፡፡
የሬጌውን ንጉስ ቦብ ማርሌይንና ፒተር ቶሽን ጨምሮ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን፣ ሬጌን በመላው አለም እንዲወደድ እንዳደረጉትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 512 times