Monday, 10 December 2018 00:00

በሉግዘምበርግ የህዝብ ትራንስፖርት በነጻ ሊሆን ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ምዕራብ አውሮፓዊቷ ሉግዘምበርግ በአለማችን የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶችን በሙሉ ያለምንም ክፍያ ለዜጎቿ የምታቀርብ የመጀመሪያዋ አገር ልትሆን ነው ሲል ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ መዲና ሉግዘምበርግ ሲቲ በመላው አለም ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ከሚታይባቸው ከተሞች አንዷ ናት ያለው ዘገባው፣ ከጥቂት ወራት በኋላ ባቡርና አውቶብሶችን ጨምሮ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች በሙሉ በነጻ ለተጠቃሚዎች ክፍት እንደሚደረጉም አመልክቷል፡፡
ባለፈው ረቡዕ በተከናወነ በዓለ ሲመት የሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣቬር ቤቴል ዜጎች የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን በስፋት የመጠቀም ልምድ እንዲያዳብሩ በማድረግ ተሽከርካሪዎች የሚያወጡት በካይ ጭስ በአገሪቱ አየር ንብረት ላይ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቀነስ በማሰብ፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት በነጻ እንዲሰጥ ለማድረግ ማቀዳቸውን ዘገባው አመልክቷል።
የሉግዘምበርግ መንግስት ከ20 አመት ዕድሜ በታች ለሚገኙ ዜጎቹ በሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎትን በነጻ እንደሚሰጥ የጠቆመው ዘገባው፣ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችም ከመኖሪያ ቤታቸው ወደ ትምህርት ቤት ያለ ክፍያ የሚሄዱበት ትራንስፖርት እንደተመቻቸላቸው ገልጧል፡፡
በአገሪቱ መዲና ሉግዘምበርግ ሲቲ የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች በፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ እያንዳንዳቸው 33 ሰዓታትን ያህል እንዳባከኑ አንድ ጥናት አስታውቆ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1212 times