Tuesday, 19 February 2019 00:00

ከ50 ዓመታት በላይ ከመፃህፍት ያልተለዩት አዛውንት

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(2 votes)


                                  “እነ ከበደ ሚካኤል፣ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ … ደንበኞቼ ነበሩ”

       የ70 ዓመቱ አዛውንት አቶ ተስፋዬ አዳል ላለፉት 56 ዓመታት ከመፅሀፍት አልተለዩም። ፍልውሃ ኮቴጅ ሬስቶራንት አካባቢ በምትገኘው “አረንጓዴዋ ቤተ መፃህፍት”፣ ያልሸጡት መፃሕፍት ያላስነበቡት አንጋፋ ደራሲ የለም፡፡ ባለፈው ዓመት “አረንጓዴዋ ቤተ መፃህፍት” በልማት ምክንያት ፈርሳ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ዲዛይኗን በአርኪቴክት ተሰርቶ ዳግም ተገንብታለች፡፡ እንዴት? ለመሆኑ አዛውንቱ ከመፃሕፍት ጋር የተቆራኙት እንዴት ነው? ከአገራችን ታላላቅ ደራስያን ጋር የነበራቸው ግንኙነት ምን ይመስላል? የንባብ ባህልን በተመለከተ ምን ይላሉ? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአዛውንቱ መፅሐፍ ሻጭ ከአቶ ተስፋዬ አዳል ጋር አውግታለች፡፡

       ከወሎ እንደመጡ አዲስ አበባን እንዴት አገኟት?
ያው ከገጠር ወደ ከተማ ስትመጪ ግራ ያጋባል፤ ያን ጊዜ ደግሞ ከገጠር ወደ ከተማ መግባት፣ መሰልጠንና መማር በጣም የሚፈለግበት ወቅት ነበር፡፡ እኔ ለመማርና ዘመዶቼን ለማግኘት መጣሁ፤ አገኘኋቸው፡፡ ትምህርቴንም ጀመርኩ፡፡ በት/ቤት ቆይታዬ አንድ መምህሬ ባመቻቸልኝ እድል እሱ ጋ ተቀምጬ፣ እስከ 8ኛ ክፍል ያለ ችግር ተማርኩ። ረዳቴ መምህሬ በሞት ሲለይ ግን ትምህርቴን የምቀጥልበት አቅም አጣሁ፡፡
ዘመዶችዎስ?
እርግጥ እነሱ ነበሩ፡፡ ነገር ግን እኔን ለማስተማር አቅም አልነበራቸውም፡፡ የነበረኝ አማራጭ ትምህርቴን አቋርጬ ስራ መጀመር ሆነ፡፡ ጋዜጣ ወደ ማዞር ገባሁ፡፡ ይህ የሆነው ከኃይለ ሥላሴ ውድቀት በፊት ነበር፤ ለ10 ዓመት ጋዜጣ በማዞር ሰርቻለሁ፡፡ በተለይ ደርግ ሲመጣ፣ በ1966 ዓ.ም ብዙ ጋዜጦችና መፅሐፍት ይሸጡ ነበር፤ ሰውም ያነብ ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይሄው በዚሁ ስራ ላይ ነኝ፡፡
እስኪ በጥድ ዛፍ ስለተሰራችው “አረንጓዴዋ ቤተ መፅሐፍት” ያውጉኝ?
አረንጓዴዋ የጥድ ቤተ መፅሐፍት የተመሰረተችው በቀላሉ አይደለም፡፡ ከዚያ በፊት ሜዳ ላይ ዘርግቼ ነበር መፅሀፍ የምሸጠውና የማስነብበው፡፡ መጀመርያ ሶስት ጓደኛሞች ነበርን፡፡ አንዱ እንግሊዝ አገር አለ። አንዱ እዚሁ የራሱን ስራ ይሰራል፡፡ እኔ ደግሞ ሜዳ ላይ ዘርግቼ  መፅሀፍት እሰራ ነበር፡፡ በተለይ በደርግ ጊዜ መንገዱ እንዳሁኑ አልተስተካከለም። አስቸጋሪም ቢሆን አማራጭ ስላልነበረ የግድ እሰራው ነበር፡፡ መፅሀፍ በአንድ በኩል፣ ጋዜጣ በአንድ በኩል መፅሔት ደግሞ በሌላ በኩል ዘርግቼ፣ ፀሐይ እየቀጠቀጠኝ ስሰራ፣ አብዮት ጥበቃ “መንገድ ላይ እንዴት ትሸጣለህ” እያለ በዱላ ይቀጠቅጠኝ ጀመር፡፡ ያን ጊዜ መፅሀፉን ተውኩትና ጋዜጣ ብቻ ከአብዮት አደባባይ እስከ ቦሌ… አምባሳደር እያዞርኩ መሸጥ ጀመርኩኝ፡፡ አብዮት ጥበቃ አያነብም፣ አያውቅም አይጠይቅም፣ ዝም ብሎ “ለምን መንገድ ላይ ትሸጣለህ?” ብሎ ሰው መደብደብ ብቻ ነው፡፡ ብትነግሪው አይሰማም፤ በዛ ምክንያት እነ “አፍሪካን ጆርናል”፣ “ሪደር ዳይጀስት”፣ “ዘ ኢኮኖሚስት”፣ “ኒውስ ዊክ” እና “ኒውዮርክ ታይምስ”ን ትቼ ጋዜጣ  ሳዞር ከረምኩ፡፡
የአረንጓዴዋ ቤተ መፅሀፍት ምስረታ “አረንጓዴው የምርት ዘመቻ” ከተሰኘው የደርግ እንቅስቃሴ ጋር ይገናኛል፡፡ እንዴት መሰለሽ… በ1970ዎቹ መጀመሪያ ላይ በዚህ ዘመቻ ከተማው እንዲለማ በአብዛኛው ጥድ ይተከል ነበር፡፡ ያን ጊዜ እዚህ ቤተ መፃህፍቷ የነበረችበት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ጥድ የሚያስተክሉ ወይዘሮ፤ “በል አንተም ትከልና ተንከባክበህ አሳድግ” ብለው ጥዷን ሰጡኝ፤ እኔም ተከልኩኝ፡፡ የምኮተኩተው ውሃ የማጠጣውም የምከረክመውም እኔ ነበርኩኝ። እዚሁ ዘርግቼ መፅሐፍት እሸጣለሁ፤ ጥዱን እንከባከባለሁ፡፡ ጥዱ እያደገ እያደገ ሲሄድ፣ ውስጡን ክፍት እያደረግሁ፣ እንደ ጎጆ እያጠላለፍኩ ውስጡን እንደ ቤት መጠቀምና መፅሀፍ ውስጡ መሸጥም ማስነበብም ጀመርኩ፡፡
ለዚህች “አረንጓዴ ቤተ መፃህፍት” እውቅና ማግኘት አጠገቧ ያለው ኮቴጅ ሬስቶራንት ጉልህ ሚና እንደነበረው ይነገራል፡፡ እውነት ነው?
ትክክል ነሽ የኔ ልጅ፡፡ መቼም ያን ጊዜ እንደ አሁኑ ሬስቶራንት በየቦታው እንደ አሸን አልፈላም ነበር፡፡ ዛሬ እንዲህ ተሰባብሮ ሊወድቅ ትልልቅ ሰው የሚገናኝበት፣ የሚገባበዝበት ትልቅ ሬስቶራንት ነበር። የማይመጣ የለም፡፡ የወቅቱ የከተማዋ ከንቲባ፣ ከንቲባ ዘውዴ ሳይቀሩ ይመጡ ነበር፡፡ ይገርምሻል … እሳቸው ራሳቸውም እየነዱ፣ በሹፌርም ከመጡ መኪናቸውን ማዶ ያቆሙና፤ እኔ ጋ ገብተው መፅሐፍት ያያሉ ይጎበኛሉ፡፡ “እንዴት ያለች ምድረ ገነት ናት በል! እዚህ ውስጥ መፅሐፍት መሸጥህ እኮ ትልቅ ነገር ነው” ብለው ያደንቁ ነበር፡፡
ታላቁ ደራሲ ከበደ ሚካኤልን የመሳሰሉ ያሉ ታዋቂ ደንበኞች እንደነበሩዎት ሰምቻለሁ እስቲ ስለደንበኞችዎ ያጫውቱኝ?
እጅግ የማከብራቸው ዶ/ር ከበደ ሚካኤል ቋሚ ደንበኛዬ ነበሩ፡፡ እየተመላለሱ ብዙ መጽሐፍት ገዝተውኛል፡፡ የሚገርምሽ እሳቸው ከሰው ብዙም ንግግር የላቸውም፤ ከመጽሐፍት ጋር እንጂ፡፡ እንዳልሺው ሌላ ቢያጡ የራሳቸውን መጽሐፍት በብዛት፣ መቶም ቢሆን ገዝተው ይሄዳሉ፡፡
የራሳቸውን መጽሐፍት ለምን እንደሚገዙ ጠይቀዋቸው ያውቃሉ?
አዎ ጠይቄያቸዋለሁ፡፡ ቀስ ብዬ “ጌቶች፤ ይሄኮ እርስዎ የፃፉት መጽሐፍ ነው፡፡ እንዴት ይሄን ሁሉ መልሰው ይገዛሉ?” ብዬ ስጠይቃቸው፤ “ጽፈን ለት/ቤቶች፣ ለመንግስት ቤተ-መጽሐፍትና ለህዝብ ሰጥተናል፤ አሁን እኔ ቤት ንብረቴ ፈርሶ፣ ሆቴል ለሆቴል እየተንከራተተኩ ነው የምኖረው፡፡ ስለዚህ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ እኔን ለመጐብኘት ሰዎች ከመጡ እየፈረምኩ በገፀ በረከትነት እሰጣቸዋለሁ። በዚህ ምክንያት ነው የራሴን መጽሐፍ የምገዛው” ብለውኝ ነበር፡፡
ሌሎች ደራሲያንስ እነማን ነበሩ?
ነፍሳቸው ይማርና አንጋፋው ተርጓሚ ደራሲ ማሞ ውድነህ፣ የስፖርቱ አባት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፣ ከነሱ በኋላ ደግሞ ደራሲ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ አምባሳደር አሰፋ ተምትም፣ አቤ ጉበኛ፣ ኧረ ስንቱን ልንገርሽ.. እኔ ጋ መጥቶ ያላነበበ፣ ያልገዛ አታገኚም፡፡ ሲያገኙ ከፍለው ሲያጡም በነፃ አንብበው የሄዱ ብዙዎቹ ዶክተሮች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ፖለቲከኞች፣ አምባሳደሮች ሆነዋል፡፡ በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡
መጽሐፍት መሸጥና ማስነበብ ከጀመሩ 56ኛ ዓመትዎን ይዘዋል፡፡ ለመሆኑ እርስዎ ያነባሉ? እውነት ነው፤ 56ኛ ዓመቴን ይዤአለሁ፡፡ የኔ ህይወት እንደምታይው የድካም ነው፡፡ መጽሐፍት እጀምራለሁ ሳልጨርስ ግን እሸጠዋለሁ፤ ወይ አውሰዋለሁ፡፡ አንብቤያለሁ ግን ጀምሬ የተውኩት ቁጥር ስፍር የለውም፡፡
ያገኘሁትን መጽሐፍ እጀምራለሁ፡፡ በብዛት የአቶ ማሞ ውድነህን መጽሐፍት ነበር የማነበው፡፡  በዚያን ጊዜ የማሞ ውድነህ መጽሐፍት በደንብ ይነበቡ ነበር፡፡ “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ድብን አድርጌ አንብቤያለሁ፡፡ ለዚህም ምክንያት ነበረኝ፡፡
ምን ነበር ምክንያትዎ?
ገና መጽሐፍት መሸጥ የጀመርኩ አካባቢ፣ ታዋቂው ዘፋኝ ተፈራ ካሳ፣ አምባሳደር አገኘኝና “ፍቅር እስከ መቃብር”ን ፈልገህ ብታመጣልኝ እገዛሃለሁ አለኝ፡፡ ያን ጊዜ መጽሐፉ 2 ብር ከ50 ሳንቲም ነበር አስታውሳለሁ፡፡ ፊልም ሊገባ ሲል ነው ያገኘሁት፡፡ ቀጠሮ ሰጠኝና አመጣሁለት፡፡ በዚያን ጊዜ ገንዘብ ምንም ሳያቅማማ 50 ብር አውጥቶ ሰጠኝ፡፡
ያኔ 50 ብር ብዙ ነበር አይደል?
ከአሁኑ 5ሺህ ብር አይሻልም ብለሽ ነው። እናም “እንካ መልስ አለህ” ስለው “አይ መልሱ ያንተ ሽልማትና ማበረታቻ ነው፡፡ ብሩን ተወውና መጽሐፉን ግን አንብበው ይጠቅምሃል” አለኝ፡፡ በደንብ አነበብኩት፡፡ ተደነቅኩሁበት፡፡ ከዚያ በኋላ በርካታ የሩሲያ የተረት መጽሐፍት፣ የማኦ ጥቅሶችን የያዙ ትንንሽ መጽሐፍትን በ10 ሳንቲም እየገዛን በ1 ብር እንሸጥ ነበር፡፡ እነሱን በብዛት አንብቤያለሁ፡፡ ስራው ወዲያ ወዲህ ስለሚያደርገኝ፣ ከመጽሐፍት ጋር የመዋል የማደሬን ያህል አንብቤያለሁ ማለት አልችልም፡፡ ከጨረስኩት ጀምሬ የተውኩት ይበልጣል፡፡ ደግሞ እድሜና ጊዜ ካገኘሁ አነባቸዋለሁ ብዬ መርጬ ያስቀመጥኳቸው መፅሐፍት አሉ፡፡ ፈጣሪ ያውቃል፡፡
አረንጓዴዋ መፅሐፍት ቤት ፈርሳ፣ ቆርቆሮ ጠጋግነውና ተጣበው አይቼዎት ነበር፡፡ መፅሐፍት ቤቷን መልሶ ለመስራት የገቢ ማሰባሰቢያ የመፅሐፍት አውደ ርዕይም መዘጋጀቱን አስታውሳለሁ፡፡ አሁን መልኳን ቀይራ በብርማ ቀለም ተሻሽላ መጥታለች። እንኳን ደስ ያለዎት?
እንኳን አብሮ ደስ ያለን፤ በጣም ደስ ብሎኛል፤ ይህን አይቼ ብሞት አይቆጨኝም ስል ነበር፡፡ እግዚአብሔር አሳየኝ፡፡
እስኪ መፅሐፍት ቤቷ እንዴት እንደፈረሰችና አሁን ደግሞ እንዴት እንደተሰራች ያጫውቱኝ?
አረንጓዴ መፅሐፍት ቤቷ የፈረሰችው የዛሬ ዓመት ነው፡፡ አንድ ዕድሜው ከ35-40 የሚገመት ሰውዬ ምሽት ላይ መጥቶ ገባ፡፡ “ልዘጋ ነበር ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ጠየቀኝ፤ “አይ ክፈትልኝ እገባለሁ” ሲል ከፈትኩለትና ገባ፡፡ ከዚያ “ፎቶ ማንሳት እችላለሁ” አለኝ፡፡ “ጋዜጠኛም ከሆንክ መታወቂያ አሳየኝ፤ ካልሆነ እንዴት ታነሳለህ” ስለው “ቤቷ ደስ ስላለችኝ ነው፡፡ ፎቶ ማንሳት ካልቻልኩ በቃ መፅሐፍት ማየትና መግዛት እችላለሁ” አለና በዕድሜዬ ሸጬው የማላውቀውን ያህል ብዙ መፅሐፍት ገዛኝ። “አሁንስ ላንሳ?” አለኝ “አይ አልፈቅድም” አልኩ፡፡ እሱ ግን ደበቅ አድርጎ አንድ ሁለት ጊዜ ፎቶ ካነሳ በኋላ እቃውን ሰበሰበና “ለመሆኑ ይህን ቦታ ማነው የሰጠህ?” አለኝ፡፡ “መንግስት” አልኩት “ንግድ ፈቃድ አለህ?” “አዎ አለኝ” አልኩት፡፡ “በጣም ጥሩ፤ እንግዲህ ወደድክም ጠላህም ይህቺ ቤት ልትፈርስ ነው” አለኝ፡፡ “አትፈርስም! ብትፈርስም እናንተ ልጆቼ እያላችሁ መልሳ ትገነባለች እንጂ ሜዳ ላይ አትጥሉኝም” አልኩት፡፡ ይህንን ያልኩት በሙሉ ልቤ ነው፤ ለማስመሰልም አይደለም፡፡
ከዚያስ…ሰውየው ምን አለዎት?
ሳቅ ብሎ ሄደ፡፡ ከወር በኋላ መጣና አየኝ “እኔ የማዝነው በቦታው መፍረስ ነው፤ ትርፍ ቦታ ካለ መልሰው መስራት ይችላሉ፡፡ ግን አይበቃዎትም” አለኝ፡፡ “እኔ ኢንጂነር አብርሃም እባላለሁ፤ እዚህ ክ/ከተማ ነው የምሰራው” ብሎኝ ስልክ ቁጥሩን ሰጥቶኝ ሄደ፡፡ ደሞ ሌላ ቀን ሁለት ወጣት ሴቶች ትራክተር አስከትለው መጡ፣ ቤቷን አይተውም አዘኑ፡፡ “እንዴት አድርገን ማዳን እንችላለን” ብለው ተጨነቁ። “ለአለቆቻችን እንንገርና መላ ይፈለግ” አሉ፡፡ እኔ ደግሞ “ምነው ተጨነቃችሁ” አልኳቸው፤ “ቤቷን ማፍረስ ከበደን” አሉኝ “ለምንድነው የምታፈርሱት” “ለልማት መኪና መንገዱ ጠበበና እግረኛ ለአደጋ እየተጋለጠ ስለሆነ መንገዱን ለማስፋት ነው የሚፈርሰው?” ሲሉ አስረዱኝ። “እኔ 55 ዓመት ተቀምጬበት ኑሮዬን እንኳን አላሻሻልኩም፤ ህዝብ ሳገለግል ነው የኖርኩት፡፡ ነገር ግን በእኔ ምክንያት ህዝብ በመኪና አደጋ ከሚያልቅ እኔ ራሴ አፍርሼ እለቃለሁ፤ አትጨነቁ” አልኳቸው። ከዚያ ቤቷ ፈረሰች፤ ትንሽዬ ቦታ ተረፈች፡፡ ትንሽዬ ቆርቆሮ ጠጋግኜ፣ ተጣብቤ ተቀምጬ፣ መጥተሸ አይተሽኝ ነበር፡፡ በዛ ሁኔታ የፈረሰችው፡፡
ከዚያስ እንዴት ተገነባች?
ያው ወጣቱ አዘነ፤ ብዙ ሰው ተበሳጨ፤ ሲፈርስ ሚዲያውም ህዝብም ተነሳ፤ ሰው አዘነ። ለሰባት ወር ተጨንቄ ከረምኩ፡፡ ወጣቶች የገቢ ማሰባሰቢያ የመፅሀፍት አውደ ርዕይ አዘጋጁ፤ ገንዘብ ሰበሰቡ። የቤተ መፃህፍቷ ዲዛይን በአርክቴክት ነው የተሰራው። ከዚያም በባለሙያ ባማረ ሁኔታ ተገነባ፡፡ የቦታው ስፋት አራት በሶስት ነው፡፡ አሁን ልጆቹ በቅርቡ ስለሚያስመርቋት የወጣባትን ወጪ ዲዛይኑንና አጠቃላይ ሂደቱን ይፋ ያደርጋሉ፡፡
ቤተ መፅሀፍቷ በዘመናዊ መንገድ ተሰርታ፣ መፅሐፍቶች በአምስት ሼልፎች ተደርድረው፣ ምንጣፉ አምሮ በማየትዎ ምን ተሰማዎ?
የኔ ልጅ ስሜቴን መግለፅ ያቅተኛል፡፡ እኔ ንግድ ፈቃድ ለስሙ አውጥቼ ብሰራም ነጋዴ አይደለሁም፡፡ ኑሮዬ እንደምታይው በጉስቁልና የተሞላ ነው፡፡ ያለው ከፍሎ ሲያነብና ሲገዛ፣ የሌለው በነፃ የሚገለገልባት ቤት ናት፡፡ እኔም ሳገኝ በልቼ፣ ሳጣም እንደነገሩ ሆኜ ነው የምኖረው፡፡ የኔ ሽልማትና ደሞዝ እዚህ በነፃ ያገለገልኳቸው ሰዎች፤ ትልልቅ ደረጃና ማዕረግ ላይ ደርሰው ማየት ነው፡፡ አሁን እየመጡ ሲጠይቁኝ ተለውጠው ሳያቸው በደስታ እፈነጥዛለሁ፡፡ ሌላው መፅሀፍት ቤቷ ከፈረሰች ጀምሮ እስካሁን ህዝቡ ከኔ ጎን ነበር:: በጣም አመሰግናለሁ:: ይህን ሁሉ ማየት ያስደስታል፡፡ በህዝቡ ጭንቅላትና ልብ ውስጥ ልክ እንደ ኮምፒዩተር ሲስተም መግባቴ በጣም ነው ያስደሰተኝ፡፡ ህይወቴም ቢያልፍ ደስታውን በቁሜ አይቸዋለሁ፤ አይቆጨኝም!
ባለፈው ዓመት  በሁለተኛው ዙር የ“ሆሄ የስነ ፅሁፍ ሽልማት” ላይ “ለንባብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ጀግና” ተብለው በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ በክብር ተሸልመዋል፡፡ ያኔ ምን ተሰማዎት?
እንደገና የተወለድኩ ነው የመሰለኝ፡፡ አንደኛ መድረኩ፤ ታላላቅ ደራሲዎችና የጥበቡ ዓለም ሰዎች የነገሱበት ነው፡፡ ሁለተኛ በዕለቱም ቢሆን ትልልቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል፤ ብዙ ከለፉና ከደከሙ ሰዎች እኩል ቆሜ በመሸለሜ በጣም ደስተኛ ነበርኩ።
አሁን ህይወት እንዴት ነው? ትዳር እንደሌለዎት ሰምቻሁ …
እንደነገርኩሽ የተስተካከለ ህይወት የለኝም፡፡ በአገልግሎት ስራ ላይ ነው የኖርኩት፡፡ እነሱን ብዬ የመጣሁባቸውን አቅመ ደካማ ዘመዶቼን ሳግዝና ስረዳ፣ የትዳሩና ቤተሰብ የመመስረቻው ጊዜ አለፈ፡፡ ትዳርም ልጆችም ያላፈራሁት በዚህ ምክንያት ነው፡፡
የአገራችንን የንባብ ባህል እንዴት ይገልፁታል የአሁኑንና የቀድሞውን ያነፃፅሩልኝ?
የንባብ ሁኔታ በቀደመው ጊዜ ራሳቸው ትልልቆቹ ሰዎች ለምሳሌ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ በጣም ያነብ ነበር፡፡ እንደነገርኩሽ ቋሚ ደንበኛዬ ነበር፡፡ ሲትሮይን መኪና ነበረው፤ ማዶ ያቆማል (አሁን የንግድ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገነባበት እያመለከቱ)፤ ይጠራኝና “እነዚህ እነዚህ መፅሀፍት አሉህ” ብሎ ይጠይቀኛል፤ እወስድለታለሁ፡፡ ከሌለኝ “ሌላ ቦታ ፈልግ” ይለኛል፡፡ መኪናው ራሱ በብዙ መፅሐፍት የተሞላ ነው፡፡ ታላቁ ደራሲ ሀዲስ ዓለማየሁ እዚህ ፊት ለፊት ካለው ሰፈር ውስጥ ነበር ቢሯቸው፡፡ ከንባብ አይናቸው ቦዝኖ አያውቅም፡፡ መፅሀፍ ፍለጋ እኛ ምስኪኖቹ ዘንድ ይመጣሉ፡፡ ሌላው ደንበኛዬ ተክለፃዲቅ መኩሪያ ነበሩ፡፡ በደንብ ይፅፋሉ፡፡ ከሚፅፉት በላይ ግን ያነቡ ነበር፡፡ ኮቴጅ ሬስቶራንት ያዘወትሩ ስለነበር አንድ ቀን “የታሪክ መፅሀፍ የማየው የእርስዎን ብቻ ነው፤ ለመሆኑ የአገራችን ታሪክ እንዴት ነው” ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ ቸኩለው ስለነበር ነገ መልሱን ይዤ እመጣለሁ ብለውኝ ሄዱ፡፡
በነጋታው መጡ?
ሁልጊዜ ወደ 11 ሰዓት ላይ ነው የሚመጡት። “አንተ ጀግና የሰጠኸኝን የቤት ስራ ሰርቻለሁ እነግርሃለሁ” ሲሉኝ “እሺ ጌቶች” አልኩ፡፡ እና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ምናሉኝ መሰለሽ… “የኢትዮጵያ ታሪክ አላለቀም … አያልቅም፡፡ እኛ ጀምረነዋል ግን ገና አልተነካም፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመስራት ብዙ ምሁራን ብዙ ካፒታል ያስፈልጋል” አሉኝ፡፡ አንድ ጊዜ የልጅ ልጃቸውን እጇን ይዘው አረንጓዴዋ መፅሀፍት ቤት አምጥተዋት ነበር፡፡ ከዚህ አገር ወደ ውጭ እስክትሄድ ድረስ የዚህ ቤት ደንበኛ ነበሩ ሁለቱም፡፡ እሳቸው ይመጡና “ያቺ ልጅ እያነበበች ነው? እስኪ ፊርማዋን አምጣ” ይላሉ፡፡ ፈርማ ነው መጽሐፍት የምትወስደው፡፡ አየሽ የድሮዎቹ የልጅ ልጆቻቸው እንኳን በንባብ እንዲተጉ ያደርጉ ነበር፡፡ ስራ ከያዘች በኋላም ለመፅሀፍ በጀት ነበራት፡፡ እዚህ ዲፖዚት ታደርግ ነበር፡፡ ጓደኞቿ ሁሉ አይቀሩም። ያኔ ኢንተርኔት የለም፡፡ ተንቀሳቃሽ ስልክ የለም፡፡ ምንም የለም፡፡
ኢንተርኔትና ሞባይል በንባብ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለው ያምናሉ?
በደንብ አምናለሁ፡፡ አንድን ወጣት መፅሃፍ አንብብ ብትይው ስልኬ ላይ አለ፤ ከኢንተርኔት አገኛለሁ የሚል ሰበብ ይደረድርልሻል እንጂ ወደ መፅሀፍ ዞር ብሎ አያይም፡፡ ደራሲያኑ ከዚያ የወጡ ናቸው፡፡ ይፅፋሉ ግን ከ3-5 ሺህ ኮፒ ነው የሚታተመው፡፡ ከዚያ በላይ ፈቅ አይልም፡፡ ድሮ የወረቀት ዋጋም ርካሽ ነበር፡፡ የመፅሀፍ ዋጋም እንደዛው፡፡ አሁን አንዱ እንቅፋት የወረቀት ዋጋ መወደድ ነው፡፡ አሁን የንባብ ሁኔታው ደከም ያለ ነው፡፡
መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
የቀደመውን ለመመለስ ለምሳሌ ት/ቤቶች ተማሪዎች አርፍደው ሲመጡ፣ በር ዘግተው የትም ከሚሰዷቸው ቤተ መፅሐፍት ከፍተው በቅጣት መልክ እንዲያነቡ ቢያደርጓቸው ምናለ? በየቀበሌው ቤተ መፅሀፍት መከፈት አለበት፤ እውነቴን ነው፤ እኔ የመፅሀፍት ፍቅር አለኝ፡፡ ለምሳሌ ከጊዮርጊስ ተነስተን ቦሌ እስክንገባ ድረስ አንድ የህዝብ ቤተ መፃህፍት የለም፡፡ እስጢፋኖስ ጋር ቡክ ወርልድ አለ፤ ግን ደሀ ድርሽ የሚልበት አይደለም፡፡ መንግስትም ሆነ ባለሀብት ፎቅ እንደሚገነቡት ሁሉ ቤተ መፅሃፍትን መገንባት አለባቸው፡፡ ያላነበበ ትውልድ የመከነ ነው፤ ዋጋ የለውም፡፡ ባለሀብትም ይህን መደጎም አለበት፡፡ ከጊዮርጊስ እስከ ቦሌ ድረስ መቶ ሺሻ ቤት ይገኛል፡፡ ይሄ ውድቀት ነው፡፡ መንግስትም ባለሀብትም ህዝቡም ይህንን ልብ ሊለው ይገባል፡፡  

Read 7079 times