Saturday, 16 February 2019 14:31

“የእምባም ይናገራል” መጽሐፍ ከፍታና ዝቅታ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(4 votes)

  ግጥሞች በውበት ያሸበረቁ፣ በሙዚቃቸው ልብ የሚያስደንሱ፣ በሀሳባቸው የሃሳብ ልዕልና ላይ የሚሰቅሉ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የዚህ ተቃራኒ ሆነው፣ እንደ እሾህ ጉንጉን ማረፊያ ያሳጡን ይሆናል፡፡ ይሁንና ብዙ ጊዜ በሀገራችን የለመድነው መካከለኛም አለ፡፡ ጥቂት መፈንደቂያ ኖሮን፣ የተወሰነ እርቃን የሚያሳዩ ግጥሞች ስለለመድን ብዙ ጉጉ አይደለንም፡፡
ለዛሬ መጽሐፍ ዳሰሳዬ ያዘጋጀሁት “እምባም ይናገራል” መጽሐፍም የራሱ ውበትና ድክመት (Limitation) አለው፡፡ መጽሐፉ ቦስተን በሚኖር ኢትዮጵያዊ የተጻፈ ሲሆን ከ135 ግጥሞች ውስጥ ከ33 በላይ የሚሆኑት በፍቅር ሃሳቦች ላይ ያጠነጥናሉ፡፡
ከዚያ ውጭ ግጥሞቹ ፍልስፍና፣ ማኅበረ ባህላዊ፣ ማህበረ ፖለቲካዊ፣ ስነ ልቦናዊና እምነትን የሚዳስሱ ጭብጦችን አካትተዋል፡፡ መጽሐፉን ሥናነብብ ደራሲው ልባቸው፣ ለሰው ልጆች ቅርብና ነፃነትን የሚናፍቅም ይመስላል፤ ለሰው ልጆች ተቆርቋሪነት፣ ለፍትህና ለፍቅር ዝምድና እንዳላቸውም ያስታውቃል፡፡
ደራሲው የመጽሐፉን ሩብ ያህል የወሰዱት ለ“ፍቅር” ነው እንበል እንጂ ከፍቅር ዘውጐች ውስጥ “ኢሮስ” የተባለው በቁጥር ቢበዛም፣ ኤፒቱምያ (በግሪክ) ፊሊዎና ሌሎችም የፍቅር ዘውጎች አሉበት።
ለምሳሌ ይህን ግጥም እንየው፡-
ሰማያዊ ፀዳል፡-
ዛሬ ግን ከወትሮው በተለየ ስሜት
ስስ ልብስ ተላብሳ ስትል ዘንከት ዘንከት
መርግ እንደተጫነው ፀጥ አልኩ ባለሁበት
---
---
ሳያት ሳያት ሳያት
ሳያት በትክታ፣ ማለት በአርምሞ
የጭሱ መዐዛ የቡናውም ቃና
ከርሷ ጋር አድሞ
    የውበቷን ግርማ አጉልቶ ቢያሳየኝ
    የማላውቀው ስሜት
    ነፍሴን አሸፍቶ ከራሴ ጋር ለየኝ፡፡
ይህ የፍቅር ዘውግ በጠባዩ የአካላዊ ስሜት መቆስቆስ የሚያሳይ ነው፡፡ ፍቅሩ ላቅ ሲል ወደ መጎምዠት ያመጣል፡፡ የሥነ ጋብቻ ምሁራን እንደሚሉት፤ ይህ ምራቅ መዋጥ ለትዳር ዘለቄታም የሚደፍነው ሽንቁር ስላለ በቦታው አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁንና እንደ አጠቃቀማችን ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል፡፡ ኢድ ዊት የተባሉ የህክምና ዶክተርና የሥነ ጋብቻ መምህር “A strong desire of any kind - sometimes good, sometimes bad!”  ይሉታል፡፡ “Physical desire for each other that expresses itself in pleasurable sexual love making” በወጉ ሲጠቀሙበት፣ በትዳር ዓለም ለአንሶላ መጋፈፍ በደስታ የሚያዘጋጅ ማለት ነው፡፡
ገጣሚው የውበቷ ነገር ነፍሱን አሸፍቶ ቀልቡን እንዳሳተው ተናግሯል፡፡ የመጽሐፉን ገፆች በውል በምንፈትሽበት ወቅት ከሌላኛው በግሪክ አከፋፈል ዘውግ “ፊሊዎ”ን የሚያስታውሱ ግጥሞች አሉት ብዬ ከላይ እንደጠቀስኩ፣ አንድ ማሳያ ቀጥዬ ማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ርዕሱ “ዝምታ ቋንቋ ነው” ይላል፡-
በክፉ ባልንጀር ህሊናው የደማ
በጭብጨባ ብዛት ሀቁን የተቀማ
የበደሉትን ብዛት ለሰው ባይቀባጥር
ገፁ ላይ ከትቦት - ለመኖር ሲያጣጥር
በፊቴ ሰሌዳ የጻፈውን ቃላት
ማንበብ የተሳነው - ደንጎላ ጭንቅላት
በቆሰለች ነፍሱ እየላከ ስንጥር
ተናዘዝ ይለዋል እንደ እንግዳ ፍጡር፡፡
ይህች አጭር ግጥም አሰነኛኘቷ - ሀሳቧ ግሩም ነው፡፡ በአጭሩ ገጣሚው የሚነግረን፣ የገፀ-ሰቡን ሀሳብ መረዳት ስላቃተው አንድ ባልንጀራ ነው። ውጭውን አንብቦ ውስጡን ማንበብ ስላልቻለ አስመርሮታል፡፡ ከሀዘኑ ይልቅ ሌላ ሀዘን የሆነበት ጓደኛቸው ሊረዳቸው አለመቻሉ ነው፡፡ ስለዚህም ጭቅጭቁ እንዳንገፈገፈው ስሜቱን ይነግረናል፡፡
መነሻችን “ፊሊዎ” የሚለውን የፍቅር ዘውግ ማሳየትም ስለሆነ ፊሊዎን ትንሽ ማብራራት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ፊሊዎ የተጓዳኞች የፍቅር መረብ ነው። ይሁንና ይህ የፍቅር ዘውግ ከአንዱ ወገን ላንዱ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ ሰጥቶ መቀበል ዓይነት ነው፡፡ “It is a love relationship-comradeship, sharing, communication, friendship” ይላሉ -  ኢድ ዊትና ግሎሪያ ኦኬስ ፔርኪን፡፡
መገለጫው ብዙውን ጊዜ ጓደኝነት ነው፤ ጥሩ ተግባቦት፣ የአንዱ ላንዱ ጥንቃቄና ክብካቤም ይጠበቃል፡፡ ከላይ ያየነው ግጥምም የዚሁ ችግር ይመስላል፡፡ ጥሩ ተግባቦት ማካሄድ ያቃተው ባልንጀራ - ይህንን የብስጭት ስሜትና ፈጥሯል። ሌላ ህመም፣ ሌላ ስቃይ ፈጥሮበታል፡፡ ጓደኛ ዓይን አይቶ፣ ፊት አንብቦ ካልተረዳ የተግባቦት ችግር አለበት፡፡ ፊሊዎ ደግሞ አፀፌታና ምላሽ ይፈልጋል፡፡
ሌላኛው “ኢሮስ” የተባለውና  የፍቅር ዘውግ ሲመጣ፣ ትዝ የሚለን የዓይን ፍቅር፣ የተቃራኒ ፆታ “የሞትኩልሽ ሞትኩልህ!” ፍቅር ነው። እውነትም ኢሮስ ከመለስተኛ ዕብደት ጋር የሚጠጋጋ ነው። ስለፍቅርና ጋብቻ በተፃፈ መጽሐፋቸው፤ [“I am speaking of ‘eros, the love that, more than any kind, carries with it the idea of romance” ይላሉ፡፡ ይህንን የጠቀሱት ከላይ ስማቸውን ያነሳኋቸው ዶክተርና አጋራቸው ናቸው፡፡
ይህ ፍቅር ሲጠቀለል፤ ስጋዊ ፍቅር፣ የተቃራኒ ፆታ ዕብደት ነው፡፡ ዓይን አውጥቶ እፍፍ ማለት። ዓለምን ሁሉ ጠቅልሎ በአንድ ሰው ውስጥ ለማኖር መሞከር፡፡ ዓለምን ባንድ ሰው ጠርዞ ባንድ ነፍስ ውስጥ ማነብነብ!
ገጣሚው የዚህ ዓይነት ብዙ ግጥሞች አሉት። ከነዚያ ግጥሞች ሶስቱ በድምቀት የሚያወሩት ስለመፍረስና ፀፀት ነው፣ ወቀሳ ነው!
የጥጋብ ጎጆዬ ሌማቱ ተደፍቶ
እንደነዳይ ምግብ ውጥንቅጡ ጠፍቶ
አንተም ተው አንቺም ተይ ..
ብሎ የሚሸመግል አስተዋይ ሰው ጠፍቶ
ዱላ የሚያቀብል የእብድ ገላጋይ በዝቶ
ተለያይተን ቀረን ፍቅራችን በስክቶ፡፡
…ይላል፡፡ (እዚህ ላይ በተለይ ቤት መምቻው ላይ ያሉት የአናባቢ ድምፆች ጠንካራ ስለሆኑ ሙዚቃውን ከፍ ያደርገዋልና የሚመሰገን ነው።)
ሃሣቡ የፈረሰ ጎጆ፣ የከሸፈ ትዳር ነው፡፡ ያልተሳካ የፍቅር ህልም፣ የጨነገፈ ውጥን ነው። ትዳር ደግሞ “አጋፔ” በተባለው የፍቅር ዘውግ ካልተደመደመ፣ መዝለቁ አጠራጣሪ ነው፡፡ “አጋፔ” ራስን ለሌሎች መስዋዕት የሚያደርግ ክርስቶሳዊ ፍቅር ነው፡፡
በዚሁ “ኢሮስ” የፍቅር ዘውግ፣ ርዕሱ ከሀሳቡ ጋር ያልተገናኘ “ሸክላ ሰሪው” በሚለው ግጥም፤ የአድናቆት ዝናቡን የሚያዘንብላት ተፈቃሪ አለች፡፡ እንዲህ ይነበባል፡-
እንደ ሱፍ አበባ ቁመትሽ ተመዞ፣
ያልታረሰ ገላ ድንግል አካል ይዞ፣
ሲገማሸር ቢውል ዝንክትክት እያለ
ያለ ጋሻና ጦር ስንቱን ግዳይ ጣለ…!!
በአነጻጻሪ ዘይቤ፣ ውበቷን ከፍ እያደረገ ያደንቃታል፡፡ “የሚያክልሽ የለም” ዓይነት ዜማ ያቀነቅንላታል፡፡ ኢሮስ ማለትም ይህ ነው፡፡ ትንሽ ትንሽ ማበድ! … በሙሉ ሰውነት፣ በሁሉም የስሜት ህዋሳት ብቻ ሣይሆን በጉበትና በሳንባ፣ በአንጀትና ጨጓራ ማጨብጨብ!
ገጣሚው መንገሻ ክንፉ፤ ፍቅርን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጭብጦችም አንስቶ፣ ስንኝ ቋጥሯል፡፡ የታዋቂውን ፈላስፋና ደራሲ የካህሊል ጂብራልን ሀሳቦች በግጥም ስንኝ ቋጥሮ፣ በዜማ እንዲዋኙ አድርጓቸዋል፡፡ ቲ.ኤስ.ኢሊየት፤ የ“ዲቫይን ኮሜዲው” ዳንቴ ነፍሴን ሰርቋታል እንደሚል፤ ገጣሚው በካህሊል ጂብራን ቀልቡ መሰረቁን ግጥሞቹ ያወራሉ፡፡ ገጣሚውም ለሰውየው ስራ ዕውቅና መስጠቱ ትልቅ ምስጋና የሚያሰጠው ነው፡፡
ወደ ሌላው ጉዳይ መለስ ስል፤ “እምባም ይናገራል” ላይ ያየሁት ነገር፤ “ንቡር ጠቃሽ” ወይም በእንግሊዝኛው “Allusion” ዘይቤ መጠቀሙ ነው፡፡ በንዑስ ክፍሉ መፅሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ፣ በመባል ይታወቃል፡፡
ለአሁን ገጣሚው “መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ” ዘይቤን ሲጠቀም የተሳካለትንና ያልተሳካለትን በጥቂቱ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ይሁንና የ“practical criticism” መጽሐፍ ደራሲ አይ. ኤ. ሪቻርድስ እንደሚሉት ከሆነ፤ “ንቡር ጠቃሽ” ዘይቤን ስንጠቀም አንባቢው ባይተዋር እንዳይሆንና ግራ እንዳይገባው በየቦታው ከመደንጐር መጠንቀቅ ይሻላል ይላሉ፡፡
ገጣሚ መንገሻ ክንፉ፣ “ንቡር ጠቃሽ ዘይቤ”ን ከተጠቀመባቸው ቦታዎች አንዱ ገፅ 20 ላይ ያለው የኢያሪኮ ታሪክ ነው፡፡ ኢያሪኮ በጩኸት የፈረሰ ከተማ ነው፡፡ መጽሐፉ ውስጥ በጣም ብዙ ጠቃሾች የታጨቁበት ግጥም ግን “በእጁ ቀረጸኝ” የሚለው ነው፡፡ የግጥሙ ርዕስ በራሱ በነቢዩ ኢሳያስ መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ ነው፡፡ ምዕራፍ 49፡16 “በእጆቼ መዳፍ ቀርጬሻለሁ” ከሚለው የተወሰደ ነው፡፡ ቀጥሎ ሁለተኛው አንጓ ላይ ያለው፡-
አንዴ ወረደና በቅዱስ መንፈሱ
የጭኔን ሹሉዳ ቢነካው በስሱ… ይላል፡፡
ይህ ደግሞ ዘፍጥረት፣ ምዕራፍ 32፣ ቁጥር 25 “እንዳላሸነፈውም ባየ ጊዜ የጭኑን ሹልዳ ነካው፤ ያዕቆብም የጭኑ ሹልዳ ሲታገለው ደነዘዘ።” በሚል ሰፍሯል፡፡ አራተኛው የግጥሙ አንጓ ላይ፡-
ቁጣው እጅግ በርትቶ
ህሊናየን አስቶ
እንደናቡከደነፆር … ግቻ በጥርሴ አስነጭቶ” እያለ ይቀጥላል፤ ይህም ከትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ የተወሰደ “ጠቃሽ ዘይቤ” ነው፡፡     
ትንቢተ ዳንኤል መጽሐፍ ምዕራፍ 4፡33 “በዚያም ሰዓት ነገሩ በናቡከደነፆር ላይ ደረሰ፤ ጠጉሩም እንደ ወፎች እስኪረዝም ድረስ ከሰዎች ተለይቶ ተሰደደ፤ እንደበሬም ሳር በላ” ይላል፡፡
እዚሁ ግጥም ላይ ገጣሚው በግጥሙ መዝጊያ ስንኞቹ የተጠቀማቸው ሁለት ስንኞች፣ ከተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መወሰዳቸው ደራሲው ለመጽሐፍ ቅዱስ ቅርበት እንዳለው ያሳያል፡፡
ለእርሱ ቤተ መቅደስ ሊያደርገኝ በጥቅል (1ኛ ቆሮንቶስ)
ሸክላ ሰሪው በእጁ ቀረፀኝ እንደሉል (ትንቢተ ኤርሚያስ)
ገጣሚው በመጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ ዘይቤው ላይ ከጠቀስኳቸውና በሌሎች ስፍራዎች በሠራቸው ሥራዎች ተሳክቶለታል፡፡ ይሁንና አንድ ግጥሙ ላይ የተጠቀመው መጽሐፍ ቅዱስ ጠቃሽ” ግን ከፍተኛ ስህተት ፈጥሮበት አይቻለሁ፡፡
የግጥሙ ርዕስ “የንጋት ኮከብ” የሚል ነው፡፡
ሸክላ ሰሪው በእጁ
ውበትን በፈርጁ
ለፍጥረታት ሲያድል
ሰማይን ሲያፀና ምድርን ሲያደላድል
     ከእርሱ ሰብዕና
     ከእርሱ ልዕልና
ብጫቂ ዘር ወስዶ
በብርሃን ጋርዶ
ከማናየው ውበት ቀምሞ ቁንጅና
የንጋት ኮከብ ሆይ በአንተ ላይ አፀና
    ነገር ግን ውበትህ
ሆኖ ትምክህትህ
ከመጎናፀፊያህ ሰማያዊ ኅብር
ከአለቅነት ስልጣን ከነበረህ ክብር
ተምዘግዝገህ ስትወድቅ ተሞልተህ በብካይ
የመመለክ ህልምህ ተሰንቅሮ ቀረ ከሔዋን ልብ ላይ!
ገጣሚው ማለት የፈለገው ሰይጣን ውብ ነበር፤ እግዚአብሄር የፈጠረው ለሌላ ዓላማና ግብር ነበር፡፡ እርሱ ግን መመለክ ተመኝቶ ወደቀ፤ ሲወድቅ ደግሞ ያንን የመመለክ ምኞቱን በሔዋን ልብ ላይ ጥሎ ሄደ ለማለት ነው፡፡
ይሁንና የገጣሚው ዐቢይ ስህተት “የንጋት ኮከብ” የማን ስም እንደሆነ ያለማወቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ራዕይ ምዕራፍ 2 ቁጥር 28 ላይ እንዲህ ያሰፈረውን እንመልከት፡-
“እኔ ኢየሱስ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ይህን እንዲመሰክርላችሁ መልዐኬን ላክሁ፡፡ እኔ የዳዊት ሥርና ዘር ነኝ፣ የሚያበራም የንጋት ኮከብ ነኝ፡፤”
የንጋት ኮከብ ኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ሰይጣን አይደለም፡፡ በተረፈ “የእምባ ይናገራል” ደራሲ መንገሻ ክንፉ፤ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦችን የፀነሰና አደባባይ ያወጣ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባዋል። በተለይ ከአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ህብረተሰብ ርቆ እየኖረ፣ ይህንን ያህል መጻፉ የሚያስደንቀው ነው፡፡ (አልፎ አልፎ የቃላት እጥረትና ዐውዱን ያለመጠበቅ ችግሮች እንዳሉበት ሳንረሳ)
በተረፈ ደስ የሚል ስሜት የሚፈጥሩ፣ የሚያዝናኑ፣ የሚያመራምሩ፣ የሚጠይቁና የሚያስጠይቁ ግጥሞቹ፤ የምናቡን ልዕቀት የሚያሳዩ ናቸውና አንባቢያን ገዝተው ቢጠቀሙበት ያተርፋሉ!        

Read 1364 times