Sunday, 17 March 2019 00:00

ከ178ሺህ በላይ የጌዲኦ ተፈናቃዮች አሁንም አስቸኳይ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ እና አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 “ተፈናቃይና የእርዳታ አቅርቦት አልተገናኙም”
                                                       

             ከባለፈው ዓመት መጋቢት 25 ቀን ጀምሮ በተቀሰቀሰ ግጭት ከምዕራብ ጉጂ ዞን የተፈናቀሉ 178ሺህ 977 ሰዎች አሁንም አስቸኳይ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የጌዲኦ ዞን አደጋ ስራ አመራር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡ በገደብ፣ ኮቸሬ፣ ይርጋጨፌ፣ ወናጐ ወረዳዎችና በዲላ ከተማ አስተዳደር በሸራ ቤት ተጠልለው የሚገኙት እነዚህ ወገኖች በአካባቢው በነበረ የፀጥታ ስጋት ምክንያት እስካሁን አስፈላጊውን እርዳታ እንዳላገኙና አሁንም ለነፍስ ማቆያ የአካባቢው ሰው፣ አንዳንድ ተቋማትና ግለሰቦች የሚያደርጉት ድጋፍ በቂ እንዳልሆነ የጌዲኦ ዞን አደጋ ሥራ አመራር ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ትዕግስቱ ገዛኸኝ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በተለይ ከምዕራብ ጉጂ በመጀመሪያው ዙር ተፈናቅለው በየዞኑ ተጠልለው የነበሩት የጌዲኦ ተወላጆች ጉዳይ በሁለቱም ክልሎች አባገዳዎችና የአገር ሽማግሌዎች አማካኝነት ግጭቱ በእርቅ ተቋጭቶ ተወላጆቹ ወደ ቀድሞ ቦታቸውና ህይወታቸው ተመልሰው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ትዕግሥቱ፤ እርቁ ብዙም ሳይቆይ በሁለቱ ህዝቦች መሃል ግጭቱ በማገርሸቱ እንደገና መፈናቀሉ መከሰቱንና ተፈናቃዮቹ እስካሁን እልባት እንዳላገኙ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት እነዚህ ተፈናቃዮች ቀደም ሲል በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከአለም አቀፍ ተቋማትም ሆነ ከአገር ውስጥ በቂ መጠለያና የምግብ አቅርቦት ባለማግኘታቸው ለከፍተኛ ረሃብ መጋለጣቸውንና የጤናም አገልግሎት ማግኘት አለመቻላቸውን ጠቅሰው፤ በቅርቡ የፌደራል መንግስት ለህፃናትና እናቶች የሚሆኑ እንደ ብስኩትና አልሚ ምግብ ማቅረብ ቢጀምርም አሁንም ካለው የሰው ብዛትና ፍላጐት አንፃር እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ቀደም ሲል እርዳታውን ሊያቀርብ የነበረው ወርልድ ቪዥንም ምግቡን ለማጓጓዝ የፀጥታው አስጊነት እንቅፋት ስለሆነበት መድረስ አልቻለም ብለዋል ሃላፊው፡፡
በረሃቡና በጤና አገልግሎት አቅርቦት እጥረት ህይወታቸው ያለፈ ዜጐች ይኖሩ እንደሆነ የጠየቅናቸው የጽ/ቤት ኃላፊው፤ “ረሃብ ካለ በተለይ በህፃናት ላይ ችግሮቹ ሊደርሱ ይችላሉ፤ ነገር ግን በዚህ ቦታ ይሄ ሞቷል ተብሎ የተመዘገበና አሁን ልናገረው የምችለው መረጃ የለም” ብለዋል፡፡ ሃላፊው አክለው እንደገለፁት፤ ሰው ትኩረት አድርጐ የሚያየው የምዕራብ ጉጂ ዞንን ተፈናቃዮች ቢሆንም ከባለፈው ዓመት ግጭት ጀምሮ ወደ ቀድሞ ቦታቸው ሳይመለሱ ጌዲኦ ዞን ውስጥ የተቀመጡ 25 ሺህ 581 የምስራቅ ጉጂ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ገልፀው፤ እነዚህም ወገኖች ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡
በግጭቱ የጉጂ አጐራባች የሆኑት የጌዲኦ ቀበሌ ነዋሪዎች 7ሺህ 969 መኖሪያ ቤቶች በመቃጠላቸውና ነዋሪዎቹ ሸሽተው ወደየዘመዶቻቸው በመጠለላቸው በአሁኑ ወቅት አንድ ዘመድ ከ10 እስከ 30 ሰው አስጠግቶ እየኖረ መሆኑን የገለፁት አቶ ትዕግስቱ፤ ይህም ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስና ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት ችግሩ ለወርልድ ቪዥን ቀርቦ ድርጅቱ ከዛሬ ጀምሮ የእርዳታ እህል ለተፈናቃዮች ለማቅረብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን መረጃ እንዳላቸው ሀላፊው ጨምረው ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የተባበሩት መንግስታትና ሌሎች አለማቀፍ የሰብአዊ ድጋፍ ተቋማትን በዋቢነት ጠቅሶ ሠፊ ዘገባ ያቀረበው ዘ ጋርዲያን፤ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ የጌዲኦ ተወላጆች ለረሃብና ለሰብአዊ ቀውስ መጋለጣቸውን አስታውቋል፡፡
በደቡብ ክልል ጐቲቲ በተባለ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ብቻ ከ20 እስከ 30ሺህ የሚደርሱ የግጭት ተፈናቃዮች ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ የምግብ እርዳታና ሕክምና ተከልክለው መቆየታቸውን ዘ ጋርዲያን በዘገባው አስታውቋል፡፡
ባለፈው አመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐች መፈናቀላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእነዚህ ውስጥ 8መቶ ሺህ ያህል ከጉጂ ዞን የተፈናቀሉ የጌዲኦ ተወላጆች ናቸው ብሏል፡፡ የጌዲኦ ተወላጆች በዚህ መጠን ተፈናቅለው ለምግብ እጥረትና ሠብአዊ ቀውስ መጋለጣቸውም ከማይናማር የሮሂንጋ ሙስሊሞች ሰብአዊ ቀውስ ቀጥሎ ያጋጠመ ትልቁ አለማቀፍ ቀውስ መሆኑን በዘገባው ተመልክቷል፡፡     
የግጭቱ ተፈናቃዮች በዚህ መልኩ ለረሃብና ሰብአዊ ቀውስ መጋለጣቸው በጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተጀመረው ሁለንተናዊ ለውጥ ላይ ጥቁር ነጥብ መሆኑን ያስታወቀው ዘ ጋርዲያን፤ በረሃብና በጤና እርዳታ የሚሠቃዩትን የጌዲኦ ተፈናቃዮች በአስቸኳይ መታደግ ይገባል ብሏል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪያት አቶ ንጉሡ ጥላሁን በበኩላቸው፤ 3መቶ ሺህ ያህል የጌዲኦ ተፈናቃዮች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ መንግስት ችግሩን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እርዳታ እያቀረበ ነው ብለዋል፡፡

Read 4548 times