Sunday, 17 March 2019 00:00

ሀገራት የቦይንግ አውሮፕላን አምራች ኩባንያን ካሣ እየጠየቁ ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ እና መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(6 votes)

   የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለ4 ወራት ብቻ የተጠቀሙበት ቦይንግ 737 ማክስ 8 ዘመናዊ አውሮፕላን ከአየር መውደቁንና 157 ሠዎች መሞታቸውን ተከትሎ በርካታ የአውሮፕላኑን ሞዴል የሚጠቀሙ የዓለም ሀገራት አውሮፕላኑን ከአገልግሎት ያገዱ ሲሆን፤ እያጋጠማቸው ላለው ኪሣራም ካሣ እየጠየቁ ነው፡፡
ባለፈው እሁድ በደብረ ዘይት ሰማይ ላይ ያጋጠመውን አደጋ መንስኤ ሙሉ በሙሉ ከጥቁር ሣጥን መርምሮ ለማወቅ አንድ አመት ይፈጃል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም ችግሩ ከአውሮፕላኑ ስሪት ነው ብለው የገመቱ ሀገራት አደጋው ከተሠማበት ጊዜ ጀምሮ አውሮፕላኑን በጊዜያዊነት መጠቀም አቁመዋል፡፡
በመጀመሪያ እርምጃ የወሰደችው ቻይና ስትሆን 41 የቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኖች ከበረራ ውጪ አድርጋለች፤ በመቀጠልም ከ5 ወራት በፊት በዚሁ የአውሮፕላን ሞዴል ባጋጠመ አደጋ የ192 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈባት ማሌዢያ የአውሮፕላኑን ሞዴሎች አግዳለች፡፡ ኖርዌይም ተመሳሳይ የእገዳ እርምጃ የወሰደች ሲሆን ያለ ስራ ለቆሙት አውሮፕላኖችም ቦይንግ ካሣ ሊከፍለኝ ይገባል ብላለች፡፡ የአውስትራሊያ አየር መንገድም ተመሳሳይ የካሣ ጥያቄ አቅርቧል፡፡
የአውሮፕላን ቴክኖሎጂ እየተወሳሰበ መምጣት እንዳሳሰባቸው የገለፁት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራፕ በበኩላቸው፤ አውሮፕላን አምራች ኩባንያዎች የተወሳሰበ ቴክኖሎጂን ማስቀረት እንዳለባቸወ አመልክተዋል፡፡
ትራምፕ በዚህ ሳያበቁ የአሜሪካ አየር መንገዶች ቦይንግ 737 ማክስ 8 ሞዴልን እንዳይጠቀሙ አግደዋል፡፡ አውሮፕላኖቹም እገዳው በተነገረ ጊዜ በያሉበት ሀገር እንዲቆሙ እንዳይንቀሳቀሱ ትራምፕ በጥብቅ አዘዋል፡፡ የአውሮፓ ህብረት በበኩሉ፤ በአውሮፓ ሰማይ ቦይንግ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን ድርሽ እንዳይል ሲል እግድ ያስተላለፈው በኢትዮጵያ አደጋው በደረሰ ማግስት ሰኞ መጋቢት 2 ቀን 2011 ዓ.ም ነው፡፡
በእነዚህ እገዳዎች ምክንያት በአሁኑ ወቅት ቦይንግ 737 ማክስ 8 የሚጠቀም ሀገር እንደሌለ የዘገበው ቢቢሲ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አውሮፕላኖቻቸው ስራ ፈተው የተቀመጡባቸው ሀገራት በቀጣይ ላጋጠማቸው ኪሣራ ካሣ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የአሜሪካ መንግስት ከፊል ባለድርሻ የሆነበት ቦይንግ ኩባንያ በበኩሉ፤ ያለው ችግር የሚፈታ ነው ብሏል፡፡
ቦይንግ እየደረሰበት ያለው ጫናም ቀላል አለመሆኑን የአቪዬሽን ተንታኞች እየገለፁ ሲሆን፤ ኩባንያው ችግሩን አጥንቶ ለመፍታት ርብርብ እያደረገ መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ከአደጋው ቦታ በቁፋሮ የተገኘውን የአውሮፕላን የአደጋ ሁኔታ መመዝገቢያ ጥቁር ሣጥን የት ሀገር ይመርመር የሚለው ጉዳይ አከራካሪ ሆኖ እንደነበርም የተገለፀ ሲሆን፤ የአሜሪካ የምርመራ ጓዶች ጥቁሩ ሣጥን አሜሪካ ሄዶ ይመርመር የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም ተቀባይነት አላገኙም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ፤ ምርመራውን በጀመርን ሀገር እንዲደረግ ቢፈልግም የጀርመን መንግስት ቦይንግ 737 ማክስ 8 ቴክኖሎጂን መመርመር የሚችል ቴክኖሎጂ የለኝም በማለቷ በመጨረሻ የሚስጢሩ ሁሉ መፍቻ የሆነው ጥቁር ሣጥን ወደ ፈረንሳይ ተልኳል፡፡
በፈረንሣይ መንግስት የሚደረገው የምርመራ አጠቃላይ ውጤት የሚታወቀውም ከ1 አመት በኋላ ይሆናል ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተቋቋመበት ታህሳስ 21 ቀን 1938 ዓ.ም ጀምሮ በ74 ዓመታት የአገልግሎት ዘመኑ በአየር መንገዱ ታሪክ የደረሱ አደጋዎች አራት ብቻ ናቸው፡፡
አየር መንገዱ ሲቋቋም ከአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል የተገዙና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያገለገሉ አምስት DC3 እና C47 አውሮፕላኖች ነበሩት፣ የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ በረራውንም ያካሄደው መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም ወደካይሮ ነበር፡፡ ከአንድ ዓመት በኋላ ሌሎች ዘመናዊ አውሮፕላኖች ተገዝተው መዳረሻውን ወደ ናይሮቢ፣ ፖርት ሱዳን፣ ቦምቤይና ጂዳ አስፋፋ፡፡  የቦሌ አየር ማረፊያ ተገንብቶ በ1954 ዓ.ም አገልግሎት መስጠቱን ሲጀምርም የመጀመሪያው ቦይንግ 720 አውሮፕላን ተገዝቶ ሥራ ጀመረ፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ቀዳሚ የቦይንግ ደንበኛ አደረጋት፡፡ ኮሎኔል ስምረት መድህኔ የአየር መንገዱ የመጀመሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት በ1963 ዓ.ም ነበር፡፡ ከዚህ በፊት አየር መንገዱ ስራውን የሚያከናውነው ከትራንስ ወርልድ ኤይርላየንስ ጋር በትብብር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ስራ የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በአሁኑ ወቅት ባሉት አንድ መቶ አስራ አንድ አውሮፕላኖች 127 አገራትን መዳረሻዎቹ አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡ አየር መንገዱ ባለፉት ሁለት ዓመታት (እ.ኤ.አ በ2017 እና በ2018 ዓ.ም) ብቻ 10.6 ሚሊየን መንገደኞችን አጓጉዟል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከበርካታ የዓለም አገራት አየር መንገዶች በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኝና ከዓለም ምርጥ አየር መንገዶች መካከል የሚመደብ ነው፡፡ አየር መንገዱ አዳዲስና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በመግዛትና ስራ ላይ በማዋልም ቀዳሚ ነው፡፡ በዚህ አየር መንገድ ውስጥ ረዘም ያለ የአገልግሎት ዘመን ያስቆጠሩ አውሮፕላኖችን ማግኘት የማይታሰብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ያሉ አውሮፕላኖችን ከሌሎች አገራት ጋር ለማነፃፀር ብንሞክር፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ያሉ አውሮፕላኖች አማካይ ዕድሜ 5 ዓመት ሲሆን የብሪትሽ አየር መንገድ 13.5 ዓመት፣ የአሜሪካ አየር መንገድ 10.7 ዓመት፣ የዩናይትድ አየር መንገድ ደግሞ 15 ዓመት ናቸው፡፡ ይህም አየር መንገዱ ሁልጊዜም አዳዲስና ዘመናዊ አውሮፕላኖችን  እንደሚጠቀም የሚያመለክት ነው፡፡ አየር መንገዱ የሚሰጠው አገልግሎትና አደረጃጀቱ የአለም ምርጥ አየር መንገድ እስከመባልም አድርሶታል፡፡ የአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድና በፍጥነት በማደግ ላይ ያለ አየር መንገድ በመባል፣ ተመርጦ አለም አቀፍ ሽልማቶችንም በተደጋጋሚ አግኝቷል፡፡
የአውሮፕላን አደጋዎች
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ የመጀመሪያው አደጋ የደረሰው በ1960 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር ይበር በነበረ አውሮፕላን ላይ ነው፡፡ አውሮፕላኑ ባህር ዳር አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ በማረፍ ላይ ሳለ ሞተሩ ውስጥ እርግቦች በመግባታቸው እሳት ተነስቶ ሰላሳ አምስት ሰዎች ሞተዋል፡፡
ሁለተኛው አደጋ ህዳር 14 ቀን 1989 ዓ.ም ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ET961 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ 175 መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ በነበረ አውሮፕላን ላይ የደረሰው አደጋ ነው፡፡ ይህ አደጋ የደረሰው በአውሮፕላኑ ውስጥ ተሳፍረው የነበሩ 3 ኢትዮጵያውያን ወደ አውሮፕላኑ መቆጣጠሪያ ክፍል በኃይል በመግባት አብራሪው የበረራ አቅጣጫቸውን በመቀየር ወደ አውስትራሊያ እንዲበር በማስገደዳቸው ነበር፡፡
በወቅቱ አውሮፕላኑን ያበሩ የነበሩት ካፒቴን ልዑል አባተ ከጠላፊዎቹ ጋር ለመነጋገርና ለመደራደር መከራ አድርገው ነበር፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ነዳጅ አውስትራሊያ ሊያደርሳቸው እንደማይችልና አንድ ቦታ ላይ አርፈው ነዳጅ በመቅዳት ጉዞአቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ነግረዋቸው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ጠላፊዎቹ በዚህ ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም፡፡ በወቅቱ ጠላፊዎቹ የአውሮፕላኑን የእሳት ማጥፊያ መሳሪያ ቦንብ በማስመሰል ይዘው ነበር የአውሮፕላን አብራሪውን ያስፈራሩት፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ ያለው ነዳጅ ከአራት ሰዓታት በላይ ለመብረር የሚያሰችል አልነበረምና አውሮፕላኑ አየር ላይ እያለ ነዳጁ አለቀ፡፡ ካፒቴን ልዑል አውሮፕላኑ መሬት ላይ ወድቆ ቢከሰከስ የሚደርሰውን ጉዳት መጠን ያውቁ ነበርና አውሮፕላኑን በውሃ ላይ ለማሳረፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገው፣ በኮሞሮስ ደሴቶች ዳርቻ ላይ ወድቆ ተከሰከሰ፡፡ በዚህ አደጋም የአውሮፕላኑን ዋና አብራሪ ካፒቴን ልዑል አባተንና ረዳት አብራሪውን ካፒቴን ዩናስ መኩሪያን ጨምሮ 50 ሰዎች በህይወት መትረፍ የቻሉ ሲሆን፤ የአውሮፕላኑን ጠላፊዎች ጨምሮ 125 ሰዎች ደግሞ በአደጋው ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በወቅቱ በደሴቱ ዙሪያ በመዝናናት ላይ የነበሩ ሰዎች አውሮፕላኑን ሲወድቅ በካሜራ እየቀረፁትም ነበር፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎችን ህይወት በመታደግ ረገድ ሥራ ላይ በባህሩ ዳርቻ ይዝናኑ የነበሩ ሰዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የአውሮፕላኑ ዋና አብራሪ ካፒቴን ልዑል አባተም ሆነ ረዳታቸው ካፒቴን ዮናስ መኩሪያ በወቅቱ ላከናወኑት ህይወት አድን ተግባር ሲመሰገኑ “እኛ የሰራነው ስራችንን ነው” የሚል ምላሽ ነበር የሰጡት፡፡ በአደጋው ከሞቱት ውስጥ ኬኒያዊው የፎቶ ጋዜጠኛ መሐመድ አሚን ይገኝበታል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ታሪክ ሦስተኛው የአውሮፕላን አደጋ የተከሰተው በቤይሩት ነበር፡፡ ጥር 16 ቀን 2002 ዓ.ም ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ 82 መንገደኞችንና 8 የአውሮፕላኑን ሰራተኞች አሳፍሮ ይጓዝ የነበረው ቦይንግ 737፣ የበረራ ቁጥር 409 አውሮፕላን ከቤይሩት አየር ማረፊያ በተነሳ በአራት ደቂቃ ውስጥ በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ወድቆ በአውሮፕላኑ ውስጥ የነበሩ 90 ሰዎች በሙሉ ሞተዋል፡፡
ባለፈው እሁድ መጋቢት 1 ቀን 2011 ዓ.ም የደረሰውንና በአየር መንገዱ ታሪክ እጅግ አስከፊ በተባለው አደጋ 149 መንገደኞችና 8 የአውሮፕላኑ ሰራተኞች ህይወት ያለፈ ሲሆን በአየር መንገዱ ታሪክ አራተኛው አደጋ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ይህንኑ አደጋ ተከትሎም በርካታ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ሰፋ ያለ ዘገባ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ የሲኤንኤን ዘጋቢው ሪቻርድ ኩዌስት፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሌሎች አየር መንገዶች ደህንነት ላይ ጥርጣሬ ሲያደርብህ የምትመርጠው አየር መንገድ ነው፡፡ አየር መንገዱ በዓለም ላይ ካሉና ምርጥ ከሚባሉ አየር መንገዶች አንዱ ነው ሲል ዘግቧል፡፡ የTRT ወርልድ ባልደረባዋ፤ “የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደካማ የደህንነት ታሪክ ያለው አየር መንገድ ነው” በማለት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ የሚሰጡትን ባለሙያ ለማሳሳት በሞከረችበት ጊዜ ባለሙያው “አትሳሳቺ፤ አየር መንገዱ እጅግ ምርጥ የደህንነት ታሪክ ያለውና ሊተማመኑበት የሚችሉት አይነት አየር መንገድ ነው” በማለት አርመዋታል፡፡
ቢቢሲ በበኩሉ፤ “አየር መንገዱ የአለማችን ምርጥ አየር መንገድ ነው፤ ይህን የሚያረጋግጥልን ደግሞ የ34 አገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች አየር መንገዱን ምርጫቸው ማድረጋቸው ነው” ሲል ዘግቧል፡፡

Read 4884 times