Sunday, 17 March 2019 00:00

በሀሳብ መንገድ ላይ

Written by  ተመስገን
Rate this item
(1 Vote)


           ሰዎች ተሰብስበው ሰልፍ ወጡ፡፡ እግዜር ዘንድ ቀረቡ፡፡
“አቤት ምን ልታዘዝ” አላቸው፡፡
“ምድሪቱን አከፋፍለህ የያንዳንዳችንን ድርሻ ስጠን” አሉት፡፡
“ምነው በደህና?”
“በቃ ወስነናል”
“የሁሉም ሰው ሃሳብ እንዲሁ ነው?” በማለት ጠየቃቸው፡፡
“ያንድም ሰውኮ ቢሆን መብት ነው” ሲሉ መለሱ።
ሳቁን አፍኖ … “ዙሪያ ገባውን ለክታችሁ ለጠቅላላው ሰው አካፍሉና ድርሻችሁን ውሰዱ” ብሏቸው ወደ ጉዳዩ ሄደ፡፡ እንዳላቸው ካደረጉ በኋላ የየድርሻቸውን ለመውሰድ መገዝገዝ ጀመሩ … እንደ ፒዛ፡፡ መሸና ደክሟቸው … ወደ ቦታቸው ተመለሱ። በማግስቱ ሲመጡ አንዱ አንደኛውን፡- “ወንዜ ወዳንተ ፈሰሰ፣ ያንተ ድንጋይ ተንከባሎ ወደኔ መጣ፣ ተራራዬን ናድክብኝ፣ ዋርካዬ ተገነደሰብኝ …ወዘተ” እያሉ ሲጨቃጨቁ እግዜር ደረሰ፡፡
“እህሳ?” አላቸው፡፡ … ስለተኳረፉ ዝም አሉ፡፡ ... “መሬት’ኮ የናንተ ብቻ አይደለችም፡፡ እንስሳቱም፣ አእዋፉም፣ ነፍሳቱም፣ ወንዞቹም ተራራዎቹም ባለቤቶች ናቸው፡፡ የሚቀጥሉት ትውልዶችም እንዲሁ፡፡ መሬትን የተካፈለ ወይንም ጨረቃን፣ ቀንና ሌሊትን፣ ክረምትና በጋን ካልተካፈለ ምን ዋጋ አለው? ደግሞም የህዋው ስርዓት (Universal order) እንደሚዛባ አትርሱ” አላቸው፡፡
“አድልዎ ስለበዛብን ነው” አሉት፡፡
“ምን ጎደለባችሁ?”
“ለአንዳንዶቻችን ብጣቂ፣ ለአንዳንዶቹ ደግሞ ጃን ሜዳን የሚያኽል መተርክላቸው፡፡ አንዳንዱን በርሃና ጠፍ፣ አንዳንዱን ለምና ቀዝቃዛ አደረግኸው … ለምን?”
“እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ አውሮፓ ዓይነቱን ትንሽ ቦታ ጠንካራ ሰራተኛና ዕውቀት ላላቸው ህዝቦች ሰጠሁት፡፡ ተጠቀሙበት፣ ሃብት አፈሩ፡፡ ሰፊ አገር የሰጠሁዋቸው ሰነፎች የሚሰደዱት ወደ እነሱ ነው፣ እዛ ነው የሚቀላውጡት፣ የመኖርያና ዜግነት ፍቃድ እንዲሰጧቸው ደጅ የሚጠኑት እነሱን ነው፡፡ በርሃ ለሆናቸው ደግሞ ነዳጅና ማዕድን ሰጠሁዋቸው፡፡ ሳይቆፍሩ፣ ሳያርሱ ዶላራቸውን ያፍሳሉ፡፡ በረዶ እየገዙ ጥማቸውን ይቆርጣሉ። ለሰነፎቹ ደግሞ ሰፊ ቦታ፣ ንፁህ አየር፣ ውሃ ሰጠሁዋቸው፡፡ አልሰሩበትም፡፡ ሀብታሞቹ እረፍት ለማድረግ፣ ለመጎብኘትና ንፁህ አየር ለመቀበል እየተመላለሱ ገንዘባቸውን ቢያፈሱላቸውም አያለሙበትም፡፡ በዚህ ላይ በተረት ተረት እየተጣሉ ተስማምተው መኖር አይችሉም፡፡” አላቸው፡፡
“ታዲያ ምን ይሻላል?” ብለው ጠየቁት
“ቦታ ልቀያይራችሁ ነው” አላቸው፡፡    
“በአንድ አፍ!” አሉት፡፡
ቀያየራቸው፡፡ ከሰፊው ወደ ጠባብ አህጉራት የሄዱት በትንንሽ ሃገራት ሲታጨቁ እርስ በርስ ለመከፋፈል፣ በዘርና ጎሳ እየተቧደኑ ለመዋጋት ጊዜም አልፈጀባቸውም፡፡ “…እንኳንስ ዘንቦብሽ --” ሆነላቸው፡፡ … ከጠባቡ ወደ ሰፊው የመጡት ደግሞ የተጣሉት ታርቀው፣ የተኳረፉት ተቃቅፈው በሀብት ላይ ሀብት፣ በፍቅር ላይ ፍቅር ጨምረው ገነትን አወረዱ፡፡ … እግዜርም እንደገና የተሰለፉትን እያየ፤
“ሰዎችን የሚያጣላቸው የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ እንጂ የቦታ መጥበብና መስፋት አይደለም” ሲል አሰበ፡፡
“ያሰብከው ትክክል ነው” አለ ዲያብሎስ ድንገት ከች ብሎ፡፡
“ያሰብኩትን በምን አወቅህ? ልልህ ነበር-- አጅሬው መሆንህን ረስቼ” አለው እግዜር… ፈገግ ብሎ፡፡
“የምታስበውን የማላውቅ ቢሆንማ እስከዚህ ዘመን እንዴት እዘልቅ ነበር?”
“አንተም የምታስበውን ባላውቅ ኖሮ፣ ህዝቦችን እርስ በራሳቸው እያናከስክ ትጨርሳቸው ነበር፡፡”
“ሁለታችንም ስራችንን ነው የምንሰራው… አንተም እኔም፡፡”
“ሰውን ማሳሳት ያንተ ስራ ነው፡፡ መልካምነትን ማስተማር ግን የኔ ስራ አይደለም”
“እንዴት?”
“ይኸን የሚያስተምሩ ብዙ የእምነት ድርጅቶች አሉ፡፡ አይሁድ፣ ክርስትና፣ ሂንዱ፣ ሺንቶ፣ ቡድሂዝም፣ እስልምና … ቆጥሬ አልጨርሳቸውም። የነሱ ነቢያት፣ ካህናት፣ ጉሩዎች፣ ሼሆች ወዘተ ኃላፊነት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የእያንዳንዱ ሰው ህሊና አለ፡፡”
“እሱማ እኔስ አለኝ አይደል”
“አንተ ደግሞ ማን አለህ?”
ነገረውና ሳቀ፡፡ እነማንን ብሎት ይሆን?
****
ወዳጄ፡- መልካም ሰው ስትሆን የሌሎች ሰዎች ደስታ ያንተ ይሆናል፡፡ ሀዘናቸው ሃዘንህ። … ብታውቃቸውም፣ ባታውቃቸውም ያው ነው። ጃፓን መሬት ተንቀጠቀጠ ሲባል፣ ነፍስህ ትንቀጠቀጣለች፡፡ ማዕበል ኢንዶኔዢያን አራዳት ሲባል ነፍስህ ትርዳለች፡፡ ውሽንፍር ኒውጀርሲን ገረፋት ወይም ጎርፍ ፓኪስታንን አጥለቀለቃት ሲባልም ይመለከትሃል፡፡ ታዝናለህ፡፡ ያዘንከው ንፋስ ለምን ነፈሰ፣ ጎርፍ ለምን ጎረፈ ወይም መሬት ለምን ተንቀጠቀጠ ብለህ ሳይሆን በነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ የሞተው፣ የተፈናቀለውና መድረሻው ያልታወቀው ህዝብ ስቃይ ስለሚሰማህ ነው፡፡ በነሱ ቦታ ብሆንስ? ብለህ ስታስብ ይዘገንንሃል፡፡ ባለፈው እሁድ የደረሰው የአውሮፕላን አደጋም አንጀትህን ያንቦጫቦጨው ለዚህ ነው፡፡ ያሳዘነህ እንደወጡ የቀሩት ሰዎች ህልፈትና የደረሰባቸው አሰቃቂ አደጋ ነው፡፡… ነፍሳቸውን ይማርልን!!
ወዳጄ፡- የምትቀጥለው ደቂቃ ምን እንዳረገዘች ማን ያውቃል? … ንጉሥ ልትሆን ትችላህ። … ጳጳስ፣ ሼህ፣ ፓስተር ወይም ጉሩ፡፡ ለውጥ የለውም። ምድራችን ከሰባት ቢሊየን ዓመታት በፊት እንደነበረች ተፅፏል፡፡… ወደፊም ትኖራለች። እኛ ያለማቋረጥ እንደሚፈሰው ወራጅ ውሃ ነን። እንፈሳለን፣ እንፈሳለን… እንፈሳለን … ወንዙ ግን ሁልጊዜም አለ፡፡ አይጎድልም፡፡
“ሰዎች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ፡፡ ሰው ግን ዘለዓለም ይኖራል” (Men come and go, but man goes forever) የሚለን ታላቁ አርስቶትል ነው፡፡
****
ወደ ጨዋታችን ስንመለስ፡- አጅሬው፤ እኔም ስራዬን የሚያግዙኝ አሉኝ ብሎ ነበር፡፡
 “እነማን?” ሲለው
“የዘር ፖለቲካ አራማጆች” ብሎ ነበር የመለሰው።
ከሰው ህይወት ‹መሬት› የሚበልጥባቸው አፈናቃዮች…!!
በነገራችን ላይ “ህይወት የሳሳች ክር ናት፡፡ መቼ እንደምትበጠስ አናውቅም” በማለት የፃፈልን ማን ነበር? እግረ መንገድህንም ለሰው ምን ያህል መሬት እንደሚበቃው ቶልስቶይን ጠይቀህ ንገረኝ፡፡
ሠላም!!

Read 328 times