Monday, 18 March 2019 13:17

ኢትዮጵያ የድንኮች ሀገር እየሆነች ነው

Written by  ደ.በ
Rate this item
(1 Vote)

“ድሮ ድሆች እንጂ ባለጌ አልነበራችሁም”
                                         
          እግዚአብሔር ምን ብሎ ይመልስ የሕዝብን እሮሮ
መንግሥትን እንዲናገር እንጂ እንዳይሰማ ፈጥሮ
የዚህ ግጥም ደራሲ ዳዊት ፀጋዬ፣ በሰሞኑ ግርግር ውስጤ ላይ እንደ ባንዲራ ሲውለበለብ እንዲከርም ግድ ያለኝ ነገር ነበር፡፡ ምናልባት ሰሞኑን ጭቅጭቅ ያስነሳው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ስለወጣለት ይሆን? ብቻ ውስጤን ሲያኝከው ከረመ፡፡
ይህንን ገጣሚ ወዳጄን በሁለት ነገሮች አስታውሰዋለሁ፡፡ አንዱ በርካታ ስደተኛ ኢትዮጵያውን በምድረ ሊቢያ- በአሠቃቂ ሁኔታ የተገደሉበት ቀን ሲሆን ሌላው የኦሮሚያ ወጣቶች በብዛት በመንግስት ጥይት የተደበደቡበት ቀን ነው፡፡
በመጀመሪያው አስደንጋጭ ክስተት ማግሥት ደቡብ ክልል ስለነበርኩ፣ ሀዘኔን በልኩ እያስታመምኩ ስልክ ደወለና የሚሠቅቅ ጩኸትና ልቅሶ አሰማኝ፡፡ ኡኡታ ብለው ይሻላል፡፡ ሣግ እየነቀነቀው እዬዬ አለ። ማንም ሰው እናቱ ብትሞት ከዚህ በላይ ያለቅሳል ማለት ይከብደኛል፡፡ እኔ አንድ ሁለቴ ጉንጬን እንባ ገርፎት፣ ሌሊቱን ሥባንን አድሬያለሁ እንጂ እንደርሱ አልሆንኩም፡፡ ብቻ በሁኔታው ተደንቄ፣ በቀኑ ውስጥ አለፍኩኝ፡፡
አንድ ሌላ ቀን ዳዊት እንደዚሁ ደውሎ እዬዬ አለብኝ?፡፡ “ምንድነው?” አልኩት፡፡
“ጨረሷቸው‘ኮ በናትህ ደረት ደረታቸውን…ግንባራቸውን በጥይት እየመቱ…” አሁንም - እዬዬ- አለብኝ፡፡ “እግዚአብሔር ዝም ብሎ ያያል!” ተንሠቀሰቀ፤ ሟቾቹ በመንግሥት ላይ ተቃውም ያሠሙ የኦሮሞ ወጣቶች ነበሩ፡፡ ወጣቶቹ በሞቱበት ጊዜ በብሔር ሲፈረጅ፣ ሶዶ ጉራጌው ዳዊት ያለቀሰውንና ልቡ የተሰበረውን ያህል አንዳች ሌላ ብሔር ያልተቀላቀለባቸው ኦሮሞ ጓደኞቼ አላዘኑም ነበር፡፡
ዳዊት በዚህ ብቻ አይደለም፤ የመሬት ጉዳይ ሲነሣ፤ ቤት ተከራይቶ የሚኖርበትን አካባቢ ጉዳይ እያነሳ ስለ ኦሮሞ ገበሬዎች መገፋት ለሰማውም ላልሰማውም ይጮሃል፡፡ መሬታቸውን በጥቂት ብር ተነጥቀው የጥበቃ ሠራተኛ የሆኑ ሰዎችን ሀዘን እያነሳ ሥሩ እየተገታተረ፣ እንባ እያቀረረ “ግፍ ነው! ግፍ ነው” ይላልው፡፡
ታዲያ - ከዳዊት የበለጠ ለኦሮሞ ህዝብ ያለቀሰ፤ ከእርሱ የበለጠ የጮኸ አለ?...ለነፃነት ጉዳይ ቢሆንስ…ሊገደል የነበረና አምላክ ያስመለጠው የታሠረ ኦሮሞ ይኖር ይሆን?
በእጅጉ የገረመኝ ነገር ይሄ ነው፡፡ እንደዚያ ለኦሮሞ ወጣቶች እንባ እየረጨ የሚያለቅስ ሰው፤ ጨጓራው እየነደደ ውሎ የሚያድር ሰው፣ እንደዚያ ለገበሬው መሬት መነጠቅ እየዬ የሚል ሰው ኦሮሞ ምድር ላይ የተሠራ ቤት እንኳን በዕጣ ደርስት፣ ከራሱ ከኦሮሞ ህዝብስ በነፃ ሊሰጠው አይገባም ነበር? ብዬ አሰብኩኝ፡፡  የኦሮሞ ሕዝብ ቢሆን ይህንን ይቅርና ከዚህ በላይ ያደርግለታል፡፡
እውነት እንነጋገር ከተባለ ሌሎቻችንስ፣ ኦሮሞ መሬቱን ሲነጥቁት ወይም በጥይት ግንባሩን ሲመታ እኛ አላመመንም? ደግሞስ “ከፈለጉ ይግደሉን” ብለን ስለ ኦሮሞ ወጣት ደም በየመገናኛ ብዙሀኑ አልጮህንም? በደንብ አድርንነዋል ምኝና ወረቀት ያላውን አይለቅምና የተፃፈው ነገር ይመሠክራል። ሰውን በብሔር መደልደል ያሳስታል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ለሀገር ልጅ ለማዘን፣ ለሀገር ልጅ ለመቆጨት ህሊና ብቻ በቂ ነው፡፡
ሰሞኑን - የምናየው ነገር የሚጐድለው ይህ ይመስለኛል፡፡ የአንድ ሀገር ልጆች መሆናችን ተዘንግቷል፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን ብቻ ማሣደድ! ሁላችንም ለራሳችን ብቻ መሟገት!
የዚህ ዓይነቱ ራስ ወዳድነት ደግሞ በአንድ ሀገር አብረን ለመዝለቅ አያስችለንም፡፡ ይልቅስ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንደሚሉት፤ ሁላችንም ግማሽ ግማሽ መንገድ መጥተን መወያየት አለብን፡፡ ከውይይትና ከሰለጠነ መንገድ በስተቀር የሚያዋጣን ነገር የለም፡፡
ከዘመኑ ጋር ያበደው የማህበራዊ ሚዲያ ቀውስ ማቆሚያ መንገዱ ግራ ቢገባም፣ ሁላችንም ልንቃወመውና ልናስወግደው የሚገባን ህመም መሆኑም በዚሁ አጋጣሚ መታወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ማንም ሳይወክለው የሆነ ብሔር ተወካይና ተቆርቋሪ መስሎ የሚቆምበት መንገድ ሃይ ሊባልና ነውርነቱ ሊወገዝ የሚገባ አደገኛ አዝማሚያ ነው፡፡
ለመሆኑ አብሮ የኖረውን የተጋባና የተዋለደውን፤ አንድ ደብር የሚያስቀድሰውን አሊያም አንድ መስጊድ የሚሰግደውን የሀገራችንን ሰው ጦር ለማሰበቅና ዘራፍ ለማለት ሥልጣኑን ማን ሰጥቶን ይሆን? የትግራይ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌና የሲዳማ ሕዝብን ማንነት የፈጠርነው እኛ ሳንሆን የተሳሰረበት ታሪካዊ ሁነትና ዳራ እንዳለ ያወቅን አይመስለኝም። አማራው ለኦሮሞው ክልል፣ ኦሮሞው ለትግራዩ፣ ትግራዩ፣ ለደቡቡ ሞቷል፡፡ አንዳችን ለአንዳችን ኖረናል፡፡ በሥጋ ተጋምደን፣ በደም ተዋህደን፣ በታሪክ ተሠፍተናል፡፡ ስለዚህ ዛሬ የምንቆሰቁሰው እሳት ይህንን የታሪክ ድርሳን ለመደምሰስ ከሆነ ፀያፍና ነውር ነው፡፡
ማን የማንን ደም ለማፍሰስ ጠመንጃ ይመለውላል? ማን የማንን አንገት ሊሰይፍ ሰይፍ ይስላል? በአንድ ሀገር በኖርንባቸው እልፍ ዓመታት ልቅሶውም፣ ሠርጉም፣ ደስታና ሀዘኑም የጋራችን እንደነበር መርሣታችን በእጅጉ ያስተዛዝባል፡፡
እዚያ ሰው ይሞታል፣ እዚያ ደም ይፈሳል
እዚህ ይጨፈራል፤ እዚህ ይደነሳል
እዚያ ሰው ያለቅሳል፣ እዚህ ሳቅ ይነግሳል
እዚያም እኛዎች ነን፣ እዚህም “እኛ” ባዮች
የደላን እኛው ነን፣ እኛው ተበዳዮች
አንድነትን ሰብከን የምንሆን ብዙዎች፡፡
እኛው ነን የሞትን፣ እኛው ነን ቀባሪ
እኛው ነን ሙሾ አውራጅ፣ እኛው ነን ጨፋሪ
አንድ ነን እያልን፣ ልዩነት ፈጣሪ፣
ይህ የበላይ በቀለ ግጥም የሚያሳየን፣ የአሁኑ ማንነታችንን ይመስለኛል፡፡ ሁላችንም በየፊናችን እንጮሃለን የምንጮኸው ጩኸት ለሀገር ጥቅም፣ ለህዝቦች እኩልነት ይመስላል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ማንም የማንንም ድምጽ አይሰማም፡፡ ሁሉም በየራሱ መንገድ በየራሱ ምኞት ይጋልባል፡፡ ዋናውና ትልቁ ችግር የዚህ ሁሉ ጩኸትና ሩጫ ግብ የት ያደርሰናል? የሚል መጥፋቱ ነው፡፡
“አዋቂ ነኝ” የሚለውና በየፌስቡኩ፣ የተማረበትን ዩኒቨርሲቲ፣ የሚሠራበትን መሥሪያ ቤት ጽፏል። እነዚህ ተቋማት በሀገሪቱ ገንዘብ የዚህ ዓይነት አውሬና ነፍሰ ገዳዮችን ካስተማሩ መጀመሪያ ደረት ጥሎ ማልቀስ ለእነርሱ ነው፡፡
ይህ ደግሞ የሚያሳየን በየተቋማቱ ውስጥ የተሰገሰጉት ሰዎች አመለካከትና ለሀገር ያላቸው ግንዛቤ ምን ያህል የተጣመመ እንደሆነ ነው፡፡ በእኔ ግምት የትምህርት ተቋማታችን ውድቀት አርባ ሁለቱ ጐምቱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በፖለቲካ ሴራ - ግቢውን ከለቀቁ በኋላ ነው፡፡ ለመሆኑ ያንድ ሀገር ሰው ሁሉ ተሣዳቢ እስኪባል ድረስ ያለመከባበርና መዘላለፍ ከየት ያመጣነው ይሆን? የት እንደተፈጠረ ማወቅ አይከብድም፣ የቀደሙት ሴረኛ - ገዢዎች በየቢሮውና በየትምህርት ቤቱ ያስተማሩት መዘራጠጥ ነው፡፡ ተማሪ አስተማሪውን የገመገመና ያብጠለጠለ ቀን፣ የዚህ ዓይነት ትውልድ ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ በጣም ብዙ ነገር ለሀገር የሠሩ ታላላቆችና ጐምቱዎችን የሚያዋርድ ህዝብ ግቡ የት ሊሆን እንደሚችል ማወቅ አያዳግትም፡፡
በተለይ በመንጋ ወጥቶ፣ በመንጋ ዘፍኖ፣ በመንጋ ጨፍሮና ተሳድቦ መኖርን እያስለመደው የመጣው የኳስ ሜዳ አውሬነት እያደገ ሲሄድ አንገት መቀላላት ያመጣል ብሎ መጠርጠር ለእኛ ሩቅ አይደለም፡፡ በአንድ ሀገር ለአንድ የሠላም ዓላማ የተሰለፉ የእግር ኳስ ቡድኖች በበላንጣነት ተካርረው እርስ በርስ በስለት እስከመቆጋት ሲደርሱ ሃይ ካላልናቸው፣ አሁን ካየነውና ከሰማነው በላይ ችግር ደጃችን ላይ እንዳለ ማሰብ አለብን፡፡
እንግዲህ ይህ የምናየው የፌስ ቡክ ክፋትና ነውር የተወለደው ከዚህና ይህን ከመሠሉ የጥፋት ማህፀኖች ነው፡፡ ይህንን መከርከምና ነቅሰው ማሳደግ ያለባቸው የሃይማኖት ተቋማትም በጥቅማጥቅም በተደለሉ መሪዎቻቸው አፋቸው ስለተሸበበ፣ እውነት ያልነገሩት ምዕመን ዱላ ቆንጨራና ድንጋይ ለሁሉ ነገር መፍትሔ እየመሰለው ቢመጣ የሚደንቅ አይደለም፡፡
“እግዚብሔር ፍቅር ነው” እያለ በጥላቻ ጅራፍ ምዕመኑን የሚገርፍ ጭንብልና እሾህ ዘርቶ ወይን ሊጠብቅ አይገባም፣ እነሆ በዚያ የተነሣ ዛሬ የምናየው አሳፋሪ ነገር ሁሉ ሆኗል፡፡
ሰሞኑን አንድ እንግሊዛዊ ጽፎታል ተብሎ በሠፊው የተሠራጨው አንድ ጽሑፍ (ማንም ይጻፈው ማንም) አሁን ያለንበትን ጉዞና ቀፋፊውን ሥዕል ያሳየን ይመስለኛል፡፡ ጽሑፍን ሙሉ መዘርዘር ባያስፈልግም ሰውየው የዓለማችንን የተለያዩ ሀገራት የጐበኘና ኢትዮጵያን ግን ቀደም ብሎ ጀምሮ የሚያውቃት እንደሆነ ይናገራል፡፡ የሚያውቃት ደግሞ በረሀብ ታሪኳ ነው፡፡ በንጉሡ ጊዜ በደርግ ዘመን፣ በአቶ መለስና በዶክተር ዐቢይ ዘመን ያውቃታል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ህዝቡ ካለበት ስካርና ጥመት ይልቅ የቀድሞው ነጠላው ድህነት ይሻል ነበር ይላል ሃሳቡ። “ድሮ ድኾች እንጂ ባለጌ አልነበራችሁም፤ አሁን ግን ድኻም ባለጌም ሆናችኋል” ይላል፡፡
በሰላሳ ዓመቴ ረሀብ ምን እንደሚመስል ያየሁት ኢትዮጵያውያን ተርበው በየሜዳው ሲያልቁ ነበር። ከ12 ዓመት በኋላ የ42 ዓመት ጐልማሳ ሆኜ፣ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያ በድርቅ ተመታ ህዝቦቿ በየሜዳው አስከሬናቸው ተዘርግቶ አለም እጁን እንዲዘረጋ ሲለምኑ ነው፡፡ ለሶስተኛ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ የሰማሁት የ52 ዓመት ሰው ሆኜ ነው፡፡ በዚህም ጊዜ ከ13 ሚሊዮን በላይ ረሀብተኛ የአስቸኳይ የምግብ እርዳታ  የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን በመጠለያ ጣቢያ አስከሬናቸው ሲጐተት ነው፡፡ በ76 ዓመቴ ስለዚህች ሀገር ስሰማ ከየትኛውም ጊዜ የባሰ በየክልላቸው ሲፈናቀሉ፣ ከሀገር ሀገር ሲንከራተቱ ነው… ይልና አትሌቶቻችሁ አሸንፈው ወርቅ ሲያመጡ ዐለም ሁሉ ስለ እናንተ የሚያወራ ይመስላችኋል፡፡ ግን አይደለም፤ ዓለም ሁሉ የሚያውቃችሁ በኋላቀርነታችሁና በረሃብ ታሪካችሁ ነው” ይላል፡፡
ፀሐፊው ዋልተር አዳም የተባለው ሰው ቢሆንም ባይሆንም ጉዳዩ እውነት ነውና ልባችንን ይነካናል፡፡ ምናልባትም አንዳንዶቻችን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የምንጮህበት ጉዳይ ይመሥለኛል፡፡
ስለዚህ አሁንም ራሳችንን ታላቅ፣ የተለየንና በእግዚአብሔር የተቀደስን አድርገን በተረትና መሠል ሽንገላዎች ከምናስር ለተሻለ ዕድገት፣ እንደየቱም ሀገር ለአንድነት ለሥልጣኔና ዕድገት መትጋት ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ስለ ፈረንጅ ዘፋኝና ተዋናይ የጫማ ቁጥር የሚወራባቸው ሚዲያዎች ሀገሪቱንና ሕዝቧን ወደተሻለና ወደሰለጠነ ትውልድ መፍጠሪያ ማዕከልነት ለማሳደግ መጣር ይበቅባቸዋል፡፡ በተለይ የማይጠቅመንን በዘርና በብሔር የመገፋፋት አካሄድ በአጭሩ መግታት መቻል አለብን፡፡ የሰው ልጅ ሚዛኑ ህሊናው እንጂ ብሔሩ ሊሆን አይገባም፡፡ ለአንድ የሰለጠነ ሕዝብ የሚያስፈልገው ነገር መነጋገር፤ መወያየት እንጂ ጡንቻ ማሳየትና ዛቻ ወይም ስድብ አይደለም፡፡ የዛቻና ስድብ ግቡ መጠፋፋት ነው፡፡ በመጠፋፋት ወቅት ደግሞ የማይጐዳ ወገን የለም፡፡ እውነት ለመናገር ያሁኑ የእኛ ችግር ድህነት እንጂ የብሔር ጉዳይ አይደለም፡፡  በሚሊየኖች የሚቆጠሩ እርዳታ ፈላጊ ረሀብተኞች ባሉበት ሀገር ለግለሰቦችና ዝናና ጥቅም ሲባል ሕዝብን ለጦርነት መገፋፋት ወደ እንስሳነት ዝቅ ማለት ይመስለኛል፡፡ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መሆን ያለብን፣ ስልጡን በምክንያት የሚያምን፣ የሚከባበር እንጂ ወንድሙ ላይ ሠይፍ የሚመዝ የድንጋይ ዘመን ሰው አይደለም!
ከላይ እንደጠቀስኩት ገጣሚ ወዳጄ አንዳችን ስለ ሌላችን አዝነን የምናለቅስ እንጂ ጠላት ሆነን የምናስለቅስ መሆን የለብንም፡፡ እውነት ለመናገር ለኦሮሞ ወጣቶችና አርሶ አደሮች ካለቀሰውና እንቅልፍ ካጣው ገጣሚ ወዳጄ ይልቅ “ኦሮሞ ነኝ” የሚል የሚኖር አይመስለኝም? ይህንን የሚፈርደው ህዝብ ቢሆን ጥሩ ነበር፡፡አሁን የሚደመጠው የህዝቡ ድምጽ ሳይሆን ህዝቡን የከበቡ መፃተኞች ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ቋንቋችንን ደበላልቀውታልና መከራው በዛ!
ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የድንኮች ሀገር እየሆነች ነው፡፡ ከዚህ አስፀያፊ ሁኔታ ለመውጣት ግን እያንዳንዳችን ሃላፊነት አለብን፡፡ ከዚያ በተረፈ እንደ ድንኳን ጣሪያ በአሥር አቅጣጫ የተወጠሩት መሪዎች ላይ ጣት መጠቆም ብቻውን የትም አያደርስም! ይልቅ ህዝባችን ያስተውል! ሁላችን እናስተውል!

Read 621 times