Saturday, 23 March 2019 12:26

የሐምሌ 28 የጅግጅጋ ግጭት ተጐጂዎችን ክልሉ ሊያቋቋም ነው

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(1 Vote)

100 ሚ. ብር ተመድቧል

              በሶማሌ ጅግጅጋ ከተማ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 28 ቀን 2010 ዓ.ም በተፈጠረው ግጭት ቤት ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጐች፣ በ100 ሚሊዮን ብር ሊያቋቁም መሆኑን የክልሉ መንግስት አስታውቋል፡፡
በግጭቱ ከ4ሺህ በላይ ዜጐች መኖሪያ ቤታቸው መውደሙንና የንግድ ተቋማትና የሸቀጣሸቀጥ መደብሮቻቸውም ከጥቅም ውጪ መሆናቸውን ያስታወሰው የክልሉ መንግስት፤ እነዚህን ተጐጂዎች ኃላፊነት ወስዶና ገንዘብ መድቦ ለማቋቋም መወሰኑን ጠቁሟል፡፡
“ሄጐ” በሚል በተደራጀ የወጣት ቡድን አማካይነት በጅግጅጋና በተለያዩ የሶማሌ ክልል ከተሞች ሐምሌ 28 ተፈጥሮ በነበረው ግጭት፤ ከ430 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመ የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሪፖርት ይገልፃል፡፡
የክልሉ መንግስት አሁን የመደበው 100 ሚሊዮን ብር የጉዳቱን ሩብ ያህል ቢሆንም ተጐጂዎችን ለማቋቋምና መሠረት ለማስያዝ ጠቃሚ ነው ብሏል - የክልሉ አደጋ ስጋት አመራርና መከላከል ጽ/ቤት፡፡
ለማቋቋሚያነት የተመደበው 100 ሚሊዮን ብር በዚህ ሣምንት ለተጐጂዎች በነፍስ ወከፍ ይከፋፈላል ተብሏል፡፡ የክልሉ መንግስት እስካሁን ለተጐጂዎች መሠረታዊ የእለት ጉርስና የቁሳቁስ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱም ተጠቁሟል፡፡

Read 6235 times