Tuesday, 16 April 2019 00:00

የፀረ ጥላቻ እና ሃሰተኛ መረጃ ህጉ - በህግ ባለሙያዎች ዕይታ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

  • የህግ አተረጓጉሙ ዲሞክራሲንና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚጋፋ እንዳይሆን አስግቷል
                  • የወንጀለኛ መቅጫ ህግ፤ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን በተመለከተ በቂ ድንጋጌዎች አሉት
                            
                 “የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን” ለመቆጣጠር የተረቀቀው አዋጅ መዘጋጀቱ ከወቅቱ የሀገሪቱ ሁኔታ አንፃር አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት የህግ ባለሙያዎች፤ ህጉ ተጨማሪ ውይይት ሊደረግበትና ሊዳብር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡
“አዋጁ መውጣቱ ወቅታዊና የሚደገፍ ነው” ያሉት አንጋፋው የህግ አማካሪና ጠበቃ ወንድሙ ኢብሣ፤ ማህበረሰብን በጥላቻ የሚያወግዙና ኢትዮጵያውያንን እርስ በእርስ የሚያጋጩና የሚያራርቁ የጥላቻ ንግግሮች በተበራከቱበት ወቅት አዋጁ መውጣቱ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ በረቂቅ ህጉ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ግልጽና የማያሻሙ መሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ወንድሙ፤ ስጋቴ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ የሚኖረው አተረጓጐምና አተገባበር ላይ ነው ይላሉ፡፡ የህግ አተረጓጉሙ ላይ ዲሞክራሲንና ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በሚጋፋ መልኩ ከሆነ አዋጁ የአፋኝነት ሚና ሊኖረው ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የበፊቱ የሽብር ህግ የሰብአዊ መብትን በግልጽ የሚጋፋ ነበር ያሉት የህግ አማካሪው፤ የፀረ ጥላቻና ሀሰተኛ መረጃ ህግ ግን መብትን የሚጋፋ ሳይሆን የሌሎችን ክብርና ሞራል የመጠበቅ ሚና ያለው ነው ብለዋል፡፡ ህጉ፤“አትሳደብ፣ አታንቋሽ” ነው የሚለው ያሉት አቶ ወንድሙ፤ ይህ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ከመገደብ ጋር አይገናኝም ብለዋል፡፡ ህጉ መከባበርን በማስፈን፣ ስድብን እንደሚያርቅ የህግ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡   
በአቶ ወንድሙ ሃሳብ በከፊል የሚስማሙት ሌላኛው የህግ ባለሙያ አቶ አዲሱ ጌታነህ በበኩላቸው፤ የጥላቻ ንግግሮች በተበራከቱበት ሁኔታ በህግ አደብ ማስገዛት ተገቢ ቢሆንም ይህን ለማድረግ ሀገሪቷ ያላት የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በቂ ነው ይላሉ፡፡ የጥላቻ ንግግር የሚለው አገላለጽ በራሱ የጠራ ብያኔ የለውም ያሉት አቶ አዲሱ፤ ይህም ለትርጉም ሠፊ ክፍተት ፈጥሮ፣ ዜጐችን ለሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳያጋልጥና ዲሞክራሲያዊ መብትን እንዳይሸረሽር ስጋት አለኝ ብለዋል፡፡  
የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች አስጊ በሆነ ሁኔታ እየተበራከቱ መምጣታቸው እሳቸውንም እንደሚያሳስባቸው የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፤ ለዚህ መፍትሔ የሚሉትን ይጠቅሳሉ፡፡  አገሪቱ ጥንቃቄ የሚጠይቅ የለውጥ ሂደት ላይ ባለችበት ወቅት ለዲሞክራሲያዊ መብቶች መታፈን በር ከፋችና አጠራጣሪ ህግ ከማውጣት ይልቅ ቀደም ሲል የነበረውን የወንጀለኛ መቅጫ ህግ በተግባር ማዋሉ ጠቃሚ ነው ይላሉ፤ህጉ ጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃን በተመለከተ በቂ ድንጋጌዎች እንዳሉት በመጠቆም፡፡ ከዚህ በፊት ከመንግስት አካላት ይሰነዘሩ የነበሩ የጥላቻ ንግግሮች ላይ ይቅርታ በመጠየቅና  ማህበረሰቡን ስለ ጥላቻ ንግግር በማስተማር፣ አደጋውን በዘላቂነት መከላከል እንደሚቻልም አቶ አዲስ ያስረዳሉ፡፡  
በህጉ ላይ ሰፊ ውይይትና ምክክር ሊካሄድ ይገባል፤ተቻኩሎ መጽደቅ የለበትም የሚሉት የህግ ባለሙያዎቹ፤ ህጉን አስፈፃሚ አካላትም ገለልተኝነታቸው መረጋገጥ አለባቸው ይላሉ፡፡
የፀረ ጥላቻ እና ሃሰተኛ መረጃ ህጉ መውጣቱን ሙሉ በሙሉ የሚቃወሙት ሌላኛው የህግ ባለሙያ አቶ ተማም አባቡልጉ በበኩላቸው፤ በህዝብ ቅቡልነት የሌለው ህገ መንግስት ሳይሻር እሱን እያጣቀሱ የሚወጡ ህጐች በሙሉ አፋኝና ለዲሞክራሲ በር የማይከፍቱ በመሆኑ አዋጁ ተገቢነት የለውም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡  
የፀረ ጥላቻ እና ሃሰተኛ መረጃ ረቂቅ ህጉ ምን ይላል?
የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመቆጣጠር የተዘጋጀውና ውይይት እየተደረገበት ያለው አዋጅ የሚከተለውን አላማ ይዟል፡፡
የአዋጁ አላማ አንደኛ፤ ሰዎች ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብታቸውን ተግባራዊ ሲያደርጉ ሰብአዊ ክብርን፣ የሌሎችን ደህንነትና ሰላም አደጋ ላይ ከሚጥል ንግግር እንዲቆጠቡ ማስቻል፤ ሁለተኛ በማህበረሰቡ ውስጥ እኩልነት እንዲሰፍን፣ መከባበር እንዲኖርና መግባባትና ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲጎለብት ማድረግ እንዲሁም ሶስተኛ አላማው፤ ለዲሞክራሲያዊ ስርአት አደጋ የሆኑ የጥላቻ አመለካከትና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭት መስፋፋትንና ተያያዥ ወንጀሎችን መከላከልና መቀነስ ናቸው፡፡ ረቂቅ አዋጁ አንቀፅ 4 ላይ የጥላቻ ንግግርን አስመልክቶ ከተቀመጡ ፍሬ ጉዳዮች መካከል ሆን ብሎ የሌላን ግለሰብ፣ የተወሰነ ቡድንን ወይም ማህበረሰብን ብሄርን፣ ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ፆታን፣ አካል ጉዳተኝነትን፣ ዜግነትን፣ ስደተኝነትን፣ ቋንቋን፣ ውጪያዊ ገፅታን መሰረት በማድረግ እኩይ አድርጎ የሚስል፣ የሚያንኳስስ የሚያስፈራራ፣ መድልኦ እንዲፈፀም ወይም ጥቃት እንዲፈፀም የሚያነሳሳ ጥላቻ አዘል መልዕክቶችን መናገር፣ ፅሁፍ መፃፍ፤ የኪነ ጥበብና እደ ጥበብ ውጤት በመስራት፣ ፅሁፍ፣ ምስል፣ ስዕል፣ የኪነ ጥበብ እደ ጥበብ ውጤት፣ ድምፅ ቅጂ ወይም ቪዲዮ በማተም፣ በማሳተም ወይም በማሰራጨት፤ መሰል ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች ብሮድካስት ማድረግ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ ማሰራጨት ወይም በሌሎች ማናቸውም መገናኛ መንገደኞች ለህዝብ መልዕክቱ እንዲደርስ ማድረግ ክልክል ነው ይላል፡፡ ማንኛውም ሰው ጥላቻ የሚያስተላልፍ መልዕክት በማህበረሰቡ ወይም ለሶስተኛ ወገን እንዲደርስ በማሰብ በህትመት ወይም በፅሁፍ መልክ ይዞ መገኘትም የተከለከለ መሆኑ በረቂቁ ተመልክቷል፡፡
የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን በተመለከተም፤ የፍሬ ነገር ወይም አንኳር ይዘቱ ውሸት መሆኑን እያወቀ ወይም ማወቅ ሲገባው ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ግልፅ በሆነ መልኩ ከፍ ያለ መረጃን ሆን ብሎ በማንኛውም መንገድ ማሰራጨትና ለህዝብ እንዲደርስ ማድረግ የተከለከለ ነው ይላል፡፡
ይህ ረቂቅ አዋጅ ለእነዚህ ድንጋጌዎችም ልዩ ሁኔታን ያስቀምጣል፡፡
በልዩ ሁኔታ ድንጋጌውም አንድ ንግግር እንደ ጥላቻ ንግግር ተወስዶ የሚያስጠይቅ፡- ድርጊቱ ለትምህርት ወይም ሳይንሳዊ ምርምር የተደረገ እንደሆነ፣ ሚዛናዊና ትክክለኛ ዘገባ፣ በዲሞክራሲ ስርአት ውስጥ ተቀባይነት ያለው ትችትና የፖለቲካ ንግግር፣ የማስታወቂያ ወይም ማስጠንቀቂያ አካል እንደሆነ፣ በቅን ልቦና የሚደረጉ ሃይማኖታዊ አስተምሮት ወይም አተረጓጎም ከሆነ ነው ይላል፡፡
አንድ ዘገባ እንደ ሃሰተኛ ዘገባ ተወስዶ በህግ የሚያስጠይቀውም፡- ንግግሩ የጥሬ ሃቅ ዘገባ ወይም ዜና ከመሆን ይልቅ ወደ ፖለቲካ አስተያየትና ትችትነት ያጋደለ ከሆነ፣ ንግግሩ ቀልድ፣ ስላቅ ወይም ልብ ወለድ መሆኑ ግልፅ ከሆነ እንዲሁም ንግግሩን ያደረገው ሰው የመረጃውን እውነተኛነት ለማረጋገጥ በሱ ሁኔታ ካለ ሰው የሚጠበቀውን ምክንያታዊ ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው ይላል፡፡
በወንጀል ተጠያቂነትም፤ እነዚህን ጥፋት አጥፍቶ የተገኘ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት አመት የሚደርስ እስራት እንዲሁም ከ3ሺህ እስከ 10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ተቀምጧል፡፡

Read 5819 times