ሆስዕና-1
(ያህያ ስንከላ)
ይሄ ቡላ አህያ . . .
የተሰነከለው፣
የፊት የግራ እግሩ
ከኃለኛው ጋራ
በጠፍር የታሰረው፣
ነጂ ፣
ጫኝ፣
አለቃው፣
ለኛ ንደነገረን . . .
‹ ያህያ ያልሆነ › ሃሣብ ስላለው ነው ፡፡
. . . // . . .
ነጂው የነገረን በቀላጤ ቋንቋ
በቱርጁማን ልሣን ፣
‹ ያህያ ያልሆነ › ሃሳብ ብሎ ሲባል
ነገሩ ‘ንዲገባን ፣
እንዲለይ ልባችን
እንዲህ ያለው ጉዳይ
እውነት ለሰንካላ
ለስር እንዲያበቃ፣
አስተርጓሚው ቀርቶ ብንሰማ ደግ ነበር
ያህያን ካህያ
ከሚሆን በስሚ
ከበላይ ካለቃ፡፡
. . . // . . .
የመናገር እድል ጉዳይ የመተንተን
ሃሣብ የማብራራት ፣
የመፈረጅ ስልጣን
ሁል ጊዜም የሚሰጥ
ለነጂው ነውና
በምልአት በስፋት ፣
ያው በሰማ ባለው
እንግዲህ እንስማ
ሃሣብ የተባለን
ያህያ ያልሆነ፣
በህሊና ሚዛን ነገሩን እያየን
ሃቅ ብጤ ንዳለው
እውነት እንደሆነ ፡፡
. . . // . . .
ነጂውን ያሰጋ ያሣብ ሁሉ አወራ
ባለቀው ሲነገር በጫኙ ሲወራ ፡፡ . . . 1
መጮኽ ያለ ፍቃድ ፣
ለተነጂ ፍጡር
ከቶ ማይገባ ባህልና ልማድ ፡፡
ስልጣን ስለሌለው
ደርሶ የመወለን ፣
ሁሌም ለተነጂ
ማሳወቅ ግድ ነው
ለመጮኽ መለመን ፡፡
መናገር ያሰበ እምነቱን አውጥቶ ፣
ማስፈቀድ አለበት ካላቀው ፊት ወጥቶ ፡፡
ሸክም በዛ ብሎ
ወይም ሰርዶ ጠፋ ፣
አይገባምና በግላጭ በይፋ
አህያ ሊያናፋ ፣
እንዲህ ያለ ድፍረት
ማሰብ መሞከሩ ፣
ባለቃ ምልከታ
ፍፁም አህያዊ
አይሆንም ነገሩ፡፡ አይሆንም ምግባሩ፡፡
ከተነጂ መሃል
ድምፁን ከፍ አድርጎ
ሃሳቡን ያብራራ ፣
በነጂው ብያኔ
ሊገጥመው ግድ ነው
የሰንከላ ብይን
የእስር መከራ፡፡
ነጂውን ያሰጋ ያሳብ ሁሉ አውራ
ባለቃው ሲነገር በጫኙ ሲወራ ፡፡ . . . 2
ጭነት በዛ ማለት
ሸክማችን ከበደ ፣
እንደምን ላህያ
እንዴት ተፈቀደ ?
በተጫኞች ማበር
በተነጂ ዕድር
መጫኛ ያላላ
ሸክም ያዘነበለ ፣
በከበደኝ ምክንያት
ጭነት ያጋደለ ፣
የፊት የግራ ግሩ
ከኃለኛው ጋራ
የተሰነከለ፡፡ . . . ስንት አለ ! ;
የሚገርመው ጉዳይ
በሰንሰለት ብዛት
ሃሣብ ላይገታ ፣
የሚገርመው ጉዳይ
በጠፍር በገመድ
ወኔ ላይመታ፣
የሚገርመው ጉዳይ
በግረሙቅ ካቴና
እውነት ላትረታ ፣
ነጂ አበሣ አየ
ስንቱን እያሰረ !
ስንቱን . . . እየፈታ ! ! ;
ነጂውን ያሰጋ ያሳብ ሁሉ አውራ
ባለቀው ሲነገር በጫኙ ሲወራ ፡፡ . . . 3
ተራራ እያቀሰትን
ዳገትና ቀበት ፣
ገደል እየናጠን
ተዳፋት ቁልቁለት ፣
ሜዳ የዳከርን
ተጭነን ዳውላ ፣
ቀልባችን ፈርቶታል
አለቃ ነጂያች
የያዝከው ዱላ ፣ . . .
በሚል ጥርጣሬ
ጉዞ እያጠፈኑ
መንገድ እያሰፉ ፣
አቅጣጫ እያበዙ
ምርጫ የጨመሩ
ከይታ የጠፉ ፣
እንዲህ ያለ ሃሣብ
ስላልሆነ የነርሱ
ከሰንካላም ኃላ ፣
ሊያገኙ ግዱ ነው
የሸሹትን ዱላ ፡፡
. . . // . . .
ነጂውን ያሰጋ
ጫኚውን ያስፈራ
ያሳብ ሁሉ አውራ ፣
እንደዚህ ይመስላል
ከብዙ በጥቂት
በበላይ ሲነገር
በአለቃ ሲወራ ፡፡
ሆሣዕና-2
( ፍቱና አምጡልን )
........................
የመናገር ዕድል
ጉዳይ የመተንተን
ሃሣብ የማብራራት ፣
ሁልጊዜም የሚሰጥ
ላለቃ ነጂ ነው
በስፋትምልአት ፡፡ . . .
የሚለውን ትተን
እንዲህ ያለ ጊዜ
ብራ ወቅት ሲጋጥመን፣
በውርንጭላ ቀን
በውርንጭላ ድምፅ
በአህያ ቋንቋ
እንዲህ እንላለን፡፡
በገጠር ቀበሌ
በከተማ ሸንጎ
መቀፍደድ መሰንከል
ሃሳብ ሰበብ አርጎ ፣
ቢመስልም ጉዳዩ
አሣቢ መርማሪ
ጠያቂ የሌለበት፣
እንደመፃፉ ቃል
እንዲህ ባለ ጊዜ
ሆሣዕና ሲደርስ
ነገሩ መታየት
መጣራት አለበት፡፡
በዝንጥፍ ዘንባባ
በቀጤማ ጎዝጓዝ
በልልታና ሆታ ፣
ሸማ ያነጠፍን
እንድንቀበለው
መጪው ትንሳኤ ነው
የተሰነከለ የታሰረ ሁሉ
ይለቀቅ ይፈታ ፡፡
Published in
ጥበብ