Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 10:24

ባህላዊ ምግቦች

Written by 
Rate this item
(10 votes)

የጉራጌ ብሔረሰብ የኢኮኖሚ መሰረት ግብርና ቢሆንም ለአትክልት፣ ለአዝርዕትና ጥራጥሬ እንዲሁም ለእንስሳት እርባታ ምቹ የሆነው የእርሻ መሬቱ በፊውዳል ባለስልጣናትና ባለጉልት በመነጠቁ አብዛኛው የብሔረሰቡ አባላት መሬት አልባ ሆነው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ከተዛባው የፊውዳሉ የመሬት ስሪት በተጨማሪ ህዝቡ ሰፍሮ የሚገኝበት መሬት አብዛኛው ክፍል ለሰብል እርሻ የማይመች ጠባብና ዳገታማ በመሆኑ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ይተዳደሩ የነበሩት የብሔረሰቡ አባላት ከእርሻቸው ተፈናቅለው ወደ ተለያዩ የሀገሪቱ ከተማዎች በመፍለስ በንግድና በቅጥር ስራ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡

በግብርና የሚተዳደረው የገጠሩ አርሶ አደር ለተመቻቸ የእርሻ መሬት (ለም ለሆነ የእርሻ መሬት) ባለመታደሉ ለሚገኝበት የተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚ የሆነው የእንስት ተክል እርሻ እንዲለምድና አብዛኛው የጉራጌ ክፍል በድቅድቅ ማረሻ መጠቀም ባህላዊ የአስተራረስ ዘዴው አድርጐታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከእንስት ተክል የሚዘጋጁት ቆጮ (ወርቄ) እና የቡላ ገንፎ የብሔረሰቡ ዋነኛ ምግብ ሊሆኑ ችለዋል፡፡
የብሔረሰቡ ዋነኛ የምግብ ምንጭ ስለሆነው የእንስት ተክል አመጣጥ በተመለከተ በህብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ አፈታሪኮች ይነገራሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በስፋት የሚነገረው ከአቡነ ዜና ማርቆስ አመጣጥ ጋር ተያይዞ የሚገለፀው አፈታሪክ ነው፡፡
ይኸውም አቡነ ዜና ማርቆስ ከሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተነስተው ክርስትናን ለማስፋፋት ወደ ምህር ቤተ ጉራጌ በመጡበት ጊዜ ይዘውት እንደመጡ ይነገራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አቡኑ ሃይማኖታቸውን የተቀበለው የምህር ህዝብ ድርቅና ሌሎች አደጋዎችን የሚቋቋም የምግብ ተክል እንዲያገኝ ባደረጉት ፀሎት በእግዚአብሔር ፍቃድ አንዲት ላም ከጣለችው እበት ላይ የበቀለ መሆኑን ይነገራል፡፡ ሆኖም የህብረተሰብ ሳይንስ እንደሚያስረዳው ከሆነ የሰው ልጅ ከስምንት ሺ ዓመት በፊት በምግብነት ይጠቀምበት የነበረው ተክል እንሰት ነበር፡፡ ስለዚህ አቡነዜና ማርቆስ ወደ ምህር ምድር የመጡበትን ወይም በምህር ምድር የኖሩበትን ዘመንና የሰው ልጅ በእንስት ተክል መጠቀም የጀመረበትን ጊዜ ስናነጻጽር እንሰት ከ600) ከስድስት መቶ ዓመት ወዲህ ከአቡነ ዜና ማርቆስ አመጣጥ ጋር እንደተገኘ የሚተረከው በተለይም ከላም እበት የተገኘ መሆኑን የሚነገረው አፈታሪክን መቀበል እጅግ ያዳግታል፡፡
ዛሬ ብሔረሰቡ በምግብነት የሚጠቀምበት የእንሰት ተክል ከሁለት መቶ በላይ ዝርያዎች እንዳሉት ተክሉን በማምረት የታወቁ ገበሬዎች ይናገራሉ፡፡ እነዚህ የእንሰት ዘሮች በግንዳቸው ወይም በኮባቸው ላይ በሚታዩት የቀለም ዓይነቶች (በመልክ ዓይነታቸው) እንደሚለዩ ከአርሶ አደሩ አካባቢ የተገኙ ማስረዳዎች ያረጋግጣሉ፡፡
..ጎጎት የጉራጌ ብሔረሰብ ታሪክ.. ከተሰኘው መጽሐፍ የተቀነጨበ

 

Read 13582 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:30