Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 10:46

ቬንገር ለትችት አልበገር ብለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አርሰን ቬንገር አርሰናል ከፕሪሚዬር ሊግ የዋንጫ ፉክክር አለመውጣቱን ተናገሩ፡፡ አርሰናል ከመሪው ማን ዩናይትድ በ11 ነጥብ ርቆ በ17ኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ያሳስበኛል ያሉት አሰልጣኙ ከዋንጫ ፉክክር ውጭ ሆኗል ለማለት ግን ጊዜው ገና ነው ብለዋል ሲል ዘ ሰን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ አርሰን ቬንገር ላለፉት ሁለት ወራት በክለባቸው ለታየው ውድቀት ተጠያቂ በመደረግ ሃላፊነታቸው አጣብቂኝ ውስጥ ቢገባም ለሚደርስባቸው ትችት አልበገር ማለታቸውን የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡  በተለይ ለ6 ዓመታት ከዋንጫ ድል ርቆ የቆየው አርሰናል ዘንድሮ በፕሪሚዬር ሊጉ ከ58 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ግዜ ባጋጠመ መጥፎ አጀማመር ማሳየቱ የቬንገርን ቆይታ ጥያቄ ውስጥ ከቶታል፡፡

አሰልጣኙ በየአቅጣጫው በተለይ ከደጋፊዎች የሚመጡ ትችቶችን ጆሮ ዳቦ ልበስ ማለታቸውም እያስገረመ ነው፡፡ አንድ የአርሰናል ክለብ ኃላፊ ቬንገር ክለቡን እንዲለቁ ግፊት እንደማይደረግና እሳቸውም የመልቀቅ ፍላጐት እንደሌላቸው እምነት አለኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ ዘገባዎች ቬንገር በተያዘው የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ በእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ኮንትራታቸው የሚያበቃውን ፋብዬ ከፔሌ ሊተኩ ይችላሉ እያሉም ናቸው፡፡ በእንግሊዝ እግር ኳስ የ15 ዓመት ልምድ ያላቸው ቬንገር ለእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በዋና ዕጩነት ተይዘዋል በሚልም ተወርቷል፡፡ ክለቡን ላለፉት 14 ዓመታት ሲያሰለጥኑ ሁሉንም ዓመት በሻምፒዮንስ ሊግ ተሳታፊ እንዲሆን ማስቻላቸውን የሚናገሩት ቬንገር ለሚቀጥሉት 14 ዓመታትም ይህን ስኬት ለመድገም ተስፋ እንደሚያደርጉና ዋና ትኩረታቸው በሃላፊነታቸው ጥሩ ተግባር ማከናወን እንጅ በትችቶች መረበሽ አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

Read 3246 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:50