Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 24 September 2011 10:47

ኃይሌ በማራቶን የሪኮርድ ሀትሪክ ሊሰራ ይችላል!?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ነገ በሚካሄደው 38ኛው የበርሊን ማራቶን የ38 ዓመቱ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ  በማራቶን የመጀመሪያውን የሪኮርድ ሃትሪክ ሊሰራ እንደሚችል ተጠበቀ፡፡  ሰሞኑን በማራቶን ሪከርዷ ላይ ማስተካከያ የተደረገባት ፓውላ ራድክሊፍ ለመጀመርያ ግዜ በበርሊን ማራቶን ትሳተፋለች፡፡ ሁለቱ የዓለም የማራቶን ሪኮርድ ባለቤቶች ከ40ሺ በላይ ተወዳዳሪዎች በሚሮጡበት የበርሊን ማራቶን ተሳታፊ መሆናቸው ለውድድሩ ያለውን ዓለም አቀፍ ትኩረት ጨምሮታል፡፡ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ በበርሊን ማራቶን ሲሳተፍ ዘንድሮ ለ5ኛ ጊዜ ሲሆን አስቀድሞ በተሳተፈባቸው ውድድሮች አራቱንም ከማሸነፉም በላይ ሁለቱን ያሸነፈው ለ2 ጊዜያት የማራቶን አዲስ ሪኮርዶችን አስመዝግቦ መሆኑ ይታወሳል፡፡

አትሌት ኃይሌ  በ2007 እኤአ ላይ 2 ሰአት ከ04 ደቂቃ ከ26 ሴኮንዶች ገብቶ የመጀመርያ ክብረወሰኑን ሲይዝ፤ በ2008 እኤአ ላይ ደግሞ ርቀቱን 2 ሰአት ከ03 ደቂቃ ከ59 ሰኮንድ በመሸፈን እስካሁን ያልተሰበረውን የዓለም የማራቶን ሪኮርድ ጨብጦታል፡፡ ኃይሌ ከ3 ዓመት በፊት የማራቶን ሪኮርዱን ሲሰብር ያገኘው አጠቃላይ የሽልማት ገንዘብ 130ሺ ዶላር ነበር፡፡ ኃይሌ ነገ ሪከርዱን በድጋሚ ለማሻሻል ከበቃ በውድድሩ ታሪክ የመጀመርያውን የማራቶን የሪኮርድ ሃትሪክ የሰራ አትሌት ይሆናል፡፡
በነገው የበርሊን ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ታላላቅ አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ለለንደን ኦሎምፒክ አስፈላጊውን የማራቶን ሚኒማ ለማምጣት ከባድ ፉክክር ይደረጋል፡፡ ኃይሌ በዘንድሮው የበርሊን ማራቶን ሲሳተፍ ዋናው ትኩረቱ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ለኦሎምፒክ የሚያበቃውን ማኒማ ለማስመዝገብ እንደሆነ ተናግሯል፡፡ ባለፈው ዓመት ኃይሌ ተሳታፊ ባልነበረበት የበርሊን ማራቶን አሸናፊ የነበረው የኬንያው ፓትሪክ ማኩና የደቡብ አፍሪካው ሄነሪክ ራማላ በወንዶች ምድብ ተቀናቃኝ ከተባሉ አትሌቶች መካከል ይገኙበታል፡፡ በሴቶች ምድብ ፓውላ ራድክሊፍን በመፎካከር ከባድ ግምት የተሰጣት የበርሊን ማራቶንን ከሶስት ዓመታት በፊት ያሸነፈችው ጀርመናዊቷ ኤሪና ሚኬቴንኮ ናት፡፡
የደቡብ አፍሪካው አትሌት ሄነሪክ ራማላ በበርሊን ማራቶን የሚሳተፈው በአዘጋጆቹ በቀረበለት ግብዣ ሲሆን ኃይሌና ሌሎች ታላቅ አትሌቶች በሚሳተፉበት ውድድር የሚቻለውን በማድረግ ተፎካካሪነቱን ለማሳየት ማሰቡን ተናግሯል፡፡ የኬንያው አትሌት ፓትሪክ ማኩ በበኩሉ በነገው ማራቶን የሃይሌን ፈጣን አሯሯጥ በመቋቋም ያልተጠበቀ ድል ለማስመዝገብ እንደሚፈልግ ገልፆ ዋናው ትኩረት ግን ለለንደን ኦሎምፒክ የሚያበቃውን ሚኒማ ለማግኘት መሆኑን አስታውቋል፡፡
የሁለት ልጆች እናት የሆነችውና በአትሌቲክስ የ20 ዓመት ልምድ ያላት የ37 ዓመቷ አትሌት ራድክሊፍ በሪኮርዷ መሰረዝ ቢከፋትም ይህ ሁኔታ በነገው የበርሊን ማራቶን የሚኖራትን ተሳትፎ እንዳማያደበዝዘው ተናግራለች፡፡ በበርሊን ማራቶን ተሳታፊ መሆን በራሱ ታላቅ ስኬት መሆኑን የገለፀችው ራድክሊፍ በጡረታ ከስፖርቱ ልትርቅ የነበረችበትን አጋጣሚ የሚቀይር ስኬት እንደሚኖራት ተስፋ አድርጋለች፡፡
የበርሊን ማራቶንን ከሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች ቢያንስ 35ሺ ያህሉ ርቀቱን ጨርሰው የሚገቡ ሲሆን ለሽልማት ከግማሽ ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደቀረበበት ታውቋል፡፡ የማራቶን ውድድሩ በ150 አገራት የቀጥታ ስርጭት ሲኖረው በዩሮ ስፖርት፣ በቢበሲ፣ በሱፐርሰፖርትና አልጀዚራ ቻናሎች ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሌላ በኩል ሰሞኑን የአይኤኤኤፍ ኮንግረስ  እንግሊዛዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ  በወንድ አሯሯጮች ድጋፍ በ2003 እኤአ ላይ በለንደን ማራቶን 2 ሰአት ከ15 ደቂቃ ከ25 ሰኮንዶች ርቀቱን በመሸፈን ያስመዘገበችው የዓለም ሪከርድ እንዲሰረዝ መወሰኑ አወዛገበ፡፡  ውሳኔውን በርካታ የእንግሊዝና የአሜሪካ መገናኛ ብዙሃናት ስፖርቱን የሚገል በሚል ቢያወግዙትም  የዓለም አምስት ታላላቅ የማራቶን ውድድሮች አዘጋጆችና የአለም የጎዳና ላይ ሩጫ ማህበር (AIMS) መደገፋቸው ጉዳዩን አወዛጋቢ አድርጐታል፡፡ ሪኮርዷ የተሰረዘባት ፓውላ ራድክሊፍ ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስቸግርና በዓለማችን ወንድና ሴትን አቀላቅለው  የሚካሄዱ የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮችን የሚያቃውስ ርምጃ ነው ስትልም ተችታዋለች፡፡ የአይ ኤኤኤፍ ኮንግረስ ባሳለፈው ውሳኔ ከእንግዲህ በሴቶች የማራቶን የዓለም ሪኮርድ ወንድ አሯሯጮች በተመደቡበት ቁልቁለታማ በሆኑ የመወዳደርያ ስፍራዎች በሚካሄድ ውድድር እንደማይዘገብ አስታውቋል፡፡ በዚህ መሰረት በሴቶች የዓለም ማራቶን ሪኮርድ ሆኖ እንዲመዘገብ የተወሰነው በ2008 እኤአ በለንደን ማራቶን ራሷ ራድክሊፍ 2 ሰአት ከ17 ደቂቃ ከ42 ሴኮንዶች በሆነ  ጊዜ ያስመዘገበችው ነው፡፡

 

Read 4819 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:51

Latest from