Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 10:52

ኢቲቪ ..ዊኪሊክስ..ን ጠረጠረው - ተዓማኒነት የለውም ብሎ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ሰነዶቼ ተሰርቀው በዊኪሊክስ ተሰራጩብኝ - የአሜሪካ መንግስት
ሰነዶቹ እውነተኛ ሰነድ መሆናቸው ያጠራጥራል - የኢቲቪ የህትመት ዳሰሳ
ኢቲቪ ከዊኪሊክስ ጋር ፀብ ለመግጠም ሲንደረደር ያየነው በሰሞኑ የህትመት ዳሰሳ ፕሮግራሙ ነው፡፡ ከፀቡ ጋር አብሮ ሲነሳ የነበረው ጉዳይ፤ ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ስለ ሱዳን መንግስትና ስለ ፕሬዚዳንት አልበሽር ..እንዲህና እንዲያ.. ተናግረዋል የሚል ሰነድ በዊኪሊክስ ዌብሳይት የመለቀቁ ጉዳይ ነው፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተዘጋጅቶ ለኤምባሲው ..የበላይ አካል.. (ማለትም ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት) የተላከው ሰነድ ምን ይላል? የሱዳን መንግስትን ወይም ፕሬዚዳንት አልበሽርን ከስልጣን አስወግዱ በማለት ጠ/ሚ መለስ ለአሜሪካ ባለስልጣናት ተናግረዋል ይላል ሰነዱ፡፡

ጠ/ሚሩ እንዲህ አይነት ሃሳብ አልተናገሩም፤ ሊናገሩም አይችሉም በማለት የኢትዮጵያ መንግስት የማስተባበያ መግለጫ እንዳሰራጨ ታውቃላችሁ፡፡ እንዲያውም፤ መንግስትን ለመገልበጥ ወይም ለመቀየር፤ በውጭ ሃይሎች የሚደረግ ተፅእኖና ጣልቃ ገብነትን  በመቃወም ጠ/ሚሩ በተደጋጋሚ እንዳስረዱ መግለጫው ይጠቅሳል፡፡ ይህንን የሚያረጋግጡና በዊኪሊክስ የተለቀቁ በርካታ ሰነዶች እንዳሉም ጠቁሟል - መግለጫው፡፡ እንግዲህ ይህን ተከትሎ ነው፤ የኢቲቪ የህትመት ዳሰሳ የቀረበው፡፡
የመንግስትን መግለጫ በስሜት እየደጋገሙና የዊኪሊክስን ሰነድ እያወገዙ የተናገሩት የህትመት ዳሰሳ አዘጋጆች፤ ምናልባት ከስሜታቸው ብዛትና ከውግዘታቸው ስፋት የተነሳ ሳይሆን አይቀርም፤ ወደ ሚያስተዛዝብና ወደ ሚያሳፍር ስህተት ተንደርድረው ገቡ፡፡ መግባት ብቻ ሳይሆን፤ በስህተቱ ውስጥ ተንከባለሉበት ማለት ይቻላል - እየደጋገሙ፡፡
በዊኪሊክስ የተለቀቀው ሰነድ ውስጥ ምን አይነት መረጃ እንደሰፈረ፤ መንግስትም በሰነዱ ውስጥ የሰፈረው መረጃ ውሸት ነው ብሎ እንዳስተባበለ መግለፅ የአባት ነው፡፡ የህትመት ዳሰሳ አዘጋጆች ግን፤ በጭፍን ተንደርድረው ዊኪሊክስን ማጣጣል ጀመሩ፡፡ በሰነዱ ውስጥ ተፅፎ የተገኘውን መረጃ ብቻ ሳይሆን፤ ከነጭራሹ ሰነዱም ከየት እንደመጣ ለማወቅ እንደሚያስቸግርና እውነተኛ ሰነድ መሆኑ እንደሚያጠራጥር የገለፁት የዳሰሳ አዘጋጆች፤ ዊኪሊክስ ራሱ ተአማኒነት የለውም በማለት ደመደሙበት፡፡
አስቂኝ ነው፡፡ እየደጋገሙ ..ዊኪሊኪ.. እያሉ መናገራቸው አይደለም የሚያስቀው - የድርጅት ስም ማጣመም ተገቢ ባይሆንም፤ ከጋዜጠኛ የማይጠበቅ ቢሆንም፡፡ ዊኪሊክስን ለማጣጣል በአላዋቂ ድፍረት ደፋቀና ማለታቸው ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ ዊኪሊክስ የአሜሪካ መንግስት ሚስጥራዊ ሰነዶችን በይፋ ሲያሰራጭ፤ በጭራሽ ማሰራጨት አልነበረበትም ብሎ መተቸትና ማውገዝ ይቻል ይሆናል - ለውግዘቱ አሳማኝ ምክንያት የሚቀርብ ከሆነ፡፡ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ማሰራጨቱ በግል የሚታወቅና በገሃድ የተፈፀመ ድርጊት ነውና፡፡ ሰነዶቹና ዊኪሊክስ ተአማኒነት የላቸውም ብሎ አሁን ውግዘት ማንጋጋት ግን...
እንዴ... ዊኪሊክስ÷\ ቢያንስ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ፤ 140ሺ ገደማ ሚስጥራዊ የአሜሪካ ሰነዶችን በኢንተርኔት ይፋ አድርጓል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ደግሞ፤ ሰነዶቹ በአሜሪካ ኤምባሲዎችና መስሪያ ቤቶች የተዘጋጁ አይደሉም ብሎ አላስተባበለም፡፡ በመላው አለም ታዋቂ የሆኑት የሚዲያ ተቋማት በሙሉ፤ በዊኪሊክስ የተለቀቁት ሰነዶች እውነተኛ ሰነዶች መሆናቸው ምንም እንደማያጠራጥር በማወቅ አመቱን ሙሉ ሲዘግቡ ከርመዋል፡፡
ሰነዶቹ ውስጥ የሰፈሩ ሃሳቦችና መረጃዎች ትክክል ናቸው ወይ? ይሄ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ ሰነዶቹ ግን በአሜሪካ ኤምባሲዎችና መስሪያ ቤቶች መካከል የተደረጉ የመልእክት ልውውጥ እውነተኛ ሰነዶች ናቸው፡፡ ታዲያ፤ የኢትዮጵያ መንግስትን የሚያስቀይሙ አንድ ሁለት ሰነዶች ስለተገኙ ብቻ፤ የህትመት ዳሰሳዎች እመር ብለው ዊኪሊክስ ተአማኒነት እንደሚጎድለው መናገራቸው ምን የሚሉት አላዋቂነት ነው? ዊኪሊክስም ሆነ ሰነዶቹ ተአማኒነት እንደሌላቸው በአላዋቂነት የተናገሩ የህትመት ዳሰሳዎች፤ ጭራሽ ይህንኑን ለማስረዳት ላይ ታች ብለዋል፡፡
ዊኪሊክስ የመረጃ መሰብሰቢያ ቅርጫት እንዳስቀመጠ የህትመት ዳሰሳዎች ገልፀው፤ ማንም ሰው የፈለገውን አይነት መረጃና ሰነድ ቅርጫቱ ውስጥ እንደሚያስገባ፤ ዊኪሊክስም እነዚህን መረጃዎችና ሰነዶችን እየሰበሰበ በዌብሳይቱ ይፋ እንደሚያደርግ በመናገር ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡ ዊኪሊክስ በየጊዜው ቅርጫት ውስጥ የሚያገኛቸውን ሰነዶች እያወጣ በኢንተርኔት የሚበትን ስለሆነ፤ ሰነዶቹ እውነተኛ ለመሆናቸው ምንም ማረጋገጫ የለውም የሚል ሃሳብ ተናግረዋል - የህትመት ዳሰሳዎች፡፡ ሆ... ጉድ ሳንሰማ መስከረም አይጠባ!
እስካሁን በይፋ የተለቀቁትንና ገና ይለቀቃሉ ተብለው የሚጠበቁትን ጨምሮ፤ 250ሺ ገደማ ሚስጥራዊ የአሜሪካ ሰነዶች በሙሉ፤ በዘፈቀደ የሆነ ተንኮለኛ ሰው የዊኪሊክስ ቅርጫት ውስጥ የጨመራቸው ኮተቶች ቢሆንስ? ዊኪሊክስ ሞኙ፤ ያገኘውን ሰነድ ሁሉ አፋፍሶ አለምን ይቀውጣል - የአሜሪካ ሚስጥራዊ ሰነዶችን አገኘሁ እያለ፡፡ የአለም መንግስታት፣ የአለም የሚዲያ ተቋማትና የአለም ህዝብም እየተስገበገቡና እየተንጫጩ ሰነዶቹን ማንበብ ተያይዘውታል - ጅልነታቸው ነው፡፡ እድሜ ለህትመት ዳሰሳዎች እንጂ፤ ይህንን መች እናውቅ ነበር?
ግንኮ፤ እነዚያ ሩብ ሚሊዮን ሰነዶች የኔ አይደሉም ብላ አሜሪካ አላስተባበለችም፡፡ ሰነዶቹ፤ በአለም ዙሪያ የሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎችና መስሪያ ቤቶች በሚስጥር የተለዋወጧቸው የመልእክት ሰነዶች አይደሉም ብሎ የአሜሪካ መንግስት አላስተባበለም፡፡ እንዲያውም፤ ሚስጥራዊ ሰነዶችን ሰርቆ በይፋ ማሰራጨት ወንጀል ነው በማለት ቁጣውን የገለፀው የአሜሪካ መንግስት፤ አመቱን ሙሉ ከዊኪሊክስ ጋር ሲወዛገብ አይተናል፡፡ ሰነዶቹና መረጃዎቹ የአሜሪካ መንግስት ንብረት እንደሆኑና በስርቆት መወሰዳቸው ወንጀል እንደሆነ የተናገሩት ሂላሪ ክሊንተን፤ ዊኪሊክስ ሰነዶቹን በይፋ ከማሰራጨት በመቆጠብ መልሶ ሊያስረክበን ይገባል በማለት ብዙ  ጊዜ ተናግረዋል፡፡ ሰነዶቹን ለዊኪሊክስ አሳልፎ ሰጥቷል የተባለ አንድ የአሜሪካ መንግስት ሰራተኛም፤ በወንጀል ተከሶ ታስሯል፡፡
ሰነዶቹ የተሰረቁበት ባለቤት፤ ስለሰነዶቹ እውነተኛነትና በዊኪሊክስ ስለመሰራጨታቸው ቀንና ሌሊት ቢናገርም፤ የአለም መንግስታትና ፖለቲከኞችም የአሜሪካ ዲፕሎማቶች ስለነሱ ምን ብለው ይፉ እንደነበር ለማወቅ ሰነዶቹን ሲያገላብጡ ቢከርሙም፤ እልፍ አለማቀፍ የሚዲያ ተቋማትና ምሁራን ሰነዶቹን ለመዘገብና ለመተንተን ቢረባረቡም፤ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሚስጥር ለማወቅ በመጓጓትም ሆነ ስለዘመናችን የፖለቲካ ውጥንቅጥ ለመገንዘብ ሰነዶቹን በማንበብ ቢጠመዱም ... ሞኝ በሏቸው፡፡ እኛ ብልጥ ነን፡፡ ሰነዶቹና ..ዊኪሊኪ.. ተአማኒነት እንደሌላቸው ህትመት ዳሰሳዎች ነግረውናል፡፡

 

Read 5494 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:57