Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 October 2011 13:07

|የየቅርባችንን ችግር ለመቅረፍ እንጣር´

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ለቤተሰቡ አራተኛ ልጅ ሲሆን በ1961 ዓ.ም በእንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ነው የተወለደው፡፡ በምህንድስና በዲፕሎም ተመርቋል፡፡ በአቢሲኒያ ሥነ ጥበብ ትምህርት ቤት ስዕል ተምሯል፡፡ ምህንድስናና ስዕሉን ጨምሮ ፈረንሳይኛ ቋንቋ በማስተማር ራሱን ያስተዳድራል፡፡ ከወዳደቁ ነገሮች የሰራቸው በመቶ የሚቆጠሩ የፈጠራ  አሉት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አግራሞትን የሚፈጥሩ የተለያዩ ነገሮችን ሰብስቧል፡፡ የአዲስ አድማሱ ፀሃፊ ብርሃኑ ሰሙ የዚህ ታሪክ ባለቤት ከሆነው አቶ በዕደ በቀለ ጋር አዲሱ ገበያ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ቆይታ
የወላጆችህ ሙያ ምንድነው?

አባቴ በስታቲስቲክስ ቢሮ እናቴ በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሁለቱም የመንግሥት ሠራተኞች ሆነው አገልግለዋል፡፡
የልጅነት ታሪክህ ምን ይመስላል?
ያው እንደማንኛውም ልጅ ነው፡፡ የተለዩ ዝንባሌዎቼን ተግባራዊ ማድረግ የጀመርኩት በልጅነቴ ነበር፡፡ ትምህርቴን ከጀማሪ አንስቶ እስከ 12ኛ ክፍል የተከታተልኩት በሊሴ ገ/ማርያም ነው፡፡ ማትሪክ ከተፈተንኩ በኋላ ቴክኒክና ከተማ ፕላን ኮሌጅ በመግባት ምህንድስናን ለ3 ዓመት ተምሬ ስጨርስ፣ በሙያው ላይ ተሰማርቼ ማገልገል የጀመርኩት አርባ ምንu በመሄድ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ አዲስ አበባ በመምጣት በማዘጋጃ ቤት ካርታ ክፍል ሰርቻለሁ፡፡ ክፍለ ከተሞች በአዲስ መልክ ሲደራጁ ቴክኒሽያን በመሆን አገልግያለሁ፡፡  የማዘጋጃ ቤቱን ሥራ ከተውኩ በኋላ በምህንድስናው፣ በስዕል ሙያዬና የፈረንሳይኛ ቋንቋን በማስጠናት በግሌ በመሥራት ላይ እገኛለሁ፡፡
ልዩ ዝንባሌዎች እንዳሉህ ሰምቻለሁ፡፡ ስለእነሱ ብትነግረኝ . . .?
ከወዳደቁ ነገሮች የምሰራቸው የፈጠራ ሥራዎች አሉ፡፡ ከእንስሳት ጋር በተያያዙ ያከናወንኳቸው ተግባሮች ሌላኛው ነው፡፡ ጥቃቅን ነፍሳትን ሰብስቤ በማድረቅ አስቀምጣለሁ፡፡ ቴምብሮች፣ ሣንቲሞች፣ የማስቲካ መጠቅለያዎች፣ ፊኛዎች እሰበስባለሁ፡፡ የተለያዩ አእዋፋትን ምስል የያዙ ፖስት ካርዶችም አሉኝ፡፡
እስቲ ስለ እንስሳቱ . . .
ሦስት ኤሊዎች ነበሩኝ፡፡ ከደብረ ዘይት ሁለት ጥንቸል አምጥቼ በማራባት 25 ደርሰው ነበር፡፡ ሁለት ጉጉቶች ነበሩኝ፡ ከአንድ ቦታ እስስት አግኝቼ አመጣሁ፡፡ እርጉዝ ስለነበረች 16 ወለደች፡፡ ጭላዳ ዝንጀሮም ነበረችኝ፡፡ እርግብና ዶሮም አረባ ነበር፡፡ እንቁላል ፋብሪካ የነበረው ቤታችንን ከተውን በኋላ በቦታ ጥበት ምክንያት እንስሳት መሰብሰቡን ትቼዋለሁ፡፡
እንስሳቱን የምትሰበስብበት ዓላማና ግብ ምን ነበር?
ነገሮችን ለማወቅ ካለኝ ፍላጎትና ያን ማድረጉ ስለሚያስደስተኝ ነበር፡፡ ብዙ ነገርም ተምሬባቸዋለሁ፡፡ ጉጉቶች በጣም ንቁዎች ናቸው፡፡ የሚያወጡት ድምጽ ማራኪ ነው፡፡ ዝንብ በሚበዛበት አካባቢ የዝንቦቹን ቁጥር ለመቀነስ እስስት ማርባት ይጠቅማል፡፡ እስስት ዝንብ ለመያዝ ምላሱን በርዝመትና በፍጥነት ሲጠቀም መመልከት በራሱ ያስገርማል፡፡
ብዙ ሰው እስስትን ይፈራል፡፡ ከእስስት ይልቅ ግን እንሽላሊት ንክሻዋ ከባድ ነው፡፡ እስስት ትንኝንም ይበላል፡፡ እስስትን በኦፕራሲዮን ያዋለድኩበት ጊዜም ነበር፡፡ በመጀመሪያ ያገኘኋት እስስት 16 ከወለደችልኝ በኋላ ወንድ እስስት አግኝቼ ስመጣ እንደገና አረገዘች፡፡ ስንት እንደምትወልድ ጉዷን አያለሁ ብዬ በመጠባበቅ ላይ ሳለሁ አንድ ቀን ጉንዳኖች ወረዋት ሞተች፡፡ ሆዷን ስቀደው 17 አርግዛ እንደነበር ማረጋገጥ ቻልኩ፡፡ 12ቱ ሲሞቱ አምስቱ በሕይወት ነበሩ፡፡ እነሱን ለማሳደግ ብዙ ለፍቻለሁ፡፡
ከሞተ እንስሳ ጋር በተያያዘ ሌላ ገጠመኝም አለኝ፡፡ አንድ ጓደኛዬ ጦጣ ነበረው፡፡ ጦጣዋ የሞተችበት ዕለት መጥቶ በሀዘን ነገረኝ፡፡ የቀበረበትን ቦታ አሳየኝና ቆፍሬ በማውጣት ቆዳዋን ገፍፌ መልሰን ቀበርናት፡፡ ቆዳዋን እንደ በግ ቆዳ በምስማር ወጥሬ አደረቅኩት፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ደግሞ ጦጣዋ የተቀበረችበትን ቦታ ቆፍሬ አጥንቷን አገኘሁ፡፡ አሁን ቆዳዋም አጥንቷም አለኝ፡፡
ዝንጀሮ ታማብኝ ለሕክምና ፓስተር የወሰድኩበት ጊዜ ነበር፡፡ ዶሮ ሳረባ ከተፈለፈሉት ጫጩቶች በጣም የደከሙትንና የሚሞቱ የመሰሉኝን በተለየ መልኩ ሙቀት እንዲያገኙ በማድረግ ሕይወታቸው ሲራዘም አይቻለሁ፡፡ በእንስሳቱ ዙሪያ እንዲህ ዓይነት ብዙ ነገሮችን ተምሬያለሁ፡፡ ያየሁትን አዲስ ነገር ጽፎ የማስቀመጥ ልምድም አለኝ፡፡
ጥቃቅን ነፍሳት አድርቀህ እንደምስታቀምጥ ሰምቻለሁ . . .
ይህን ሀሳብ የወሰድኩት ከወንድሜ ነው፡፡ ከአዲስ አበባና ከደብረ ዘይት የሰበሰብኳቸው 750 የሚደርሱ ጥቃቃን ነፍሳትን አድርቄ በተለያዩ ፍሬሞች አስቀምጫለሁ፡፡ እንደ እንስሳቱ ሁሉ ጥቃቅን ነፍሳቱም በአመጋገብ፣ በአረባብ፣ የየራሳቸው የሆነ መለያ አላቸው፡፡ ማታ፣ ጠዋት፣ በበጋ ወቅት፣ በክረምት ጊዜ፤ በረዶ ሲዘንብ ብቻ የሚታዩ ጥቃቅን ነፍሳት አሉ፡፡ በዚህ መልኩ የሰበሰብኳቸውን በአልኮል በማድረቅ ነው የስብስቤ አካል ያደረኳቸው፡፡
እስቲ ደግሞ ስለ ቴምብር፣ ሣንቲምና ማስቲካ ስብስብህ ንገረኝ . . .
3ሺህ የሚደርሱ ቴምብሮች አሉኝ፡፡ የሣንቲም ስብስቦቼ ያን ያህል ብዙ አይደሉም፡፡ 300 የሚደርሱ የተለያዩ ብራንዶች ያላቸው የማስቲካ ማሸጊያ ወረቀቶች አሉኝ፡፡ የአእዋፋትን ምስል የያዙት የፖስት ካርድ ስብስቦቼ ጥቂት ናቸው፡፡
ከወዳዳቁ ነገሮች የተሰሩ ወንበር፣ ጠረጴዛ፣ የራስጌ መብራት፣ የልብስ መስቀያ . . . የመሳሰሉ በርካታ ነገሮችን በቤትህ ውስጥ አያለሁ፡፡ በዚህ መልኩ የሰራኋቸው የፈጠራ ውጤቶች ስንት ይሆናሉ?
በትንሹ 100 የሚደርሱ ይመስለኛል፡፡ በሁለት ምክንያቶች ነው እነዚህን የምሰራው፡፡ አንደኛውና ቀዳሚው ሰዎች የሚቸገሩበትን ነገር ለመቅረፍ ሲሆን ሌላኛው እንደ መዝናኛና መደሰቻ ነው፡፡ ለችግሮች መፍትሔ ለማግኘት የሰራኋቸው የፈጠራ ሥራዎች ግን ይበዛሉ፡፡
ለምሳሌ ጣራ ላይ ወጥቼ ለምሰራው አንድ ሥራ ምላu ቢያስፈልገኝ ምላጩን በምን ይዤው ልውጣ? በኪሴ? በጥርሴ? በእጄ? ሁሉም አደጋ ያለው መሆኑን ሳይ ወገቡ ላይ በሚታሰር ቀበቶ ላይ ማግኔት በማኖር፣ ምላጩን እዚያ ላይ በማስቀመጥ በቀላሉ ወደ ጣራ መውጣት እንደሚቻል ታሰበኝና ሀሳቡን ወደ ፈጠራ ለወጥኩት፡፡
ሴቶች ቤት ውስጥ (ወንድም ሊሆን ይችላል) ከምድጃ ላይ ድስት ሲያወርዱ የድስቱን ጆሮ በጨርቅ ይይዛሉ፡፡ አተር አሹቀው፣ ፓስታ ቀቅለው ድስቱ ውስጥ ያለውን ውሃ የሚያንጠፈጥፉ ከሆነም ስቃይ በተሞላበት ሁኔታ እያነሱና እያስቀመጡ ነው የሚያንጠፈጥፉት፡፡ ይህን ችግር ማየቴ የድስቱን ሁለት ጆሮ፣ የክዳኑን እጀታ በአንድነት ይዞ ማንጠፍጠፍ በቀላሉ እንዲከናወን የሚያስችል የፈጠራ ሥራም አለኝ፡፡
የፈጠራ ሥራዎቼ ቀላል፣ ሳይንስን መሠረት ያደረጉና በአካባቢያችን ከሚገኙ ቁሳቁስ የተሰሩ ናቸው፡፡ እኔ ትምህርት ቤት እያለሁም ለሳይንስ ትምህርት ልዩ ፍቅር ነበረኝ፡፡ ችግር መፍቻ የሚሆኑት የፈጠራ ሥራዎቹን እንድሰራ ሳይንሳዊ ዕውቀቱም አስተዋጽኦ አድርጎልኛል፡፡
ምን ምን ሰርተሃል?
ቧንቧ ላይ የደቀንከው ባልዲ ውሃ ሲሞላ የሚጠራ አላርም፤ ቤት ውስጥም ይሁን ውጭ የለኮስነው ሻማ ሳይጠፋ መብራት የሚያስችለው ነፋስ መከላከያ ያለው የሻማ ማስቀመጫ፣ ቤት ውስጥ ወለል ላይ ውሃ ወይም ሌላ ፈሳሽ ቢፈስ በትንፋሽ በሚሳብ ቱቦ፣ በቀላሉና በፍጥነት መምጠጫ ዘይትና ጋዝ ከትልቅ በርሜል ወደ ትንሽ ጀሪካን በቀላሉ የሚያገላብጥ መሣሪያ፤ በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ ማብሰያ ምድጃ፤ የክብሪት እንጨት ሙሉ ለሙሉ እስኪነድ ድረስ ይዞ የሚያቆም መቆንጠጫ፤ በፀሐይ የሚሰራ የሻወር ቤት ውሃ ማሞቂያ . . . የመሳሰሉት ብዙ ናቸው፡፡  
እነዚህ ሥራዎችህን በሳይንስና ቴክኖሎጂ የማስመዝገብ ለሌሎችም እንዲደርስ የማድረግ ወይም በኤግዚቢሽን ለማሳየት ምን ያደረግኸው ጥረት አለ?
እስካሁን አንዳንድ ወዳጆቼ ቤት ሲመጡ ከሚያዩት ውu ምንም የተለየ እንቅስቃሴ አላደረኩም፡፡ በስዕል ኤግዚቢሽን የተሳተፍኩበት ጊዜ ግን አለ፡፡
የተቀመጥክበትን ወንበር የሚገዛ ቢመጣ በስንት ትሸጠዋለህ?
እነዚህን ወንበሮች ለመሥራት ስነሳ አባቴ |ገበያው ውስጥ አለልህ አይደለም፤ ለምን ከገበያ አትገዛም´ ብሎኝ ነበር፡፡ የገበያው እኔ ከሰራሁት በቅርጽም፣ በይዘቱም፣ በተሰራበት ቁሳቁስም፣ በዓይነቱ ልዩ ስለሆነ ምናልባትም በዓለም ላይ ብቸኛው ወንበር ስለሚሆን ዋጋ ማውጣቱ ያስቸግረኛል፡፡
ለማጠቃለያ የምታነሳው ሀሳብ ካለ . . .
በአገራችን የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ችግሮቹን ለመቅረፍ ሁሉም ሰው የየችሎታውን ቢያዋጣ ለውጥ ይመጣል፡፡ እኔ በቅርቤ ያየኋቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ስለጣርኩ ነው በመቶ የሚቆጠሩ የፈጠራ ሥራዎችን መሥራት የቻልኩት፡፡ ፈረንጆቹም የሚበልጡን ችግርን ለመቅረፍ ስለሚሰሩ ነው፡፡ የየቅርባችንን ችግር ለመቅረፍ እንጣር፡፡

 

Read 4373 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 13:10