Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 October 2011 13:11

ጥያቄዎች ሁሉ ለምን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ይንደረደራሉ?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ህይወታችን ..ሆረር..፤ ፊልማችን ..ኮሜዲ!..
መቼም እንኳንስ ለእንደኛ አገሩ ህዝብ ቀርቶ በዕድገት ለገሰገሱትም ሆነ በሃብት ለመጠቁት የዓለማችን ህዝቦችም ቢሆን አንዳንድ የማይፈቱ ችግሮችና እንቆቅልሾች አንዳንዴ አይጠፉም፡፡  የእኛን ትንሽ አሳሳቢ የሚያደርገው ኑሮአችን ሁሉ በችግሮችና በእንቆቅልሾች የተበተበ መሆኑ ነው - አንዳንዴ ሳይሆን ሁልጊዜ፡፡ እናም ሁሌም ጥያቄዎች አሉን - መልስ የሚሹ፡፡ ሁሌም ችግሮች እንደተጋረጡብን  ነው - መፍትሔ የሚፈልጉ፡፡ ሁሌም ..እንቆቅልሽ ምናውቅልሽ.. እንደተባባልን ነው፡፡ እንቆቅልሹን የሚፈታልን ግን የለም፡፡ የቱንም ያህል ስንጠያየቅ ብንውል እንቆቅልሻችን ሳይፈታ ነው የሚያድረው፡፡

የእንቆቅልሽ አገር ማለት ኢትዮጵያችን ናት፡፡ በእርግጥ እግዜሩ እኛን ብቻ መርጦ ጭንቅላት አልነሳንም፡፡ ለማሰብ ግን አልታደልንም፡፡ በአዕምሮአችን አላጌጥንበትም፡፡ እናም ችግሮች፣ ጥያቄዎች፣ እንቆቅልሾች ወዘተ ሲያጨናንቁን አስበን መፍትሄ ከመሻት ይልቅ የሚቀናን አቋራጭ መንገድ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ መሮጥ ይመስላል፡፡ በአካል ባንችል እንኳን በሃሳባችን መባዘናችን አይቀርም፡፡ እኔን አብዝቶ የሚያስገርመኝ ግን የእኛ ለትንሹም ለትልቁም ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ መንደርደር ብቻ አይደለም፡፡ የእሳቸው (yጠ/ሚኒስትሩ) አለመታከት ጭምር ነው፡፡ እኔ እሳቸውን ብሆን ግን (መቼም የምሆን አይመስለኝም!) አንድ ጠንከር ያለች ህግ አወጣ ነበር፡፡ (አፋኝ ህግ እኮ አይደለም፡፡) እንደው የሥራ ጫና የምትቀንስ ቀጠን ያለች መመሪያ ቢጤ ማለቴ ነው፡፡
ሆኖም ጠ/ሚኒስትሩን አይደለሁምና (እሳቸውን መሆን ይከብዳል!) ከዚህ ሀሉ ጣጣ ፈንጣጣ ተገላግያለሁ፡፡ ለነገሩ እሳቸውም እኮ የተለያዩ ችግሮችና እሮሮዎችን የመስማትና በተግባር ባይሆንም በአፋቸው ጊዜያዊ መፍትሄ (Pain killer ቢጤ) ማዘዝ ወይም መጠቆም ሳያስደስታቸው የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ይሄስ ባልከፋ ነበር፡፡ ችግሩ ግን ምን መሰላችሁ? ከ20 ዓመት የኢህአዴግ የሥልጣን ዘመን በኋላም ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ብቻ እየተምዘገዘጉ መሆናቸው ነው፡፡ እኔ የምለው ግን ጠ/ሚኒስትሩ የማይመለከታቸው ችግርና ጥያቄ የለም እንዴ? እኔስ አሁን የናፈቀኝ ጠ/ሚኒስትሩ የማይፈቱት ችግር ብቻ ነው፡፡  
አሁን ለምሳሌ በአሜሪካ የአገሪቱ ችግሮችና ጥያቄዎች ሁሉ የግድ ለኦባማ መድረስ አለባቸው እንዴ? ምን ማለት ፈልጌ መሰላችሁ? የሥራ ክፍፍል የሚባል ነገር የለም? ታዲያ ለምን እነዚያ ሁሉ መሥሪያ ቤቶች ተቋቋሙ? ከንቲባዎች፣  ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የተለያዩ አነስተኛ ሹማምንቶችስ ሥራቸው ምንድነው?  ጠ/ሚኒስትሩ አርቲስቶችን ያወያዩ ጊዜ የሆነውን አይታችኋል አይደል? ቆይ አሁን የጥበብ ቀን እንዲኖረን ለመጠየቅ ጠ/ሚኒስትሩ ያስፈልጋሉ? ይሄ ጥያቄ የመነጨው ደግሞ ከፈጠራ ሰዎቻችን መሆኑ ጉዳዩን ምፀት ያደርገዋል፡፡ ሴቶች በወንዶች የሚደርስባቸውን የሃይል ጥቃት በተመለከተም ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትሩ መፃፉን ሰምተናል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?  
የኮፒራይት ጉዳይ ለጠ/ ሚኒስትሩ፤ የሴቶች የሃይል ጥቃት ለጠ/ሚኒስትሩ\ የዩኒቨርስቲ መምህራን የመኖርያ ቤትና የመኪና ችግር ለጠ/ሚኒስትሩ (የትምህርት ጥራት እንኳን ቢሆን የአባት ነው) የፊልም ኢንዱስትሪው የተጋረጡበት ችግሮች ለጠ/ሚኒስትሩ\ የባልና ሚስት ጠብ ለጠ/ሚኒስትሩ\ የሃይማኖት መሪዎች ውዝግብ ለጠ/ሚኒስትሩ\ የታክሲ የቀጣና ስምሪት ችግር (አሁንም) ለጠ/ሚኒስትሩ\ የመብራት መቋረጥና የውሃ ችግር ለጠ/ሚኒስትሩ\ የስልክ ኔትዎርክ መጨናነቅ ለጠ/ሚኒስትሩ\ የአትሌቶች ድል ማጣት ለጠ/ሚኒስትሩ\ የንባብ ባህል አለመዳበር ችግር ለጠ/ሚኒስትሩ ወዘተ ... ወዘተ... ወዘተ...  አንዳንዴ ሳስበው እንኳንም ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ዘው ተብሎ የማይገባ ሆነ እንጂ ራሳቸው ጠ/ሚኒስትሩ ..ሥልጣን በቃኝ.. ብለው አገር ጥለው ይጠፉ ነበር፡፡ እንዴ እኛም እኮ ሲበዛ ይሉኝታ አጣን፡፡ ከእኛም የባሰ ይሉኝታ ያጡት ግን የጠ/ሚኒስትሩ ሹመኞች  ናቸው፡፡ ሥልጣንና ደሞዙን ብቻ እየበሉ ሥራውንና ሃላፊነቱን ወደ እሳቸው ብቻ  መግፋት ተገቢ ነው? ፈጣሪስ ይወደዋል? እሳቸው ዝም አሉ ተብሎ ከሃላፊነት መሸሽስ ተገቢ ነው እንዴ? በእርግጥ ጠ/ሚኒስትሩም ለዚህ ችግር ሙሉ በሙሉ ባይባልም በመጠኑም ቢሆን ተጠያቂ ይመስሉኛል፡፡ እንዴት በሉ... ሁሉን ነገር በየዋህነት መቀበላቸው ተገቢ አይደለማ! አንዳንዴ እንኳ |No! ሠርታችሁ ብሉ!.. ለምን አይሏቸውም? ለምሳሌ የዩኒቨርስቲ መምህራንን ባነጋገሩበት ወቅት ከቀረቡላቸው አያሌ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ..እኛ እኮ የምንፈልገው መጠለያና አንዲት ባለ አራት ጐማ ቆርቆሮ ብቻ ነው፤ እነዚህን ካገኘን ተረጋግተን እናስተምራለን.. የሚል ሲሆን መልስ የማያጡት ጠ/ሚኒስትሩ እንዲህ ብለው መለሱ አሉ ..ባለአራት ጐማ ባንችል እንኳን ባለሦስት ጐማ ቆርቆሮ እንፈልጋለን.. ይህችን የሰማ ሁሉ ገና ትንሽ ችግር ሲገጥመው በራሱ መንገድ መፍትሔ ከመሻት ወይም ሌላ የመንግስት መ/ቤትን ወይም  ሹማምንትን ደጅ ከመጥናት ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ መፃፍ እየቀለለው መጣ፡፡ ቆይ በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን የሃይል ጥቃት አስመልክቶ በሸራተን በተካሄደ ውይይት ላይ መቼ የሚመለከተው የመንግስት አካል ተገኘ? ለጠ/ሚኒስትሩ ግን ደብዳቤ ተፏል፡፡ አያችሁ ይሄ ዓይነቱ አካሄድ ለቀጣዩ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትርም መትረፉ አይቀርም፡፡ እናም እንደምንም ወግና ሥርዓት ቢይዝ ለሁላችንም የሚበጅ ይመስለኛል፡፡
እኔ በበኩሌ ለአገሩ እንደሚቆረቆር አንድ ዜጋ አንዲት ቀጠን ያለች ፕሮፖዛል ለማርቀቅ አስቤአለሁ፡፡ ለትንሹም ለትልቁም ብድግ እያሉ ለጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ መቸክቸክን የሚያስቀረው አዲስ ፕሮፖዛሌ ተግባራዊ ሲሆን ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ሳይሆን ወደየሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ያመራሉ፡፡ ይሄ ማለት ደግሞ ሁሉም ሹመኛ ሰርቶ ይበላል ማለት ነው፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም በሥራ ጫና ከሚመጣ ውጥረት (Stress) ይገላገላሉ የሚል ግምት ሳይሆን እምነት አለኝ፡፡
ጥያቄዎች ሁሉ ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ባያመሩ ምን እንደምንጠቀም ሳልነግራችሁ ወጌን ልቋጭ ነበር - በዝንጋታ፡፡ አያችሁ አንዳንድ ያልተገቡ ጥያቄዎችን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ከማምዘግዘግ ስንታቀብ፣ እሳቸው ለተገቡ ጥያቄዎች መልስ ለመሻት ፋታ ያገኛሉ፡፡ በጥሞና ለማሰብ እና የፈጠራ ችሎታቸውን ሙሉ አቅም ለመጠቀም በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ስለ ኢኮኖሚ ፖሊሲው፣ ስለ ዲሞክራሲ ሥርዓቱ፣ ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ፣ በኢህአዴጋውያን ስለተሞላው የህዝብ ፓርላማ፣ ነጋዴውን ስለሚያማርረው የግብር ሥርዓት፣ ስለሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ስለሥራ አጥነት፣ አንዴም እህል ቀምሶ ማደር ስለተሳነው ዜጋ፣ ስለኑሮ ውድነቱ ወዘተ የማሰብያ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ እኛ ፋታ ስንሰጣቸው እሳቸውም (እንደ መንግስት) የኑሮ ፋታ እናገኝ ዘንድ መላ መላውን ይዘይዱልናል!!
ወደ ቀጣዩ ወጌ ልውሰዳችሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ተዘግቦ ያነበብኩት አንድ ሰፊ ሪፖርታዥ ነው ለዚህ ወጌ መነሻ የሆነኝ፡፡
ባለፈው ሳምንት እዚሁ ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ሳነበው ያስደነገጠኝና በሃዘን ስሜት ውስጥ  የከተተኝ ዘገባ በሴቶቻችን ላይ ስለሚፈፀመው የሃይል ጥቃት በስፋት ያትታል፡፡ ይሄን ዘገባ ካነበብኩኝ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን እንዲህ የሚል ሃሳብ ወደ አዕምሮዬ ከተፍ አለብኝ፡፡ እነዚያ ሁሉ ሴቶች እንዲያ ያለ አሰቃቂ ጥቃት በገሃድ ከተፈፀመባቸው ለምንድነው ይሄንን እውነት የፊልሞቻችን ጭብጥ እያደረግን የማንሰራው ብዩ አሰብኩ፡፡ በእውነቱ እነዚህን ጉዳዮች የፊልሙ ጭብጥ አድርገን ጥሩ ድራማ ፊልም ብንሰራ ጥሩ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ቅንጣት አልጠራጠርም፡፡ በተለይ ፊልሙ በእንግሊዝኛ ከተሰራ ለኦስካር የማንታጭበት አንዳችም ምድራዊ ምክንያት አይኖርም (በኔ ይሁንባችሁ!) ችግሩን ግን ድራማ ብለን የሰራነውን የፊልም ዘርፍ ፈረንጆቹ Horror ነው ብለው ያስደነግጡናል፡፡ ምን ያድርጉ? ነገርዬው ያሰቅቃላ! እስቲ በጋዜጣው ላይ ከተዘገበው አንድ ሁለቱን አስፈሪና አሰቃቂ ትዕይንቶች (የሃይል ጥቃቶች) ላሳያችሁና እኔን ታዘቡኝ ወይም እመኑኝ፡፡
•    .....ድምፁን በወንድሟ ድምጽ ቀይሮ ወደ ውጭ ይጠራታል፡፡ በሩን ከፍታ ስትወጣ ሰልፈሪክ አሲድ ከፊቷ ጀምሮ በደረቷ እና በሰውነቷ ላይ ደፍቶባት በወደቀችበት ትቷት ይሄዳል.....
•    .....የምትኖርበት ቤት በመሄድ እጆቿን አስሮ ዓይኗን በስለት ወጋግቶ ካጠፋ በኋላ በአካላቷ ላይ ተጨማሪ ጉዳት አድርሶ፣ ራሷን ስታ በወደቀችበት ትቷት መሄዱ.....
•    ..ስማቸውን መግለጽ ያልተፈለገ ተጐጂ ከተጠርጣሪው ጋር በጋብቻ ኖረዋል፡፡  ልጆች ወልደዋል፡፡ በ2002 ዓ.ም ተጠርጣሪው ተጐጂዋ ላይ የፈላ ውሃ ደፍቶባቸዋል፡፡ ጉዳዩን ለማጣራት የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር በሄደበት ወቅት ከዓመት በፊት አፍንጫቸውን ቆርጠዋቸው እንደነበር  ተረድቷል.....
$r YBÝN! አይሰቀጥጥም? ይሄ ሁሉ እዚሁ አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ እኔ  መቼም ከዚህ የከፋ አሰቃቂ ድርጊት አላየሁም፡፡ አልሰማሁም፡፡ እንኳን በገሃዱ ዓለም በፊልምም ቢሆን፡፡ እኛ አገር ግን እንዲህ መሰሉ ድርጊት በየጓዳው ተደብቆ እንጂ ሞልቶ ተትረፍርፎናል፡፡ እንዴ የዕለት ተዕለት ህይወታችን አካል የሆነ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ እንዲህ መሰሉ የህይወት እውነታ በተንሰራፋበት አገር እየኖርን የምን ኮሜዲ ፊልሞች ላይ ብቻ መረባረብ ነው? የምን አስቂኝ የፍቅር ታሪክ ብቻ መስራት ... በጥናት እስኪረጋገጥ እንዲህ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ቢሆንም የፊልሙ ኢንዱስትሪ ያልጠነከረውና ወደ ላይ ያልተመነደገው የማናውቃቸው ጉዳዮች ላይ የሙጥኝ በማለታችን ሊሆን ይችላል የሚል መላምት አለኝ፡፡ ህይወታችን ሆረር፤ ፊልማችን ኮሜዲ በመሆኑ ማለቴ ነው፡፡ በሴቶች ላይ የሚፈፀመውን አሰቃቂ ጥቃት የመከላከል ዘመቻው እንደተጠበቀ ሆኖ ይሄንኑ ለጆሮና ለዓይን የሚያሰቅቅ እውነታችንን በፊልም ብንሰራው ጥሩ ይመስለኛል፡፡ በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ መማሪያ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡
አሁን ደግሞ ሰሞኑን ብልጭ ያለልኝን አንድ ..ሸላይ ሃሳብ.. ለምን አልነገራችሁም ወይም አላካፍላችሁም? (ተካፍሎ መብላት ባህላችን አልነበር እንዴ?) በእርግጥ የኑሮ ውድነቱ ይሄን የቆየ ኢትዮጵያዊ ባህል እየሸረሸረብን እንደሆነ አንዳንድ አገራዊ ጥናቶች እየጠቆሙ ነው፡፡ ይሄ የኑሮ ውድነት ምን ያላመጣብን ጣጣ አለ? እንኳንስ በየባሩ ድራፍት መገባበዝ ይቅርና በአውዳመት የተለመደውን የጐረቤት መጠራራት ሁሉ እያስቀረብን እንደሆነ በዓይናችን በብሌኑ እያየነው ነው - ከቀን ወደ ቀን ከመርገብ ይልቅ እየናረ ባለው የኑሮ ውድነት፡፡ በአሁኑ ጊዜ እኮ አብዛኛው ህዝብ የኑሮ ግሽበቱ ተጠቂ ስለመሆኑ ራሱ ኑሮው ይመሰክራል፡፡ (ኢኮኖሚው አድጓል የሚል yIMF   ስታቲስቲክስ አያስፈልገንም)
የኑሮ ኢንፍሌሽን ነገር - ዓለማችንን እያዛባብን እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጋላችሁ? በጣም  ቀላል ነው፡፡ እኔን ብቻ መመልከቱ አይበቃችሁም? አያችሁልኝ ምን ጀምሬላችሁ ምን እንደቀጠልኩ፡፡ ይሄም የኑሮ ግሽበቱ ውጤት ነው፡፡ ለማንኛውም ብልጭ አለልኝ ወዳልኳችሁ ..ሸላይ ሃሳቤ.. ልመልሳችሁ፡፡ እንግዲህ ከዘመኑ ጋር መዘመን የግድ አይደል. . .እናም ምን አሰብኩ መሰላችሁ? በ2003 ዓ.ም በጋዜጣው ላይ ያቀረብኳቸውን ፖለቲካዊ ወጐች በእናንተ በአንባብያን ማስገምገም፡፡ የማስገምገሙ ዋና ፋይዳ ምን እንደሆነ ልንገራችሁ? ዓመቱን ሙሉ ከወጡ ጽሑፎቼ 1ኛ የምትሉትን በመምረጥ ሽልማት መሸለም ነው፡፡ አንዳንዶች ለራሴው ጽሑፎች ራሴው ሽልማት ማሰቤ በጣም በጣም ሊያስገርማቸው ይችል ይሆናል፡፡ ግዴለም ይገረሙ፡፡ ምናልባት እኮ ምክንያቴን ሲያውቁ መገረማቸውን ያነሱ ይሆናል፡፡ የራሴን ጽሑፍ በአንባብያን አስገምግሜ ለመሸለም ያሰብኩት በኑሮ ግሽበቱ የተነሳ እንደሆነ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡  
አያችሁ! . . . ሁሉም በኑሮ ውድነት የተነሳ ወከባ ውስጥ ስለሆነ የእኔን ጽሑፎች አወዳድሮ የሚሸልም እንደማይገኝ ተገነዘብኩና ራሴን በራሴ ልሸልም ተነሳሁ (ችግር አለ እንዴ?) እናም እናንተ የተከበራችሁ አንባቢያን 1ኛ ደረጃ የሰጣችሁትን ወግ bSMS ..830.. ትልኩልኛላችሁ፡፡ የመላኪያው ዋጋ ደግሞ 3 ብር ብቻ ሲሆን እኔና ቴሌ ግማሽ ግማሽ ከገቢው እንካፈላለን፡፡ አይዞአችሁ ገቢው በሙስና ይመዘበራል የሚል ስጋት አይግባችሁ፡፡ ኦዲተሮች እቀጥራለሁ፡፡ ከዛም 50 ፐርሰንት ድርሻዬን እናንተ አንደኛ ደረጃ ለሰጣችሁት የፖለቲካ በፈገግታ ጽሑፍ እሸልማለሁ ማለት ነው፡፡ ልብ አድርጉ! የገንዘብ ሽልማቱ ለእኔ ሳይሆን ለጽሑፌ ነው፡፡ (ምነው ብልጥ ሆንኩባችሁ እንዴ?) ለነገሩ የተሻለ አማራጭ ካገኘሁ በጨረታው አልገደድም፡፡ እዚህ ጋ ግን በ830 አጭር መልዕክት አገልግሎት ለመጠቀም ለምን እንዳሰብኩ ባብራራ ደስ ይለኛል፡፡ ጥቅም ለማጋበስ አልሜና አቅጄ ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል (እኔ እንደ አንዳንድ ስግብግቦች የጥቅም ሰው አይደለሁም) ይልቁንም bSMS የመጠቀም ባህልን በአገሪቱ እንዲስፋፋ ለማድረግ ባለኝ አገራዊ ራዕይ የተነሳ ብቻ ነው ይሄን የማደርገው እንዴት ነው በሸቃችሁብኝ?

 

Read 4802 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 13:13