Saturday, 08 October 2011 09:24

ኑሯችንም ፊልማችንም “ሆረር” ከሆነ፣ ሁላችንም በአንድ ቀን ተሠደን አናልቅም?

Written by  ናርዶስ ጂ.
Rate this item
(0 votes)

ባሳለፍነው ሣምንት በዚሁ ጋዜጣ፣ አንድ ስማቸውን ያልገለፁ ፀሐፊ፣ “ዋናው ችግር የኑሮ ውድነት ሳይሆን፤ የፈጠራ ችሎታ እጦት ነው” በሚለው ፅሁፋቸው መራራ ኑሮዎችን ለመሸንገል በምንጠቀምባቸው የምር የኑሮ ስልታችን ላይ በመሣለቃቸው የተፈጠረብኝን “ንዴት” ገልጬ ነበር፡፡ በሚገርማችሁ ሁኔታ ግን እኚሁ ፀሐፊ ይሁኑ ሌላ ሰው ብቻ፣ “ዋናው ችግር የነፃነት መታፈን ሣይሆን፤ “የፈጠራ ችሎታ” እጦት ነው” በሚል ርዕስ ሣምንትም ተመሣሣይ ፅሁፍ ቀረበ፡፡ “ከልማታዊ መንግስታችን” እና  ከመራራ ኑሯችን ጋር ተስማምተን፣ ወስፋታችንን እያዳመጥን ስለ ነፃነታችን መታፈን አንድም ቀን ሣንጠይቅ መቀመጣችን እረፍት የነሣቸው አንዳንድ አልኩ ባይ ፀሐፊዎች፣ ያልበላንን ለማከክ የሚያደርጉትን ጥረት “ከመታዘብ” በቀር ምን ማድረግ ይቻለናል?

የእኚህ አላጋጭ አሽሙረኛ ፅሁፍ ሣያንሠን ደግሞ፣ አቶ ኤልያስ የተባሉት “የፖለቲካ በፈገግታ” አምድ ፀሐፊ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትራችን የተቆረቆሩና ያዘኑ መስለው፣ በተለየ “ብቃትና ስልት” አንድ ላይ ያከማቹትን ሥልጣናቸውን በታትነው መቅኖ እንዲያሣጡትና እንዲሸረሽሩት የሚያደርግ ምክር ለገሡ፡፡
አቶ ኤልያስ ኧረ ለመሆኑ፣ “ጥያቄዎች ሁሉ ለምን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ይንደረደራሉ?” እያሉ ክቡርነታቸዉን የሚያሣጣ ጥያቄ የሚያቀርቡት፣ እውነት ምላሹን አጥተውት ነው? አንድ ቦታ በተሠባሰበው ስልጣናቸው ቀንተው እንደሆነ እንጂ! ለነገሩ እርስዎ በቅናት ደበኑ፣ አሙና ምን ሊያመጡ ነው!? እስኪ እንግዲህ የሚሆኑትን እሰማለሁ ወይም አያለሁ! የምቀኛቸው ምላስ ይለምልም፣ ለፈጣሪያቸው ምስጋና ይግባውና ተዘርዝሮ የማያልቅ ስልጣን አላቸው፤ ለምሣሌ የሁሉም ሚኒስትሮች አለቃና ጠርናፊ እንዲሁም የሃገሪቱ እጣ ፈንታ አድራጊና ፈጣሪ ከመሆናቸዉ በላይ የህወሀት ዋና ሊቀመንበር፣  የኢህአዴግ ዋና ሊቀመንበር፣ የህወሀትና የኢህአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴዎች ሰብሳቢ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ . . . ናቸው፡፡ እንግዲህ ምን ያመጡ!?
እንደውም እንደ እርስዎ ያለ አጉል መካሪ አማክሯቸው፣ የጠነሠሡት የህዳሴው ግድብ፣ እንዲህ መላ የሃገሪቱን ህዝብ በአንድ እንዲነሣ የሚያደርግላቸው መሆኑን ገና ሣይሞክሩት እንኳ አጣድፈው፣ “”ለሚቀጥለው ምርጫ ስልጣኔን ለተተኪው አስረክባለሁ” እንዲሉ አደረጓቸው እንጂ፣ በህገ መንግስቱ ላይ የሃገሪቱ ርዕሰ ብሔር የስልጣን ዘመን ሢገደብ፣ የእርሣቸው አልተገደበምና በድርጅታቸው እስከተመረጡ ድረስ ያለ ገደብ በስልጣን ላይ መቆየት ይችላሉ፡፡ ቢያንስ የህዳሴውን ግድብ አስገንብተው እስኪያስጨርሱ ሥልጣን ላይ ይቆዩ ነበር፤ “ቃል የእምነት ዕዳ” ይሆንባቸዋል እንጂ! እናም እሣቸው ደከመኝ፣ ሥራው ውጥረት (Stress) ፈጠረብኝ ሣይሉ የእርሥዎ አጉል አዛኝ መሆን ምን ይባላል!? ቅቤ አንጓች!
ዜጎች ለሣቸው ያላቸዉን አድናቆት በመግለጽና “ኳሷ በሳቸው እግር ላይ እንዳለች” በመረዳት ጥያቄያቸውን እንዳያቀርቡ፣ አቶ ኤልያስ በፅሁፋቸው እንዲህም ብለዋል፤ “አያችሁ አንዳንድ ያልተገቡ ጥያቄዎችን ወደ ጠ/ሚኒስትሩ ቢሮ ከማምዘግዘግ ስንታቀብ፣ እሳቸው ለተገቡ ጥያቄዎች መልስ ለመሻት ፋታ ያገኛሉ በጥሞና ለማሰብና የፈጠራ ችሎታቸውን ሙሉ አቅም ለመጠቀም በቂ ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ስለ ኢኮኖሚ ፖሊሲው፣ ስለ ዲሞክራሲ ስርአቱ፣ ስለ ፖለቲካ ምህዳሩ፣ በኢህአዴጋውያን ስለተሞላው የህዝብ ፓርላማ፣ ነጋዴውን ስለሚያማርረው የግብር ሥርአት፣ ስለ ሸቀጦች ዋጋ መናር፣ ስለ ሥራ አጥነት፣ አንዴም እህልም ቀምሶ ማደር ስለተሳነው ዜጋ፣ ስለ ኑሮ ውድነቱ ወዘተ የማሰቢያ ጊዜ ያገኛሉ፡፡ እኛ ፋታ ስንሰጣቸው እሳቸውም (እንደ መንግስት) የኑሮ ፋታ እናገኝ ዘንድ መላ መላውን ይዘይዳሉ፡፡”  
ውድ አንባቢያን ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የአቶ ኤልያስን ፅሁፍ ልብ አላችሁ፡፡ በርግጥ እኔ እንደሳቸው አይደለሁም፤ በቅናት ተነሣሥቼ የሃገሪቱን ዋና ዋና ወቅታዊ ችግሮች ምንጥር አድርገው የማውጣት ብቃታቸውን ለማድነቅ አልሣሣም፡፡ ግን እኮ ይኼ ምፀተኛ ሸሟሪ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለነዚህ ለሃገሪቱ አንኳር ጥያቄዎች ማሰቢያ ጊዜ አልነበራቸውም ማለቱም ይሆን እንዴ? እንደተባለው ለነዚህ የህልውና ጥያቄዎች ማሰቢያ ጊዜ አጥሯቸው እስከ አሁን ካላዩዋቸውማ ጉድ ሆነናል በሉ! አቶ ኤልያስ እንዳሉት “በጥቃቅንና አነስተኛ” እየተደራጀን ልንፈታቸው የሚገቡ ጥቃቅን ጥያቄዎችን በነገር ዶሴ አጭቀን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካልተገኙ እያልን እንቧ ከረዩ ማለታችንን እናቁም! ካልሆነማ ለአንኳር ጥያቄዎቻችን ምላሽ የምናገኝበትን ጊዜ በገዛ ፈቃዳችን እያራዘምነው ነው!    
ለነገሩ አቶ ኤልያስ፣ ሌሎች ሚኒስትሮች ስልጣናቸዉን ሣይሠሩበት ቁጭ ብለው እየበሉ ነው በማለት ለጠ/ሚኒስትሩ ያዘኑላቸው መስለው፣ ስልጣናቸውን ለመከፋፈል ያደረጉት ሤራ መስሎኝ ነው እንጂ፣ እርግጥም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስንቱ ይሁኑ!? በዚህ የኑሮ ውድነት፣ እንኳን 80 ሚሊየን ህዝብ አንድ ብቻን ሆኖ ማስተዳደር ይቅርና አንድ ጐጆ መምራትም ከባድ ነው (“እንኳን ከሞቀ ስልጣን ላይ፣ ከሞቀ ምርቃና ላይ መነሣትም ይከብዳል” የሚሉትን የአንዳንድ ጥገኛ ባለሀብቶችን አባባል በፍፁም እቃወማለሁ!)፡፡
እስከ አሁን ያነሣሁት እግረ መንገዴን እንጂ፣ ከኤልያስ ጋር የተጋጨሁበት ዋና ሀሣብ ከአሁን በኋላ የማነሣው ነው፤ አቶ ኤልያስ በፅሁፋቸው፣ የሀገራችን ሴቶች በባሎቻቸውና በፍቅረኞቻቸው እየደረሠባቸው ያለው የአሲድ ቃጠሎና የመሣሠሉት ጥቃቶችን ከዘረዘሩ በኋላ፣ “እነዚህ ሁሉ ሴቶች እንዲያ ያለ አሰቃቂ ጥቃት በገሃድ ከተፈፀመባቸው ለምንድን ነው ይሄንን እውነት የፊልሞቻችን ጭብጥ እያደረግን የማንሰራው ብዬ አሰብኩ” ይላሉ፡፡ ቀጥለውም፣ “በጥናት እስኪረጋገጥ እንዲህ ነው ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ቢሆንም የፊልሙ ኢንዱስትሪ ያልተጠናከረውና ወደ ላይ ያልተመነደገው የማናውናቃቸው ጉዳዮች ላይ የሙጥኝ በማለታችን ሊሆን ይችላል የሚል መላምት አለኝ፡፡ ህይወታችን ሆረር፤ ፊልማችን ኮሜዲ በመሆኑ ማለቴ ነው” ይላሉ፡፡
አንባቢያን የአቶ ኤልያስን ሃሳብ ልብ አላችሁ፡፡ እንደ ኑሯችን ፊልማችንም ሆረር ይሁን እያሉን እኮ ነው! እንዴዬ! ለመሆኑ እነዚህ የዚህ ጋዜጣ ፀሐፍት ምንድን ነው ነገረ ሥራቸው? መራራ ኑሯችንን፣ እርሃባችንን፣ እርዛታችንን፣ የነፃነት እጦታችንን እኛ ችለን ለተቀመጥን እነሡን ምን እንዲህ አደረጋቸው?  
መራራ ኑሯችንን የምናሸንፍባቸው ስልቶቻችን ላይ እንዲህ የቃላት ሚሳይል የሚያዘንቡት ለምንድን ነው? እኛ ኮ ኑሯችን፣ ሥራችን፣ ማህበረ ፖለቲካዊ ህይወታችን “ሆረር” ሲሆኑብን ዝም ብለን አልተቀመጥንም፤ እድሜ ለልማታዊ መንግስታችንና ለልማታዊ ከያኒዎቻችን እንጂ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተን በብድር ካገኘነው ገንዘብም ቢሆን እየመነዘርን ሆረሩን ኑሯችንን እየሸሸን በየሲኒማ ቤቱ ኮሜዲ ፊልም በማየት እራሳችንን እናዝናናለን፡፡
አቶ ኤልያስ ታዲያ እርስዎ ምንዎት ተነካ? እድሜ ለልማታዊ መንግስታችን እንጂ፣ እርስዎ አላበደሩን መንግስታችን እያሳተመ በሚሰጠን ብር ኮሜዲ ፊልም ማየታችን ምንድን ነው ችግሩ!? የምንበደረው የሃገር ገንዘብ እያሳሰብዎት ከሆነ፣ ብዙ አይጨነቁ፡፡ ብድራችንን ተረጋግተን ሥናገኝ እንመልሳለን፡፡ እድሜ ለልማታዊ መንግስታችን እንጂ፣ የብር ኖት ችግር የለበትም፤ ባንመልስስ ደግሞ፤ የእኛስ የዜግነታችን ድርሻ አይደል?  የሃበሻ ባህሪ እኮ አይጠፋኝም፤ ሙስና መፈፀሙ፣ ተርቦ ማደሩ ወዘተ እኮ አያንጨረጭረውም፤ ባይሆን ሙስናውን እኔ ሰርቼው በነበር ወይም እነከሌ ለምን በልተው አደሩ ወዘተ ነው እረፍት የሚነሳው፤ እርስዎም የኮሜዲ ፊልም የሚያዩበት አጥተው ከሆነ፣ ሰበብና ግርግር ሳያበዙ እንደኛ ተደራጅተው ብድር ሊያገኙ ይችላሉ፡፡  ከዚያ ሆረር ኑሮዎ እንደ ክረምት ብጉንጅ እየጠዘጠዘ ሰላም ሲነሳዎ፣ ዘለው ፊልም ቤት ጥልቅ ነው፤ እርስዎም ለመግባት ያብቃዎት እንጂ ልማታዊ ከያኒያኑማ ኮሜዲ ፊልም ለማሳየት ዝግጁ ናቸው፡፡ ሆረር ከሆነ ማህበረ ፖለቲካዊ አውድ እንደመጡ ስለሚያውቁ፣ ችግርዎትን እያሰላሰሉ ከማበድዎት በፊት፣ መራራ ኑሮዎን ለደቂቃዎችም ቢሆን እረስተው አእምሮዎትን እንዲያዝናኑ “ኮሜዲ ፊልም” በማቅረብ “ልማት ተኮር ግዴታቸውን” ይወጣሉ፡፡ የፊልም ባለሙያዎቹማ ልጅ ይውጣላቸው! እነሡም እንደ ኑሯችን ፊልሙንም ሆረር ቢያደርጉት ኖሮ ምን ይውጠን ነበር!? ያው ሁላችንም በአንድ ቀን ሀገር ለቀን እንሰደድ እንደሆነ እንጂ! ከያኒያኑስ ቢሆኑ መራራው የኑሮ ውድነት ሲያንገፈግፈን፣ ከልማታዊው መንግስታችን ጋር እንዳንጋጭና ፀብ ውስጥ እንዳንገባ አእምሯችንን በኮሜዲ ፊልም አዝናንተው የተረጋጋ ሰላማዊ ህዝብ መፍጠር በመቻላቸው አይደል፣ “ልማታዊ ከያኒያን” በማለት መንግስታችን የሚያሞካሻቸው፡፡ ኑሮው ሆረር በሆነበት ህዝብ ኮሜዲ ፊልም እንዲመለከት ብር እስከ ማበደር መድረስማ ታላቅ ትራንስፎርሜሽናዊ አስተሳሰብ ነው፡፡ በነገራችን ላይ አቶ ኤልያስ፣ “ኪነጥበብ (ፊልምን ይጨምራል) የገሃዱ ዓለም ነፀብራቅ ነው” እያሉ የሚሰብኩ አንዳንድ ያልበሰሉ የኪነጥበብ ካድሬዎችን፣ ታዘቧቸው!?  አባባላቸውስ ምን ያህል ተዓማኒነት እንደሚጐድለው አስተዋሉ!? ለነገሩ ይኼ እንኳን አይጠፋዎትም፡፡ ባይሆን አሽሙርና ነገር አመል ሆኖብዎት እንደሆነ እንጂ፣ እዚህ ላይ መጠየቅ ካለብዎት፣ ህይወታችን “ሆረር” ሆኖ ሳለ ፊልማችን ለምን ኮሜዲ ሆነ የሚል መሆን አልነበረበትም!? ይልቅ፣ ለልማታዊ ከያኒዎቻችን ውርጅላሌ (ኦርጅናል ለማለት ሲሆን ነፍሱን ይማረውና ከታዋቂው የስነጽሑፍ ተመራማሪና መምህር ከብርሃኑ ገበየሁ ሥራ ተውሼ ነው) “ኮሜዲ ፊልም የመፍጠሪያ ጥበቡም ‹ሆረር› ሆነባቸው እንዴ፣ የማይደፍሩት አይነት ጥልቅ ጥበብ” የሚል መሪ የምርምር ጥያቄ ቢያነሱ ይሻል ነበር፡፡ በመጨረሻ፣ አንድ ነገር ላስታውስዎና ጽሑፌን (“እሮሮዬን”ም ሊባል ይችላል) ላብቃ፡፡ ቀደም ካለው ዘመን ምናልባት ከአገው ንግስቷ ከዮዲት ጉዲት (“እሳቷ” እያሉም የቤተክህነት ሰዎች ስሟን ያበጃጁታል) ጊዜ ጀምሮ፣ በርግጠኝነት ደግሞ ከ1960ዎቹ ጀምሮ፣ በሀገራችን ፖለቲካ “ሆረር” ሆኗል ማለት አይቻልም? እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ያልበሰሉ የየመንደራችን ለሆዱ አደር ካድሬዎች የፀረ ሽብርተኛ አዋጁን የመሳሰሉ እያጣቀሱ የዛሬው ፖለቲካ ነው “ሆረር” በማለት ከልማታዊ መንግስታችን ጋር ሊያጣሉኝ ይሞክሩ ይሆናል፡፡ ኢህአዴግ ግን “ሆደ ሰፊ” ነው፣ አይሰማቸውም እንጂ ለመሆኑ የእኛ ሀገር የገነተረ ሆረር ፖለቲካ፣ መቼ በፈገግታ የሚለዝብ ሆነና ነው “ፖለቲካ በፈገግታ” የሚሉት ብለን የምር ሳንጠይቅ፣ በዚች የሀበሻ አሽሙርዎና ምፀታዊ የፖለቲካ ሂስዎ እያማለሉ በየሣምንቱ ስናነብዎ፣ የደንበኝነታችን ትርፉ እንዲህ ሆረር ፊልም መጋበዝ ሆነ!? ምንም አይደለም! ሰሞኑን የደርግ ባለስልጣናትን የፈታው ኢህአዴግና እኔ ይቅር ባዮች ነንና ነገም የሚጽፉትን ማንበቤ አይቀርም፡፡ ግን እርስዎ ሆረሩን ፖለቲካ በፈገግታ አለዝበው እንደሚያቃምሱን ሁሉ፣ ልማታዊ ከያኒዎቻችንም ሆረሩን ኑሯችንን በኮሜዲ ፊልም እየቀየሩ እንዲያዝናኑን የክቡርነትዎን ፍቃድ እንዲያገኙ፣ እርስዎንም በማህበር አደራጅተን መለመን ይኖርብን ይሆን እንዴ? ለማንኛውም፣ ምፀታዊ የማህበረ ፖለቲካ ሂስዎትን እንፈልገዋለንና እኔም “ሆረር” ሆኘብዎት መጻፍዎትን እንዳያቆሙት አደራ

 

Read 3088 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:27