Saturday, 08 October 2011 10:37

አትሌቲክስ እየተሰደደ ነው

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(0 votes)

በ10 የተለያዩ አገራት ከ30 በላይ ኢትዮጵያውያን ዜግነት ቀይረው ይሮጣሉ
በባህሬን የጨመረው ስደት በእንግሊዝም ተባብሷል
ስደተኛ አትሌቶቹ ምርጥ ሰዓትና ሚኒማ ያላቸው ናቸው
ከምስራቅ አፍሪካ ተሰድደው በኤሽያ፤ በአውሮፓና በአሜሪካ ለሚገኙ አገራት ዜግነታቸውን በመቀየር የሚሮጡ አትሌቶች እየበዙ መጥተዋል፡፡ በተለይ በአትሌቲክስ ከመካከለኛ እስከ ረጅም ርቀት በሚደረጉ ውድድሮች የኬንያና የኢትዮጵያ አትሌቶች ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በላይ በአይኤ.ኤኤፍ ፈቃድ አግኝተው ዜግነታቸውን ወደ ሌላ አገር የቀየሩ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ብዛት ከ30 በላይ ሆነዋል፡፡ ኬንያውያኑ ደግሞ ከ40 በላይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ትውልድ ያላቸው አትሌቶች በተለያዩ 10 አገራት የሚገኙ ሲሆን ባህሬን፣ ቱርክ፣ እንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ቤልጄዬም፣ ሆላንድ አውስትራሊያ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ወደ ኳታርና ባህሬን ዜግነት የቀየሩ የአፍሪካ ቀንድ አትሌቶች እንደማበረታቻ ከ1ሺ እስከ 5ሺ ዶላር ወርሃዊ ደሞዝ እስከ ህይወት ዘመን መጨረሻቸው እንደሚታሰብላቸው ይነገራል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ወይም በሌሎች መድረኮች በሚያስመዘግቧቸው ውጤቶችም እስከ 200ሺ ዶላር እንደሚሸለሙ ይገለፃል፡፡ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ ወደ ባህሬን እና ቱርክ በብዛት እየፈለሱ ናቸው፡፡ ለስደታቸው ዋናው ምክንያት ደግሞ የሚያማልለው ገንዘብ ብቻ አይደለም፡፡ የውድድር እጦት፣ የአስተዳደር ድክመት፣ የመሠረተ ልማት አለመጠናከርና ሌሎች ሰው ሰራሽ ችግሮችም ይጠቀሳሉ፡፡
ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በዜግነት ዝውውር ኢትዮጵያዊቷ ዘነበች ቶላና ኬንያዊው ስቴፈን ቼረኖ ፈርቀዳጅ ሆነው ይነሳሉ፡፡ ዘነበች ቶላ ሆና ከአገሯ የተሰደደችው ማርያም የሱፍ ጀማል  በሁለት የዓለም ሻምፒዮናዎች ለባህሬን ሁለት የወርቅ ሜዳልያዎችን  ያስመዘገበች ከመሆኑም በላይ ከ5 በላይ ክብረወሰኖችን በባህሬን አትሌቲክስ ያስመዘገበች ናት፡፡ የማርያም ሪኮርዶች በባህሬን በ800፤ በ1500፤ በማይል፤ በ2000ሜ፤ በ3000ሜ፤ በ5000ሜ የተመዘገቡ ናቸው፡፡ በሶስት ሺ መሰናክል የዓለም ሻምፒዮን የሆነውና ሪኮርድ የያዘው ኬንያዊው ስቴፈን ቼሮኖ አሁን ሳሊፍ ሰይድ በሚል ስሙ ለኳታር  አትሌቲክስ ታሪክ ሰርቷል፡፡  ከማርያምና ከሳሊፍ ወዲህ ከ70 በላይ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ዜግነት ቀይረዋል፡፡
ባለፉት 3 ዓመታት ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን ዜግነት በማስቀየር ትኩረት የሰጠችው ቱርክ ናት፡፡ ባልተጠበቀ ሁኔታም ወደ እንግሊዝ፤ አውስትራሊያና አሜሪካም የሯጮች ኩብለላ ተጠናክሯል፡፡
ባለፈው ዓመት አይኤኤኤፍ ወደ ሃብታም አገራት ዜግነት ቀይረው የሚዛወሩ አትሌቶችን ለመቆጣጠር የነበረውን ህግ ማስተካከያ አድርጎበታል፡፡ አንድ አትሌት ዜግነቱን ለቀየረለት አገር ለመሮጥ በትውልዱ አገሩ ውክልና ካደረገው የመጨረሻ ውድድር ከ3 ዓመታት በኋላ እንዲሆን ደንግጓል፡፡ በዝውውሩ ላይ የአገራቱ ፌደሬሽኖች በሚያደርጉት ስምምነት የመሮጥ ፈቃዱ በ1 ዓመት ሊያጥር ይችላል፡፡
ዜግነታቸውን የቀየሩ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች አንዳንዴ በአስገዳጅ ሁኔታዎች ወይም በሌላ ምክንያት ስማቸውን ይለውጣሉ፡፡ ስማቸውን ሳይቀይሩ በሌላ አገር ዜግነት የሚሮጡ  አትሌቶችም ብዙ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ አትሌቶች በዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች ዜግነታቸውን ከቀይሩ በኋላ በአዲሱ አገራቸው ዜግነት መወዳደር የሚችሉበትን የጊዜ ገደብ በመጨረስ ህጋዊ ዕውቅና አግኝተው ከ1990ዎቹ መጨረሻ ወዲህ እየሰሩ ናቸው፡፡ ከ2013 እ.ኤ.አ ጀምሮ ለሌላ አገር ዜግነታቸውን ቀይረው ለመሮጥ ማረጋገጫ ያላቸውም ይገኙበታል፡፡
ከሌሎች አገራት ውጤታማ  አትሌቶችን ዜግነት በመስጠት  ዋና ተዋናይ ከሆኑ አገራት ኳታርና ባህሬን ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡ ከአውሮፓ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፤ ፊንላንድ፣ ከሰሜን አሜሪካ ካናዳና አሜሪካ እንዲሁም አውስትራሊያ በዚሁ የአትሌቶች ዝውውር ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡ ዜግነት በቀየሩ አትሌቶች ስፖርቱን በማስተዳደር  ፈርቀዳጅ ሆና የምትጠቀሰው አገር ኳታር  ናት፡፡ የኳታር አትሌቲክስ አስተዳደር ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቶችን ለማደን በሚያደርጉት እንቅስቃሴ መልማይ ማናጀሮችና አሰልጣኞችን በተደራጀ ኔትዎርክ በመላው ዓለም አሰማርተዋል፡፡ የአትሌቲክስ የልምምድ ማዕከላትንም በሞሮኮ፣ በብራዚል፣ በደቡብ አፍሪካና በአሜሪካ በማቋቋምም እየተሰራ ነው፡፡
በህገወጥ የአትለቶች ዝውውር ብቻ ሳይሆን በህጋዊ ሁኔታ የአይ ኤ ኤፍ ዕውቅና አግኝተው ወደ ገልፍ አገራት፣ ወደ አውሮፓና ወደተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚሰደዱ አትሌቶች ብዛት በተለይ ከ2000 እ.ኤ.አ የሲድኒ ኦሎምፒክ ወዲህ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል፡፡ በየዓመቱ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ከ20 በላይ አትሌቶች ዜግነት ለመቀየር ለአይኤኤ ኤፍ ያመለክታሉ፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ የኬንያና የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው አትሌቶች ብቻ ሳይሆኑ ኡጋንዳዊ፣ ታንዛንያዊና ብሩንዳዊ ዜግነት ያላቸውም በተመሳሳይ አቅጣጫ ገብተዋል፡፡
አትሌቶች ለሌላ አገር ዜግነት ቀይረው መወዳደራቸው  በዓለም የአትሌቲክስ ስፖርት  ዛሬም ድረስ አከራካሪ ጉዳይ ነው፡፡ከኢትዮጵያ ሆነ ከኬንያ ዜግነታቸውን የቀየሩ አትሌቶች ለዓለም ሻምፒዮና ወይም ለኦሎምፒክ ተወዳዳሪነት የሚያበቃ ሚኒማ  የሚያሟሉና  በየውድድር ዘመኑ የምርጥ ሰአት ደረጃ የሚሰለፉ መሆናቸው በየአገራቱ የአትሌቲክስ እንቅስቃሴ ላይ ጠባሳ እያሳረፈ ነው፡፡ በሌላ በኩል በግን ዓለም ሻምፒዮናው ለእንግሊዝ  በአምስት ሺ የወርቅ ሜዳልያ ለወሰደው ሶማሊያዊው ሞፋራህና በአሜሪካዊው በርናንድ ላጋት ተቀናቃዕነት ለታዘበ ሁለቱ ታላላቅ አገራት በአትሌቲክስ ስፖርት ያላቸውን ትኩረት ስለሚያመለክት ሊደገፍም ይችላል፡፡ዜግነት ቀይረው ለሌላ አገር የሚሮጡ አትሌቶች ለስደታቸው ዋናው ምክንያት  የገቢ ተጠቃሚነት ቢሆንም በየአገራቱ ያለው አትሌቲክስ አስተዳደርና እድገትም አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡  የስፖርት ውድድሮች ከአገር ውክልና ባሻገር በብቃት የሚደረጉ ፉክክሮችን እየጠየቁ መምጣታቸውንም አንዳንድ ባለሙያዎች በአዎንታዊነት ያነሳሉ፡፡ አንዳንድ ስፖርት አፍቃሪዎች ደግሞ ለሌላ አገር ዜግነት ቀይረው በተሳካላቸው አትሌቶች ውጤታማነት  ይደሰታሉ፡፡ አንዳንዶች ግን የአትሌቲክስ ስፖርት ዜግነት በሚቀየሩ አትሌቶች ተሞልቶ ውድድሮች በተመሳሳይ ትውልድ ባላቸው ምርጥ አትሌቶች የበላይነት መቀጠሉን ሊያባብስ መቻሉ ያሳስባቸዋል፡፡በዓለም ሻምፒዮና ወይም በኦሎምፒክ መድረክ በተለይ በ3ሺ መሰናክል ውድድር እንዲህም በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናዎች የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ብቻ የተሰለፉበት ውድድር እንዳይካሄድ ሰግተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት አይኤኤኤፍ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን በሁለት ዓመት አንዴ እንዲካሄድ ሲወስን ዋናው ምክንያት በየአገር አቋራጭ ሻምፒዮናው የኬንያና የኢትዮያ አትሌቶች የበላይነት መብዛቱ የሌሎች አገራት ውክልና አደብዝዟል ብሎ ነበር፡፡ ዜግነት በቀየሩ አትሌቶቻቸው አንዳንድ አገራት በዚሁ በአገር አቋራጭ ሻምፒዮናና በሌሎች የአይኤኤፍ ውድድሮች መብዛታቸው ግን ይህንኑ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የውጤት የበላይነት ማባባሱን ቀጥሏል፡፡ አትሌቶች ለገንዘብ ብለው በሌላ አገር ባንዲራ መወዳደራቸው የስፖርቱን ስነምግባር ማጉደፍ ነው ብለው የሚቃወሙም አሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ ማንም ሰው ዜግነቱን የመቀየር መብት አለው ማለቱ ግን አትሌቶችንም ይጨምራል፡፡ የኬንያ  አትሌቲክስ ፌደሬሽንና አንጋፋ አትሌቶች በአገሪቱ ዜጐች ወደ የገልፍ አገራት ስደት ደስተኞች አይደሉም፡፡ የዝውውሩ ህገወጥ ደላሎች በዕድሜያቸው ገና የሆኑ አትሌቶችን ወደ አረብ አገራት ማስኮብለላቸውና አሰልጣኞች በደላልነት አብረው መስራታቸውም ከፍተኛ ትችት እያስከተለ ይገኛል፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ኃላፊ የሆኑት ኢሳያህ ኪፕላጋት ባንድ ወቅት  ታዳጊ ወጣቶችን ከት/ቤት በማስኮብለል የሚሰሩ ህገወጥ የዝውውር ደላሎችን ሲያወግዙ ህፃናቱን ዜግነት ቀይረዋል ከማለት ይልቅ ስደተኞች ሆነዋል በሚል ተማርረው ነበር፡፡ ወደ ኳታርና ባህሬን አገራት የተዛወሩ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በአገራቱ ለአትሌቲክስ ምቹ የሆነ አየር ንብረት ባለመኖሩ የውድድር ዝግጅታቸውን በትውልድ ምድራቸው ለመስራት መገደዳቸው አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ሲከታቸውም አጋጥሟል፡፡ አንዳንድ ጠንካራ አትሌቶች ዜግነታቸውን ከቀየሩላቸው አገራት በቦነስ ክፍያ፣ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች አለመከፈልና በልዩ ልዩ አገልግሎቶች እጦት መቸገራቸውም ይነገራል፡፡ ዜግነታቸውን በመቀየር ለሌሎች አገራት የሚወዳደሩ አትሌቶች ባንዳንድ መገናኛ ብዙሐናትና የስፖርቱ ደጋፊዎች አገርን የከዱ ወይም የሸጡ ተብለው ከፍተኛ ውግዘት ይደርስባቸዋል፡፡ ዜግነታቸውን በቀየሩበት አገራት አንዳንድ ችግር ገጥሟቸው ወደ ሀገራቸው ዜግነት ለመመለስ ያመለከቱ ትኩረት ማጣታቸው ከዚሁ ቁጣ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ ስደተኛ አትሌቶች

በ1984 እ.ኤ.አ
ቢሊሱማ ሱፔ  ወደ ባህሬን
ደጀኔ ረጋሣ ወደ  ባህሬን
አላፍ ቢምሮ ወደ እስራኤል
በ1991 እ.ኤ.አ
ሰጠኝ አበበ ወደ እስራኤል
ዋደሬ ሃቭዳያ ወደ እስራኤል  
በ1998 እ.ኤ.አ
ኤልባን አብይ ለገሰ ወደ ቱርክ
ተክዬ ገ/ስላሴ ወደ ሆላንድ
ኡዜሪዬተ ታምራት ወደ ቱርክ
ሱርኬሊ ትዝታ ወደ ቱርክ
ደጀኔ ብርሃን ወደ ታላቋ ብሪታኒያ
በ1999 እ.ኤ.አ
ሚዛን መሃሪ ወደ አውስትራሊያ
በ2001 እ.ኤ.አ
ካሣ ታደሰ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ
ኤርባህ ሙስተፋ ወደ ጣሊያን
በዛብህ ሲሳይ ወደ አውስትራሊያ
በ2003 እ.ኤ.አ
ባደር ካህሊል ባደር ወደ ባህሬን
ሳሌዝ ማርኩት ወደ ባህሬን
በ2004 እ.ኤ.አ
ዘነበች ቶላ ወይም ማርያም
ዮሴፍ ጀማል ወደ ባህሬን
ራሺድ ኬ ጀማል ወደ ባህሬን
ኤድሪስ ከማል ኢዬሳ ወደ ባህሬን
ያሬድ ሸጉሞ ወደ ፖላንድ
በ2005 እ.ኤ.አ
ገርነሺ ታምራት ወደ ታላቋ ብሪታኒያ
በ2006 እ.ኤ.አ
ቶማስ አብዩ ወደ ታላቋ ብሪታኒያ
በ2008 እ.ኤ.አ
አለማየሁ በዛብህ ወደ ስፔን
ሰለሚ ባይራክ ወደ ቱርክ
ሱልጣን ሃይደር ወደ ቱርክ
የሺጥላ በቀለ ወደ ቤልጅየም
በ2010 እ.ኤ.አ
ማዲና ከድር ወደ ዩናይትድ
አረብ ኢምሬትስ
ማርያን አብዱልሃ ሙባረክ ወደ          ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ

 

Read 3796 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:40