ታላቁ ሩጫ ከ10 ዓመት በፊት ሲጀመር የመሮጫ ቲሸርቱን ለመሸጥ አንድ ወርና ከዚያም በላይ ጊዜ ይወስድ እንደነበር የሚያስታውሱት የውድድሩ አዘጋጆች በየዓመቱ ይሄው የምዝገባ ጊዜ እየቀነሰ መሄዱን አመልክተዋል፡፡ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች በ10 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው በብቃት ለመሳተፍ ከመካሄጃው ቀን 6 ሳምንት ቀደም ብሎ መዘጋጀት የሚኖርባቸው ሲሆን ከዛሬ መጀመር አለባቸው፡፡ ጀታላቁ ሩጫ በኢትዮያ ኦፊሴላዊ ድረገፅ ላይ በቀረቡ መረጃዎች ለልምምዳቸው ጠቃሚ ምክር እንደሚያገኙ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ታላቁ ሩጫ በኢትዮያ ከተባበሩት መንግስታት ጋር በመተባበር” በ2011 ለህፃናት እሮጣለሁ” በሚል መርህ በሚያደርገው ዘመቻ 1 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ እስካሁን 509ሺ ብር ማግኘቱ ታውቋል፡፡ ይህንኑ የገቢ ማሰባሰብ ዘመቻ ለ6 አመታት ከ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫው ጋር በማያያዝ አከናውኖ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ለግብረሰናይ ድርጅቶች ለግሷል፡፡ አምና በ9ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮፕያ በተመሳሳይ ዘመቻ 808778 ብር ተሰብስቦ ለሜሪ ጆይና ለአበበች ጎበና የበጎ አድራጎት ተቋማት መበርከቱ ይታወሳል፡፡በተያያዘ ዜና ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከኮካኮላ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው የ7 ኪሎሜትር ተከታታይ የጐዳና ላይ ሩጫ 2ኛው ሂደት በነገው እለት ይቀጥላል፡፡ 3ሺ ተሳታፊዎች ያሉት ይህ ውድድር ማይክሮቺፕ በተገጠመላቸው የመሮጫ ጫማዎች መደረጉ ልዩ ያደርገዋል፡፡ በመጀመርያው ውድድር ተሳታፊ የሆኑ አትሌቶች 7 ኪሎ ሜትሩን የገቡበትን ሰዓት ከታላቁ ሩጫ በኢትዮያ ኦፊሴላዊ ድረገፅ በማግኘት በነገው ተሳትፎ መቅረብ መቻላቸው የተሻለ ሰዓት ለማስመዝገብ ይረዳቸዋል ብለዋል የውድድሩ አዘጋጆች፡፡