Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 22 October 2011 10:52

በሂደት መገንባት፤ በሂደት ማፍረስ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የአገር ጉዳይ ነው እየተባሉ በየሥፍራው የጥፋት ስንቃቸውን ይዘው የሚዞሩት የመረዳት ችሎታ የሌላቸው ስለሆኑ ነው ወይንስ የሀሰት ንድፈ ሀሣብ ሰለባ በመሆናቸው ነው? ዛሬ ሥርዓቱ ራሱ ተኩሶ የተተኮሰበት ይቅርታ እንዲጠይቀው የሚሻ ነው፡፡
መገንባት እና ማፍረስ ተፈጥሯዊ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ሊያፈርሱ ተነስቶ መፍረስ እንዳለ ሁሉ ለመገንባት ተዘጋጅቶ ወደ ማፍረስ አዙሪት መመለስም አለ፡፡

አገር እንደ እውነቱ በጥቂት ጊዜያት አትገነባም፡፡ የመንገዱ የትነት በውል ሳይለይ እና የሚመከለታቸው ሁሉ ሳይመክሩበት በቁጥር ጥቂት የሆኑ፣ ሁሉን በአምሳያችን እንፍጠር ባዮች በወሰኑት መንደፋደፍ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡
የግንባታ አስተሳሰብ አዎንታዊ ነው፡፡ መሆንም አለበት፡፡ አገር አፍርሶ በሌላ መንገድ ልንገባ ብሎ መነሳት የረዥም ዘመን አሰላሳይነትን የሚፈልግ ብቻ ሳይሆን በአገር ስም ከመንገድ ውጪ የህዝቡን አፋዊ ዝንባሌ በመተው ህሊናዊ አቋሙን ማጥናት እና ለአንድነት ምሰሶ እንዲመች ማድረግ ከሩቅ ዘመን ግብ አንፃር ግዴታ ነው፡፡
የተቆራረሰ አገር ለገዢው ጭቆና ከሚመች በቀር፣ የዚህ ልምድ ተፅዕኖ በተለያዩ ቤተሰቦች፣ ግለሰቦች እና ፓርቲዎች ላይ በይዘት ልዩነት በሌለው መልኩ ተመሳሳዩን የመፈፀም “ዕውቀት” በተግባር ያሳየ ከመሆኑም በላይ፣ እንደ አገሪቱ የተበታተነን አቅም ይዞ የፈለጉትን ተፅዕኖ ለማድረግና ለመምራት መንገድ ይሆናል፡፡
በትዕዛዝ መገንባትና ማፍረስ፣ ሥርዓትና ደምብ ያልተዘረጋለት ከመሆኑም በላይ በርካታ የጥፋት ሥራዎችን ለማባዛት ያመቻል፡፡ የግል ውሣኔን የሕግና የሥርዓት ፈቃድ አድርጐ ለማቅረብ ዕድል ይሠጣል፡፡
በሂደት አገርም ሆነ ግለሰብ ይገነባል፡፡ በምን ሃሣብ እና ከነማን ጋር ተኹኖ ነው የሚገነባው? በአገር ግንባታ እና እመርታ የማይደሰት ካለ በራሱ ሕይወት ላይ ለውጥ ሳይመለከት ለመኖር የወሰነ ሊሆን ይችላል፡፡
የራስን ሕይወት ከጤናማው ሥርዓት ውጪ በሆነ መንገድ የሚገነቡ ግለሰቦች፣ ይህን ትችት ላለማስማት የሚችሉትን እንቅፋት ሁሉ ሊዘረጉ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡ ይህን እረፍት ማጣት በድጋፍ ሊያሽሞነሙን የፈለገ ሥርዓት የሚገነባው ይዘትና ርቀቱ ያልጣማቸውን ወደዚህ ተፅዕኖ እንዲገቡ የተለያዩ የፍልፈል ጉድጓዶች ሊምስላቸው እንደሚችል አዲስ ዕውቀት አይደለም፡፡
ራሱንም ሆነ ኅብረተሰቡን መገንባት የፈለገበት አቅጣጫ ከሚሸከመው በላይ በጉድለቶች የተሞላ ስለመሆኑ የሚያረጋግጡለት ቢኖሩም፣ የወደፊቱን በመስጋት በዘረጋው መዋቅር እና መሪ ትዕዛዝ አንዳንዴም መሀሉ ከሚገኙት የተወሰኑ ጤናማ አስተሳሰብ ካላቸው ሰዎች በመሰወር የተለመደውን ሥልታዊ ጫና ማካሄድን ይመርጣል፡፡
የአገሪቱ ዜጐች ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን መገንባት የሚችሉት እያፈረሱ እንዲሆን ከተፈለገ፣ አንድ ነገር እንዳለ ያመለክታል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህ ድርጊት ተባበሩን ማለት ግን የሚፈልጉትን የሚያገኙበትን መንገድ አለማወቅ ብቻ አይደለም፡፡ ብዙ ነገር ማለት ነው፡፡
ሥርዓቱ ከሚበትነው የአገሪቱ ሀብት ይልቅ ለገንቢ ነፃነት ቀናዒ ቢሆን ኖሮ ከሚያዘጋጀው አጉል ሀብት በላይ በውድድር ሠርቶ ማግኘት ይቻላል፡፡ የሀብት ክፍፍሉ በማዕከላዊነት መከማቸት የኃላፊነት ስሜትን አይፈጥርም፡፡ በፉክክር ሳይሆን በውድድር የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ዋስትና ያለው ሕይወት መኖር ቢችሉ ኖሮ አገሪቱ በመልካም ጐኑ የሚገመት የለውጥ መስመር ሊኖራት በቻለ ነበር፡፡
በዚህ መንገድ አገርን የመገንባት ተልዕኮ እና “ራስን የመገንባት ሚስጥር” የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች አይደሉም፡፡ የኋለኛውን በድፍረት ፊት ለፊት የሚያቀርቡት ካለመሆኑም በላይ የሰላምና የልማት መድህን አለመሆኑን እያወቁ የሚኖሩበት ነው፡፡
በርካታ የሰለጠኑ አገራት ሀብትና እውቀታቸውን በሥርዓቱ ሊጠቀሙ በመቻላቸው፣ “ለሁሉም” አመቺ የሆነ ዲሞክራሲያዊ መዋቅርና ሥርዓት በመዘርጋታቸው የተመቻቸ ኑሮ ባለቤት ናቸው፡፡
የገነቡ መስሎ ከማፍረስ አባዜ አለመላቀቅ፣ የጥፋት ዓይነቶች በተለያዩ መንገዶች ሲገለፁ ማሾፍ ለራሱ ለባለቤቱ የተጠቀመ እስኪመስል ድረስ ጥርጣሬን ይዘራል፡፡
የአገሪቱን “የቅኔ ዘረፋ” አካሄድ በተለየ ሁኔታ መረዳት ለቻለ የግንባታው “ቅኔ” ይገለፅለታል፡፡ ለዚህ “ቅኔ ዘረፋ” አለመተባበር የፈለገ መብቱ ነው፡፡ የሚዘጋጁበትን እንዲደገፍ ለማድረግ በሁለትዮሽ የሚፈፀም የመሰለው ግፊት የራሱን ሰዎች ሲያገኝ እንጂ አነሳስና ሂደቱን መረዳት ለቻለ፣ የስየራ ጉንጐናውን ላወቀ ነገርዬው እምብዛም አይናፍቀውም የሚያሽከረክሩትን “ጐማ” ማወቅ ከብዙ አጓጉል ያድናል፡፡
የገዢም ሆነ የተቃዋሚ አባል የቆመበት ጥግ ሳይሆን መመዘን ያለበት በይፋና በከለላ የሚሰራው ወንጀል ነው፡፡ በዚህ መንገድ ደግሞ የሚገነባ መልካም ነገር የለም፡፡ የሚፈርስ ግን ሞልቷል፡፡ በረዥም ጊዜ የቤትና የውጭ ጫና ወደ ራስም ሆነ ወደ ተቃራኒ ገፍቶ የማስገባት የአምባገነንነት ጥረት አይሳካም፡፡ ትችቱ ግን እንደ አስፈላጊነቱ ይቀጥላል፡፡
ያለፉት ሥርዓቶች አገሪቱን በመገንባት እና በማፍረስ ዕርምጃው የሠሩት ስህተት አለ ብሎ የተነሳ መንግስት፤ መጪ ሥርዓቶች እንዲያርሙለት የሚያነሳሳ ሥህተት መስራት ለምን ፈለገ? ባንድ በኩል ከሚሰራቸው መካከል የማፍረስ ተፅዕኖውን እያሳረፈ፣ በሌላ በኩል ለሌሎች ተመሳሳዩን ለማቆየት መወሰኑ የገባበት ወጥመድ መኖሩን ያመለክታል፡፡ ከግንባታ ይልቅ ጣፎርዴነት እየተስፋፋ ስለመምጣቱ፣ ጭራው የጠፋቸው አንዳንድ ተቋማት እና ባለሟሎቻቸው ከሚፈፅሙት ተከታታይ እና እያረፉ ከአንጓው የመቀጠል የጥፋት ዝንባሌያቸዉን መመልከት ይበቃል፡፡
በጊዜ ውስጥ ግንባታም ሆነ ማፍረስ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ በሂደት አስተሳሰብን ለመዝራትም የሚቻል ነው፡፡ በርቀት ጤንነትን በማስተጓጐል የተፈለገውን አሉታዊ ጫና ማሳረፍ ይቻላል ብለው የሚያምኑ ካሉም፣ ከሰውነት ማንነታቸው እየወጡ መሆናቸውን በራሳቸው ትጋት ያረጋገጡ ናቸው፡፡
ፍቅር እና ጥላቻ የመገንባት እና የማፍረስ አቅማቸው ከሁሉም የላቀ ቢሆንም በተለይ የሥርዓቱ የተወሰኑ ሰዎች እየፈፀሙ ያሉትን የማያውቁ መስለው ለመታየት መሞከራቸው የራሱ አሉታዊ ሚና አለው፡፡ ሊታሰብ የማይገባውን እንዲታሰብ ማድረግ፣ ሊፈፀም የማይታሰበውን እንዲፈፀም ማመቻቸት አገሪቱን አፍርሶ የመገንባት ተልዕኮ ቢመስለንም አይፈረድብንም፡፡
ሁሉም ሊገነባ የሚችለው በስየራ ነቢብ ብቻ አይደለም፡፡ ወይንም የተወሰኑ ሰዎች የገቡበት ማጥ አለ ተብሎ በጊዜ ሂደት ይህን ሊደግፍ የሚችል ተመሳስሎ፣ ከግለሰቡ ዝርዝር ዕውቅና ውጪ እንዲፈፀም በማመቻቸት በአንድ ያልታወቀ መንገድ ውስጥ ለማስገባት መዋከብ በመፍጠርም አይሆንም፡፡
ከሌላኛው ወገን የማፍረስ ግንኙነት የሌለው ሥርዓት የሚተክለውን ቢያንስ ያውቃል፡፡ ሌላኛውም ማወቅ ግዴታው ነው፡፡
የአገር ጉዳይ ነው እየተባሉ በየሥፍራው የጥፋት ስንቃቸውን ይዘው የሚዞሩት የመረዳት ችሎታ የሌላቸው ስለሆኑ ነው ወይንስ የሀሰት ንድፈ ሀሣብ ሰለባ በመሆናቸው ነው?
ዛሬ ሥርዓቱ ራሱ ተኩሶ የተተኮሰበት ይቅርታ እንዲጠይቀው የሚሻ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የጥቃት ዋጋ ይጠየቅ ነበር ማለትና ዛሬ ውሃ የረጩትን መጠነ ሰፊ ጉዳት ሊያደርስባቸው ከሞከረ በኋላ ይቅርታ ይጠይቁኝ ማለት ሌላ ድብቅ ተልዕኮ ከሌለው በቀር የነገሮች ተፈጥሯዊ ሂደት ውጤት አይደለም፡፡
የአገር ጉዳይ መሆኑ ከልብ ቢታመንበት ኖሮ ይህ ሁሉ ትርምስ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ይሁንና የግል ዝና፣ የተወሰኑ ሰዎች የስልጣን ምቾትና የሚያስጠብቁት ፍላጐት፣ የውጭ ሀይሎች ጥላ፣ ከስልጣን በኋላ ያለው የጊዜ ተፅዕኖ፣ ፍርሃት፣ የተቃራኒዎች ወደ ፊትና ወደ ኋላ መወዛወዝ፣ በሥርዓቱ ውስጥ የአንዳንድ ግለሰቦች በህገ-መንግስታዊው የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ አምኖ ለዚያ አለመስራት፣ የኅብረተሰቡ ፅናት መቀነስና በኅብረተሰቡ የኑሮ ደካማ ጐን መግባት እንዲሁም የዋልጌ አስተሳሰቦችና ድርጊቶች ማስፋፊያ ለመሆን መፍቀድ ሊኖር የሚገባውን ግንባታ እያስቀየሰው ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፣ የፖለቲካው ለውጥ በማያቋርጥ የብሽሽቅ “መርሀ ግብር” የተደገፈና ለዚህ ወጪ የተመደበለት መሆኑ ሌላው በአገሪቱ የተወሰኑ ስብስቦች የደረሱበት ልቀት ሆኗል፡፡ የነገሮች ጉዞ የብተናን መንገድ ከማጠናከር ይልቅ የስብሰባን ባህርይ እንዲላበሱ ቢሆን መልካምነቱና ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ የተሻለ በሆነ ነበር፡፡
በእርግጥ የራስ ሀሣብ የጥፋት ተልዕኮን ካነገበ ድጋፍ ሊኖረው አይገባም፡፡ ውስጥ ለውስጥ ወደ ጥፋት የመግፋት የሥርዓቱ የተወሠኑ ግለሰቦች ጨዋታም ስልቱ በታወቀ መንገድ የሚጓዝ ቢመስልም አገሪቱ ወይስ ሥርዓቱ ወይስ ተቃራኒዎቹ በእግዜር እጅ የተያዙ የመሰሉት? የሚለውን በተመለከተ ዞሮ ዞሮ የሕዝቡ ጉዳይ በመሆኑ ሕዝቡንም ሆነ ሥርዓቱ አውቆ የተሳሳተባቸውን ግለሰቦች በተለያዩ መንገዶች (ህገ-ወጥ) ተፅዕኖውን በማሳረፍ ላይ ስለሚገኝ ምላሽ መስጠት ያለበት ራሱ ነው፡፡ ሲወጠውጥ የቆየበትን ያውቃልና፡፡
እንደ ሥርዓት የሚገነባውን ማወቅ፣ የማይታሰበውን አለማሰብ፣ ለዛሬ ብቻ አይደለም፡ ሥርዓትን ተከልሎ ማንኛውም አባል ይሁን ሌላ ወገን መልካሙን ለማፍረስ የሚጠቀምበት “መሣሪያ” ሁሉም ተረድተውት የሚተውት ላይሆን ይችላል፡፡ መሬት ላይ የሚኖረው ዕውነት ሁሌም እንደሚመኙት አይሆንም፡፡
አገርን የመገንቢያ ጤናማ አስተሳሰቦችን መጋራትም ማጋራትም ያልቻሉ ሰዎች ፍላጐታቸውን መገመት ይቻላል፡፡ እንደ’ኔ ካላሰባችሁ ባዮችም ርቀታቸውን ያላወቁ ናቸው፡፡ የሰው አስተሳሰብ እና የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ አስተሳሰብ ጥልቅ ልዩነት ነው ያለው፡፡ አንዳንዶቻቸው የተመኛችሁት አፍራሽ ባህርይ እዚህ ባይደርስ ይህን በማስታከክ የኢኮኖሚና ፖለቲካን መሳሪያዎች በመጠቀም፣ አብዛኛውን ነዋሪ ለማሽመድመድ የምታደርጉት ጥረት ሰው ሰራሽ በመሆኑ ከዚህ ድርጊት መታቀብ አለባችሁ፡፡ ይኼ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሲባል ነው፡፡ ለራሳቸው ነው፡፡ ለሁሉም ነው፡፡
መገንባት እና ማፍረስ የአገሪቱ “ቅኔ ዘረፋ” ሆኖ የሚቀጥለው እስከመቼ ይሆን?

 

Read 4562 times Last modified on Saturday, 22 October 2011 11:00