እግር ኳስ ተጨዋች የነበረውና የቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ የሆነው ሳኢዲ ጋዳፊ ሆሊውድን ባልተተገበሩ ፕሮጀክቶቹ መበደሉን የገለፀው ቫራይቲ መፅሄት፤ ከ2 ዓመት በፊት “ናቹራል ሴሌክሽን” በሚል በመሰረተው ኩባንያ በ100 ሚሊዮን ዶላር በጀት ቢንቀሳቀስም አንድ ፊልም ብቻ እንደሰራ አውስቷል፡፡ ኩባንያው በጋዳፊ ልጅ ሲቋቋም በአምስት ዓመት ውስጥ 20 ፊልሞችን ለመስራት አቅዶ የነበረ ሲሆን፤ በ2009 ፎረስት ዊቴከር እና አድራያን ብሮዲ የሚተውኑበትን ‹ዘ ኤክስፐርመንት› የተባለ ፊልም በ12 ሚሊዮን ዶላር በጀት ፕሮዲውስ ቢያደርግም በ3 ሚሊዮን ዶላር በጀት ‹አይሶሌሽን› የተባለ ፊልምን ሳይጨርስ ትቶታል፡፡ ሚኪ ሮኪ፣ ፎረስት ዊትቴከር እና አድራያን ብሮዲ ከሳኢዲ ጋዳፊ ጋር የስራ ውል ከነበራቸው የሆሊውድ ምርጥ ተዋናዮች መሀል ይጠቀሳሉ፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በሆሊውድ የፊልም ስራ ሲንቀሳቀስ የቆየው ይህ ኩባንያ፤ በሊቢያ የህዝብ አመፅ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ሙሉ ለሙሉ ስራ አቁሟል፡፡ የ38 ዓመቱ ሳኢዲ የጋዳፊ ትንሹ ልጅ ነው፡፡ በተቃዋሚ ሃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉ ሁለት የጋዳፊ ልጆች አንዱ የሆነው ሳኡዲ፤ በንፁሃን ላይ የግድያ ትዕዛዝ ሰጥቷል በሚል በኢንተርፖል ይፈለጋል፡፡ ባለፉት ዓመታት የጋዳፊን ቤተሰብ በማዝናናት ከሰሩ ምርጥ ሙዚቀኞች መካከል ቢዮንሴ፤ 50 ሴንት፤ ኤነሪክ ኢግላስያስ፤ ሊዮኔል ሪቼ፤ ማርያ ኬሪና አሸር ከስመ ጥር ገናና ከያኒያን ዋነኞቹ ናቸው፡እነዚህ ዘፋኞች ለጋዳፊ ቤተሰብ መስራታቸው መጥፎ ዝና ቢፈጥርባቸውም በተለያዩ በዓላት በሚያቀርቡት መዝናኛ እስከ 2 ሚሊዮን ዶላር ይከፈላቸው ነበር፡፡