Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 08:32

3 የወዳጅነት ጨዋታዎች የተገኙት በስፖርት ጋዜጠኛ ነው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የእግር ኳስ ቡድን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ለሚኖረው ተሳትፎ የብቃት መፈተሽያ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ያዘጋጀው ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ መንሱር አብዱልቀኒ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ለማዘጋጀት የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርግም ሳይሳካለት እንደቀረ የታወቀ ሲሆን አንድ የስፖርት ጋዜጠኛው በግሉ ባደረገው ጥረት ሦስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማስገኘት ችሏል፡፡ ጋዜጠኛው የወዳጅነት ጨዋታዎች የብሄራዊ ቡድኑን አቅም ለመፈተሽ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው በማመን ከፍተኛ ጥረት ማድረጉን ገልፆ፤ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ለዝግጅት መጫወት የቡድኑን አቅም ያጠናክራል ብሏል፡፡

ጋዜጠኛው ከኒጀር፣ ከጊኒና ከቱኒዝያ ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎች እንዲደረጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱ ታውቋል፡፡ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 16 ቀናት የቀረው ሲሆን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ነገ በአዲስ አበባ ስታድዬም ከኒጀር ጋር የመጀመርያውን የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል፡፡ የፊታችን ሐሙስ ከቶጎ ጋር እንደሚያደርግ ተጠብቆ የነበረው ሁለተኛው የወዳጅነት ጨዋታ ሊሳካ ባለመቻሉ ከጊኒ ጋር ለመጋጠም በድርድር ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የገና እለት ደግሞ ዋልያዎቹ ኳታር ውስጥ ከቱኒዚያ ቡድን ጋር እንደሚጫወቱ ተረጋግጧል፡፡ ጋዜጠኛው ከአገራት ጋር ደብዳቤ በመፃፃፍና የእግር ኳስ ኤጀንት ኩባንያዎችን ድጋፍ በመጠየቅ የወዳጅነት ጨዋታዎቹን እንዳገኘ ይናገራል፡፡ 
የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማዘጋጀት ብዙ ፈታኝ ነገሮች እንዳሉት የጠቀሰው ጋዜጠኛው፤ በእንግሊዝኛም ሆነ በፈረንሳይኛ ቋንቋዎች ደብዳቤዎችን ተፃጽፎና ጉዳዮችን ተከታትሎ የማስፈፀም ብቃት ማነስ እንዳለም ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋልያዎቹ) ዋና አሰልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ሰሞኑን ለአልጀዚራ በሰጡት ቃለ ምልልስ ቡድናቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዘው ለሽንፈት ሳይሆን ዋንጫውን ይዞ ለመምጣት ነው ብለዋል፡፡
ትናንት በአዲስ አበባ ስታድዬም ለአፍሪካ ዋንጫ ስላደረጉት ዝግጅት በሰጡት መግለጫ፤ የመጀመሪያውን ዙር ለማለፍ የመጨረሻ ጦርነት እንከፍታለን ያሉ ሲሆን፤ የቡድኑ አምበል ደጉ ደበበ በበኩሉ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በምንሰለፍበት የአፍሪካ ዋንጫ ስንሳተፍ አላማችን ከምድቡ በማለፍ ራሳችንንም አገራችንንም ለማስጠራት ነው ብሏል፡፡
ከፍተኛ ጫና የነበረብን ለአፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ስናደርጋቸው በነበሩ ማጣሪያዎች ነው ያሉት አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው፤ አሁን በውድድሩ ለመሳተፍ ወደ ደቡብ አፍሪካ ስንጓዝ ወደፊት በተከታታይ በአፍሪካ ዋንጫ መሳተፍ የምንችልበትን ልምድና ተሞክሮ ለማዳበር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ዋንጫ 16 ቀናት የቀሩት ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚጓዘው ውድድሩ ሊጀመር ሦስት ቀናት ሲቀሩት እንደሆነ ታውቋል፡፡

Read 4786 times