Saturday, 29 December 2012 08:56

የጡት ካንሰር አሳሳቢ በሽታ ሆኗል!

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ metijossy@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

መንስኤዎቹ ምንድን ናቸው? ህክምናውስ?
የማይድን በሽታ ነው ይባላል…እውነት ነው?
በሚሰማት የህመም ስሜት ሣቢያ በሥራ ገበታዋ ላይ በአግባቡ ለመገኘት አለመቻሏ ከቅርብ አለቃዋ ጋር በተደጋጋሚ አጋጭቷታል፡፡ ህመሙ መጣ ሲሉት እየጠፋ፣ ጠፋ ሲሉት እየመጣ ግራ ሲያጋባት፣ ሁኔታውን ለቅርብ ጓደኛዋ አማከረቻት፡፡ ከግራ ጡቷ ሥር እብጠት መኖሩንና የጡቷ ጫፍ ሰርጉዶ ወደ ቢጫነት ያደላ ፈሣሽ መውጣቱን እንዳስተዋለች የነገረቻት ጓደኛዋ፤ ወደ ሆስፒታል ሄዳ የጡት ካንሰር ምርመራ እንድታደርግ መከረቻት፡፡ ይህንን ምክር ለመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግ ሣምንታት ፈጅቶባታል። ካንሠርማ ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ ምን አድርጌ ነው የጡት ካንሰር የሚይዘኝ? አላገባሁ! አልወለድኩ! አላጠባሁ! የጡት ካንሰር ሊይዘኝ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ጓደኛዋን ሙግት ገጠመቻት፡፡

የጡት ካንሰር በማንኛውም ዕድሜና ሁኔታ ውስጥ ሊከሰት እንደሚችል፣ ማግባት ወይም አለማግባት፣ ጡት ማጥባትና አለማጥባት በሽታውን ከመከሰት ሊያስቀረው እንደማይችል ጓደኛዋ አሣመነቻት፡፡ በ26 ዓመት ዕድሜዬ የጡት ካንሰር በሽታ ሊይዘኝ ይችል ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ባይኖራትም የጓደኛዋን ቃል ለማክበር ወደ አንድ የግል ሆስፒታል ሄደች፡፡ የተለያዩ ምርመራዎች እንድታደርግ ከታዘዘች በኋላ፣ ውጤቷ የጡት ካንሰር በሽታ እንዳለባት የሚያረጋግጥ ሆነ፡፡ አዕምሮዋ እውነታውን አምኖ ለመቀበል ፈፅሞ ፈቃደኛ አልነበረም፡፡ “ሊሆን አይችልም፤ አይደረግም” አለች ለራሷ፡፡ 
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ በድግሪ ተመርቃ፣ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች ገና አንደኛ ዓመቷ ነው፡፡ ትምህርቷን ለመቀጠልና ራሷን ለማሻሻል ትልቅ ተስፋ ነበራት። የገጠማት ነገር ግን ይህንን ህልምና ተስፋዋን የሚያጨልምባት መስሎ ተሰማት፡፡ በሽታው ሊድን የማይችል እና ለሞት የሚዳርግ እንደሆነ ሲነገር በመስማቷ፣ የእሷም እጣ ፈንታ ከዚህ ሊርቅ እንደማይችል አመነች። በዶክተሯ በተሰጣት ሙያዊ የምክር አገልግሎትና በጓደኛዋ ገፋፊነት ህክምናዋን ጀመረች። በሽታው ወደ ሌላ የሰውነት ክፍሏ ባለመሰራጨቱ ምክንያት፣ በህክምና ሊድን እንደሚችልና ሙሉ ጤናማ የመሆን እድሏ ከፍተኛ እንደሆነ በሃኪሟ ተነግሯታል። አሁን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ የሚሰጠውን የካንሰር ህክምና እየተከታተለች እንደሆነና የሚሰማት የህመም ስሜትም እየቀነሰ መምጣቱን አጫውታኛለች፡፡
ይህቺን ስሟ እንዲለገጽ ያልፈቀደች ወጣት ያገኘኋት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው፡፡ እንደ እሷ ለተለያዩ የካንሰር ህመሞች ህክምና ከመጡ ሰዎች ጋር ሆና ተራዋ እስከሚደርስ ከምትጠባበቅባት ቦታ ላይ ሆነን ያወጋችኝ ለዚህ ለዛሬው ጽሑፌ መነሻ ሃሳብ ሆነኝና በጊዜውና በወቅቱ ታውቆ ህክምና ካልተደረገበት ገዳይ ስለሆነው የጡት ካንሰር በሽታ ትንሽ ማለት ፈለኩ። በሽታው በጊዜው ከተደረሰበትና ህክምና ከተደረገለት ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል በሽታ ሲሆን ይህንን ባለማወቅ በሽታው ገዳይ እንደሆነና በበሽታው ከተያዙ ሞት የማይቀር ጽዋ እንደሆነ በማሰብ ብቻ ወደ ህክምና ባለመሄድ በሽታውን ለከፋና ለተወሳሰበ ችግር መነሻ የሚያደርጉ ሰዎች ቁጥር በርካታ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲዳብር በማድረግ ህብረተሰቡ በሽታው በገጠመው ጊዜ በአስቸኳይ ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ይኖርበታል፡፡ አለበለዚያ በሽታው ችላ በተባለና በተረሳ ቁጥር ህመምተኛውን ለከፋና ለተወሳሰበ ችግር መዳረጉ አይቀሬ ነው፡፡
ካንሰር ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ የህመም አይነቶች አጠቃላይ መጠሪያ ስም ነው፡፡ በሽታው ከሌሎች በሽታዎች ተለይቶ የሚታወቀው ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ማደጉና ሴሎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመውረር በመቻሉ ነው፡፡ በዓለማችን ብዛት ያላቸው የካንሰር አይነቶች ቢኖሩም ከቁጥጥር ውጪ በሆነ ሁኔታ ማደግና መራባት በሁሉም ካንሰር አይነቶች ላይ የሚታይ የጋራ ባህርይ ነው፡፡
ለጊዜው መድሃኒት ያልተገኘለትና ባለብዙ አይነት ህመሙ ካንሰር መንስኤዎቹም ለጊዜው አልታወቁም፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናት በሽታው የበለፀጉ አገራት ችግር ሆኖ የቆየ ሲሆን ከቅርብ አመታት ወዲህ ግን በታዳጊ አገራት ስርጭቱ እየጨመረ በመሄድ የድሃ አገራት አሳሳቢ ችግር ሆኗል፡፡ ሴቶች በአብዛኛው ከሚሞቱባቸው የካንሰር አይነቶች መካከል የጡት ካንሰርና የማህፀን ካንሰር ከፍተኛውን ደረጃ ይይዛሉ፡፡
በአገራችን በዚህ በሽታ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር በተመለከተ የተካሄደ ጥናት ባይኖርም በአሜሪካ እ.ኤ.አ በ2011 ዓ.ም ብቻ 200 ሺህ ሴቶች እና ከ1500 በላይ ወንዶች የጡት ካንሰር ተጠቂ ሆነዋል፡፡ ይህ ቁጥር በየዓመቱ እየቀነሰ የሄደ መሆኑንም በአሜሪካ የካንሰር ተጠቂዎች ማህበር መረጃ ይፋ አድርጓል፡፡ በሽታው ከዓመታት በፊት የበለፀጉ አገራት አሳሳቢ ችግር ሆኖ የቆየ ቢሆንም አገራቱ በተለያዩ መንገዶች በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባደረጉት ከፍተኛ ጥረት የበሽታው ስርጭት እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በተገላቢጦሽ ዛሬ በሽታው በታዳጊ አገሮች እየጨመረ ይገኛል፡፡ በዓለማችን በጡት ካንሰር በሽታ በዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ሰዎች የሚጠቁ ሲሆን ከእነዚህ ሰዎች ¾ ውስጥ ወደ 80 በመቶ የሚጠጉት ሴቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡
ዕድሜና ፆታ ያልገደበው የጡት ካንሰር በሽታ የሚከሰተው በጡት ላይ ሲሆን በሽታው በአጭር ጊዜ በመዛመት ወደመላው የሰውነት አካል ሊሰራጭና የከፋ ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
ጡት በተፈጥሮ በውስጡ ወተት ለማመንጨት የሚያስችሉ በርካታ ከረጢት መሰል ነገሮች አሉት፡፡ እነዚህን ነገሮች ከጡት ጫፍ ጋር የሚያገናኙ ቱቦዎች ያሉት ሲሆን እነዚህ ቱቦዎች በእርግዝና ወቅት ወተት ለማመንጨት ትልቅ ሚናን ይጫወታሉ፡፡ የጡት ካንሰር በአብዛኛው ማደግ የሚጀምረው በእነዚህ ቱቦዎች ውስጥ ነው፡፡ የጡት ካንሰር ተፈጠረ የሚባለው አንድ ጤነኛ ያልሆነ ህዋስ በሰውነታችን ውስጥ ሲፈጠርና ከገደብ በላይ መራባት ሲጀምር ነው፡፡ ይህ የተራባው ህዋስ በጊዜ ሂደት ጤነኛ የነበሩ ህብረ ህዋሳትን በማጥቃት ጤነኛውን የአካል ክፍል በሽተኛ ያደርጋል፡፡ የጡት ካንሰር በሽታ መንስኤዎች ለጊዜው ባይታወቁም የዘር ውርስ፣ የአካባቢ ተጽእኖ፣ የሆርሞኖች መዛባት፣ የሴሎች ዕድገት ከቁጥጥር ውጪ መሆን፣ ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ዕድሜና ከመጠን ያለፈ ውፍረት እንደበሽታው መንስኤ ይጠቀሳሉ፡፡ በቤተሰብ ውስጥ የጡት ካንሰር ተጠቂ ካለ በበሽታው የመያዝ ዕድሉ የሚጨምር ሲሆን በአካባቢ ተጽእኖ ማለትም በከፍተኛ ጨረር ውስጥ ያለምንም መከላከያ የሚሰሩ ሰዎችም በጡት ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ጤናማ ባልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት የጡት ካንሰር በሽታ ሊከሰት የሚችልበትን ሁኔታ ባለሙያዎች ሲያብራሩ፤ በአብዛኛው ቅባታማ ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት በሰውነታችን ውስጥ የስብ ክምችት እንዲፈጠር በማድረግ በካንሰር የመያዝ ዕድላችንን ይጨምረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በቂ ቫይታሚን አለማግኘትም በካንሰር የመያዝ ዕድልን ይጨምራል ይላሉ፡፡
ማንኛውም የካንሰር አይነት ተሰራጭቶ ወደ ሌላ የሰውነት አካል ከመድረሱና ከመባዛቱ በፊት ከተደረሰበት ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል በሽታ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ክፍሌ ሲሳይ፤ በሽታው ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተም ደግሞ በስፋት ከመሰራጨቱ በፊት በሚደረግ የመከላከል ዘዴና ህክምና ሙሉ በሙሉ ሊወገድ ይችላል ሲሉ ይናገራሉ። ማንኛውም ዕድሜዋ ከ16 ዓመት በላይ የሆነች ሴትና ወንድም ጭምር በአካላቸው በተለይም በጡታቸው አካባቢ የሚፈጠር እብጠትና የቆዳ ቀለም መቀየር በሚያጋጥማቸው ወቅት በአስቸኳይ ወደ ህክምና መሄድና ምርመራ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉም ያክላሉ፡፡ ማንኛዋም ሴት ወይም ወንድ በየጊዜው ጡታቸውን በእጃቸው በመዳሰስ የተለየ የመጓጐልና የመጐርበጥ ነገር መኖር አለመኖሩን መለየት ይችላሉ። በሽታው መኖሩ በጊዜ ከታወቀም በተለያዩ የህክምና ዘዴዎች ከበሽታው መፈወስ ይቻላል። በጊዜ ያልታወቀ የጡት ካንሰር በጡት ውስጥ በብዛት በመራባት እብጠትን በማስከተልና ወደ ደምስሮች በመግባት እየተራቡ በሽታን የመከላከል አቅምን ያዳክማሉ፡። ጉበት፣ ሳንባና አንጐል በካንሰሩ ሊጐዱም ይችላሉ። በሽታው ከገጠር ይልቅ በከተሞች አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን በስፋት ያጠቃል፡፡ ይህ ደግሞ ከአኗኗር ዘይቤና ከአመጋገብ ሁኔታ ጋር የሚፈጠር ችግር እንደሆነ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ በጡት ካንሰር በሽታ ሁለቱም ፆታዎች የሚጠቁ ቢሆንም ሴቶች ከወንዶች ይበልጥ ከ100 እጥፍ በላይ በበሽታው የመጠቃት እድላቸው ሰፊ ነው፡፡
የጡት ካንሰር መኖሩ ከተረጋገጠ በኋላ በተለያዩ መንገዶች ህክምና ይደረግለታል፡፡ ከእነዚህ መንገዶች መካከልም የቀዶ ህክምና፣ የጨረር ህክምናና የመድሃኒት ህክምና ዋነኞቹ ናቸው፡፡ ለጡት ካንሰር ህመም የሚደረግ ህክምና በእብጠቱ ዓይነት፣ በእብጠቱ መጠን፣ በመዛመት ባህርይውና በህመምተኛው ሁኔታ የሚወሰን ነው፡፡
የቀዶ ጥገና ህክምና እብጠቱ የተከሰተባቸውን የሰውነት ክፍሎች በቀዶ ጥገና ቀዶ የማውጣት ሕክምና ሲሆን ይህ በሰውነት ቅርፅ ላይ ለውጥ የሚያስከትል በመሆኑ በብዙ ታማሚዎች ዘንድ የማይመርጥ ህክምና ነው፡፡ የጨረር ህክምናው ደግሞ ካንሰሩ ያለበት አካባቢን በጨረር በማስመታት የሚደረግ ህክምና ሲሆን ውጤቱ እንደ ቀዶ ህክምናው ነው፡፡ ይህ ህክምና በታማሚዎች ዘንድ በአብዛኛው ተመራጭ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ ደግም ህክምናው በታማሚዋ የሰውነት ቅርፅ ላይ ልዩነት አለመፍጠሩ ነው፡፡ የመድሃኒት ህክምና (ኬሞቴራፒ) የጐንዮሽ ጉዳቶች አሉት - ማቅለሽለሽ፣ ማስመለስ፣ የፀጉር መርገፍ፣ መድማት፣ የልብ ህመም፣ መካንነት በሽታን የመከላከል አቅምን ማዳከምና “ሉኰሚያ” የተባለውን የደም ችግር ሊያስከትል ይችላላ። በጡት ካንሰር በሽታ የተያዙ ሰዎች ዘላቂና የህይወት ዘመን የጡት ካንሰር ህክምና ክትትል ያስፈልጋቸዋል፡፡

Read 6326 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 09:10