Saturday, 12 January 2013 09:10

ወደ አረብ አገራት የሚጓዙ ወንዶች በኤጀንሲዎች ያለአግባብ ተበዘበዝን አሉ

Written by  ሰላም ገረመው
Rate this item
(7 votes)

አንዱአለም ተገኝ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የሄደው 20ሺ ብር ለኤጀንሲ ከፍሎ እንደሆነ ይናገራል -ለተለያዩ የግል ወጪዎቹም 5ሺ ብር አውጥቷል፡፡ ይሄን ሁሉ ገንዘብ ያወጣው ሳኡዲ አረቢያ በሹፍርና እንደሚቀጠርና ደሞዙም 28ሺ ብር እንደሆነ ከኤጀንሲው ስለተነገረው እንደነበር ይገልፃል፡፡ ሆኖም እዚያ ሲደርስ ቃል የተገባለትን አላገኘም፡፡ “ያገኘሁት ስራ ገጠር ውስጥ የእርሻ መኪና ላይ ነበር፣ እሱን ደግሞ አልቻልኩትም፡፡ ከዚያም በሁለት መቶ ዶላር ላሞችን የማለብ ስራ አግኝቼ ስሰራ ብቆይም ከአቅሜ በላይ ሲሆንብኝ ጥየው መጣሁ” ብሏል፡፡ እዚህ ሲመጣ ደግሞ ሌላ ችግር እንደገጠመው ይናገራል፡፡ “ኤጀንሲዬ ያወጣሁትን ወጪ ክፈል ብሎ ዋሴን ይዞብኛል” ያለው አንዱአለም፤መፍትሔ ፍለጋም ወደ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በጋርድነት ለመቀጠር ለአንድ ኤጀንሲ 25ሺ ብር ከፍሎ ወደ ሳኡዲ አረቢያ የተጓዘው ዳንኤል ሽፈራውም እዚያ ከደረሰ በኋላ የተባለውን ስራ ሳያገኝ ለሁለት ወራት በኤጀንሲው ወኪል ቢሮ ተቀምጧል፡፡ ስራው ተገኘ ተብሎ ሲሄድ ደግሞ ቀጣሪዎቹ እኛ የምንፈልገው ሹፌር ስለሆነ ትንሽ ታገስ ተባለ፤ይሄኔ ጊዜዬን አላጠፋም ብሎ ወደ አገሩ መመለሱን ዳንኤል ይናገራል፡፡ 
አሸናፊ አውራሪስ ደግሞ 28 ሺ ብር ከፍሎ ወደ ጂዳ የተጓዘው ለድርጅት ሹፌርነት በወር 40ሺ ብር ደሞዝ እንደሚከፈለው ተገልፆለት ነበር፡፡ እዚያ ያገኘው ስራ ግን በአንድ መኖርያ ቤት ውስጥ የባለቤቶቹን እናት ከቤት ወደ ሆስፒታል የማመላለስ ስራ ሲሆን ደሞዙም 40 ሺ ብር ሳይሆን 300 ዶላር እንደነበር ይናገራል፡፡ “እኔ ክፈል ያሉኝን የከፈልኩት ተበድሬ ነው፤ ያንን ያህልም የከፈልኩት የተባለውን ደሞዝ አግኝቼ ህይወቴን ለመቀየር ነበር” ያለው አሸናፊ ጂዳ የገጠመው ግን ሌላ መሆኑን ገልጿል፡፡
በኤጀንሲዎች የደረሰባቸውን በደል ካዛንቺስ በሚገኘው የሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማመልከት መጥተው ያገኘናቸው በርካታ አረብ አገር ደርሰው የተመለሱ ወንዶች እንደሚሉት፤ ኤጀንሲዎች ጥሩ ስራ በጥሩ ደሞዝ እናስቀጥራችኋለን እያሉ ከፍተኛ ገንዘብ ቢያስከፍሏቸውም እዚያ ሲደርሱ ግን የተባለውን እንደማያገኙና አንዳንዶች ተስፋ በመቁረጥ ወደሌላ አገር ለማምለጥ ሲሞክሩ ተይዘው እየታሰሩ ነው፡፡ መንግስት ባወጣው መመሪያ እንጂ ኤጀንሲዎች የሚጠይቁትን የተጋነነ ክፍያ አልከፍልም ያለ ሰው ፓስፖርቱ ኤጀንሲው ጋ እንደሚከርም የገለፁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ኤጀንሲው የሚጠይቀውን ክፍያ የሚከፍሉ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቪዛው እንደሚመጣላቸው ተናግረዋል፡፡
በኤጀንሲዎቹ ይፈፀማል የተባለውን ብዝበዛ አስመልክቶ የጠየቅናቸው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ግርማ ሸለሞ፤“ድርጊቱ ህገወጥ ነው፣እንዲህ የሚያደርጉትን በህግ እንፋረዳለን፣መንግስት የሚያውቀው የህክምና፣የፓስፖርትና የአሻራ ምርመራ ክፍያ መሆኑን ነው” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል እስካሁን በህጋዊ መንገድ ለስራ ሲኬድባቸው የነበሩ የአረብ አገራት ሁለት ብቻ ሲሆኑ አሁን ግን መንግስት ከኳታር እና ከዮርዳኖስ ጋር ውል በመፈራረም ኤጀንሲዎች ወደ ሁለቱ ተጨማሪ አገራት ሠራተኞችን መላክ እንደሚችሉ ታውቋል፡፡ ለሁለት አመት ተቋርጦ የነበረው የዱባይ ጉዞም በቅርቡ ይጀመራል ተብሏል፡፡ ወደ ባህሬንና ቤሩት የሚደረጉ ጉዞዎች ግን እስካሁን እንደተቋረጡ ሲሆኑ በቅርቡ የመጀመር እቅድ እንደሌለም ታውቋል፡፡

Read 5527 times